2ኛ ቆሮ. 5፡1-10

ጥያቄ 15. በቁጥር 1 ላይ «ድንኳን» የሚለውን በአንድ ወገን፥ «ሕንጻ» የሚለውን በሌላ ወገን አድርጉ ሁለቱን ያነጻጽራል፤ ድንኳንና ሕንጻ ምንና ምንን ያመለክታሉ? 

ጥያቄ 16. ከቁጥር 2-4 ባለው ክፍል ውስጥ የሚከተሉትን ቃላት አብራራ። መልበስ፣ ራቁት መገኘት፣ መገፈፍ፣ መቃተት፡፡ 

ጥያቄ 17. በስደት መኖርና ማደር እያንዳንዱ ምን ማለት እንደሆን አስረዳ፡፡ 

ጥያቄ 18. በሥጋ የተሠራውን በብድራት ለመቀበል በክርስቶስ ወንበር ፊት መገለጥ ማለት ምን ማለት ነው? 

በቁጥር 1 ላይ ድንኳን የሆነው ምድራዊ መኖሪያችን የሚለው ይህንን በሥጋ በዚህ ዓለም ያለንን ኑሮ ነው። ጠቅላላ የሃሳቡም ትርጉም ከዚህ ዓለም በሞት ብንለይ እግዚአብሔር የዘላለም የትንሣኤ አካል አዘጋጅቶልናል ማለት ነው። ይህ ሥጋችን ፈራሽ ስለሆነ ድንኳን ተብሏል፤ ነገር ግን የትንሣኤ አካላችን ሕንጻ ተብሏል፤ የማይፈርስ ስለሆነ። 

በዚህ ውስጥ እንቃትታለን ማለት የዚህ ዓለም ኑሮ ከባድ ነው ማለት ነው። በዚህ ዓለም በሽታ፥ ስደት፥ ሥቃይ፥ ድካም ስላለ የዚህ ዓለም ኑሮ የመቃተት ኑሮ ነው። ይህም መቃተት የመናፈቅ ወይም ለውጥን የመፈለግ መቃተት ነው። “እስከ መቼ ነው?” እንደ ማለት ነው። ይህን ሃሳብ ከሮሜ 8፡22 ጋር አስተያይ። 

የምንናፍቀው ወይም በምጥ የምንጠብቀው የትንሣኤን ጊዜ ነው። “በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለን።” በዚህ የሚለው ይህንን ሥጋችንን ነው። የምንቃትተውም «ከሰማይ የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ» በመናፈቅ ነው። 

የትንሣኤን አካል ከአጎናጸፈን በኋላ ራቁታችንን አንገኝም። ይህም ማለት አንሞትም ማለት ነው። ነፍስ ከተሰጣት ሥጋ በሞት ስትለይ ሥጋን ወይም ልብሷን ተገፈፈች ይባላል። አሁን የለበስነው አካል ሟች ስለሆነ በሞት ልንገፈፍ እንችላለን። የትንሣኤን ልብስ ከለበስን በኋላ ግን ከምት ባሻገር ስለምንሆን ዳግመኛ አንገፈፍም። 

«የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ» ይህ አነጋገር የትንሣኤ አነጋገር ነው። 1ኛ ቆሮ.15:51-57ን ተመልከት። በዚህ መሠረት የክርስቲያን ተስፋ ሞት ሳይሆን የክርስቶስ መምጣት ነው። ምክንያቱም በሕይወት እያለን ጌታ ከተመለሰ ሞትን ሳናይ የትንሣኤን አካል በመለወጥ እንለብሰዋለን፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው “ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ” በማለት ይናገራል። አሁን ሞትን ቀምሰን ሥጋችን ከበሰበሰ በኋላ በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ ትንሣኤን ከመጕናጸፍ፥ አሁን በሕይወት እያልን ጌታ መጥቶ የትንሣኤን አካል ብንለብስ እንመርጣላን። «ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ» ማለቱ የትንሣኤን አካል ልንቀበል እንጂ ልንሞት አንወድም ማለቱ ነው። ለዚህ ለትንሣኤ ተስፋ የመንፈስ ቅዱስን መያዣ ሰጠን፤ (ቁጥር 5 )። ከሞት እስከምንነሣ ድረስ የሚጠብቀን መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ከሞት ከተነሣን በኋላ የተለየ አካል መልበሱ ደግሞ በእግዚአብሔር በኩል የተሰጠ የተስፋ ቃል ነው። 

ከቁጥር 6-8 ባለው ክፍል ውስጥ የሚናገረው በሥጋችን በዚህ ዓለም ከጌታ ተለይተን ከመኖር ይልቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ከጌታ ዘንድ ያለሥጋ ትንሣኤን መጠበቅ የተሻለ መሆኑን ነው። የትንሣኤን አካል የምንለብሰው በዳግም ምጽአት ጊዜ ከሆነ ከዳግም ምድጽአት ወዲህ የሚዋቱ ክርስቲያኖች በጌታ ዘንድ ናቸው። ግን ከሥጋቸው ተለይተው ስለሆነ ከሁሉም የሚመርጡት የትንሣኤን አካል በመጕናጸፍ ከጌታ ጋር መሆንን ነው። «ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር» ማለት ከዚህ ከሥጋችን ተለይተን ያለትንሣኤ አካል መኖር ማለት ነው። ሆናም በሥጋ ከማደር በስደት መኖር ይመረጣል፤ ምክንያቱም አሁን ከሥጋ መለየት ከጌታ ዘንድ ማደር ስለሆነ ነው። 

የጅሆቫ ምስክሮች ሰው ሲሞት ከትንሣኤ በፊት በሕይወት የለም የሚሉት ትምህርት ይህንን የሐዋርያውን ቃል ይጻረራል። ምክንያቱም ከዚህ ዓለም በሞት ከሥጋችን መለየት ማለት በገነት ከጌታ ጋር ማደር እንደሆነ ሐዋርያው ስለሚናገር ነው! (5:8)። 

ጥያቄ 19. ሞትን እንዳይፈሩ ይህ ለክርስቲያኖች ማበረታቻ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? 

ቁጥር 9 «ብናድር ወይም ተለይተን ብንሆን» ሲል በሕይወት ብንኖርም ወይም በሞት ከዚህ ዓለም ተለይተን ብንሆን ማለቱ ነው። የእያንዳንዱ ክርስቲያን ግብ እግዚአብሔርን ሁሌ ማስደሰት መሆን ይገባዋል። በዚህች ምድር ሳለን ነው እግዚአብሔርን ማስደሰት የሚኖርብን፡፡ ይህም ማልት አካላችን፥ መንፈሳችን፥ አእምሮአችንና ፈቃዳችን በሙሉ ለእግዚአብሔር ክብርና ደስታ መስጠት አለባቸው። ይህ በዓለም የምንኖረው ሕይወት ጊዜያዊ በመሆኑ ለዘላለም አብረነው የምንኖረውን እግዚአብሔርን የማስደሰቱን ነገር በቂ ግንዛቤ ልንሰጠው ይገባናል። 

ጥያቄ 20. ይህ አመለካከት ለእግዚአብሔር ያለንን አገልግሉትና አኗኗሪችንን በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ነው ሊቀይር የሚችለው?

ቁጥር 10፡- ክርስቲያን በዳግም ምድዓት ጊዜ በሕይወቱ ስላደረገው አገልግሎት ሊጠየቅ በጌታ የፍርድ ወንበር ፊት ይቀርባል፡፡ ይህ የጥያቄ ጊዜ የፍርድ ወይም የኩነኔ ጥያቄ ሳይሆን የሽልማት ጉዳይ ነው። «መልካም ቢሆን ክፉ» ማለት መልካም የሚለው ወርቅ ብር የከበረ ድንጋይ እንዳለው ዓይነት ነው፤ (1ኛ ቆሮ.3፡13-15)። ክፉ የሚለውም እንደዝሙት፥ እንደመስረቅ፥ እንደመዋሸት የመሳሰሉ ለሰው ዓይን የተገለጡ የኃጢአት ሥራዎች ሳይሆኑ አሁን ሰው ከጌታ ምጽአት በፊት ሊመዝናቸው የማይችል ናቸው። ግን ጌታ በመምጣቱ የሚገልጣቸው እስከዚያ ቀን ግን ለእኛ ጥሩ መስለው የሚታዩ ናቸው። ለእኛ አሁን መጥፎ መሆናቸው ከታየ ቤተ ክርስቲያን በቅጣት ልታስወግዳቸው ይገባል፤ (1ኛ ቆሮ. 5:12 እና 13)። በዚህ ፍርድ ድርጊታችን፥ ሥራችንና ምኞታችን በሙሉ ይገለጻል። ለእግዚአብሔር ክብር የሚያስገኘውና በንጹሕ ሕሊና የተሠራው ነገር ነው የሚቆጠርልንና የሚያሸልመን፡፡ እግዚአብሔርን የማናገልገል ከሆነ አስተሳሰባችንም ጥሩ ካልሆነ እግዚአብሔር ሊሰጠን ያቀደውን ሽልማት አናገኝም። 

ብድራት ማለቱ ጽድቅን ወይም ኩነኔን ሳይሆን ሸልማትን ማለቱ ነው። ይህ የጥያቄ ጊዜ ስላለ ሕይወታችንን ለጌታ አገልግሎት በመስጠት ወደኋላ አንበል፡፡ ብድራትን የሚሰጠን ራሱ ጌታ ስለሆነና ደግምም ሳናገለግለው ኖረን በእርሱ ፊት ማፈርን አንፈልግምና። ከሞት በኋላ አንደገና ተመልሰን እግዚአብሔርን የማገልገሉን ዕድል አናገኘውም። 

ጥያቄ 21. ይህ እውነት ሕይወታችንን እንዴት አድርገን ለእግዚአብሔር አገልገሎት መጠቀም እንዳለብን የሚያሳስበን በእንዴት ዓይነት መልኩ ነው?

Leave a Reply

%d bloggers like this: