2ኛ ቆሮ.4፡1-6

ምዕራፍ 4 ክርስቲያን በአገልግሎቱ መታከትና ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት የሚያሳይ ነው። የክርስቲያን አገልግሎት ከባድ ቢሆንም ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። ተስፋ ባለመቁረጥም አገልግሎታችንን በንድሕና እንፈድማለን። አገልጋይ በአገልግሎቱ ተስፋ በሚቆርጥበት ጊዜ በሕይወቱም እየደከመ ጌታን ማሳዘን ይጀምሪል። ስለዚህ በአገልግሎታችን አንታክትም ሲል ሐዋርያው ይመሰክራል። 

5፡1-20 ደግሞ ስለ ክርስቲያን ከሞት በኋላ ስላለው ተስፋው የሚያበስር የተስፋ ቃል ነው። የትንሣኤው ተስፋ የመንፈስ ቅዱስ መያዣ እንደተሰጠን ይናገራል። ስለዚህ ክርስቲያን ፍጻሜውን ስለሚያውቅ በጊዜያዊ ፈተናና ችግር አይፈታም ማለት ነው። 

ጥያቄ 1. የእግዚአብሔርን ቃል ስለ አለመቀላቀል ከዚህ በፊት በየትኛው ክፍል ተወያይተን ነበር? 

ጥያቄ 2. «ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ቁጥር 1 እና 2፡- ሐዋርያው ምንም ፈተናና ትግል ቢገጥመው የአገልግሎቱ ክብር ሁልጊዜ የልብ ጥንካሬ ይሰጠዋል። ግን ሰው በአገልግሎቱ ተስፋ ሊቆርጥና ሊታክት የሚችለው በሕይወቱ ድካምን ሲያጠራቅም ብቻ ነው። ሐዋርያው በአገልግሎቱ ያልታከተው 1ኛ/ የአገልግሎቱ ታላቅነት ሁልጊዜ ልቦናውን ስለሚደግፍ። 2ኛ / አገልግሎቱን በንጹህ ሕሊና ይመራ ስለበር። 

ይህም ንጹሕ ሕሊና በሁለት ደረጃ ይከፋፈላል። 1ኛ/ በግል ሕይወቱ «የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥሏል» ። ይህም ማለት ሐዋርያው በጨለማ ሥራ ሕይወቱን አያጠላልፍም ነበር። ሕይወቱን ለምእመናን አርአያ አድርጎ «እኔ ጌታን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ይል ነበር። በ2ኛ ደረጃ አገልግሎቱን በንጹሕ ሕሊና ይመራ የነበረው የእግዚአብሔርን ቃል በጥቅምና በስሕተት አለመበረዙ ነበር፡፡ «የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም»። (ይህን ሃሳብ በ2፡17 ላይ በሰፊው ስለተወያየንበት ለዚያ ጥቅስ የተሰጠውን ማብራሪያ ተመልክት)፡፡ ስለዚህ ለአገልጋይ ጥንካሪ የሚሰጠውና ታክቶ ተስፋ ከመቁረጥ የሚጠብቀው በቀጥተኛነት የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፉ ነው። 

ጥያቄ 3. ሀ/ መሪዎች አገልግሎታቸውን ሊያጠፋና ሊያበላሸባቸው የሚችል ምስጢር የሆነ ምን አሳፋሪ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ? ለ/ ክርስቲያኖች እንዴት አድርገው የእግዚአብሔርን እውነት ሊያጣምሙ እንደሚችሉ ወይም ደግሞ የሚሰብኩበት ጊዜ እንዴት አድርገው የተሳሳቱ መንገዶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን በመጥቀስ ዘርዝረህ ጻፍ። 

«በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሁሉ ሕሊና ራሳችንን እናመሰግናለን» የሚለውን ዐረፍተ ነገር ለመረዳት ከዚህ በፊት በ3፡1 ላይ «የማመስገኛ ደብደቤ» ለሚለው የተሰጠውን ማብራሪያ ተመልከት። በዚህ ክፍል የዐረፍተ ነገሩ ትርጉም «ይህ ሰው ጥሩ አገልጋይ ነውና ተቀበሉት» ብሎ ለአንድ ታማኝ ወንጌላዊ የማስተዋወቂያ ደብደቤ እንደሚልክ፥ እንዲሁም ሐዋርያው ሕይወቱን ንጹሕ ነው ብሎ ለሌሎች ሕሊና ይናገራል። ይህም ንጹሕ ሕሊና እውነትን በግልጽ የሚናገር ለመሆኑ ምስክር ነው። ይህ ግልጥ የሚለው መጋረጃ የሌለበት ማለቱ ነው። የአለማመንና የተንኮል መጋረጃን ቀዶ የጣለ ሰው ነበር። ስውር ነገር የሚለው በማያምኑት ልብ ውስጥ ያለውን መጋረጃ ያመለክታል፤ እውነትን በግልጥ መናገር ማለትም ያለ መጋረጃ የሆነ የአዲስ ኪዳን አገልግሎት መሆኑን ያመለክታል። 

ቁጥር 3 እና 4:- ሐዋርያው ይህን ሲል አንዱ «ታዲያ ለምን ሁሉም ሰዎች ስብከትህን አይቀበሉም?» ብሎ ሊጠይቅ አንደሚችል ተገንዝቦ አስቀድዋ መልስ ይሰጣል። ምንም እንኳ ወንጌልን በግልጥነት ቢሰብክም አእምሮአቸው ወንጌልን የማይቀበል አሉ። እነርሱም የዚህ ዓለም አምላክ የሆነው ሰይጣን አእምሮአቸውን ስላጨለመባቸው ነው። ሰይጣንን የዚህ ዓለም አምላክ ያለው ሰዎች አምላካቸው አድርገው በሰይጣን ሀሳብ እየተመሩ እግዚአብሔርን ስለሚክዱ ነው እንጂ እውነትስ ሰይጣን አምላክነት ኖሮት አይደለም። 

ቁጥር 5፡- ከላይ ራሳችንን ለሰው ሕሊና እናመሰግናለን ሲል ራሱን የሚሰብክ አድርገው እንዳይነቅፋት አስቀድሞ መልስ ይሰጣል። የሚሰብከው ክርስቶስን እንጂ ራሱን አልነበረም። ይህም ለቤተ ክርስቲያን ራስን ባሪያ አድርጎ በታማኝነት መገኘት ማለት ነው። 

ጥያቀ 4. ይህ ጥቅስ ምን መስበክ እንደሚገባንና የቤተ ክርስቲያንን ምሪት በተመለከተ የሚሰጠን ግንዛቤ ወይም ትምህርት ምንድነው? 

ቁጥር 6:- የወንጌል አገልጋዮች በብርሃንና በግልጥነት እንዲያገለግሉ ሕይወታቸውን ብርሃን ያደረገ የብርሃን አምላክ ራሱ እግዚአብሔር ነው። ይህም ብርሃን በክርስቶስ ፊት ላይ አንጸባርቋል። በሙሴ ፊት ላይ ያንጸባረቀው ብርሃን ወደ እስራኤላውያን አልተላለፈም። እንዲያውም ከሙሴ ፊት ላይ ጠፋ። በክርስቶስ ፊት ላይ የነበረው ብርሃን ግን ለምእምናን ሁሉ ይተላለፋል። ግን በውጭ ለጊዜው የሚያበራ ሳይሆን ለዘለዓለም በልባቸው ውስጥ ይበራል። ይህም ማለት በክርስቶስ አማላጅነት መንፈስ ቅዱስ በምእመናን ልብ ውስጥ ብርሃንን ይፈጥራል። ይህም ብርሃን ንጹህና ግልጽ የሆነ ሕይወትንና አገልግሎትን ለምእመናን ይሰጣል። 

ጥያቄ 6. በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ፥ መሪነትን በተመለከተ የተሰጡትን ዋና ዋና መመሪያዎች በዝርዝር ደፍ። 

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading