2ኛ ቆሮ. 6፡1-13

ጥያቄ 13. በቁጥር 1 ላይ «አብረን እየሠራን» ሲል አብረን ያለው ማንን ሲጨምር ነው? 

ጥያቄ 14. በቁጥር 1 ላይ እንደተጻፈው የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ መቀበል ማለት ምን ማለት ነው? 

ጥያቄ 15. ቁጥር 3ን አብራራ። 

ጥያቄ 16. በቁጥር 4 ማማጠን ምን ማለት ነው? 

ጥያቄ 17. ቁጥር 12ን አብራራ። 

በቁጥር 1 ላይ አብረን እየሠራን ያለው ሐዋርያው ከእግዚአብሔር ጋር ይሠራል ማለት ነው። ለዚህ ተመሳሳይ ሀሳብ በ1ኛ ቆሮ. 3፡9 ላይ ተመልከት። ይህም ሐዋርያው ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የሚሠራው የማስታረቅን ሥራ ነው። ከላይ በ5፡19 ላይ እግዚአብሔር ዓለሙን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ይማልዳል ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ ሐዋርያውም የቆሮንቶስን ክርስቲያናት ከእግዚአብሔር ጸጋ ፈቀቅ እንዳይሉ ይለምናል። በሐሰተኛ አስተማሪዎች በመታለል ከእምነታቸው ፈቀቅ ብለው የተቀበሉትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳያዳርጉ ይለምናቸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከጳውሎስ ጋር ተባብረው የጠፉትን ኃጢአተኞች ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነበረባቸው። የመዳንን ሥጦታና የማስታረቅን አገልገሎት ስጦታ በተሳሳተ አመለካከት ወይም በራስ ወዳድነት ማሰናከል አይገባንም። 

ቁጥር 2፡- ይህን ጥቅስ ከኢሳይያስ 49፡8 ላይ በመጥቀስ በክርስቶስ በኩል አሁን የመዳን ዘመን መሆኑን ያስታውሳቸዋል። ለዚህ ነው እግዚአብሔርም በኃጢአተኞች ላይ እንደመፍረድ ፈንታ እንዲድኑ የሚለምነው። ግን ይህ የመለመኛ ሰዓት የሚያልፍበት ወቅት ስለሚመጣ ሰው አሁን ንስሐ ቢገባ ይሻለዋል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ርቀው ወንጌልን በመጀመሪያ ወደ ሰበከላቸው ወደ ጳውሎስ እንዲመለሱ ያመለክታቸዋል። 

በቁጥር 3 ላይ ሐዋርያው ሕይወቱ ለማንም ሰው መሰናክል እንዳልሆነ ይናገራል። ሕይወታችንን ካልጠበቅን የእግዚአብሔርን መንግሥት ወደፊት እንደማራመድ ወደኋላ እንዲጎተት እናደርጋለንና፤ ሕይወታችንን ጌታ ይጠብቅልን! በውድቀታችንም በእግዚአብሔር ጸጋ የምንታደስ መሆናችንን መዘንጋት የለብንም! 

ጥያቄ 18. አንዳንድ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ወንጌልን የሚከላከልና ለሌሎች የመሰናከያ ድንጋይ ሊሆን የሚችል ነገር ምንድነው? 

በቁጥር 4 ላይ ማማጠን ማለት ከዚህ በላይ በ3፡1 የማመስገኛ ደብዳቤ ካለውና በ4:2 ሕይወቱን ለሰዎች ሕሊና ማመስገን ከሚለው ሃሳብ ጋር ይዛመዳል። በዚህ ቦታ ትርጉሙ ሕይወቱን በጥንቃቄ በመምራቱ ማንንም አላሰናከለም ግን እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ በጥንቃቄ የኖረ መሆኑን ያስረዳል። 

ከቁጥር 5-10: ባለው ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ለወንጌል ሲል ምን ያህል መከራና ችግር ይቀበል እንደነበር ያስረዳል። ግን በችግሩ ሁሉ ጌታ ከእርሱ ጋር ስለነበር አልተረታም! 

መሪነትን በተመለከተ ሁለት እውነታዎች አሉ፡- 

አንደኛ፡- መሪዎች ከሌሎች የበለጠ ችግር የሚደርስባቸው መሆኑን እናያለን። ለጳውሎስ ይህ ችግር ስደት፥ እንቅልፍ ማጣት፥ ከባድ ሥራ፥ ወዘተ ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ የጠፋ ኃጢአተኞች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ካለው ጉጉት የተነሣ ይህንን ጉዳት ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። አንዳንድ መሪዎች ከክርስቲያኖችና ካልዳኑት ሰዎች ጋር አለመግባባት ያጋጥማቸዋል፤ ነገር ግን የፈለገው ዓይነት መሰናክል ቢያጋጥማቸውም አገልገሎታቸውን መቀጠል አለባቸው። 

ጥያቄ 19. ሀ/ ለወንጌል ሲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መሪዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ምንድናቸው? ለ/ ይህ ክፍል መሪዎች በራሳቸው ፍላጎት ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥሪ ላይ ተመሥርተው አገልገሎታቸውን መጀመር እንደሚገባቸው የሚያሳየን እንዴት ነው? ሐ/ ይህ ክፍል አንድ መሪ የጠፋውን ሰው ወደ ኢየሱስ ለማምጣት ሊኖረው የሚገባውን ፍላጎት የሚያሳየን በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ነው? 

ሁለተኛ፡- ጳውሎስ አነጋገሩና አረማምዱ አንድ ዓይነት መሆኑን ያይ ነበር። ወንጌልን ይሰብክ የነበረው በእንደዚህ ዓይነት ችግር ብቻ አልበረም፤ ከበስተኋላ ያለው አስተሳሰቡ ንጹሕ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተደግፎ ማገልገሉንና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወቱ መታየታቸውንም ጭምር ነበር የሚመለከተው። 

ጥያቄ 20. አንድ መሪ ሲመራ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወቱ ውስጥ መታየታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ። 

ቁጥር 11-13፡- «አፋችን ለእናንተ ተከፍቷል» ማለት ሐዋርያው ምንም ሳያስቀር በንግግሩ ሃሳቡን የገለጻ መሆኑን ያስረዳል፡፡ «ልባችን ሰፍቶላችኋል» ማለት በሙሉ ልቡ ይወዳቸዋል ማለት ነው። «በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል» ማለት የሐዋርያው ልብ ሰፋ ብሉ በፍቅር ሲቀበላቸው የቆሮንቶስ ምእመናን ግን ለሐዋርያው ልባቸውን አጠበቡ! ይህ መሆን የለበትም! እርሱ እንደ ልጆቹ እያፈቀራቸው ሳለ ልባቸውን ለአባታቸው ከማጥበብ ይልቅ እርሱ እንዳፈቀራቸው ሊያፈቅሩት ይገባል። 

ጥያቄ 21. በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስለመሪነት የተሰጡትን መመሪያዎች በዝርዝር ጻፍ። 

Leave a Reply

%d bloggers like this: