2ኛ ቆሮ. 8፡1-7

በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 8 እና 9 ሐዋርያው ስለመስጠት በሰፊው ያስተምራል። በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያኖች ከአይሁዳውያን በደረሰባቸው ስደት ምክንያት ብዙ ችግር ነበረባቸው። የችግራቸው መንሥኤ ያላቸውን ማካፈላቸው አልበረም፤ (የሐዋ.4:32-37)። ግን ይህ ያላቸውን ማካፈላቸው በስደት ምክንያት የደረሰባቸውን ችግር ለመቋቋም የወሰዱት እርምጃ ነበር እንጂ! 

ክርስትናን ላካፈሏቸው አይሁዳውያን የአሕዛብ ዕርዳታ በክርስቶስ ያላቸውን አንድነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ ተገንዝቦት ነበር። ስለዚህ ለዚህ አገልግሎት በጣም ይተጋ ነበር። ስለዚህ ነገር በሮማ 15:25-27 ያለውን ክፍል በመመልከት በበለጠ መረዳት ይቻላል። 

ጥያቄ 8. በቁጥር 1 ላይ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠው ጸጋ የምን ጸጋ ነው? 

ጥያቄ 9. «የጽህነታቸው ጥልቅነት የልገስናቸውን ባለጠግነት አብዝቶአል» ሲል ምን ማለቱ ነው? (ቁጥር 2) 

ጥያቄ 19. የክርስቲያን ስጦታ መነሻው ምንድነው? (ቁጥር 6) 

በቁጥር 1 ላይ ለመቄዶንያ ተሰጠ ያለው ጸጋ በልግስና የመስጠት ጸጋ ነበር። የክርስትና ሕይወት ምንጩ ምንጊዜም ቢሆን ጸጋ ነው። 

«በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠሪ እግዚአብሔር ነውና» (ፊልጵ.2:12-13)። የመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተባሉትም የፊልጵስዩስና የተሰሎንቄ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። 

ከቁጥር 2–3:- እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸው ምንም እንኳ ብዙ የሌላቸው ቢሆኑም ሠውተው ስለሰጡ ድህነታቸው የልግስናቸውን ትልቅነት አሳየ። ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ በማርቆስ 12:41-44 ተጽፏልና ያን ክፍል አውጥተህ አንብብ። 

በቁጥር 4፡- ቅዱሳን የተባሉት በኢየሩሳሌም የነበሩት ምእመናን ነበሩ። በቁጥር 5 እንደተጻፈው እውነተኛ የክርስቲያን መስጠት መንሥኤው አስቀድሞ ራስን ለእግዚአብሔር መስጠት እንደሆነ ይናገራል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንዳበለጸጉ ሁሉ አሁንም በዚህ በመስጠት ጸጋ መበልጸግ እንዳለባቸው ይነገራቸዋል (ቁጥር 7)። 

ጥያቄ 11. ራሳችንን አሳልፎ መስጠቱ አሥራት ከመስጠቱ የሚቀድመው ለምንድነው? 

መስጠትን በተመለከተ የመቄዶንያ ክርስቲያኖች በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ተምረዋል። አንደኛ፡- መስጠት መጀመር ያለበት ሁለንተናችንን “ለእግዚአብሔር በመስጠት” መሆን እንዳለበት ተማሩ፡፡ እግዚአብሔር ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንንም ጭምር እንዲቆጣጠርልን ለእርሱ አሳልፈን መስጠት ይገባናል። ሁለተኛ፡- እግዚአብሔር በሚሰጡት አሥራት ብቻ ደስተኛ እንደማይሆን ተገንዝበዋል፡፡ ያላቸው ሁሉ የእግዚአብሔር እንደሆነና ለእርሱ መሰጠት እንዳለበትም ተምረዋል። 

ጥያቄ 12. ከገንዘብ ሌላ ለእግዚአብሔር ልንሰጣቸው የሚገቡንን ነገሮች ጥቀስ። 

በመጨረሻም መስጠት ግዴታ ሳይሆን መታደል እንደሆነ ተረድተዋል። ምንም እንኳ በቦታው ባንገኝ፥ በመስጠታችን እግዚአብሔር በሌሎች ሥራ ውስጥ ተካፋዮች እንድንሆን ያደርገናል። ስለዚህ ጳውሎስ «ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው» (የሐዋ.20፡35) የሚለውን ቃል ደግሞ መጻፋ ሊያስገርመን አይገባም። 

ጥያቄ 13. እነዚህን መመሪያዎች በመጠቀም ሌሎች ለምን ለእግዚአብሔር መስጠት እንደሚገባቸው ልናሳውቅና ልናስተምራቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ። 

Leave a Reply