ሀ. የምርጫ ውሳኔ
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚገልጠው፥ በራሱ ምርጫ ዓለማትን እንደፈጠረና አስቀድሞ ባቀደው መሠረት ታሪክን የሚመራ ፍጹም ሉዓላዊ አምላክ መሆኑን ነው። እግዚአብሔር ሉዓላዊና ደስ ያሰኘውን የማድረግ ብቃት ያለው መሆኑ የሚታመነው፥ ሁሉን ቻይና የማይደረስበት አምላክ ከመሆኑ አሳብ ጋር ተያይዞ ነው። ይሁንና ስለዚህ ዓይነቱ የእግዚአብሔር አሠራር የሰው ልጆች የሚኖራቸው የግንዛቤ አቅም ማነስ እጅግ ብዙ ችግሮችን ያስከትላል። በተለይም በእግዚአብሔር አሠራር በተፈጠረው ዓለም ሰው የቱን ያህል ሰነጻነትና በተጠያቂነት መሥራት የሚኖርበት መሆኑን መረዳቱ የዋዛ አልሆነም።
ሰብአዊ የአስተሳሰብ ዘዴዎች የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዓላማ በፍጹማዊነት ወደሚስተናገድበት ወይም ደግሞ የእግዚአብሔር ቁጥጥር እስኪነጋ ድረስ የሰው ነጻነት ወደሚጋነንበት እክራሪ የአስተሳሰብ ዘዬዎች ሲያጋድሉ ኖረዋል። እንዲህ ዓይነቱን አስቸጋሪ ጉዳይ ለማቃለል ብቸኛው መፍትሔ፥ መለኮታዊውን መገለጥ መጠየቅና ሰብእዊውን ልምምድ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መሠረት ለመፍታት መሞከር ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጠው፥ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዓላማ ግለሰቦችንም ሆነ አገሮችን ይመለከታል። እስራኤል በእግዚአብሔር የተመረጠ ሕዝብ መሆኑ ተገልጧል (ኢሳ. 45፡4፤ 65 : 9፥ 22)። “ምርጥ” የሚለው ቃል ለድነት ለተመረጡ ሰዎች መጠሪያነት በተደጋጋሚ አገልግሷል (ማቴ. 24፡22፥ 24፥ 31፤ ማር. 13፡20፥ 22፥ 27፤ ሉቃስ 18፡7፤ ሮሜ 8፡33፤ ቆላ. 3፡12፤ 1ኛ ጢሞ. 5፡21፤ 2ኛ ጢሞ. 2፡10፤ ቲቶ 1፡1፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡2፤ 5፡13፤ 2ኛ ዮሐ. 1 እና 13)። ስለ ክርስቶስም ይኸው አገላለጥ አገልግሏል (ኢሳ. 42፡1፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡6)። “ምርጥ” ከሚለው ቃል በተጨማሪ የምርጫ እውነታም ተጠቅሷል (ሮሜ 9፡11፤ 11፡5፥ 7፥ 28፤ 1ኛ ተሰ. 1፡4፤ 2ኛ ጴጥ. 1፡10)። ምርጫ ውስጥ የሚገኘው ፅንሰ አሳብ የሚያመለክተው፥ የተጠቀሰው ግለሰብ ወይም ቡድን ላአንድ መለኮታዊ ዓላማ መመረጡን ሲሆን፥ ብዙውን ጊዜ ከድነት ጋር ይዛመዳል።
“ምርጥ” የሚለው ቃል ለእስራኤል (ኢሳ. 44፡1)፥ ለቤተ ክርስቲያን (ኤፌ. 1:4፤ 2ኛ ተሰ. 2: 13፤ 1ኛ ጴጥ.2፡9)፥ ለሐዋርያት መጠሪያነት (ዮሐ. 6፡70፤ 13፡18፤ ሐዋ. 1፡2) አገልግሏል።
ምርጫን በተመለከተ የተለያዩ ገለጣዎች አሉ፤ ለምሳሌ አስቀድሞ ማወቅን (ሮሜ 8፡29-30፤ ኤፌ. 1፡5፥ 11፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡20)፥ የመሳሰሉ በሐዋርያት ሥራ 4፡28 እንደተመለከተው ቅድመ ውሳኔን፥ ወይም ይሁዳ 4 እና ኤፌሶን 2፡10 ውስጥ እንደተጠቀሰው ቅድመ ስያሜን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ 2ኛ ዜና 25፡16፥ ኢሳይያስ 19፡17፤ ሉቃስ 22፡22፥ የሐዋርያት ሥራ 17፡26 በመሳሰሉ ስፍራዎችም ይኸው “ውሳኔ” የሚለው ፅንሰ-አሳብ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። በዚህ ሁሉ ቃላት ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት፥ የእግዚአብሔር ምርጫ ተግባርን የሚቀድምና በራሱ ሉዓላዊ ፈቃድ የሚወሰን መሆኑን ነው።
ምርጫ፥ ቅድመ ስያሜና ቅድመ ውሳኔ እንደ እግዚአብሔር መለኮታዊ ዓላማ የሚከናወኑ ሲሆኑ (ኤፌ. 1፡9፤ 3፡11)፡መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከእግዚአብሔር ቅድመ ግንዛቤ ጋር የተያያዙ ናቸው (ሐዋ. 2፡23፤ ሮሜ 8፡29፤ 11፡2፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡2)። “ጥሪ” የሚለው ቃልም ሮሜ 8፡30 እና ሌሎችም በርካታ ምንባቦች ውስጥ ተጠቅሷል (1ኛ ቆሮ. 1፡9፤ 1፡18፥ 20-21፥ 22፥ 24፤ 15፡9፤ ገላ. 5፡13፤ ኤፌ. 4፡1፥ 4፤ ቆላ. 3፡15፤ 1ኛ ጢሞ. 6፡12፤ ዕብ. 5፡4፤ 9፡15፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡21፤ 3፡9፤ 1ኛ ዮሐ. 3፡1)። “ጥሪ” ስዎችን ወደ እግዚአብሔር መሳብ መሆኑን ጌታችን ዮሐ፡12፡32 ውስጥ አመልክቷል (ከዮሐንስ 6፡44 ጋር ያነጻጽሩት)። እነዚህ ሁሉ ምንባቦች የሚያስገነዝቡን ሉዓላዊው አምላክ ዓላማውን በማሳካት ላይ መሆኑን ነው። የተወሰኑ ግለሰቦች በዚሁ ዓላማው መሠረት ለድነት የተመረጡ ሲሆን፥ የተወሰኑ ሕዝቦችም መለኮታዊውን ልዩ ዓላማ ለማሳካት እንዲሁ ተመርጠዋል። በተለይ እስራኤላውያን የተለየ መለኮታዊ ዓላማ ለማገልገል ተመርጠዋል።
ለ. የመለኮታዊ ምርጫ እውነትነት
ምንም እንኳ የምርጫ እስተምህሮ ከስብእዊ ግንዛቤ ሰላይ ሲሆን፥ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሆኑ ግን አያጠያይቅም። እግዚአብሔር በመለኮታዊ ምርጫው የተወሰኑ ግለሰቦችን ለድነት በመምረጥ፥ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስን ባሕርይ ይመስሉ ዘንድ ወስኗል (ሮሜ 16፡13፤ ኤፌ. 1፡4-5፤ 2ኛ ተሰ. 2፡13፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡2)። ምርጫ ከእግዚአብሔር መሆኑና የዘላለማዊ ዕቅዱ እካል መሆኑ ግልጥ ነው።
መለኮታዊ ምርጫ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ አካል እንጂ፥ ሰው ከተፈጠረ በኋላ የተወሰነ አይደለም። ይህም “ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን” በሚለው ኤፌሶን 1፡4 እና ሌሎች ብዙ ምንባቦች ውስጥ ተገልጧል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡9 እንደሚለው ደግሞ፥ መመረጣችን “እንደራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው። ይህም ጳጋ ከዘላለም በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን።” የእግዚአብሔር ዕቅድ ዘላለማዊ በመሆኑ፥ ምርጫም በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ውስጥ ሆኖ ዘላለማዊ ነው።
ሰምርጫ አስተምህሮ ውስጥ ከሚገኙ ውስብስብ ችግሮች እንዱ ምርጫ ከቅድመ ግንዛቤ ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑ ነው። የምርጫን ፅንሰ-አሳብ አለሳልሶ የሚያቀርሰው አንድ የአተረጓጎም ስልት፥ እግዚአብሔር በክርስቶስ የሚያምኑትን ቀደም ብሎ ያውቅ ስለነበር፥ በዚሁ እውቀት ላይ ተመሥርቶ ለድነት መርጧቸዋል በሚለው አሳብ ዙሪያ ትንታኔውን ያቀርባል። ይሁንና፥ ይህ አሳብ እግዚአብሔርን ራሱ ሉዓላዊ ላልሆነበት ዕቅድ ተገዥ አድርጎ የሚያቀርበው ስለሚመስል ችግሮች አሉበት። ምንም እንኳ ምርጫና ቅድመ ግንዛቤ ተያያዥነት ቢኖራቸው፥ ቅድመ ግንዛቤ በራሱ ወሳኝ አይሆንም።
ምንም እንኳ የሥነ-መለኮት ምሁራን ከነዚህ ችግሮች ጋር ታግለው ከአርኪ ድምዳሜዎች ላይ ለመድረስ ባይችሉ፥ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው አንድ ነገር የእግዚእብሔርን ሁሉን አዋቂነት ማለት፥ ለዓለማት የሚያሻቸውን ዕቅድ ሁሉ እንደሚያውቅ ከመገንዘብ መጀመሩ ነው። ስፍር ካሌሳቸው ዕቅዶች ውስጥ እግዚአብሔር አንዱን መረጠ። አንድን ዕቅድ በመምረጥና የዕቅዱን ዝርዝር በማወቅ፥ እግዚአብሔር የሚድኑትንና የሚመረጡትን እስቀድሞ ሊያውቅ፥ ከድነታቸው ጋር የሚዛመዱ እውነታዎችንም ሊገነዘብ ይችላል።
ይህን የእግዚአብሔር ቃል ለመተርጎም የሚሞክር ሰው የሚገጥመው ችግር የሰው ልጅ ነጻነት ጉዳይ ነው። ከልምድም ሆኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚታየው፥ ሰው ምርጫዎች አሉት። ይሁን እንጂ፥ ሁሉም ነገር አስቀድሞ የተወሰነበት ከሆነ፥ ሰው በራሱ ጤናማና ነጻ የሆነ ሥነ-ምግባራዊ ምርጫ ለማድረግ እንዴት ይቻላል? ይህ ከሆነስ ሰብአዊ ተጠያቂነት እንዴት ትዕከል ይሆናል? በዚህ አስቸጋሪ አስተምህሮ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሚያጋጥሙት ችግሮች እነዚህ ናቸው።
የሥነ-መለኮት ምሁራን መለኮታዊ ምርጫ ከሰብአዊ ምርጫዎችና ሥነ-ምግባራዊ ተጠያቂነት ጋር በተዛመደ መልኩ ያለበትን ችግር እስከዛሬ ሙሉ በሙሉ ለማቃለል አልቻሉም። ይሁንና፥ ችግሩ እልባት የሚያገኘው፥ እግዚአብሔር የመረጠውን ዕቅድ በዘፈቀደ ሳይሆን፥ ሙሉ ለሙሉ በመምረጥ ይመስላል። ሰዕቅዱ ማን እንደሚድንና ማን እንደማይድን ዕቅዱን ከመምረጡ በፊት አውቋል። እግዚአብሔር ከሁሉም የተሻለውን ዕቅድ እንደመረጠ በእምነት መቀበል እለብን። ከዚህ የተሻለ ዕቅድ ቢኖር ኖሮ እግዚአብሔር ያን ይመርጥ ነበር። ዕቅዱ በአብዛኛው እግዚአብሔር ራሱ የሚሠራቸውን ነገሮች አካቷል። እነዚህም እንደ ፍጥረትና የተፈጥሮ ሕግ መደንገግን የመሳሰሉ ናቸው። ዕቅዱ እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ ራሱ የሚፈጽማቸውን ነገሮች፥ ማለትም በነቢያት አማካይነት ራሱን በመግለጥ ሰዎች ምንም እንኳ ስለምርጫቸው ተጠያቂ ቢሆኑ፥ መልካም ምርጫ እንዲኖራቸው ጫና ማድረግን የሚያካትት ነበር።
በሌላ አባባል፥ ዕቅዱ ሰው ስምርጫው በኃላፊነት የሚጠየቅበትን የተወሰነ ነጻነት አካቷል ማለት ነው፡እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ዕቅዱ ሰው ምን እንደሚያደርግ ማወቁ፥ እያንዳንዱ ሰው የማይፈልገውን እንዲያደርግ የሚያስገድደውና ለድርጊቱም የሚቀጣው መሆኑን አያመለክትም።
የእግዚአብሔር ዕቅድ ሁሉ በተካተተበት የክርስቶስ መስቀል ወቅት፥ ጲላጦስ በነጻነቱ ተጠቅሞ ክርስቶስን ለመስቀል መርጧል፤ ለዚህም ምርጫው ተጠያቂ ሆኗል። የአስቆሮቱ ይሁዳም ክርስቶስን አሳልፎ ለመስጠት ነጻ ውሳኔ አድርጓል። ነጻ ውሳኔውም በኃላፊነት እንዲጠየቅ አድርጎታል። ይሁንና፥ የይሁዳም ሆነ የጲላጦስ ምርጫዎች የእግዚአብሔር ፕሮግራም አካላት በመሆናቸው፥ ሰዎቹ ሳይፈጽሟቸው ሰፊት ይታወቁ ነበር።
ስለሆነም፥ ከሰብአዊ ግንዛቤ ረገድ ችግሮች ቢኖሩም፥ ከሁሉም የሚሻለው መፍትሔ ቢገባንም ሳይገባን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት መቀሰሉ ነው።
ምርጫና ከዚሁ ጋር የሚመሳሰሉ ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጥ ቀርበዋል ብሎ ለመደምደም ይቻላል። ይህም አንዳንዶች ድነት እንደተመረጡና ሌሎች ግን ሳይመረጡ መታለፋቸውን የሚያመለከት ነው። ምርጫ ዘላለማዊ የእግዚእብሔር ተግባር ነው። ምርጫ ከእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ጋር ይያያዛል። ይህንን አስተምህሮ፥ ሙሉ ስሙሉ መረዳት ባይቻልም እንኳ፥ ስመለኮታዊው መገለጥ መገዛቱ ተገቢ ነው።
ሐ. የምርጫ አስተምህሮ መረጃ
ምንም እንኳን አንዳንድ የሥነ-መለኮት ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ክደው የምርጫን አስተምህሮ ሰማግለል ችግሩን ለመፍታት ቢጥሩ፥ መለኮታዊ ምርጫን በመቃወም የሚሰነዘሩ የመሟገቻ ነጥቦች ባብዛኛው አሳቡን ባለመረዳት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ብዙ ጊዜ ምርጫ እግዚአብሔር ያለ ምንም በቂ ምክንያት እንደሚሠራው ተደርጎ ይነገራል። ይህ አባባል የሚመነጨው ካለማመን ነው። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ሲሆን፥ ሉዓላዊነቱ ሁልጊዜ ጥበብ፥ ቅድስና፥ በጎነትና ፍቅር የተሞላ ነው።
ብዙ ጊዜ የሚሰነዘረው ሌላ ተቃውሞ ደግሞ፥ አንዳንዶች በእግዚአብሔር የድነት ዓላማ ውስጥ አለመካተታቸው፥ እግዚአብሔርን ፍትሕ አልባ እንደሆነ ተደርጎ የሚገለጠው ነው። እዚህ ላይ ሊታወቅ የሚገባው ነገር፥ እግዚአብሔር ማንንም የማዳን ግዴታ እንደሌለበትና የሚያድናቸው ሰዎች ደግሞ የሚያምኑ መሆናቸው ነው። አንድ ሰው በክርስቶስ አምኖ የሚድንበት ሁኔታ የእግዚአብሔር አሠራር ምሥጢር ሲሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች እንዲያምኑ በግልጥ ያዛቸዋል (ሐዋ. 16፡31)። ማንም ከፈቃዱ ውጭ አይድንም። ማንም ያለ ፈቃዱ አላምንም የሚል የለም። በሁለቱም ውስጥ የሰው ፈቃድ አለው።
ይህን አስተምህሮ አስመልክቶ ዘወትር የሚሰነዘረው ተቃውሞ፥ ከድነት ስራቁ ሰዎች ወንጌል የማድረሱን አገልግሎት እንደሚያዳክምና፥ ለመዳን የሚፈልጉትንም ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆኑ ነው። የዚህ መልሱ እግዚአብሔር ለፍጥረት ሁሉ ወንጌል እንዲሰበክ በዕቅዱ ውስጥ ማካተቱና፥ የሰውን ሁሉ መዳን የሚሻ መሆኑን መገንዘቡ ነው (2ኛ ጴጥ. 3፡9)። ይሁን እንጂ፥ ሰዎች ለማመንም ሆነ ላሰማመን የሚመርጡበት ሁለንተናዊ ሕሊና የተሰጣቸው እስከሆነ ድረስ አንዳንድ ሰዎች አለመዳናቸው አይቀሬ እውነት ነው።
ሌላው ተቃውሞ፥ አንዳንዶች ለድነት ከተመረጡና ሌሎች ግን ላላመዳን ከተመረጡ፥ ያልተመረጡት ተስፋ የሌላቸውና የጠፉ ናቸው የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፥ ድነትን የሚፈልጉ ሰዎች ድነትን የሚያጡት ሊያገኙት ባለመቻላቸው ሳይሆን፥ ለመዳን በመምረጣቸው መሆኑ ነው። ሮሜ 9፡21-22 እና 2ኛ ጴጥሮስ 3፡9 ውስጥ እንደተመለከተው፥ የእግዚአብሔር ምሕረት ትዕግሥቱ ውስጥ ታይቷል። ማንም ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፥ “እኔ ልጅን ፈልጌ ነበር፤ ዳሩ ግን ስላልተመረጥሁ ይህን ላደርግ አልቻልሁም” የሚልበት ወቅት ከቶ አይኖርም።
ታላላቅ የሚባሉ የሥነ-መለኮት ምሁራንና ማናቸውም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከዚህ አስቸጋሪ አስተምህሮ ጋር መታጎላቸውን ይቀጥላሉ። የመለኮታዊ ምርጫ እውነት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጥ ቀርቧል። የዳኑ ሰዎች ምንም እንኳ በዳኑበት ወቅት አስተምህሮውን ሳያውቁትም፥ ከዘላለም በፊት በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን ያድርጊቱ ያስገነዝባል። ይህ ድነታቸው የእግዚአብሔርን ጸጋ ታላቅነት ያሳያል። ልዑልና ዘላለማዊ የሆነ አምላክ በማንኛውም ሁኔታ ሲታሰብ የታቀደ ፕሮግራም ይኖረዋል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው መገለጥ መሠረት፥ አንድ አማኝ የእግዚእብሔር ዕቅድ ቅዱስ፥ በጥበብ የተሞላና መልካም መሆኑን ከማመን በቀር የሚለው አይኖርም። ይህ ብቻ አይደለም፤ እግዚአብሔር ታጋሽና ክርስቶስ የሞተበትን ድነት አሻፈረኝ ብለው ለጠፉት የሚገደው አምላክ እንደሆነም ይረዳል።
ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡