2ኛ ቆሮ. 5:16-21

ጥያቄ 7. ክርስቶስን በሥጋ ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው? 

ጥያቄ 8. በቁጥር 17 ላይ «ሁሉም አዲስ ሆኖአል» ማለት ምን ማለት ነው? 

ጥያቄ 9. በቁጥር 19 ላይ «እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ቁጥር 16፡- «ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም» ሲል ሥጋ ማለቱ በተፈጥሮ ሰው አስተሳሰብ መንገድ ማለቱ ነው። ለምሳሌ በዘር ወይም በእውቀት በሀብት መመካት የሥጋ ፀባይ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን የሚያገኘው በእነዚህና በመሳሰሉት ነገሮች አይደለም። በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ዳግመኛ ስለተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሰውን የምንገምተው «ክርስቶስን ያውቃል ወይስ አያውቅም?» በማለት ብቻ ነው። 

ጥያቄ 10. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎችን የሚያዩት በዓለማዊ አመለካከት ነው (ማለትም ዓለማውያን በሚመዝኑበት መመዘኛ ነው የሚመዝኑት) ወይስ መንፈሳዊ በሆነ አመለካከት? 

«ክርስቶስንም በሥጋ እንደሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም።» ክርስቶስን በሥጋ ማወቅ ማለት ጌታን በአዳኝነቱና በእግዚአብሔር ልጅነቱ ሳይሆን እንደተራ ሰው ማወቅ ነው። ለምሳሌ በምድር በነበረበት ጊዜ ብዙዎች «ይህ የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?» እያሉ በሥጋ ብቻ ነበር ያወቁት። ከእነዚያ ውስጥ ሐዋርያው አንዱ ነበር፡፡ አሁን ግን በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ጌታን በሚገባ አውቆታል። 

ቁጥር 17:- በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ተጀምሮአል። በመጀመሪያ ጌታን የተቀበሉ ሁሉ አዲስ ልደትን ተቀብለው የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን ታድሰዋል። ሁለተኛው ክርስቶስ ከመቃብር በመነሣቱ አዲስ ዓለም ተጀምሮአል። ይህንን በክርስቶስ ትንሣኤ የተገለጠውን አዲስ ዓለም እኛም በትንሣኤ ጊዜ እንቀበለዋለን፤ ግን አሁን የትንሣኤው ፍሬ የሆነውን መንፈስ ቅዱስንና ዳግመኛ መወለድን ተቀብለናል። የአዲሱን ዓለም ፍሪ አሁኑኑ በቅምሻ ስለተቀበልነው አዲሱ ዓለም አንደተጀመረ ይቆጠራል። “ሁሉም አዲስ ሆኖአል፡፡” 

ጥያቄ 11፣ አንድን ሰው እግዚአብሔር አዲስ ፍጥረት አድርጎ ካዳነው በኋላ የሚከሰቱትን ለውጦች በዝርዝር ጻፍ። 

ከቁጥር 18-21:- በዚህ ክፍል ውስጥ ሦስት ሃሳቦችን እዘረዝራለን፡፡ 

1ኛ/ የማስታረቅ አገልገሎት ተሰጠን! እኛ ከክርስቶስ ጋር ስለታረቅን በወንጌል ስብከት በኩል ሌሎችም ከክርስቶስ ጋር እንዲታረቁ ክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሉት ሰጠን። 

2ኛ/ ይህ የማስታረቅ አገልግሎት የእኛ ልመና ሳይሆን «ታረቁኝ» የሚል የእግዚአብሔር ልመና ነው። «እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና» ። እግዚአብሔር ራሱ ተበድሎ እኛን ጥፋተኞችን “ኑ ታረቁኝ” በማለት 

አስታራቂ የሆነውን አማላጅ ክርስቶስን ላከ። 

3ኛ/ ይህ ኃጢአተኞችን ከእግዚአብሔር ጋር የማስታረቅ ነገር በቀላሉ አልተገኘም። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ይቅር የሚለው ክርስቶስ የኃጢአተኞችን በደል በራሱ ላይ ስለወሰደ ነው። 

(ቁጥር 21) ክርስቶስ በእኛ ምትክ ኃጢአት ሆነ! እኛም በእርሱ የእግዚአብሔር  ጽድቅ ሆንን! 

ክርስቲያኖች ዛሬ እንደ እግዚአብሔር አምባሳደሮች ወይም አስታራቂ መልእክተኞች ናቸው። እግዚአብሔርን ወክለው ነው የሚናገሩት። ይህ ታላቅ አገልግሎት ኢየሱስን የሕይወት ዋጋ አስከፍሎታል፤ አስታራቂ መልእክቱንም የሚያቀርቡትን ሰዎች ከዚህ የበለበጠ ያስከፍላቸዋል። ይህ የእርቅ መልእክት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ይህን ወንጌል «ክርስቶስ ለኃጢአታችን ሞቶ የእርሱን ጽድቅ ሰጥቶናል» በማለት ልናጠቃልለው እንችላለን። 

ጥያቄ 12. ሀ/ እንደ እግዚአብሔር አምባሳደር የምትሠራው እንዴት ነው? ለ/ እግዚአብሔር በአንተ በኩል እንዴት አድርጎ ሰዎችን ወደ እርቁ እንዳመጣ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ። 

Leave a Reply