2ኛ ቆሮ.2:5-11

ጥያቄ 5. በዚህ ክፍል አጥፊው በሃዘን እንዳይዋጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይቅር እንድትለው ያዛል፡፡ ይህ አጥፊ ጥፋቱ ምን ነበር? (1ኛ ቆሮ.5፡1-2)። 

በቁጥር 5 ላይ አጥፊው የበደለው የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን በሙሉ እንጂ በተለይ ሐዋርያውን እንዳልሆነ ያስገነዝባቸዋል። በቁጥር 6 «ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና» ይላል። ከእናንተ የምትበዙት ሲል በስብሰባቸው ላይ በድምፅ ብልጫ የተወሰነውን ውሳኔ ያመለክታል። በ1ኛ. ቆሮ.5፡3-5 ላይ ከእንጀራ እናቱ ጋር የዝሙት ሥራ የፈፀመ አባል መቀጣት እንዳለበት ጽፎ ነበር። የቆሮንቶስም መዕመናን ይህን ሐዋርያዊ ትዕዛዝ ፈጸሙ። ተሰብስበው በድምጽ ብልጫ ቅጣት ወሰኑ። ይህም ቅጣት ንስሐ እስኪገባ ድረስ ከቤተ ክርስቲያን ማኅበር መስወገድ ነበር። ይህን ቅጣት የወሰኑት አብዛኞቹ ሲሆኑ ጥቂቶች ግን የሐዋርያውን ትእዛዝ እንዳልተከተሉ እንረዳለን፡፡ 

አሁን ግን ይህ ሰው ንስሐ ስለገባ እንደገና በፍቅር እንዲቀበሉት ያዛል፤ «የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ሃዘን እንዳይዋጥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል»። በክርስቶስ መንግሥት ሰው ንስሐ ከገባ ምሕረትን የሚቀበል መሆኑን ቃሉ ይመሰክራል፤ (1ኛ ዮሐ.1:9-2:1)። 

በቁጥር 8 መጨረሻ ላይ “እለምናችኋለሁ” ካለ በኋላ አራት ነጥብ መኖር አለበት። ቁጥር 9 “ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና” የሚለው ከሚከተለው ጋር እንጂ ካለፈው ጋር አይያያዝም፡፡ ከዚህ ቀደም የጻፈው ንስሐ የገባውን እንዲቀበሉት ሳይሆን እንዲቀጡት ነበር፤ (1ኛ ቆሮ.5፡1)። ስለዚህ ቁጥር 9 የሚለው አጥፊው ይቀጣ ብዬ የጻፍሁት መታዘዛችሁን ለማየት ነበር፤ በመቅጣታችሁ መታዘዛችሁን አየሁ! ያ የጻፈላቸው ደብዳቤም 1ኛ ቆሮንቶስ ነበር። 

ንስሐ የገባን ሰው ቶሎ በፍቅር አለመቀበል ለሰይጣን እድል መስጠት ነው ሲል ሐዋርያው ያስጠነቅቃል፤ (ቁጥር 11)። የሰይጣን አንዱና ዋነኛው ግቡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍልን ፈጥሮ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ተስፋ መቁረጥንና ስደትን ማስከተል ነው። አንድ ክርስቲያን ወደ ትክክለኛው መንገድ ከተመለሰ በኋላ ምንም ዓይነት የፍቅርና የይቅርታ መንፈስ የማያይ ከሆነ ተስፋ ይቆርጥና እምነቱን ይተዋል። በቤተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ ክፋት የሥነ ሥርዓት መሠረት ከሆነና አባሎቻችን ይቅርታ ለማድረግና ፍቅርን ለመግለፅ ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ ከሆነ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ይፈፀማል፡፡ ሰይጣን የምንሰጠውን ማንኛውንም አጋጣሚ ቤተ ክርስቲያንንና ሕይወታችንን ለማበላሸት እንደሚጠቀምበት አስተውሉ። 

ጥያቄ 6. ትክክለኛ ያልሆነውን የሥነ ሥርዓት እርምጃ በመጠቀም ወይም ይቅር ባይ ባለመኖሩ ሰይጣን እንዴት አድርጎ የምታውቀውን ሰው እንዳጠቃ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ። 

አንዳንድ ሊቃውንት አጥፊው ሐዋርያው ጳውሎስን በሁለተኛ ጉብኝቱ ጉዞው የተቃወመው ሰው ነው ብለው ይገምታሉ። ለዚህ ግን ምንም ማስረጃ የለም። እንዲያውም ይህ እንዳልሆነ የምንገነዘበው ሐዋርያው አጥፊውን ሳይገስጽ ዝም ብሉ ሄዶ በሩቅ ሳለ ቤተ ክርስቲያኑን ቅጡት ቢል ኖሮ እውነትም ከሳሾቹ እንዳሉት በመልእክቱ እንጂ ፊት ለፊት ፈሪ ነበር ማለት ነው፤ (10:10 እና 11)። ይህንም አንቀበልም። አጥፊው ከላይ እንደተባለው ዝሙትን የሠራው ነው። 

Leave a Reply

%d bloggers like this: