2ኛ ቆሮ.3:1-3

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አጥብቀን ልናስተውል የሚገባን በቁጥር ሦስት ላይ ያለው “ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ” የሚለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠው ለማያነቡት ሰዎች፥ ክርስቲያኖች ሕያዋን የሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለባቸው። የክርስቲያን ሕይወት ክርስቶስን የሚያሳይ ግልጽ መድሐፍ መሆን አለበት። 

ጥያቄ 1. የማመስገኛ መልእክት ምን ነበር?

ጥያቄ 2. የቆርንቶስን ቤተ ክርስቲያን «በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

የአማርኛው ትርጉም “የማመስገኛ ደብዳቤ” ብሎ የተረጕመው ትክክለኛ ትርጉም አይደለም። ትክክለኛ ትርጉሙ «የመሸኛ ደብዳቤ» ወይም «የማስተዋወቂያ ደብዳቤ» ነው። መሠረታዊ ሃሳቡ አንድ ወንጌላዊ ከአንድ ቤተ ክርስቲያን ለአገልገሎት ወደማያውቀው ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ ከነበረበት ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የመታወቂያ ደብደቤ ተሰጥቶት ይሄዳል። በዚያ ደብዳቤ መሠረት የሄደበት ቤተ ክርስቲያን በአክብሮት ተቀብሎ አገልገሎቱን ይቀበላል። 

ሐዋርያውም የዚህ ዓይነት የማስተዋወቂያ ደብደቤ ለሚያስፈልጋቸው አገልጋዮች ይሰጥ ነበር፤ (1ኛ ቆሮ.16፡10 እና 11፡ 2ኛ ቆሮ. 8:22-24፤ ሮሜ 16፡1 እና 2)። አሁን ግን የቆርንቶስን ቤተ ክርስቲያን እርሱ ራሱ የመሠረታት ስለሆነች ለቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን የማስተዋወቂያ ደብዳቤ ይዞ ሊቀርብ አይገባውም። እንዲሁም በሁሉም ቦታ ሐዋርያነቱ የታወቀ ስለሆነ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያውን የሚያስተዋውቅ ደብደቤ ልትሰጠው አይገባም። «የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን?» ብሎ በአሽሙር ይጠይቃል። 

በተጨማሪም «እንደሌሎች» በማለት የሚጠቅሳቸው ከእርሱ በኋላ ሐዋርያ ነን እያሉ የማስተዋወቂያ ደብደቤ ይዘው ወደ ቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የገቡ ሐሰተኛ ሐዋርያት እንደነበሩ ያመለክታል፤ (2ኛ ቆሮ.11:13-15)። 

ሐዋርያው በቀለም የተጻፈ ደብዳቤ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተጻፈ መታወቂያ መልእክት ነበረችው፤ እርሱም የተከላት የሐዋርያነቱ ማህተም የሆነች የቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። የቆርንቶስ ሰዎች ከዓለማዊነት ተለውጠው የክርስቶስ ሰዎች የሆኑት በእርሱ አገልግሎት ስለሆነ በይፋ የቆመ ማንም ሰው የሚመለከተው መልእክት ናቸው፤ (1ኛ ቆሮ. 6፡9-11)። ይህ መልእክት በሐዋርያውም ልብ ደግሞ አለ። ይህም ማለት ሐዋርያው በልቡ በፍቅር ይመለከታቸዋል ማለት ነው። 

ጥያቄ 8. ሀ/ ሁላችንም የዓለም መልእክት ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው? ለ/ ሕይወታችን ማሳየት ያለበት ምን ዓይነት መልእክት ነው? 

በቁጥር 3 ላይ የልብ ጽላትና የድንጋይ ጽላትን ያነጻጽራል (በተቃራኒ ያስተያያቸዋል)። ጽላት የሚለው ቃል አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈበት በእግዚአብሔር ለሙሴ የተሰጠው ድንጋይ ነው፤ (ዘፀ. 31:18)። አዲስ ኪዳንንና ብሉይ ኪዳንን ያነጻጽራል። 

ሐሰተኞቹ ሐዋርያት በሙሴ ሕግ የሚመኩ ሳይሆኑ አይቀሩምና ስለዚህ የእርሱ አገልግሎት የብሉይ ኪዳን ሳይሆን የአዲስ ኪዳን መሆኑን ያስረዳል፤ (ኤር.31:33)። 

የብሉይና የአዲስ ኪዳን ተቃራኒነት የመጻፊያው እቃ ነው እንጂ የተጻፈው አይደለም፡፡ ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ጽላት ሲጻፍ አዲስ ኪዳን ግን በልብ ጽላት ላይ ተጻፈ። ነገር ግን በሁለቱ ጽላት ላይ ያለው ያው የእግዚአብሔር ሕግ ነው እንጂ የተለያየ አይደለም። እግዚአብሔር ለአዲስ ኪዳን ምእመናን ከአሥርቱ ትእዛዛት ሌላ አዲስ ትእዛዝ አልሰጠም፤ አሥርቱ ትእዛዛትንም አልሻረም። ግን በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስን ስለተቀበልን ሕጉን ለመጠበቅ እንችላለን። ስለዚህ ነጥብ የሚከተሉትን ጥቅሶች በጥንቃቄ አጥና፤ (ዘፀ. 20፡3-17፤ ሕዝ.36፡26-27፤ ማቴ. 5:17፤ ሮሜ 13:9-10፤ 1ኛ ዮሐ.1:5-8)። 

ጥያቄ 4. የእግዚአብሔር ቃል በልባችን የመጻፉ እውነታ በብሉይ ኪዳን ጊዜ በድንጋይ ላይ ከተጻፈው የእግዚአብሔር ሕግ የሚበልጠው እንዴት ነው? 

Leave a Reply

%d bloggers like this: