2ኛ ቆሮ. 9፡6-15

ጥያቄ 7. በቁጥር 6 ላይ ሐዋርያው መስጠትን ከምን ጋር ያመሳስላል? 

ጥያቄ 8. በቁጥር 10 መሠረት መስጠት የማይችል ክርስቲያን ሊኖር ይገባዋል? 

ጥያቄ 9. በቁጥር 12 መሠረት የመስጠት መንፈሳዊ ውጤት ምንድነው? 

ጥያቄ 10. የመስጠት አርአያችን ማነው? (ቁጥር 15) 

ቁጥር 6፡- መስጠት እንደመዝራት ይመስላል። በግብርና ዓለም በጥቂት የዘራና በብዙ የዘራ እኩል አያጭድም። እንዲሁም በመስጠት ለጋስነት ብዙ በረከትን ያስገኛል፤ (ሉቃ.6፡38)። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ብዙ ለመሰብሰብ ብሎ በንግድ መንፈስ መስጠት የለበትም። ይህ አሰጣጥ በደስታ የሚደረግ መሥዋዕት ሳይሆን ንግድ ስለሚሆን እግዚአብሔርን አያስደስተውም፤ (ዕብ.13:16)። ነገር ግን በልግስና ለሚሰጥ ክርስቲያን ይህ የዘሪው ተስፋ መጽናኛ ሊሆነው ይገባል። 

ጥያቄ 11. በመስጠትና በመዝራት መካከል ያለውን መመሳሰል ወይም ግንኙነት አብራርተህ ገልጽ። 

ቁጥር 7:- የክርስቲያን ስጦታ እንደግብር በገድ ሊሆን አይገባም። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምስጋና መሥዋዕት ስለሆነ በግድ ከሆነ ትርጉሙን ይቀይራል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከስስት መንፈስ ነፃ ሆነው በልግስናና በደስታ መስጠት አለባቸው። አለመስጠትም በደል ነው፤ ቅር እየተሰኙ መስጠትም በደል ነው። ስለዚህ ትክክለኛው ነገር የማይነገረውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እያሰብን በልግሥናና በደስታ መስጠትን መማር ነው። 

ጥያቄ 12. ለምንድነው በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ሰዎች አሥራት የሚሰጡት? ከልማድ የተነሣ ነው? የሚሰጡበትስ ምክንያት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነው? ለምን? 

ከቁጥር 8-9:- ከመዝሙረ ዳዊት 111 (112) በመጥቀስ የክርስቲያንን መስጠት ይደግፋል። በዚህ መዝሙር ላይ የተጻፈው ስለጻድቅ ሰው ነው። በቁጥር 1 ላይ “እግዚአብሔርን የሚፈራ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድ ሰው ምስጉን ነው” ብሎ ይጀምራል። ከዚያም በቁጥር 9 ላይ ይህንን በ2ኛ ቆሮንቶስ 9፡8 እና 9 የተጠቀሰውን እናነባለን። «በተነ ለችግረኞች ሰጠ» በማለት የአሰጣጡን ልግስና ይገልጻል። ለቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ይህንን እንዲህ ለመስጠት የሚያስችለውን ጸጋ እግዚአብሔር ስለሆነ የሚሰጠው ለእነርሱም ሊሰጥ ዝግጁ መሆኑን ያስረዳል። 

በቁጥር 8 ላይ ጳውሎስ አንድ ትልቅ እውነታን ያስተምረናል። እግዚአብሔር በግላችን የሚሰጠን በረከቶች ከአሰጣጣችን ጋር ግንኙነት እንዳለው ያስተምረናል። በለጋስነት የሚሰጥን ሰው እግዚአብሔር ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን አግኝቶ ለበጎ ሥራ ይበዛ ዘንድ ጸጋን እንደሚያበዛለት ቃል ይገባል። አንድ ሰው እንዳለው «እግዚአብሔር ከሚሰጠን በላይ ለእርሱ መልሰን የምንሰጠው ከቶ አይኖርም።» እግዚአብሔር በሚሰጠን በትንሽ ነገር ታማኞች መሆናችንን ካሳየን፥ በትልቁ ነገር ሊተማመንብን ይችላል። የሚሰጡትን የተለያዩ ስጦታዎች በአግባቡ የማንጠቀምበት ከሆነ ሌላ የበለጠ ስጦታ ለመስጠት በእኛ ላይ አይተማመንብንም፤ (ሚልክ.3፡ 6-12 ተመልከት )። 

ቁጥር 10፡- ማንም ክርስቲያን «የምሰጠው የለኝም፤ ስለዚህ ተቀባይ እንጂ ሰጭ መሆን አልችልም» ማለት አይገባውም። በእግዚአብሔር ፊት የስጦታ ትልቅነት የሚመዘነው በተሰጠው ብዛት ሳይሆን ባስቀረው ብዛት ነው። በብሉይ ኪዳን ከአሥር አንድ መስጠት ተገቢ ነበር። የአሥራቱ ብዛት ሳይሆን በእርግጥ ሰው ካለው አሥራት መስጠቱ ነበር የሚታየው። በስጦታ ብዛት ከሆነ ሀብታም ከአንድ ሺህ ብር ሃምሳ ብር ቢሰጥ ስጦታው ትንሽ ነው፤ አሥራቱ ከሺህ ብር መቶ ብር እንጂ ሃምሳ ብር ስላልሆነ። ጽሃው ግን ሃምሳ ብር ኖሮት ከሃምሳው አሥራት አምስት ብር ብቻ ሳይሆን አሥር ብር ቢሰጥ ሃምሳ ብር ከሰጠው የእርሱ ይበልጣል፤ (ማር.12: 43-44)። 

በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከውጭ አገር ከሐብታም ክርስቲያኖች የሚላከውን የስጦታ ብዛት በማየት እራሳችን ከመስጠት በመቆጠብ የመስጠትን ጸጋ ልናጣ ስለምንችል መጠንቀቅ አለብን። መፍትሄው ስጦታውን አለመቀበል ሳይሆን «ስጡ» የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል መከተል ነው። «ለዘሪ ዘርን… የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል»! (ቁጥር 10)። 

ጥያቄ 13. ሀ/ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙ ድኃና ሀብታም ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን አሥራት ይሰጣሉን? ለ/ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ችግር በቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ ይታያል? እንዴት? 

ቁጥር 11:- «በሁሉ ነገር ባለወጠጎች ትሆናላችሁ» ማለቱ ስለቁሳቁስ ብልጽግና ሳይሆን ስለመንፈሳዊ ቸርነትና መልካም ተግባር ነው የሚናገረው። የእግዚአብሔር ልጆች በመልካም ሥራ ድሆች እንዲሆኑ እግዚአብሔር ፈቃዱ አይደለምና ለበጎ ሥራ የተጋን እንሁን፤ (ኤፌ. 2:10)። 

ከቁጥር 12-14:- ክርስቲያን ለተቸገረ ወንድሙ ሲሰጥ ያ ችግረኛው ወንድም ስለተቀበለው ስጦታ እግዚአብሔርን ስለሚያመሰግን የክርስቲያን ስጦታ እግዚአብሔርን ያከብራል። ስለዚህም የክርስቲያን ስጦታ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል። እንዲሁም በተቀባዩ ዘንድ የክርስቲያንን ፍቅር ይመሠርታል። ፍቅርም ስላለ ክርስቲያኖች እርስ በርስ በጸሎት ይደጋገፋሉ፤ (ቁጥር 14)። 

ቁጥር 15፡- በክርስቲያን የስጦታ አገልግሎት አለመሰለፍ የማይነገረውን የእግዚአብሔርን ስጦታ አለመገንዘብ እንደሆነ መረዳት አለብን። ይህ በልጁ በኩል የሰጠን ስጦታ ነው፤ (ዮሐ.3፡16)። የእግዚአብሔርን ታላቅ ስጦታ በነፃ ስላገኘን እኛም እንደአባታችን ይህንን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ፈቃደኞች መሆን አለብን። 

ጥያቄ 14. ከምዕራፍ 8 እና 9 መስጠትንና አሥራትን በተመለከተ ልንከተላቸው የሚገቡንን የተለያዩ መመሪያዎች በዝርዝር  ጻፍ። 

Leave a Reply

%d bloggers like this: