ጥያቄ 22. ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ማለት ምን ማለት ነው?
ጥያቄ 23. በቁጥር 17 እና 18 ላይ «ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ» ሲል ምን ማለቱ ነው?
ቁጥር 14:- ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ የሚለው ስለ ጋብቻ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ ከማያምኑ ጋር ያለንን ግንኙነት ይመለከታል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ምእመናን ከማያምኑ ጋር በሚከተሉት መንገዶች እንዳይጠመዱ ይከለክላል። ጋብቻ 1ኛ ቆሮ. 7፡12-15፤ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ አለመብላት 1ኛ ቆሮ. 10፡27፤ በማያምኑ አጠገብ በልሳን አለመናር (ስላማይገባቸው ይሰናከላሉና በማያምኑ ፊት በልሳን መናርን ከለከለ።) 1ኛ ቆሮ. 14፡24፤ በማያምኑ ዳኞኛ ፊት ምእመናንን አለመክሰስ 1ኛ ቆሮ. 6፡5።
«አለ መጠመድ» ማለት በክርስቲያንና ክርስቲያን ባልሆነ መካከል ያለውን ልዩነት በሚያጠፉ መንገድ ከማያምን ጋር በአንድ ቀንበር ሥር መገኘት ማለት ነው፡፡ የሚያምንንና የማያንን ሲያነጻጽር ብርሃንና ጨለማ፥ ክርስቶስና ሰይጣን፥ የሚያምንና የማያምን፥ ቤተ መቅደስና ጣዖት ይላል። እንግዲህ እግዚአብሔር እንዲህ የለያያቸውን ሰው ማጋጠም የለበትም።
ሐዋርያው «በማይመች አካሄድ ከማያምኑ ጋር አትጠመዱ» አለ እንጂ በጠቅላላው ከማያምኑ ተለዩ አላለም፤ (1ኛ ቆሮ. 5፡9-10)፡፡ እነዚህም የማይመቹ መንገዶች ከላይ የተዘረዘሩት ዓይነቶች ናቸው። ኢየሱስ «እናንተ በዓለም ውስጥ ናችሁ እንጂ የዓለም አይደላችሁም» ይላል። እኛ የዓለም ብርሃንና ጨው መሆን አለብን። ይህም ማለት የማያምኑ ሰዎችን ማነጋር እነርሱን መርዳትና ለእነርሱ መመስከር ይገባናል። ይህን ስናደርግ እነርሱ የእኛን ሕይወት እንዳይቀይሩ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የእነርሱ አስተሳሰብ፥ አኗኗርና ስሜት ከእኛ የተለየ ነው የሚሆነው። ክርስቲያን ከእነርሱ ጋር በሚገናኝበት ጊዜ ራሱን ንጹሕ አድርጎ መጠበቁን መዘንጋት የለበትም።
ጥያቄ 24. አንድ ክርስቲያን ከዓለማውያን ጋር በአኳኋን ወይም በአስተሳሰብ ወይም ደግሞ በስሜት እንዴት አድርጎ ሊቆራኝ ይችላል?
በቁጥር 17 እና 18 ላይ ከማያምኑ ተለዩ ያለው ክክፉ ሥራቸው ተባባሪዎች አትሁኑ ማለቱ ነው፤ (መዝ.1:1 ተመልከት )። እግዚአብሔር አባት ሆና እንደልጆቹ ስለሚቀበለን እርሱን ከማይወዱት ጋር በመተባበር ልናሳዝው አይገባም። በ7፡1 ላይ ሐዋርያው ሀሳቡን በማጠቃለል የዚህ ተስፋ ቃል ካለን ቅድስናን ፍጹም እናድርግ ይላል፡፡ የተስፋ ቃል የሚለው እግዚአብሔር እንደ ልጆች አድርጎ እቀበላችኋለሁ ያለውን ነው።
ጥያቄ 25. ሀ/ ሰውነትን ያረክሳሉ ብለህ የምትገምታቸውን ነገሮች ዘርዝረህ ጻፍ። ለ/ መንፈስንም ሊያረክሱ የሚችሉ ነገሮችን ዘርዝረህ ጻፍ። ሐ / «ቅድስናን ልንጎናጸፍ» የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ስጥ።
ተባረኩልኝ ለረጅም ጊዜ ይሄን ጥናት እከታተላለሁ እና ተጠቅሚለሁ ተባረኩ