ጥያቄ 5. «በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን» ሲል «እምነት» ማለቱ ምን ማለቱ ነው? ጥያቄ 6. «ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል» ሲል ምን ማለቱ ነው?
«በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን» ማለቱ የአዲስ ኪዳን አገልጋይነት መቀበሉን ማመልከቱ ነው። በቁጥር 3 ላይ «በእኛም የተገለገለ» ያለው ወንጌልን ለቆሮንቶስ ሰዎች ስለሰበከ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሕይወታቸው ተቀየረ ለማለት ነው። ይህ በሰው ኃይል የሚከናወን ስላልሆነ ሐዋርያውን ይህን ሥራ ለመሥራት እግዚአብሔር አስቻለው። እግዚአብሔር እንዲህ እንደሚያስችለው ወደ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል እምነት አለው።
ጥያቄ 7. ይህ ዛሬ መሪዎች በሥራቸው ላይ ሊኖራቸው ከሚገባው እምነት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
ቁጥር 5 በቁጥር 4 ላይ በአጭሩ የተጻፈውን ሃሳብ በሰፊው ያብራራል። የአዲስ ኪዳን አገልጋይ ያዳረጋቸው፥ ለሥራው ብቃትን የሚሰጣቸው እግዚአብሔር እንጂ በእነርሱ ውስጥ ምንም ብቃት የለም። ብቃት ማለቱም ሥራውን ለማከናወን በቂ ኃይል መኖር ማለት ነው።
ጥያቄ 8. መሪዎች የእግዚአብሔርን ሥራ በራሳቸው ኃይል ለመሥራት ሲሞክሩ ምን ያጋጥማቸዋል?
በቁጥር 6 ላይ ይህን አገልግሎት እንደገና ማብራራት ይቀጥላል፤ «በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን»። እዚህ ላይ ፊደል የሚለው በቁጥር 3 በድንጋይ ላይ የጻፈው ካለው ጋር ይስማማል። እንግጺህ የፊደል አገልገሉት ማለት በልብ ሳይሆን በውጭ በድንጋይ ጽላት ላይ ብቻ የሚጻፍ የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት ያመለክታል።
ቀጥሎም «ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል» ይላል። ይህም ማለት ሕጉ አድርግ ብሎ ከማዘዝ በስተቀር ልቦናን ቀይሮ ትእዛዝን የመጠበቅ ችሎታን አይሰጥም። ስለዚህ ሕጉን ካልጠበቅህ ትሞታለህ ስለሚልና ሰውም ሕጉን መፈጸም ስለማይችል ሕግ ይገድላል ይላል። ይህን ሃሳብ በሮሜ 7:7-12 ዘርዝሮአልና ያን ክፍል በጥንቃቄ አንብብ።
አዲስ ኪዳን የመንፈስ አገልግሎት እንጂ የሕግ አገልግሎት ስላልሆነ በውስጥ በልብ በመንፈስ ቅዱስ ሠሪነት ሕጉን ይጽፋል። ይህም ማለት ሕይወትን ይቀይራል።
ጥያቄ 9. የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልግሎት ከፊተኛው ቃል ኪዳን አገልግሎት የሚሻለው በምን መልኩ ነው? ሁለቱን ቃል ኪዳኖች አነፃፅር።