2ኛ ቆሮ. 9፡1-5

ጥያቄ 5. ቁጥር 4ን አብራራ፤ በተለይ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኗችሁ … እኛ እንዳናፍር ይሁን» ያለውን አብራሪ። 

ከቁጥር 1-2:- ሐዋርያው ጳውሎስ ከአንድ ዓመት በፊት የቆሮንቶስ ሰዎች ይህን መዋጮ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል ብሎ ለመቄዶንያ ሰዎች ተናግሮ ነበር። የቆሮንቶስ ሰዎች በውስጣቸው በተነሣው ጭቅጭቅ ምክንያት የሰጡትን ተስፋ ገና ሥራ ላይ ስላላዋሉት ጳውሎስ ስለእነርሱ ለመቄዶንያ ሰዎች በተናገረው ማፈር አልፈለገም። ሆኖም ይህ ከአንድ ዓመት በፊት የቆሮንቶስ ሰዎች ማዘጋጃት ለመቄዶንያ ሰዎች መነሳሻ ሆኖ እንደነበር ይነግራቸዋል። አሁን በአጸፋው የመቄዶንያ ሰዎች የቆሮንቶስን ሰዎች እንዲያበረታቸው ሐዋርያው ስለመቄዶንያ ክርስቲያኖች ትጋት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይናገራል። ይህ የቅንዓት ፉክክር ሳይሆን ቅዱስ የሆነ እርስ በርስ ማበረታታት መሆኑን ተገንዝበን የአንድ ቤተ ክርስቲያን ትጋት ሌሎችን እንደሚያበረታታ ማወቅ አለብን። 

ቁጥር 3፡- ይህ የተመካባቸው ትምክህት ወሬ ብቻ ሆኖ እንዳይገኝ ተግተው የገቡትን ቃል ኪዳን ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚያበረታቷቸውን ወንድሞች አስቀድሞ ወደ ቆሮንቶስ ይልካል። 

ቁጥር 4:- ይህንንም የደረገበት የመቄዶንያ ሰዎች ወደ ቆሮንቶስ ከሐዋርያው ጋር ከመጡ ሐዋርያው እንዳያፍር ነው። ሆኖም እዚህ ላይ የሐዋርያውን ጥበብ መገንዘብ አለብን፡፡ በሐዋርያውና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል መቃቃር ስለነበር «እናንተ እንዳታፍሩ» ብሎ መናገር አልፈለገም። የሰጡትን ተስፋ ሥራ ላይ ለማዋላቸው ሐዋርያው ብቻ ሳይሆን እነርሱም ማፈር እንደሚገባቸው ገልጽ ነው። ይህንን ከመናገር ግን ሐዋርያው ይቆጠባል። 

ቁጥር 5፡- «ከስስት ሳይሆን» ይላል። ስጦታ በደስታ መደረግ አለበት እንጂ በቅሬታ መሆን የለበትም። የቆሮንቶስ ሰዎች ከመቄዶንያ አስቀድመው ተስፋ እንደሰጡ መጠን አሁንም ከመቄዶንያ አስቀድመው ስጦታውን ማዘጋጃት እንዳለባቸው ይነግራቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኃይለ ቃልንና ችክ ያለ ልመናን በመጠቀም ምዕመናን ገንዘብ እንዲሰጡ ያደርጋሉ። በዚህ ምክንያት ሰዎች ከደስታ ሳይሆን ከአንገት በላይ በሆነ ስሜት ተገፋፍተው ይሰጣሉ። መሪዎች የአሥራትን አሰጣጥ እውነታ የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው፤ ይህም ሲሆን በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ከሰዎች ልቦና ውስጥ ማውጣት አይገባቸውም። 

ጥያቄ 6. እንዴት አድርገው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምዕመናንን ለተሳሳተ ዓላማ ገንዘብ እንዲሰጡ ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ።

Leave a Reply

%d bloggers like this: