ጥያቄ 14. በቁጥር 10 ላይ «ይህ ትምክሕት» ሲል ስለምንድነው የሚናገረው?
ጥያቄ 15. ቁጥር 12 ላይ «ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ» የሚለውን አብራራ።
ጥያቄ 16. በቁጥር 13 ላይ ዋናው የሐሰተኛ አስተማሪዎች ፀባይ ምንድነው ይላል?
ከቁጥር 7-9፡- ሐዋርያው ወንጌልን በመስበክ የወንጌል ተገልጋዮች ሊደግፉት የተገባ እንደሆነና ይህንን መብቱን ግን እንዳልተጠቀመበት አስቀድሞ በ1ኛ ቆሮ. 9:1-18 ዘርዝሮአል። አሁን ደግሞ በተጨማሪ በዚህ ክፍል ይህንኑ ነጥብ ያነሳል። ለቆሮንቶስ ወንጌልን ሲሰብክ ከእነርሱ ሳይሆን ከመቄዶንያ ቤተ ክርስቲያን እርዳታ ይቀበል ነበር። ይህንንም ሃሳብ ሲገልጥ «እናንተን ለማገልገል … ሌሉችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ» ይላል። ሌሎች ክርስቲያኖች በሚከፍሏቸው ወንጌላውያን እየተገለገሉ ድርሻን አለመወጣት ዝርፊያ ይባላል፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ በረከትን የሚያመጡልንን አገልጋዮች በአቅማችን በደመወዝ ክፍያ መርዳት አለብን!!
ቁጥር 10፡- በቁጥር 10 “ይህ ትምክህት” የሚለው ወንጌልን ያለ ደመወዝ መስበኩን ነው። አሁን ይህንን የተናገረው ደመወዝ ፍለጋ አለመሆኑን ያረጋገጥላቸዋል። አካይያ የቆሮንቶስ ከተማ የምትገኘበት አውራጃው ነው።
ከቁጥር 11-12:- እርዳታ ከቆሮንቶስ ሳይሆን ከመቄዶንያ የተቀበለው የቆሮንቶስን ምእመናን ስላልወደደ እንዳልሆነ «እግዚአብሔር ያውቃል» በማለት በእርግጥ የሚወዳቸው መሆኑን ያረጋግጥላቸዋል። ነገር ግን ወዳፊትም ቢሆን የገንዘብ እርዳታ ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የማይቀበለው የሐሰተኛ አስተማሪዎችን አፍ ለማዘጋት እንደሆነ ይናገራል።
እነዚያ ወደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የገቡት ሐሰተኛ አስተማሪዎች በነፃነት ገንዘብ ይቀበሉ ስለነበር ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ገንዘብ ስላልተቀበለ እንደእነርሱ ተቀብሎ ከእነርሱ እኩል እንዲሆን ይፈልጉ ነበር። ሐዋርያው ግን ገንዘብ ከተቀበል ለእነርሱ አመቺ እንደሚሆንላቸው ስላወቀ አልቀበልም አለ። ይህን ያደረገው ስላልወደዳቸው ሳይሆን ሐሰተኞችን ለማጋለጥ ፈልጎ ነበር! “እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ ምክንያትን ከሚፈልጉት ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ”። ብዙ ጊዜ ሐሰተኛ መምህራን ሌሎችን ወደ ራሳቸው የሚስቡት ያሉትን መሪዎች ድክመት በመጥቀስ ነው። ብዙ ጊዜ ወጥመድ አዘጋጅተው መሪዎች እንዲሰናከሉ ያደርጋሉ። ወይም ጥሩ ለሆኑ ድርጊቶች የተሳሳተ ትርጓሜ ይሰጣሉ።
ጥያቄ 17. ይህ ሲደረገ አንዴት እንዳየህ የሚገልጽ ምሳሌ ስጥ።
ከቁጥር 13-15፡- በዚህ ክፍል ተጨማሪ የሆነ የሐሰተኛ አስተማሪዎች ፀባይ ይዘርዘርልናል።
– የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን ይለውጣሉ።
– ውሸተኞች ሐዋርያት ናቸው።
– ተንኮላኛ ሠራተኞች ናቸው።
– የሰይጣን ፀባይ አላቸው፤ ሰይጣን የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን እንደሚለውጥ እነርሱም የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን ይለውጣሉ። ነገር ግን እውነተኛው ፈራጅ ፍጻሜአቸውን እንደሥራቸው ያደርጋል!
የጨለማው አምላክ ሰይጣን ብዙ ጊዜ ሌሎችን የሚያስተው «የብርሃን መልአክ» መስሎ በመቅረብ ነው። በሌላ አነጋገር የሚጠቀምባቸው ዘዴዎችና ሁኔታዎች ሁሉ ክርስቲያኖች ጥሩ ናቸው ብለው የሚገምቷቸውን ነገሮች ነው። በዚህም ምክንያት ብዙዎችን ወደ ኃጢአት ይመራል። የእርሱ አገልጋዮች የሆኑት ሐሰተኛ መምህራንም ብዙ ጊዜ ጥሩ ነው ተብሎ የሚገመተውን ነገርና ሁኔታ በመጠቀም ነው ሌሎችን እነርሱን እንዲያምኑ የሚያደርጉት። ያም ሆነ ይህ ዋናው ዓላማቸው ሌሎችን አታለው ወደ ጥፋት መምራት ነው። ምንም እንኳን በመጃመሪያ አኳኋናቸው በቀላሉ ከጥሩ መሪዎች ለይተን ልናውቃቸው ባንችልም፥ ቀስ በቀስ ግን መከፋፈልን ይፈጥራሉ። በዚህም የራሳቸውን ሐሰተኛ መምህርነት ይፋ ያወጣሉ።
ጥያቄ 18. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሐሰተኛ መምህራን የሰይጣን አገልጋዮች ሆነው ሳለ «የብርሃን መልአክ» መስለው ለመቅረብ የሞከሩበት ጊዜ አለ?