ጥያቄ 1. በቁጥር 19 ላይ «በምናገለግለው በዚህ ቸር ሥራ ከእኛ ጋር እንዲጓደድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመረጠ» ሲል ቸር ሥራ ያለው ምኑን ነው? (መጓደድ ማለት መጓዝ ማለት ነው)።
ጥያቄ 2. ቁጥር 20 እና 21ን በሰፊው አብራራ።
ከቁጥር 16-17:- ለኢየሩሳሌም ምእመናን ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበውን ገንዘብ ወደ ኢየሩሳሌም ለማድረስ መሪ ሆና እንዲያገላገል ቲቶ ተመረጠ። ቲቶም በሐዋርያው ስለታዘዘ ብቻ ሳይሆን በራሱ ልብ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያንና ለዚህ ለተባለው መዋጮ ታላቅ ትጋትን ያሳየ ሰው ነበር። ከዚህ ላይ የምንማረው አንድ ሰው በቤተ ክርስቲያን ለአንድ ሥራ ሲመረጥ ያ ሰው ለዚያ ሥራ ትጋትና ፍላጉት ያለው ሰው መሆን አለበት።
ከቁጥር 18-19፡- ቲቶ ብቻውን የአብያተ ክርስቲያናትን ገንዘብ ከቆሮንቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ እንዲሄድ የሐዋርያው ፈቃድ አልነበረም። ይህ ከሆነ ሐሜት እንደሚነሣ አውቆ ይህን ጥርጥር በሰው አእምሮ ውስጥ ላለማሳደር ከቲቶ ጋር ሌሎችን ለመላክ ወሰነ። እነዚህም በታማኝነታቸው በአብያተ ክርስቲያናት የተመሰከረላቸው ወንድሞች እንደሆኑ ያስታውቃል።
ከቁጥር 20-21:- «ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን»። ይህ ማለት ስለሚሰበሰበው ገንዘብ ሐሜት እንዳይነሣ ጥንቃቄ እናደርጋለን ማለት ነው። ይህንም ያዳረገው በአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን በርከት ባሉ ሰዎች እጅ ገንዘቡን በመላክና የተላኩት ሰዎች ስለታማኝነታቸው በአብያተ ክርስቲያናት የተመሰከረላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ነበር። «በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን የሰው ፊት ደገሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና» ። ይህም ማለት ንጽሕናንና ጥሩ ስምን በሰው ዘንድ መጠበቅ በክርስትና ሃይማኖት የሚፈለገብን ነገር ነው ማለት ነው። «ጌታ ልቤን ያውቃል ሰው ስለኔ በሚለው አልጨነቅም» ማለት መልካም እያደረገን በግፍ በምንታማበት ጊዜና ያን ሐሰተኛ ሐሜት ለማስተባበል ማስረጃ አቅርበን ሳይሳካልን ሲቀር እንጂ ሐሜት የሚያስነሣ ነገር እየሠራን መሆን የለበትም፤ 1ኛ ጴጥ.4፡14 እና 15ን ተመልከት።
እንደቤተ ክርስቲያን መሪ፥ ጳውሎስ ገንዘብ ነክ ነገሮችን የተለየ ትኩረት ሰጥቷቸው ነበር። ከዚህ በፊት እንደተመለከትነው ወንጌልን ለመስበክ ያነሣሣውን ሃሳብ እንዳይጠይቁት ሲል ደመወዝ ላለመቀበል ወስኖ ነበር (1ኛ ቆሮ. 9፡7-18)። አሁን ደግሞ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያናት ተብሎ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለብቻው በኃላፊነት ለመያዝ ፈቃዳኛ አልሆነም። ፈተና ውስጥ ለመግባት አይፈልግም ነበር። በተጨማሪም ምስክርነቱን የሚያጎድፉ ነቀፋዎች እንዲሰነዘሩበት አይፈልግም፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን የሚያጠፋበት አንደኛው የሰይጣን መንገድ ገንዘብን በተመለከተ ያላቸውን ምስክርነት የጎደፈና የተጠላ ማድረግ ነው።
ጥያቄ . ሀ/ የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በቅጡ ባለመያዙ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ምስክርነቱ ሲበላሽ አይተህ ታውቃለህ? ለ/ ገንዘብን በተመለከተ ጥሩ የሆነ ምስክርነት ማግኘቱ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድነው?
ከቁጥር 22-23፡- ሐዋርያው ገንዘቡን ይዘው ስለሚሄዱት ሰዎች የራሱን ምስክርነት ይሰጣል። እነዚህ ሰዎች ለዚህ ሥራ ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው የሐዋርያው ብቻ ሳይሆን የክርስቶስም ክብር ሆነው ተገኙ። እኛም በተጠራንበት ጥሪ ታማኝ በመሆን እንዲህ ለጌታና ለሚመኩብን ወንድሞች የማናሳፍር ሠራተኞች ሆነን እንድንገኝ ጌታ ይርዳን!
ከቁጥር 24፡- ፍቅር በልብ ቢኖር በሥራ መገለጥ አለበት። ይህንን እንዲያዳርጉ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያው ይመክራል።
ጥያቄ 4. ገንዘብ ነክ ነገሮችን በተመለከተ አንድ ቤተ ክርስቲያንና መሪዎችዋ መውሰድ የሚገባቸውን ጥንቃቁ የሚገልጹ መመሪያዎችን በዝርዝር ጻፍ።