ምሳሌ 1-9

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች የሚፈተኑባቸውና ማድረግ የሚፈልጉትን የኃጢአት ዓይነት ዘርዝር። ለ) በጣም የተለመደው የትኛው ነው? ለምን? ሐ) የእግዚአብሔርን ጥበብ በተገቢው መንገድ መረዳት ወጣት ክርስቲያኖችን በኃጢአት ከመውደቅ እንዴት ይጠብቃቸዋል? 

እግዚአብሔርን በሚያስከብርና ክርስቲያኖችን በሚጠቅም መንገድ ለመኖር የሚያስችለው ፈሪሀ-እግዚአብሔር የሞላበት ጥበብ ብዙውን ጊዜ ከአብያተ ክርስቲያናችን ከሚጕድሉ ነገሮች አንዱ ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማምለክ እንወዳለን፤ መዘምርና ስብከት መስማትም እንወዳለን። አሥራታችንን ለመስጠት እንኳ ፈቃደኞች ነን፤ ዳሩ ግን ከሰኞ እስከ ቅዳሜ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የመኖር ነገር ሲመጣ የበለጠ ያስቸግረናል። በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መኖር ለብዙ ክርስቲያኖች አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶች ራሳቸውን ከማያምኑ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ይለያሉ፤ ሌሎች ደግሞ ከማያምኑ ሰዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመፍጠር ኃጢአት ወደሞላበት ኑሮ ይዘፈቃሉ። 

ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች ልክ እንደማያምኑ ሰዎች ስለሚኖሩ፥ በዓለም ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ተጽዕኖ ያጣሉ። የማያምኑ ሰዎች ጉቦ ይቀበላሉ። በሥራ ቦታ ያሉ የበታቾቻቸውን ቅን ፍርድ በጐደለው መልክ በመያዝም ሆነ በሚያከናውኑት ሥራ ከማያምኑ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ዝንባሌ አላቸው። እንደ የማያምኑ ሰዎች በፍትወተ ሥጋ ኃጢአት ይወድቃሉ። ጥሩ ነጥብ ለማግኘት ከሌሎች ተማሪዎች የፈተና ወረቀት መልስ ይገለብጣሉ፤ ለልማት የተመደበን ገንዘብ ወይም እህል ባልሆነ መንገድ ለማግኘት ይሞክራሉ። የሚያሳዝነው በማያምኑ ሰዎችና በክርስቲያኖች መካከል ልዩነት አለመኖሩ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ጥበብ የሚገኘው በጥቂቱ ነው። ሆኖም እኛ በስም ክርስቲያኖች ብንሆንም ብዙ ጊዜ ከእግዚአብሔር ይልቅ በዓለም አመለካከት ለመጠበብ እንሞክራለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በዓለም አመለካከት ጥበበኞች ለመሆን በመፈለግ ወጥመድ ውስጥ የሚገቡት እንዴት ነው? ሐ) ይህ ብዙውን ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ላይ የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው? 

በመጽሐፈ ምሳሌ እንደተጻፈው ፈሪሀ-እግዚአብሔር የሞላበት ጥበብ የተሻለ አምልኮ እንድናቀርብ የሚረዳን አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንድንኖር ይረዳን ዘንድ የተጻፈ ነው። እንደ ዓለም መኖር የምንጀምረውና በክርስትና ሕይወታችንም ፍሬ አልባ የምንሆነው መጸሐፈ ምሳሌን ቸል በምንልበት ጊዜ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 1-9 አንብብ። ሀ) በአኗኗራችን ፈሪሀ-እግዚአብሔር የሞላበት ጥበብ ሊሰጡን የሚችሉትንና በዚህ ክፍል ውስጥ በቀረቡት ምሳሌዎች ውስጥ ያሉትን የተለያዩ የሕይወት ክፍሎች ግለጽ። ለ) ከእነዚህ የሕይወት ክፍሎች መካከል ብዙ ክርስቲያኖች ለመከተል የሚከብዷቸው የትኞቹ ናቸው? ለምን? ) እነዚህ ምሳሌዎች ለእግዚአብሔር ክብር የተሻለ ሕይወት እንድንኖር ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው? 

የመጽሐፈ ምሳሌ የመጀመሪያ ዐቢይ ክፍል የሆነው ምሳሌ 1-9፣ በአመዛኙ በአሳብ የተያያዙ በርካታ ምሳሌዎችን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህ ትምህርት ሰጪ ምሳሌዎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ በተናጥል ከሚታዩ ምሳሌዎች ይልቅ አጭር ስብከት ሊሆኑ የሚችሉና ጥበብን ለሚፈልጉ ሰዎች መመሪያ የሚሆን እውነትን የሚሰጡ ናቸው። ከምዕራፍ 10 ጀምሮ ግን ምሳሌዎቹ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉት ኦጫጭር ኣባባሎች እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እውነቶችን የሚያንጸባርቁ ይሆናሉ። 

ባለፈው ጥናታችን የጥበብን ልዩ ልዩ ዓላማዎች ተመልክተናል (ምሳሌ .4፡7)። ይህ የመጽሐፉ መግቢያ ምሳሌዎቹን የማወቅና የመታዘዝ አስፈላጊነትን ይነግረናል። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ በእውነት ጥበበኞች እንሆናለን። ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ሰዎች ጋር ትክክለኛ የሆነ ግንኙነት ይኖረናል። ቀጥሎ በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተካተቱትን ዐበይት ትምህርቶች ተመልከት፡- 

1. በኢየሱስ ክርስቶስ ከማያምኑና የሕይወት አኗኗራቸው እግዚአብሔር ከሚፈልገው አኗኗር ጋር ከማይጣጣም ሰዎች ጋር ከመጠን በላይ የመቀራረብ አደገኝነት (ምሳሌ 1፡8-19)፡- ለጓደኝነት የመረጥካቸውና በከፍተኛ ደረጃ የምትቀርባቸው ሰዎች በሕይወትህ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ጓደኞችህ የማያምኑ ሰዎች ከሆኑ ወይም ክርስቲያኖች ነን እያሉ ፈሪሀ-እግዚአብሔር የሌለበትን ኑሮ የሚኖሩ ከሆነ ወደ ጥፋት እንደሚመሩህ ጥርጥር የለውም። እነርሱ የሚጋፈጡትን ቅጣት አንተም ትቀበላለህ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ጓደኞችህ ለክፉ ወይም ለመልካም ነገር ተጽዕኖ ያሳደሩብህ እንዴት ነው? 

2. ፈሪሀ-እግዚአብሔር የሞላበትን ጥበብ የመተው አደገኛነት (1፡20-33)፡- በቅኔያዊ ቋንቋ አቀራረብ፥ ጥበብ ሁሉም ሰዎች እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲኖሩ እንደምትፈልግ ሴት ሆና ቀርባለች። አልተደበቀችም፤ ነገር ግን በዓለም ሁሉ በመዞር ሰዎች እንዲሰሟት፥ እንዲከተልዋትና ፈቃደኛ ለሆኑት የሕይወትን ቃል ኪዳን፥ ሊሰሟትና ሊከተሏት ለማይፈልጉ ሁሉ ደግሞ ፍርድ እንደሚመጣባቸው በመናገር ታስጠነቅቃለች። 

3. እውነተኛ ጥበብ ለግለሰቡ የሚያስገኘው ጥቅም (ምሳሌ 2-4)፡- ጥበብ ሊከተላት ለሚጥር ሰው ምን ታደርጋለች? እነዚህ ጥቅሶች በጥበብ መራመድ የሚያስገኛቸውን በርካታ ጥቅሞች ይዘረዝራሉ። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረት ለመጠበቅ የሚችለው «እግዚአብሔርን የሚፈራ» እና ጥበበኛ ሲሆን ብቻ ነው፤ ይህንን ሲያደርግ መንፈሳዊ ጥቅሞችን ያገኛል። ጥበብ የሰውን አስተሳሰብና ድርጊት ይለውጣል። ሰዎችን ከሚያጠምድ፥ ባሪያ ከሚያደርኛ ከሚያጠፋ ኃጢአት ላይ እንዳይወድቁ ይከላከላል። ጥበበኛ ለሆነው ሰው ደግሞ ሥጋዊና ዘላለማዊ በረከትን ያመጣል። 

4. ጥበብ ወጣቶችና የበሰሉ ሰዎች ጊዜያዊ በሆነ የፍትወተ ሥጋ እርካታ እንዳይሳቡ ትጠብቃለች (ምሳሌ 5-7)። የተሳሳተና ጊዜያዊ እርካታ በሚሰጥ የፍትወተ ሥጋ ግንኙነት የተሳተፉትን ሰዎች ጥፋተኛነታቸውን እንዲገነዘቡ ታደርጋለች። እግዚአብሔር በሰጠን የትዳር ጓደኛ ብቻ እንድንረካ ታስተምራለች። በዚህም ከእግዚአብሔርና ከትዳር ጓደኛችን ጋር ዘላቂ የሆነ ደስታና መተማመን ይኖረናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ ክፉና የተሳሳተ የፍትወተ ሥጋ ኃጢአት ሰዎችን ሲያጠፋ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) በርካታ ሰዎች በፍትወተ ሥጋ ኃጢአት የሚወድቁት ለምንድን ነው? ሐ) ስለ ፍትወተ ሥጋ ኃጢአት የመጨረሻ ውጤት ከመጽሐፈ ምሳሌ ምን መማር ይችላሉ? 

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 6፡16-19 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር የሚጠላቸውን ሰባት ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ሰባት ነገሮች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚታዩት እንዴት ነው? ) የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆንህ መጠን የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች በእነዚህ ሰባት ኃጢአቶች እንዳይካፈሉ ምን ማድረግ ትችላለህ? 

5. ጥበብና ሞኝነት ተነጻጽረው እናገኛለን (ምሳሌ 8-9)። ሰዎች ጥበብንና ከእርስዋም የሚገኘውን ጥቅም በመካፈል ደስ ይላቸው ዘንድ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ከምትጣራ ሴት ጋር ተነጻጽራለች። 

ማስታወሻ፡- ብዙ ክርስቲያኖች በምሳሌ 8 የተጠቀሰው ጥበብ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይናገራል ብለው ያስባሉ። የምሳሌ ምዕራፍ 8 ጸሐፊ በተምሳሌት የሚናገረው ስለ ጥበብ እንጂ ስለ እግዚአብሔር አይደለም፡፡  ሆኖም ፈሪሀ- እግዚአብሔር የሞላበት መለኮታዊ ጥበብ የሰራችው አብዛኛዎቹ ሥራዎች (ለምሳሌ፡- በመፍጠር ሥራ ተካፋይ መሆን) ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የተከናወኑ ናቸው። በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥበብ ተብሎአል (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡24፤ ቈላስይስ 1፡1)፡፡ 

የጥበብ ጠላት ሞኝነት ነው። ጥበበኛ ሰው እግዚአብሔርን በመፍራትና ትእዛዛቱን በመጠበቅ ሲኖር፥ ሞኝ ደግሞ የእግዚአብሔርን ጥበብ መናቅና በኃጢአት ወጥመድ በመያዝ ለቅጣት ይዳረጋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሰዎች በጥበብ ይኖሩ ዘንድ በቤተ ክርስቲያንህ ለማስተማር እነዚህ ምዕራፎች እንዴት ሊጠቅሙ ይችላሉ? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

1 thought on “ምሳሌ 1-9”

  1. ሠላም ሠላም ወገኖቼ
    ሠላም ለእናንተ ይሁን ይህን ክፍል ሳነበው ስለ ምሳሌ ምዕራፍ 8 እኔም ከመጀመሪያው በእግዚአብሔር መንፈስ የተረዳሁት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ነው ።
    አሁንም እኔ የምቀበለው ምሳሌ ምዕራፍ 8 ን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተነገረ ነው ።
    የምፈልገውንም ወስጃለሁ (ተጠቅሚያለሁኝ) ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ።
    እግዚአብሔር አምላክ ይባርካችሁ ።

Leave a Reply

%d bloggers like this: