የመጽሐፈ ምሳሌ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) አንድን ሰው ጠቢብ የሚያደርገው ምንድን ነው? በኢትዮጵያ ውስጥ የጠቢብ ሰው ባሕርያት ምንድን ናቸው? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ እንደ ጠቢባን የሚቆጠሩትን ሰዎች ስም ዘርዝር፤ እነዚህ ሰዎች ከሌሎች የሚለዩት እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ ምሳሌ ሲባል ምንድን ነው? ለ) ሰዎች የሚጠቀሙበት እንዴት ነው? ሐ) ሁለት ምሳሌዎችን ጥቀስ፤ ምን እንደሚያስተምሩ ተናገር። 

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እጅግ ተግባራዊ የሆኑ ነገሮችን ከሚያስተምሩ የላቁ መጻሕፍት ውስጥ አንዱ መጽሐፈ ምሳሌ ነው።  የሚያሳዝነው ግን ብዙ ሰዎች የሚያነቡት ወይም ከሕይወታቸው ጋር የሚያዛምዱት መጽሐፍ አለመሆኑ ነው። መጽሐፈ ምሳሌ በሁሉም የሕይወታችን ክፍል እንዴት በጥበብ መኖር እንዳለብን ይነግረናል። ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በማዳበር እንዴት እውነተኛውን ጥበብ እንደምናገኝ ይነግረናል። በፍትወተ ሥጋ ኃጢአት እንዳንወድቅ ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብንና የፍትወተ ሥጋ ኃጢአት በሕይወታችን ውስጥ የሚያመጣቸውን አደጋዎች ያስረዳናል። የንግድ ተግባርን እንዴት እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ማካሄድ እንደምንችል፥ ስለ ታማኝነት፥ ከአለቆቻችን ወይም ከእኛ በታች ከሚሠሩ ሠራተኞቻችን ጋር ሊኖረን ስለሚገባው መልካም ግንኙነት ይነግረናል። ወላጆች የሆንን ደግሞ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ልጆቻችንን እንዴት ማሳደግ እንዳለብን ይነግረናል። የወደፊት የትዳር ጓደኛችንን እንዴት መምረጥ እንዳለብን፥ በዚህ ሂደት ውስጥ ማድረግ ስላለብንና ስለሌለብን ነገር ይነግረናል። በአጭሩ መጽሐፈ ምሳሌ በብዙ ሁኔታዎችና በሕይወት ውስጥ «የእግዚአብሔር ፈቃድ» ምን እንደሆነ ያስተምረናል። እግዚአብሔር ስለ ራሱ ፈቃድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገለጣቸውን ጉዳዮች ሳንከተል፥ የፈቃዱን ሌሎች ገጽታዎችን ይገልጥልን ዘንድ መጠበቅ የለብንም። 

የውይይት ጥያቄ፡- በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ማወቅ ለእኛ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? 

በግጥም መጻሕፍት ጥናታችን፥ እስካሁን ድረስ መጽሐፈ ኢዮብንና መዝሙረ ዳዊትን ተመልክተናል። እያንዳንዱ መጽሐፍ በአብዛኛው ግጥሞችን ቢያካትትም እንኳ አንዱ ከሌላው በጣም የተለየ ነው። መጽሐፈ ኢዮብ፡- ጻድቃን ኃጢአት ባላደረጉበት ጊዜ ለምን መከራን ይቀበላሉ? የሚል ጥያቄ ያለበትን የኢዮብን ትግል የሚያሳይ የግጥም ታሪክ ነው። እግዚአብሔር ኃጢአት የሚያደርጉትን ሰዎች የሚቀጣበት ጊዜ ቢኖርም እንኳ መከራ በአንድ ሰው ሕይወት የኃጢአት ውጤት የማይሆንባቸው ጊዜያት መኖራቸውን ለማስተማር የሚፈልግ መጽሐፍ ነው። ጻድቅ መከራን ይቀበላል። ሰው መከራን የሚቀበልባቸው ምክንያቶች ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው ናቸው። አንድ ሰው መከራና ሥቃይ የሚቀበለው በሕይወቱ ኃጢአት ስላለ ነው በማለት ፈጥነን ከመፍረድ መቆጠብ አለብን። 

መዝሙረ ዳዊት የብሉይ ኪዳን የመዝሙር መጽሐፍ ነው። ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ጸሎቶች የሚገኙባቸውን በርካታ የተለያዩ ግጥሞች ወይም መዝሙሮች ይዟል። ብዙዎቹ ግጥሞች በችግር ጊዜ ከእግዚአብሔር እርዳታን መጠየቂያ ናቸው። እግዚአብሔርን ስለ ባሕርያቱ ለማመስገን ካስፈልገም በርካታ ግጥሞች አሉት። መዝሙረ ዳዊት የተጻፈው እግዚአብሔር በምናቀርበው አምልኮ እንዲረዳን ነው። 

ዛሬ ደግሞ ሦስተኛው የግጥም መጽሐፍ የሆነውን መጽሐፈ ምሳሌን መመልከት እንጀምራለን። ይህም መጽሐፍ በአብዛኛው የተጻፈው በምሳሌ መልክ በመሆኑ ለየት ያለ ነው። ምሳሌዎች ሰዎችን በባሕርያቸው ለመቅረጽ መሠረታዊ እውነትን የሚያንጸባርቁ አጫጭር አባባሎች ናቸው። ብዙ ጊዜ አንድን እውነት የሚወክል ተምሳሌትና እውነቱን ራሱን በማወዳደር የሚጻፉ ናቸው። አንዳንዶች በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ 915 ምሳሌዎች እንዳሉ ይናገራሉ። 

በብሉይ ኪዳን የመጽሐፈ ምሳሌ ሥረ መሠረት የተፃፈ በተገቢው መንገድ ባልተደራጁባቸው በርካታ ባህሎች ውስጥ ያሉ ሰዎች፥ እውቀትን ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ የሚያስተላልፉት ብዙ ጊዜ በአማጭር አባባሎች ነው። እነዚህ አጫጭር አባባሎች ወይም ምሳሌዎች በቀላሉ ሊታወሱ የሚችሉ እውነቶች ናቸው። ሰዎች በሕይወት ውስጥ በሚያስተውሉአቸውና በሚያንጸባርቋቸው ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ተከታዩ ትውልድ መሠረታዊ እውነቶችን እንዲማርና ከሕይወቱ ጋር በማዛመድ እንዲኖር ለማገዝ የሚረዱ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች ናቸው። 

በጥንታዊው ዓለም፥ ከሞላ ጐደል ሁሉም ባህሎች ምሳሌዎች ነበሯቸው። አይሁድ ምሳሌዎችን ይወዱ ነበር። ከሰሎሞን ጊዜ ጀምሮ ምሳሌዎችን መሰብሰብ ጀመሩ። ስሎሞን ራሱ ከ3000 የሚበልጡ ምሳሌዎችን ጽፏል። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተጠቃለሉት ግን ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው (1ኛ ነገሥት 4፡30-32)። ጊዜያት ባለፉ ቍጥር መሠረታዊ እውነቶችን የመረዳት ችሎታ ያላቸውና «ጥበበኞች» በመባል ይጠሩ የነበሩ ሰዎች ለይሁዳ ነገሥታት ልዩ አማካሪዎች ሆኑ። እንዲያውም እነዚህ ጥበበኞች በይሁዳ ከነበሩ ዋና ዋና መሪዎች ማለትም ከካህናት፥ ከነቢያትና ከነገሥታት ጋር በአንድነት ይታዩ ነበር (ለምሳሌ ኤርምያስ 18፡18፤ ሕዝቅኤል 7፡26-27)። እነዚህ ጥበበኞች የአይሁድን ባህላዊ እውቀት በማስተላለፍ ብቻ ሳይወሰኑ፥ ከእስራኤል ውጭ ይገኙ ከነበሩ አገሮች እውቀትን ይፈልጉ ነበር። የመጽሐፈ ምሳሌ የመጨረሻ ሁለት ምዕራፎች የሚያሳዩት ከእስራኤል ውጭ ስለተገኙ ጥበባት ነው። እንደምታስታውሰው፥ ሕፃኑ ኢየሱስን በቤተልሔም ሊጎበኙ የመጡት ሰዎች «ጥበበኞች» ነበሩ (ማቴ. 2)። 

አንዳንድ ምሁራን እነዚህ ምሳሌዎች ያገለገሉት የሚቀጥለውን የእስራኤል ሕዝብ መሪዎች ለማሠልጠን የነበረ ይመስላቸዋል። ጠቢባን፥ የነገሥታትና የመሪዎች ልጆች፥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ለማስተማር በምሳሌዎች ይጠቀሙ ነበር። 

እነዚህ ሰዎች፥ ልጆቹ መሪዎች በሚሆኑበት ጊዜ በሚገባ እንዲመሩና ሕዝቡም መልካም ሕይወት ለመኖር ይችል ዘንድ፥ ምሳሌዎቹን እንዲሰበሰቡና እንዲማሯቸው ይደረጉ ነበር (ምሳሌ 20፡28፤ 24፡21፤ 25:2-7)። እነዚህ ምሳሌዎች የተገኙት ከሰሎሞን፥ ከእርሱም በኋላ ደግሞ ከሰሜኑ መንግሥት-ከእስራኤል ሳይሆን ከደቡቡ መንግሥት ከይሁዳ መሆኑን ማየት የሚያስገርም ነው። ይህም የሆነው ምናልባት የሰሜኑ ነገሥታት በእግዚአብሔር ጥበብ ለመግዛት ፍላጎት ስላልነበራቸው ይሆናል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ምሳሌ የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት። በውስጡ የሚገኙትን ጠቃሚ ትምህርቶች ዘርዝር። 

የመጽሐፈ ምሳሌ ርእስ 

መጽሐፈ ምሳሌ ርእሱን ያገኘው በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኘው የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ነው። ስሙ እንደሚያመለክተው፥ መጽሐፉ በአብዛኛው የያዘው የተለያዩ ዓይነት ምሳሌዎችን ነው። 

የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊና የተጻፈበት ጊዜ 

እንደ መዝሙረ ዳዊት ሁሉ፥ መጽሐፈ ምሳሌም የተጻፈው በብዙ መቶ ዓመታት ውስጥ ነው። አብዛኛዎቹ ምሳሌዎች የተጻፉት ከ971-931 ዓ.ዓ. በነገሠው-በሰሎሞን ነበር። ነገር ግን ከብዙ ዓመታት በኋላ የተጻፉ ምሳሌዎችም ነበሩ። ከእነዚህ ምሳሌዎች መካከል የአንዳንዶቹ ጸሐፊዎች ይታወቃሉ። ለምሳሌ የመጨረሻዎቹ ሁለት መዝሙራት የተጻፉት በአጉርና በልሙኤል ነበር። እነዚህ ሰዎች በዐረቢያ የሚኖሩ የነበሩ የማሳ ነገድ አባላት የነበሩ ዐረቦች ሳይሆኑ አይቀሩም። በ701 ዓ.ዓ. አካባቢ በእስራኤል የነገሠው ሕዝቅያስም የተለያዩ ምሳሌዎችን በማሰባሰብ አስተዋጽኦ አድርጓል (ምሳሌ 25)። 

ስለዚህ ልክ እንደ መዝሙረ ዳዊት፥ በመጀመሪያ የተለያዩ ምሳሌዎችን ስለ-ጻፈው ሰው መነጋገር፥ ቀጥሎም ምሳሌዎችን የሰበሰበው ወይም ያቀናበረው ማን እንደሆነ ማየት አለብን። የተለያዩ ምሳሌዎችን የጻፉ ሰዎች ቀጥሉ ተዘርዝረዋል፡- 

1. ሰሎሞን (ምሳሌ 10፡1-22፡16፡25-29)፡- መጽሐፈ ምሳሌ በአብዛኛው የተጻፈው በሰሎሞን ነበር። በአይሁድ ዓይን ስሎሞን የጥበበኞች ሁሉ ዋነኛ ተቀዳሚ ምሳሌ ነበር (1ኛ ነገሥት 4፡29-34 ተመልከት)። የእርሱ ጥበብ የተገኘው እግዚአብሔርን በመለመኑ የተነሣ ነበር። ትክክል የሆነውን ትክክል ካልሆነው ለይቶ ለመወሰን ባሳየው ችሎታ ጥበበኛ መሆኑን እናያለን። እውነተኞች ጥበበኞች የሆኑ ሰዎች በጥበባቸው ሰሎሞንን መምሰል ነበረባቸው። 

2. አጉር (ምሳሌ 30)፡- አጉር የኖረው መቼ እንደነበረ አናውቅም። ሆኖም ምሁራን አጉር የኖረው ከሰሎሞን በኋላ ብዙ ዓመታት ቆይቶ እንደሆነ ይገምታሉ። ይህ ሰው ዐረብ እንጂ አይሁዳዊ እንዳልሆነም ይገምታሉ። 

3. ንጉሥ ልሙኤል (ምሳሌ 31)፡- እንደ አጉር ሁሉ ይህ ሰው መቼ እንደኖረና እንደጻፈ አናውቅም። በጥበቡ የታወቀ ዐረብ ሳይሆን አይቀርም። 

4. ሁለት ያልታወቁ ጠቢባን (ምሳሌ 22፡17-24፡22፥23-34)። 

በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ምሳሌዎች የተጻፉት ከ971 እስከ 586 ዓ.ዓ. ከምርኮ በፊት ነው። አንዳንድ ምሁራን (ከ1-24) በሰሎሞን ጊዜ፥ (ከ25-29) በሕዝቅያስ ጊዜ እንደተጻፉ ይገምታሉ። ምዕራፍ 30ና 31 ግን መቼ እንደተጻፉ አያውቁም። 

የተለያዩ ምሳሌዎች ተሰብስበውና ተጠርዘው በአንድ የመጽሐፍ ዓይነት የተቀመጡት ከሰሎሞን ጊዜ ጀምሮ እንደነበር አያጠራጥርም። ምናልባት በየትውልዱ የነበሩት ጥበበኞች ሰዎች በምሳሌዎቹ ላይ በየዘመናቱ ላይጨምሩ አልቀሩም ይሆናል። ከዚያም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ አንድ ያልታወቀ ሰው ምሳሌዎቹን በሙሉ ሰብስቦ ዛሬ በምንመለከታቸው ቅደም ተከተል አስቀምጦአቸዋል። 

የመጽሐፈ ምሳሌ አስተዋጽኦ 

የመጽሐፈ ምሳሌን አስተዋጽኦ ማዘጋጀት አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም የአብዛኛዎቹ ምሳሌዎች ይዘት አንድ ባለመሆኑ ነው። መጽሐፈ የያዘው የተለያዩ አርእስቶች ያላቸው አጫጭር ምሳሌዎችን ነው፡፡ ሆኖም ግን ቀጥለን መጽሐፈ ምሳሌ ሊቀናበር ከሚችልባቸው መንገዶች መካከል ጥቂት አብነቶችን እንመለከታለን። 

የመጽሐፈ ምሳሌ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች፡- 

1. እውነትን ለማስተማር የሚያገለግሉ ምሳሌዎች ክፍል (1-9)፥ 

2. የልዩ ልዩ ምሳሌዎች ስብስብ (10-29): 

3. በምሳሌዎች ላይ የተጨመሩ ነገሮች (30-31) ናቸው፡፡ 

ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በይበልጥ ዝርዝር የሆነ አስተዋጽኦ እንመለከታለን። በተለያዩ የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊዎች ዙሪያ መቀነባበሩን ትመለከታለህ፡-  

1. የመጽሐፈ ምሳሌ መግቢያና ዓላማ (1፡17) 

2. ስለ ጥበብ መንገድ መንፈሳዊ አባቶች የሰጡት ምክር (1፡8 እና ምዕ. 9)፡-  

ሀ. ስለ እውነተኛ ጥበብ የተሰጡ ትምህርቶች (1፡8-4፡27)፥ 

ለ. ስለ ጋብቻና ዝሙት የተሰጡ ትእዛዛት (5-7)፥ 

ሐ. በጥበብ መኖር እንዴት እንደሚቻል (8-9)፡ 

3. የሰሎሞን ምሳሌዎች (10፡1-22፡16)፥ 

4. ጸሐፊያቸው የማይታወቅ ተመሳሳይ የጥበብ አባባሎች (22፡17-24፡22) 

5. ጸሐፊያቸው የማይታወቅ ተጨማሪ የጥበብ አባባሎች (24፡23-24)። 

6. ተጨማሪ የሰሎሞን ምሳሌዎች (25-29)። 

7. በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ የተጨመሩ፡-  

ሀ. የአጉር ንግግሮች (30)። 

ለ. የንጉሡ ልሙኤል ንግግሮች (31፡1-9) እና 

ሐ. ልባም ሚስት (31፡10-3) ናቸው። 

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥበብ ከሰው ልጅ ጥበብ ጋር ሲነጻጸር 

የውይይት ጥያቄ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡18-2፡5 አንብብ። ሀ. ጳውሎስ ዓለማዊ ጥበብን ፈሪሀ-እግዚአብሔር ከሞላበት ጥበብ የሚያወዳድረው እንዴት ነው? ለ. ዛሬ በዓለም ላይ ይህ ልዩነት የሚታየው እንዴት ነው? 

የመጽሐፈ ምሳሌን ዓላማ ከመመልከታችን በፊት፥ መጽሐፍ ቅድሱ ጥበብን እንዴት እንደሚመለከትና እኛ ደግሞ ጥበብን የምንረዳበት ዝንባሌ ምን እንደሆነ ማነጻጸር አለብን። ለብዙዎቻችን ጥበብ የተለያየ እውቀትን የያዘ ነገር ነው። ጥበበኞች የምንሆነው ትምህርት ቤት በመግባት፥ በርካታ መጻሕፍትን በማንበብ፥ ብዙ መሠረታዊ እውነቶችን በማወቅ ነው። ጥበበኞች ብለን የምናስባቸው ሰዎች ከፍተኛ ትምህርት የተማሩና ብዙ የተለያዩ ነገሮችን የሚያውቁ ይመስለናል። ዳሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ጥበብን የሚያየው በተለየ መንገድ ነው። አንድ ጥበበኛ ሰው በርካታ ነገሮችን ማወቁ አስፈላጊ ቢሆንም፥ የእነዚህ ነገሮች እውቀት ግን ጥበበኛ አያደርገውም። ጥበበኛ ሰው የሕይወትን ጉዳዮችና ችግሮች ለመረዳትና እውቀቱን የተሻለ ሕይወት ለመኖር ሊጠቀምበት የሚችል ሰው ነው። አይሁድ ጥበብን የሚያዩት ሰው በተፈጥሮው ሊያገኘው የማይችል ነገር እንደሆነ አድርገው ነው። ጥበብ ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣት አለበት፤ ስለዚህ አንድ የማያምን ሰው ምንም ያህል እውቀት ቢኖረውም በመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ጥበበኛ ሊሆን አይችልም። ጥበበኛ መሆን የሚጀምረው ከእግዚአብሔር ጋር ተገቢና ትክክለኛ የሆነ ግንኙነት ሲመሠርት ነው። «እግዚአብሔርን በመፍራት» (ምሳሌ 9፡10) ሰው ጥበበኛ ሊሆን የሚችልበትን መሠረት ያገኛል። በዚህ መሠረት ላይ በመገንባት ጥበበኛ የመሆን ችሎታን ያገኛል። ሰው ጥበበኛ ለመሆን ጥበብ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ለመሻት ልቡን ሙሉ በሙሉ መስጠትና በዕለታዊ ሕይወቱ ሁሉ እግዚአብሔር የሚነግረውን ነገር ሁሉ በተግባር ላይ ማዋል አለበት፡፡ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የጥበብን ሕይወት መኖሩን ለመቀጠል ሕይወቱ ሁሉ በእግዚአብሔር ቍጥጥር ሥር ሊሆንና እርሱን በሚያስከብር መዓዛው ሊኖር ያስፈልጋል። እግዚአብሔርን ለማክበር ደግሞ መጠበቅ ያለባቸው ሁለት መሠረታዊ ግንኙነቶች አሉ፡- 

1. ግላዊ የሆነና የሚያድግ ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖረው ይገባል። እግዚአብሔር እርሱን ለሚፈልጉና ራሳቸውን ለሚያስገዙለት ሰዎች ጥበብን እንደ ስጦታ ይሰጣቸዋል። 

2. ከሌሎች ሰዎች ጋር ትክክለኛ የሆነ ግንኙነት ሊኖርው ይገባል። ሰው ጻድቅ ሊሆንና ከሰዎች ሁሉ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ትክክለኛ ኑሮ ሊኖር በሚችልበት መንገድ የእግዚአብሔርን ሕግ ለመጠበቅ መቍረጥ አለበት። ይህ ግንኙነት ከድሆች፥ ከአለቆች፥ ከአገልጋዮች ወዘተ. ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ሁሉ ይጨምራል። ጥበብ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ ከመሆኑም በላይ፥ ወገናችን ወደ ሆነውም ሰው ሁሉ ይደርሳል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች ስለ ጥበብ ያላቸውን የተለመደ ግንዛቤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ግንዛቤ ጋር አነጻጽር። ለ) ከእግዚአብሔር ጋር ባለህ ግንኙነት እንዴት ጥበበኛ እንደ ሆንክ ግለጽ። ሐ) ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት እንዴት ጥበበኛ እንደ ሆንክ ግለጽ። መ) በእግዚአብሔር አመለካከት የበለጠ ጥበበኛ እንድትሆን ልታደርጋቸው የምትችል ነገሮች ምንድን ናቸው? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

One thought on “የመጽሐፈ ምሳሌ መግቢያ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.