ጥያቄ 8. በቁጥር 13 ላይ «ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አንጽፍላችሁና» ሲል ምን ማለቱ ነው?
ቁጥር 12 ላይ በቅንነትና በቀጥተኛነት በመካከላቸው እንደኖረ ሕሊናው ይመሰክርለታል። “በዓለማዊ ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት” አንዳንዶች የእውነት መንገድ ሳይስማማቸው ሲቀር ወደ ማጭበርበርና ወደ ውሸት ያዘነብላሉ። ይህም የዓለም መንገድ ነው። ሐዋርያው ግን በእግዚአብሔር ተማምኖ ሥራውን ሁሉ በቅድስናና በቅንነት ይፈድም ነበር፡፡ ለዚህም የራሱ ሕሊና ምስክሩ ነበር፡፡
ጥያቄ 9. ክርስቲያኖች እንዴት ቅዱስና ቅን ሳይሆኑ ሊኖሩና ሊናገሩ እንደሚችሉ ምሳሌዎች ስጥ። ይህ ችግር በሁሉም ላይ ያለ ነውን?
ሰው ሥራውንና ሃሳቡን ከሌላ ሰው ሊሰውር ይችላል፤ ከራሱ ግን በምንም ዓይነት ሊሰውር አይችልም። ስለዚህ የሰው ሕሊና የእግዚአብሔር ረዳት በመሆን ሌላ ሰውም እንኳ ባያውቅ ሰውን ስለራሱ ሥራ ይከሰዋል። ሐዋርያው ግን በቅድስናና በቅንነት ይኖር ስለነበር እንኳን ሰው ቀርቶ የራሱም ሕሊና ይመሰክርለት ነበር።
በቁጥር 13 እና 14 ላይ “ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አንድፍላችሁምና” ይላል። አንዳንዶች በሐዋርያው ላይ የሐሰት ክስ ሰንዝረው ነበር። ይህም ሐዋርያው በዚህ ጊዜ እመጣለሁ ብሉ ባለበት ወቅት ሳይመጣ ስለቀረ “በተናገረው አይረጋም” የሚል ክስ ተሰነዘረበት፤ (ቁጥር 15-17ን ተመልከት)። ደግሞም “በደብዳቤው አንድ መልክ ይዞ ይቀርባል፤ ፊት ለፊት ግን መልኩን ይቀይራል” ብለውም ከሰውት ነበር፤ (10፡10 እና 11)። ስለዚህ ሐዋርያው በዚህ ክፍል ውስጥ ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አልድፍላችሁም ይላቸዋል። አንዳንዶች በዓለማዊ ልማድ ስለሚኖሩ የሚናገሩትና የሚያደርጉት ግንኙነት የለውም። በሐዋርያው ዘንድ ግን ይህ ዓይነት መቀላመድ የለም። እኛም ሁላችን የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን እርሱ እውነት እንደሆነ በዓለም መንገድ በውሸት ሳይሆን በእውነት መንገድ መመራት አለብን። ለዚህም ሰውን ልናታልል ብንችልም የራሳችንን ሕሊና ግን ልናታልል አንችልምና በውስጣችን የልቦና ክስ የሌለብን ንጹሕ ክርስቲያኖች እንሁን።
ጥያቄ 10. ሀ/ አንዳንድ መሪዎች በሚናገሩትና በሚሠሩት መካከል ልዩነት የሚያሳዩት እንዴት ነው? ለ/ በምስክርነታቸውስ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው?
ሰው አሁን በሕሊናው ደንዝዞ በውሽት ቢኖር በእግዚአብሔር ፍርድ ፊት አንድ ቀን ይጋለጣልና በጥንቃቄ መኖር አለበት። “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን” እያለ በዚያን ጊዜ እርስ በርስ የማንተፋፈር ሆነን መገኘት እንዳለብን ያሳስበናል። ሐዋርያው ሕይወቱን በጥንቃቄ ስለመራ በፍርድ ቀን የቆርንቶስ ምእመናን ይኮሩበታል እንጂ አያፍሩበትም። በእነርሱ የማያፍርባቸው ሆነው እንዲገኙ ያሳስባቸዋል።
ጥያቄ 11. ሀ/ የአንተን ሕይወት በተመለከተ ይህን ዓይነት ምስክርነት ልትሰጥ ትችላለህ? ለ/ በዚያን ቀን (በክርስቶስ ቀን) ያለነቀፋ ትሆን ዘንድ ጊዜ ወስደህ ስለፈጸምካቸው የተሳሳቱ ድርጊቶችም ሆነ በልብህ ውስጥ ስላለህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ራስህን መርምር።