2ኛ ቆሮ.1:1-11

አጠቃላይ መግቢያ 

በ 1ኛ ቆሮ.16፡5-9 ላይ ሐዋርያው የጉብኝት ፕላኑን እንደቀየረ ይነግራቸዋል። ከዚህ በፊት ከመቄዶንያ ሲመለስ ሳይሆን ወደ መቄዶንያም ሲሄድ እንደሚጉበኛቸው እንዲሁም ከመቄዶንያ ሲመለስ ደገሞ እንደሚጐበኛቸው ነገሮአቸው ነበር ማለት ነው፤ (2ኛ ቆሮ.1፡15-16)፡፡ ነገር ግን ይህን እንዳሰበው ሊፈድም እንዳልቻለና ከመቄዶንያ ሲመላስ ብቻ እንደሚጎበኛቸው በ1ኛ ቆሮ.16፡5-9 ባለው ክፍል ይነገራቸዋል። 

በዚህ ምክንያት የሐዋርያው ተቃዋሚዎች «ጳውሎስ በተናገረው አይረጋም» የሚል ክስ ይሰነዘሩበታል፤ (2ኛ ቆሮ.1:17-19)። እርሱም ይህ እንዳልሆነ ግን ያልጎበኛቸው ዳግመኛ በኃዘን እንዳይጐበኛቸው ለእነርሱ አዝኖ እንደሆነ ይነገራቸዋል፤ (2ኛ ቆሮ.2:1-4)። ሦስተኛ ጉብኝቱን በቶሎ እንደሚፈድም እነሱም ለዚህ ጉብኝቱ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁት ያስታውቃቸዋል፤ (2ኛ ቆሮ.12:14፤ 13:1)። ጠቅላላ መልእክቱም በዚህ ዝግጅት ይከፋፈላል። 

ክፍል 1:- እመጣለሁ ብሎ ባለበት ጊዜ ያለመምጣቱን ምክንያት ያስረዳል፤ ከምዕራፍ 1-7። 

ክፍል 2:- ለቅዱሳን ዕርዳታ መዋጮው ተሰብስቦ እንዲጠብቀው፤ ምዕራፍ 8 እና 9፡ 

ክፍል 3፡- ሦስተኛ ጉብኝቱ በእርግጥ ስለቀረበ ያመፁበትና እስካሁን ንስሐ ያልገቡትን እንደበፊተኛው ጊዜ ያላቅጣት እንደማይለቃቸው ማስጠንቀቂያ ከምዕራፍ 10-13 

ጥያቄ 1. 2ኛ ቆሮንቶስን በሙሉ አንብበህ ከዚህ በላይ የተሰጠውን መግቢያ ከጥቅሶቹ አንብበህ ስለተሰጠው መግቢያ ያለህን አስተያየት በአጭሩ ጻፍ። 

ጥያቄ 2. በቁጥር 1 ላይ ቅዱሳን የሚለው እነማንን ነው? 

ጥያቄ 3. በቁጥር 5 ላይ «ክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደበዛ» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 4. በቁጥር 10 እና 11 ላይ «በብዙ ሰዎች በኩል ስለተሰጠን ስለጸጋ ስጦታ» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ቁጥር 1:- ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሲጽፍ ሐዋርያነቱን ይጠቅሳል፤ ሐዋርያነት ሥልጣኑን የማይቀበሉ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ተነሥተው ነበርና። ጢሞቴዎስ የተባለው ወጣት በመጀመሪጀው የሐዋርያው ጉዞ ጌታን ተቀብሎ የሐዋርያው ተከታይ እንዲሆን በሁለተኛው ጉዞው መረጠው፤ (የሐዋ.16፡1-3)። አካይያ የተባለው አውራጃው ሲሆን ቆሮንቶስ ደግሞ ከተማው ነው። ይህ መልእክት የተጻፈው በቆሮንቶስ ትገኝ ለነበረችው ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በመላው ግሪክ ለነበሩ ክርስቲያናችም ጭምር መነበብ ነበረበት። 

ቁጥር 2:- ሐዋርያው ምንም በልቡ ሃዘን ቢሰማው ልጆቹ የሆኑትን ምእመናንን ከማጽናናት አይሰለችም። 

ከቁጥር 3-6፡- «የርኅራኄ አባት» እግዚአብሔር በርኅራኄው ሰፊ ስለሆነ የርኅራኄ አባት ተባለ። ልጆቹ ሲሠቃዩ እግዚአብሔር አባታችን ይገደዋል። «የመጽናናትም ሁሉ አምላክ» መጽናናት የሚለው ቃል ከመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነው፤ (ዮሐ. 14፡16)። 

«የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት» ክርስቶስ በአምላክነቱ እግዚአብሔር አባቱ ነው፤ ያም ማለት ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው። ግን ሰው ሆኖ አማላጃችን ስለሆነ በሰውነቱ አብ አምላኩ ነው፤ (ዮሐ. 20: 17)። 

ከቁጥር 4 ጀምሮ ሐዋርያው ስለመከራው ይናገራል። ይህም ስለ ወንጌል ከመከራ በስተቀር ከሰው ሌላ ክብር እንዳላገኘ ያስረዳል። መከራውም የእውነተኛነቱ ማረጋገጫ ማህተም ነበር። በመከራው የእግዚአብሔርን መጽናናት አየ። ይህ ማጽናናት ከመከራ ማዳን ብቻ ሳይሆን በመከራም ውስጥ የመንፈስ ጥንካሬ መስጠት ነው። ክርስቲያን በመከራ ውስጥ መጽናናትን ስለሚቀበል ዞሮ በመከራ ያሉትን ማጽናናት ይችላል። 

ጥያቄ 5. ሀ/ በሕይወትህ መከራን በማምጣት እግዚአብሔር በእምነትህ ሲያሳድግህ ያየኸው እንዴት ነው? ለ/ ይህ መከራ ሌሎችን በመከራ ውስጥ ያሉትን እህትና ወንድሞችህን እንድትረዳቸው ያደረገህ እንዴት ነው? 

“የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደበዛ” ክርስቲያን በወንጌል ምክንያት መከራ ሲቀበል ከክርስቶስ ጽዋ ተካፋይ ይሆናል። ይህም እንደክርስቶስ እርሱ አዳኝ ይሆናል ማለት አይደለዎ። ግን በክርስቶስ ምክንያት ስለ ጽድቅ መሰደድ ከክርስቶስ ጋር መተባበር ስለሆነ ይህ መልሶ የክርስቶስን መጽናናት በልብ ያመጣል። ክርስቶስ አሁን በክብር እንጂ በሥቃይ አይደለም። ያለፈውን የክርስቶስን መከራ የሚካፈሉ አሁን በመከራቸው የክርስቶስን መጽናናት በመጠኑ እንደቅምሻ ያህል ይቀበላሉ (ፊልጵ. 3:10፤ 1ኛ ጴጥ.4:13፤ ማቴ.20፡23)። 

የሐዋርያው ሥቃይና መጽናናት ለቤተ ክርስቲያን በረከት ሆነ። ያም ወንጌልን ስላስተማረና በተቀበለውም መጽናናት አሁንም በቃሉ እኛን በዚህ ዘመን ስለሚያጽናናን ነው። በሐዋርያውና በቆርንቶስ ክርስቲያኖች መካከል በክርስቶስ በመጽናናት መደጋገፍ ሊበዛ እንጂ ክርስቲያን ለሌላ ክርስቲያን የሐዘን ምክንያት መሆን የለበትም! (ቁጥር 6)። 

ከቁጥር 8-11:- በእስያ የደረሰበት ሥቃይ ለሕይወቱ እንኳ የሚያሰጋው ነበር፤ ግን በክርስቲያኖች ጸሎትና በክርስቶስ የትንሣኤ ኃይል ምክንያት ከብዙ አደጋ ተበበቀ። ጳውሎስ በእስያ ውስጥ ምን ዓይነት ችግር እንዳጋጠመው በግልጽ ባናውቅም በጣም ጠቃሚ ትምህርት እንዳስተማረው ግን እናውቃለን። በመከራው ውስጥ ጳውሎስ በራሱ ኃይል መተማመን ሳይሆን ለእግዚአብሔርም ሁለንተናውን መስጠትን ተምሯል። 

ጥያቄ 6. ሀ/ 2ኛ ቆሮ.12፡9-10 አንብብ። እነዚህ ሁለት እውነታዎች የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ለ/ እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ነው በኃይልህና በጥበብህ ከመታመን ይልቅ በእርሱ መታመንን ያስተማረህ? 

ጳውሎስ ከመከራው የተገላገለው በሌሎች ሰዎች ያላሰለሰ ጸሎት እንደነበር ተረድቷል። ይህ ለጳውሎስ የተሰጠ የጸጋ ስጦታ ነው። ጳውሎስ አንድ ፍሪ ያለው አገልገሎት ሊኖረው የሚችለው በጌታ ወንድምና እህቱ የሆኑ ሁሉ በጸሎት ሲያስቡት አንደሆነ ተገንዝቧል። እግዚአብሔር በእኛ ጸሎት አማካኝነት በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ ይሠራል። 

ጥያቄ 7. በጸሎትህ ሰዓት ለሌሎች (መጋቢዎች፥ ወንጌላውያን፥ ሽማገሌዎች፥ ወዘተ …) ምን ያህል ትጸልያለህ? ጸሎትህ ለእነዚህ ሰዎች አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ ይገባሃል። አሁን ትንሽ ጊዜ ወስደህ የቤተ ክርስቲያንህን መሪዎች በጸሎት አማካኝነት በእግዚአብሔር ፊት አስባቸው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: