ጥያቄ 10. በቁጥር 7 ላይ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት» የሚለው ምኑን ነው?
ጥያቄ 11. ቁጥር 10ን በጥንቃቄ አንብበህ አጭር መግለጫ ጻፍ።
የብሉይ ኪዳን የሕግ ሥነ ሥርዓት በክብር መጣ፡፡ ይህ ክብር በዘፀ.34፡29-32 ባለው ክፍል ተተርኳል። ይህን ክፍል አንብብ። ሙሴ በሲና ተራራ ሕጉን በተቀበለ ጊዜ በተራራው ላይ ካለው ክብር የተነሣ ፊቱ በብርሃን አንፀባርቆ ነበር። ይህ የክብር መንፀባረቅ የብሉይ ኪዳን ክብር ነበር።
“የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስን” ማለቱ ሙሴ ፊቱ ያበራ ስለነበር እስራኤላውያን መፍራታቸውን መግለጹ ነው። ይህ እንደዚህ ክብር የተሰጠው የሕይወት ሳይሆን የሞት አገልገሎት ነው። ከላይ እንደተመለከትነው ሕጉ ራሱ የሞት መሣሪያ አይደለም፤ ግን ኃጢአት በሰው ላይ ስላለ ሕጉ በኃጢአተኛው ላይ ሞትን አስከተለ። እንግዲያስ ጉድለቱ ከሕጉ ሳይሆን ከኃጢአተኛው ከሰው ነው።
ጥያቄ 12. ጥሩ ሥራ በመሥራት ወይም የተወሰኑ ሕገጋትን በመጠበቅ እንድናለን ለሚሉ ሰዎች ይህ እውነታ ምን የሚያስተምራቸው ይመስልሃል?
የሞት አገልገሎት የሆነው እንዲህ ክብር ከነበረው ለኃጢአተኛው ሕይወትን የሚሰጠው የመንፈስ አገልግሉት እንዴት የበለጠ ክብር አይኖረውም? የመንፈስም አገልግሎት ክብር አለው። እንዲያውም ከሕጉ ክብር የበለጠ ክብር አለው።
ይህ የአዲስ ኪዳን ክብር ምንድነው? በሥጋ ፊት ላይ የሚያበራ ሥጋዊ ክብር ሳይሆን የቅድስናና የድድቅ ክብር በነፍስ ውስጥ የሚያበራ ውስጣዊ ክብር ነው። ኃጢአተኛን ቀይሮ ክርስቶስን መምሰልን የሚሰጠው የጽድቅ ክብር አለው።
በቁጥር 9 ላይ ኩነኔንና ጽድቅን ያወዳድራል። የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ኩነኔን አመጣ። ሕጉን ጠብቅ ሕይወት ታገኛለህ አለ፤ (ሮሜ 10፡5)። ሕጉ ስላልተጠበቀም የተባለው ኩነኔ መጣ። አዲስ ኪዳን ግን «ክርስቶስ ሕጉን በአንተ ምትክ ጠብቀልሃልና ክርስቶስን በመቀበል ጽድቅን ተቀበል» ይላል፤ (ሮሜ 10፡4)። ከዚህም ጨምሮ አዲስ ኪዳን የሕይወት ለውጥን (ቅድስናን) በመንፈስ ቅዱስ ሠሪነት በክርስቲያን ሕይወት ይሰጣል፡፡
ቁጥር 10 የሚለው የአዲስ ኪዳን ክብር ከብሉይ ኪዳን ክብር እጅግ ስለሚበልጥ የብሉይ ክብር ከአዲስ ኪዳን ክብር ጋር ሲወዳደር ፈጽሞ ክብር እንደሌለው ሆኖአል። ቁጥር 11 ብሉይ ኪዳን ጊዜያዊ አዲስ ኪዳን ግን ጽንቶ ይኖራል ይላል። የሙሴ ፊት ክብር አለመቆየት የብሉይ ኪዳንን ጊዜያዊነት አሳየ። ስለዚህ አሁን ብሉይ ኪዳን ተሽሮአል። ይህ ማለት ግን ሕጉ ሕይወታችንን አይቆጣጠርም ማለት አይደለም። ግን እንደ ብሉይ ኪዳን በውጭ ሳይሆን በልባችን ሕጉ ተድፎአል። ሕጉን የመጠበቅ ችሎታ መንፈስ ቅዱስ ይሰጠናል፤ (ሮሜ 8፡2-4)። በዚህም በ2ኛ ቆሮ.3፡11 ተሻረ ያለው ሕጉን ሳይሆን የብሉይ ኪዳንን አሠራር ነው። ሕጉ ዘላለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚገልጥ ስለሆነ ለዘለዓለም አይሻርም። አሠራሩ ግን በውጭ በአዋጅ የሆነ የብሉይ አሠራር ተቀይሮ አሁን በኃይል በልብ ለውጥን የሚያመጣ የመንፈስ ቅዱስ ያም የአዲስ ኪዳን አመራር ተተክቷል። በአማርኛው ትርጉም አገልግሎት እያለ የሚተረጉመው አሠራር ተብሎ መተርጉም ይቻላል።
ጥያቄ 13. የአዲሱን ቃል ኪዳን ክብር ከበፊቱ ቃል ኪዳን ክብር ጋር አነፃፅር። እንዴት ነው የሚመሳሰሉት? እንዴት ነው አንደኛው ከሌላኛው የሚበልጠው?