2ኛ ቆሮ. 8:8-15

ጥያቄ 14. “በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አብራራ። 

ጥያቄ 15. የክርስትና ልግሥና መመርያ ምንድነው? (ቁጥር 9) 

ጥያቄ 16. ቁጥር 15ን የጠቀሰው ከየት ነው? ከየት እንደተጠቀሰ ካመለክትህ በኋላ ታሪኩን ሰፋ አድርገህ አብራራ ።

ቁጥር 8:- ሐዋርያው ማዘዝ ሲችል ግን በፍቅር ይለምናቸዋል። የእግዚአብሔር ሥራ በፍቅር እንጂ በግድ መደረገ የለበትም፡፡ በሌሎች ትጋት ሲል ቀደም ሲል የጠቀሳቸውን የመቄዶንያን አብያተ ክርስቲያናት ማለቱ ነው። «የፍቅራችሁን እውነተኛነት ልምረምር» ማለቱ ያላቸውን የክርስትና ፍቅር ሥራ ላይ በማዋል ማረጋገጥ እንዳለባቸው ማለቱ ነው። ከዚህ ጋር 1ኛ ዮሐ.3:17-18ን ተመልከት። 

ቁጥር 9:- የክርስቲያን ስጦታ ምንጩ የክርስቶስ ራሱን ለእኛ መስጠቱ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ላይ ከመምጣቱ በፊት በምንግሥተ ሰማይ ወስጥ በሺህ በሚቆጠሩ መላእክት በመገልገሉ፥ የሁሉም ነገር ፈጣሪ በመሆኑ፥ የሁሉም ነገር ባለቤት በመሆኑ ሀብታም ነው ማለት እንችላለን። ነገር ግን እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ለማድረግ ሲል መንግሥተ ሰማያትን ትቶ ወደ ምድር በመምጣት እንደ ድሃ ሰው ኖረ። ይህ ሁሉ የሆነበት ምክንያት እኛ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል እንድንሆንና የእግዚአብሔር በረከት ወራሾች እንሆን ዘንድ ነው። ጌታ ራሱን የሰጠው በምድራዊ ነገር ሀብታም እንድንሆን ሳይሆን ከምድራዊ ሀብት በበለጠው በመንፈሳዊ በረከት ሀብታም እንድንሆን ነው። 

ጥያቄ 17. ይህ ሁኔታ ለሌሎች መስጠትን በተመለከተ ምን ያስተምረናል? 

ከቁጥር 10-12:- መስጠት የምንችለው ካልን ነው። ሰው እንዳለው መጠን እንዲሰጥ ይጠበቅበታል እንጂ ከአቅሙ በላይ እንዲሰጥ አይጠበቅበትም። እንዲሁም ለመስጠት ፍላጎት ካለ ያ ፍላጐት በሥራ ላይ ካልዋለ ወሬ ብቻ ሆኖ ይቀራል። «ማድረጉንም ፈጽሙ» በማለት ይህንኑ ይመክራቸዋል። 

ከቁጥር 13-14:- የክርስቲያን መስጠት አንደኛ፡- በግድ ሳይሆን በፈቃዱ ነው። ሁለተኛ፡- ያላቸው ባዶ ሆነው የሌላቸው በእነርሱ እንዲበለጽጉ ሳይሆን ባላቸውና በሌላቸው መካከል እኩልነት እንዲመሠረት ነው። “ትክክል እንዲሆን ነው እንጂ … የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ”። በትክክል እንዲሆን ማለት እኩልነት እንዲመሠረት ማለቱ ነው። እኩልነት በፈቃድ እንጂ በአዋጅ ወይም በገድ እንዳይሆን የክርስትና ሃይማኖት ያስተምራል። እንዲሁም የክርስትና ሃይማኖት አንድ ሰው ባለው ሀብቱ የፈለገውን እንዲያደርግበት ሳይሆን የራሱን ችግር ካቃለላ በኋላ ለሌላቸው በልግስና እንዲያካፍል ነው! (በተጨማሪ ኤፌ.4፡28፤ 1ኛ ጢሞ. 6፡14-19)። 

ጥያቄ 18. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሀብታምና ድሃ ምእመናንን በተመለከተ ይህ ነገር እንዴት ነው ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው? 

ቁጥር 15፡- ይህን ክፍል የሚጠቅሰው ከዘፀ.16፡ 17ና 18 ላይ ነው። እስራኤላውያን መና እንዲሰበስቡ ታዘዙ፡፡ ለየቤተሰባቸው የሚበቃቸውን እንጂ ትርፍ እንዲሰበስቡ አልተፈቀደላቸውም ነበር። አንዳንዶች ግን ከስገብገብነት የተነሣ ትርፍ ሰበሰቡ። ግን በኋላ በተሰፈረ ገዜ «አንዱ አብዝቶ አንዱም አሳንሶ ለቀመ። በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂት ለለቀመም አልጎደለበትም፡፡” አሁንም በክርስትና እምነት ሳለን ሰው የሚበቃው ካለው ትርፋን ከማጃብ ላሌለው ወንድሙ እንዲያካፍል ታዟል። ይህም የፍቅርና የርኅራኄ መግለጫ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔርም የመታመን መግለጫ ነው። የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፤ ማቴ.6፡25-33፤ ኤፌ.4:28 1ኛ ጢሞ.6፡17-19። 

ጥያቄ 19. ከምዕራፍ 8 መስጠትንና አሥራትን በተመለከተ የተማርከው ትምህርት ምንድነው?

Leave a Reply

%d bloggers like this: