ኢዮብ 15-31

እግዚአብሔር መከራ እንድንቀበል ከሚፈቅድባቸው ዓላማዎች አንዱ ሌሎች መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ ማስተዛዘንና ማጽናናት እንድንችል ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 1፡3-7 ተመልከት)። እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በማጣቱ ስለተሠቃየና ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በመስቀል ላይ በተቀበለው መከራ ስለተሠቃየ፥ በመከራችን ጊዜ እንዴት እንደሚያጽናናን ያውቃል (ዕብራውያን 2፡17-18)። እኛም ደግሞ መከራና ሥቃይ በምንቀበልበት ጊዜ፥ በዙሪያችን ያሉ መከራ የሚቀበሉ ሰዎችን ለመርዳት እንችላለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መከራ የተቀበለ ሰው መከራ የሚቀበሉ ክርስቲያኖችን ለማጽናናት ከሌሎች የሚሻልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ መከራ በመቀበል ላይ ያሉትን ሰዎች ለማጽናናት ከዚህ በፊት መከራ በተቀበሉ ሰዎች ምሳሌነት ስለ መጠቀም ምን ያስተምረናል? 

የኢዮብ ወዳጆች እንደ እርሱ መከራ አልተቀበሉም ነበር፤ ስለዚህ ሊራሩለት አልቻሉም። ለኢዮብ የሰጡት መልስ ሊታገሱት ያለመቻላቸው ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነበር። እነርሱ ለኢዮብ አጽናኞቹ ሳይሆኑ ከሳሾቹ ሆኑ። መልካም የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ቢጠቀሙም ትክክል አልነበሩም። አሳባቸውም ጥፋተኛ ያልነበረውንና ያለ ኃጢአቱ መከራ የተቀበለውን የኢዮብን ሕይውት የሚመለከት አልነበረም። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢዮብ 15-31 አንብብ። ሀ) የኢዮብ ወዳጆች በኢዮብ ላይ የቀረቡትን ክስ አሳጥረህ አቅርብ። ለ) ኢዮብ ለክሶቹ የሰጣቸውን መልሶች አሳጥረህ አቅርብ። ሐ) ከዚህኛው የመጽሐፈ ኢዮብ ክፍል የምትማራቸውን መንፈሳዊ እውነቶችን ዘርዝር። 

ኢዮብ 15-31 በኢዮብና በወዳጆቹ መካከል የተደረጉ ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ክርክሮች 

ኢዮብ 15፥ የኤልፋዝ ክስ፡- ኢዮብ ለወዳጆቹ በሚሰጠው ምላሽ እጅግ ቍጠኛ እየሆነ በመጣ ቁጥር፥ የወዳጆቹም ትዕግሥት እየቀነሰ መጣ። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የምናገኛቸው የወዳጆቹ ንግግሮች ትሕትና የጐደላቸው ናቸው። ኢዮብ ራሱን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ሞኝነትንና ጻድቅ ያለመሆንን እንደሚታይበት በመግለጥ ኤልፋዝ ከሶታል። የኃጥአንን የመጨረሻ ዕድል በማስታወስ፥ ኢዮብን ንስሐ እንዲገባ አበረታትቶታል። 

ኢዮብ 16-17 የኢዮብ ምላሽ፡- ኤልፋዝ የኢዮብ ችግር ኃጢአተኝነቱ እንደሆነ አድርጎ በማቅረቡ፥ ኢዮብ ሁለት ዋና ዋና እውነቶችን መሠረት በማድረግ ምላሹን አቀረበ። በመጀመሪያ፥ ሊወነጀልበት የሚገባ ጉልህ የሆነ ኃጢአት እንደሌለበት ተናግሯል። በሁለተኛ ደረጃ፣ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነገር የማድረግ ችሎታ እንዳለውና ኢዮብን በደዌ መምታት እንኳ እንደሚችል ተናግሯል፤ ዳሩ ግን ኢዮብን ጎዳው፤ ምክንያቱም አሁን እርሱ ላይ የሚያደርገው ነገር ወዳጁ ሳይሆን ጠላቱ እንደሆነ የሚያስመስል በመሆኑ ነው፡፡

ኢዮብ 18፣ የበልዳዶስ ክስ፡- የበልዳዶስ ንግግር ያተኮረው በኃጥአት እጣ ፈንታ ላይ ነበር፡፡ ኢዮብን ክፉና ኃጢአተኛ ነህ ብሎ በቀጥታ ባይናገረውም እንኳ፣ የሚያመለክተው ግን ያንኑ ነበር፡፡ የኃጥአን ዕጣ ፈንታ በማሳየትና ኢዮብ ንስሐ ካልገባ በስተቀር የሚጠብቀውን ነገር በማመልከት አስጠንቅቆታል። 

ኢዮብ 19፥ የኢዮብ ምላሽ፡- ኢዮብ አሁንም ጥፋተኛ አለመሆኑን በመግለጽ ለበልዳዶስ ክስ ምላሽ ሰጥቶአል። ኢዮብ አሁን ያለበትን ስንመለከት በእግዚአብሔር እንደተፈረደበት ኃጢአተኛ ሰው ቢመስልም፣ ያልተናዘዘው ኃጢአት ግን አልነበረም። አሁን ተስፋ የቆረጠ ቢመስል፣ የሚቤዥው ሕያው እግዚአብሔር ስለሆነ፥ የሦስቱ ወዳጆቹ አስተሳሰብ ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔር በመጨረሻ ሁሉን ግልጽ በማድረግ እንደሚያቆመው ተናግሯል (ኢዮብ 19፡25)። 

ኢዮብ 20፥ የሶፋር ክስ፡- የሶፋር ንግግር የሁለቱ ወዳጆቹ ንግግር ድግግሞሽ ነበር። እርሱም ስለ ኃጢአተኞች ዕጣ ፈንታ በመናገር ንስሓ እንዲገባ ኢዮብን አበረታትቶታል። 

ኢዮብ 21፥ የኢዮብ ምላሽ፡- ኢዮብ በዚህ ምላሹ ቀደም ሲል ወዳጆቹ የተናገሩትን ነገር ሁሉ በመከለስ ተቃውሞአቸዋል። በኢዮብና በወዳጆቹ መካከል የተደረገው ሁለተኛ ዙር ክርክር እንደተጠቃለለ፥ የኢዮብ ወዳጆች እያንዳንዳቸው የመጨረሻ ንግግራቸውን ያቀረቡበት ሦስተኛ ዙር ክርክር ቀጥሉአል (ኢዮብ 22-31)። በዚህ ዙር ንግግር ሶፋር አንዳችም ነገር አለማለቱ የሚያስገርም ነው። ኢዮብ በዚህ ዙር ለእያንዳንዳቸው መልስ በመስጠት፥ ለምን መከራ በመቀበል ላይ እንዳለ በመጠየቅና ከእግዚአብሔር ምን እንደሚፈልግ በመናገር አጠቃልሏል። 

ኢዮብ 22፥ የኤልፋዝ ክስ፡- ከኢዮብ ሦስት ወዳጆቹ ደጉና ምናልባትም በዕድሜ የላቀው ኤልፋዝ፥ አንድ ጻድቅ ሰው አንዳችም ጥፋት ሳይኖርበት ለምን መከራ እንደሚቀበል ለመረዳት አልቻለም ነበር። ስለሆነም እንደገና ኢዮብ ከኃጢአቱ ጋር እንዲፋጠጥና ንስሐ እንዲገባ ለማድረግ ሞከረ። 

ኢዮብ 23-24፥ የኢዮብ ምላሽ፡ – ኢዮብ ለኤልፋዝ ሲመልስ፥ እርሱ የሚፈልገው ጉዳዩን ያይለት ዘንድ እግዚአብሔርን ለመገናኘት እንደሆን ገልጿል። እግዚአብሔር ነፃ እንደሚያደርገው እርግጠኛ ነበር። ችግሩ ግን እግዚአብሔር የማይደረስበት መሆኑና ጉዳዩን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ እመቻሉን መግለጹ ነበር። ሰይጣን እንደፈለገው፥ ኢዮብ እግዚአብሔርን ባይረግምም እንኳ፥ ቅንና ጻድቅ የሆነ ፍርድ እንዳላደረገ በመናገር እግዚአብሔርን ወቅሶታል። ለኢዮብ ትልቁ ተስፋ አስቆራጭ የሆንበት ጸሎቱንና ክሱን ባለመመለስ እግዚአብሔር ዝም በማለቱ ነበር። 

ኢዮብ 25 የበልዳዶስ ክስ፡- ወዳጆቹ በኢዮብ ላይ የሚያቀርቡት ክስ ተጠናቅቆ ነበር። ቢሆንም በልዳዶስ የመጨረሻ ንግግር የማድረግ ዕድል አግኝቶአል። ቀደም ሲል በኢዮብ ላይ ከቀረቡት ክሶቹ አንዳንዶቹን ደግሞ ተናግሮአቸዋል፤ አዲስ ትምህርቱ ግን ጥቂት ነው። ከዚህ በኋላ ሶፋር የሚናገረው አንዳችም ነገር አልነበረውም፤ ስለዚህ ዝም አለ። 

ኢዮብ 26-31፥ የኢዮብ የመጨረሻ ምላሽ፡- በመጨረሻ ኢዮብ የወዳጆቹ ክስ ሁሉ ስሕተት እንደሆነ አጠር አድርጎ ተናግሯል። ኢዮብ ጻድቅ መሆኑን ያውቅ ነበር። እንዲሁም እግዚአብሔር ትክክለኛ እንደሆንም ያውቅ ነበር። እነዚህ ሁለት እውነቶች እንዴት ሊስማሙ እንደሚችሉ ግን አያውቅም ነበር። ኢዮብ አሁን ካለበት መከራ፥ ችግርና ሥቃይ ይልቅ እጅግ የተሟላ በረከት የነበረበትን የቀድሞውን የደስተኛነት ሕይወቱን አስታወሰ። ኢዮብ በብርቱ ሥቃይና በድህነት ውስጥ የሆነው በኃጢአቱ ምክንያት እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች የምትማራቸውን አንዳንድ እውነቶች ዘርዝር። ለ) የኢዮብ ወዳጆች ክስ ከብዙ ክርስቲያኖች አስተሳሰብ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) የተሳሳቱት እንዴት ነው? መ) ኢዮብን ለማበረታታት ማድረግ የነበረባቸው ነገር ምን ይመስልሃል? ያኔ አንተ ብትኖር ኖሮ ኢዮብን እንዴት ትመክረው ነበር?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.