ሰንበት እና የጌታ ቀን

ሀ. ሰንበት በብሉይ ኪዳን 

[በአማርኛ “ሰንበት” የሚለው ቃል እሁድ እንደሆነ ቢታሰብም በመጽሐፍ ቅዱስ ለአይሁድ ሰባተኛ ቀን የሆነውን ቅዳሜ የሚያመለክት ነው (ዘፀ. 16፡23-29፤ 20፡10፤ ዘሌዋ. 23፡3፤ ዘዳግ. 5፡14)። ይህን የእረፍት ቀን” (ሰንበት) በመጠበቅ አይሁዶች ለእግዚአብሔር የተለዩ ሕዝቦች መሆናቸውን የሚያሳዩበት መለያቸው ነበር (ዘፀ. 31፡13)። በሙሴ ሕግ (የሚያርሱበትን” ምድር ሰሰባተኛው ዓመት የሚያሳርፉበት “የዓመት እረፍት የሚባል ሥርዓት ደግሞ ነበራቸው (ዘሌዋ. 25፡2-8፤ 26፡34-35፥ 43፤ 2ኛ ዜና . 36፡21)። በዚህ መጽሐፍ “ዕንበት” የሚለው ቃል ቅዳሜን ማለትም “እረፍት ቀን” በመሳል ለአይሁድ የተሰጠውን ቀኝ እና ሊጠብቁት የሚጎባውን ዕለት የሚያመለክት ነው።]

እግዚአብሔር ከራሱ የፍጥረት ሥራ በመጀመር፥ የሁሉንም ጊዜ አንድ ሰባተኛ እጅ ለመቀደስ ወይም ለመለየት መርጧል። ለእስራኤላውያን ሰባተኛው ቀን የእረፍት ቀን እንዲሆን ወሰነ። በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱ እንድታርፍ ተደርጓል (ዘዳ. 23፡10-11፤ ዘሌ. 25፡2-7)። ለሰባተኛው ዓመት ለሰባተኛ ጊዜ ለማሰብም ኀምሳኛው ዓመት እንደ ኢዮቤልዩ ይከበር ነበር። በተላያዩ ዝርዝር ጉዳዮች የሰንበትና የኢዮቤልዩ ዓመታት ለእግዚአብሔር መንግሥት ትንቢታዊ ናቸው። ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ሰባተኛና የመጨረሻ የአገዛዝ ሥፍረ-ዘመን ሲሆን፥ የሚታወቀውም ለፍጥረት ሁሉ የሚፈጸም የሰንበት እረፍት ሰመሆን ነው። በአሁኑ ዘመን የሚከበረው ዕለት ከአዲሱ ፍጥረት ጅማሬ ሳቢያ ሰመለኮታዊ አሠራር ከሰባተኛው ወደ አንደኛው ቀን ቢለወጥም፥ በጊዚ አከፋፈል አሁንም ለእረፍት የሚውለው ተመሳሳይ መጠን፥ ማለትም ከሰባቱ ቀናት አንዱ ሆኗል። 

“ሰንበት” የሚለው ቃል መተውን ወይም ከሥራ ሙሉ በሙሉ ማረፍን ያመለክታል። ክማያቋርጡት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችና በዓላት ባሻገር፥ ዕለቱ በምንም መልኩ የአምልኮ ወይም የአገልግሎት ጊዜ አይደለም። 

ሰንበትን አስመልክቶ የሚታየውን ግራ መጋባት ለማቃለል፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትክክለኛ መልእክት በጥንቃቄ ማጥናቱ አስፈላጊ ነው። 

ሰንበትን ከተለያዩ የዘመን ክፍሎች ጋር ስናገናዝብ፥ በተወሰነ ደረጃ ግልጥ ማስረጃ ለማግኘት ይቻላል። 

ከአዳም እስከ ሙሴ በነበረው ጊዜ እግዚአብሔር የስድስት ቀናት ሥራውን ጨርሶ እንዳረፈ ሲገለጥ (ዘፍጥ. 2፡2-3፤ ዘዳ. 20፡10-11፤ ዕብ.4፡4)፥ ሰውን በተመለከተ ስለ ሰንበት በዚህ ወቅት የተጠቀሰ ነገርን አናነብም። እስራኤላውያን ከግብፅ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ፥ ሰው የሰንበትን ቀን እንዳከሰረ የሚያመለክት አሳብ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ አልተጠቀሰም። 

መጽሐፈ ኢዮብ የእምነት አባቶችን ሃይማኖታዊ ሕይወትና ልምምድ ይገልጣል። ምንም እንኳ እነዚህ አባቶች ለእግዚአብሔር የነበራቸው የተለያዩ ኃላፊነቶች ቢገለጡ፥ ስለ ሰንበት ዕለት ግዴታ የሚናገር አሳብ ግን አልተጠቀሰም። በሌላ በኩል ግን የሰንበት በሙሴ እጅ ለእስራኤላውያን መሰጠት፥ ሰንበት በሰው ልጆች ዘንድ መከበር የጀመረበት ጊዜ መሆኑን በግልጥ ያመለክታል (ዘጸ. 16፡29፤ ህ . 9፡14፤ ሕዝ. 20፡12)። 

በተመሳሳይ ሁኔታ፥ መጀመሪያ ከተደነገገው ሰንበት አንድ ሳምንት ወይም ሰባት ቀናት ቀደም ብሎ፥ የእስራኤል ልጆች የሰንበትን ሕግ በማፍረስ ረዥም መንገድ ተጉዘው ከኤሊም ወደ ሲና ምድረ በዳ እንደመጡ ከመጀመሪያዎቹ የሰንበት ድንጋጌ ዘገባዎች ለመረዳት ይቻላል (ዘጸ. 16፡1-35)። በዚያ ምድረ በዳ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በማጉረምረሙ፥ በዕለቱ ከሰማይ ምግብ ይወርድላቸው ጀመር። ምግቡ ለስድስት ቀናት እንጂ፥ በሰባተኛው ቀን መሰብሰብ አልነበረበትም። ስለዚህ በሰንበት ዕለት ጉዞ ማድረጋቸው የሚያስረዳው፥ ዕለቱን እንደ ሰንበት ያላከበሩት መሆኑን ነው። 

ከሙሴ እስከ ክርስቶስ በነበረው ዘመን፥ የሰንበት ሕግ ሥራ ላይ ውሏል። ሰንበት የማከበሩ ጉዳይ ሕግ ውስጥ የተካተተ ሲሆን (ዘጸ. 20፡10-11)፥ የሰንበትን ሕግ ለተላለፈ ሰው ይደረግ የነበረው መለኮታዊ መፍትሔም በመሥዋዕቶች ሕግ ውስጥ ተካቷል። እዚህ ላይ የሰንበት ሕግ ለአሕዛብ እንዳልተሰጠና በያህዌና በእስራኤል መካከል የሚከናወን ልዩ ምልክት እንደነበር መገንዘቡ ተገቢ ነው (ዘጸ. 31፡12-17)። ከእስራኤል ኃጢአቶች መካከል ሰንበትን ለማክበርና ለምድሪቱም እረፍት እለመስጠታቸው የተለየ አጽንኦት የተደረገባቸው ናቸው። 

በዚህ የሕግ አማካይ ክፍለ ጊዜ፥ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ ከሚደርሱት ፍርዶች አንዱ የሰንበታቶቿ ማክተም መሆኑን ተንብዮአል (ሆሴዕ 2፡11 )። ይህ ትንቢት ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ነውና አንድ ቀን መፈጸሙ የግድ ነበር። 

ከሞቱ ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ የክርስቶስ ምድራዊ ሕይወትና አገልግሎት ክሕግ በታች ነበር። በዚህም ምክንያት ክርስቶስ ሕግን እንደሚጠብቅ፥ እንደሚተነትንና በሥራ ላይ እንደሚያውል ታይቷል። በመሆኑም ክርስቶስ የሰንበት ሕግ በሰዎች ትውፊትና ትምህርቶች እንደተዛባ በመገንዘብ በዘመኑ ካሉ አስተማሪዎች የተለየ ትምህርት አስተምሯል። ስለዚህ ሰንበት ለሰው ልጅ ጥቅም እንደተሰጠና ሰው ከሰንበት ወጎች የተነሣ ቀኑ ሸክም ይሆንበት ዘንድ እንደማይገባ እስተምሯል (ማር. 2፡27)። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰንበትን ላካተተው የሙሴ ሕግ ሁሉ በታማኝነት ይታዘዝ ነበር። ይህ የሆነው ጌታ በነበረበት ዘመን ሕግ በሥራ ላይ ስለነበረ ነው። ይሁን እንጂ፥ ይህ ሁኔታ በጸጋ ዘመንና በሌላ ሥፍረ-ዘመን የሚኖረው ክርስቲያን የክርስቶስን የሰንበት አክባሪነት ምሳሌ ሊከተል ይገባል ለሚል ትምህርት አባባል መሠረት ሊሆን የማይችል መሆኑን ይህ ግልጥ እውነት ያስገነዝባል። 

ለ. ሰንበት ሰአሁኑ የቤተ ክርስቲያን ዘመን 

ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ፥ በአዲስ ኪዳን በስሕተት እንኳ ሰንበትን ያከበረ አማኝ አልተጠቀሰም። ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የተመለሱ እያሌ እማኞች ሰንበትን ማከበራቸው ግልጥ ቢሆንም፥ እንዲህ ዓይነቱ አከባበር በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ አልተጠቀሰም። እንደዚሁም፥ ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ለአይሁዶች፥ ለአሕዛብ ወይም ለክርስቲያኖች ሰንበትን ያከብሩ ዘንድ የተሰጠ ትእዛዝ አናገኝም፡፡በሰንበት ቀን መሥራትም እንደ ኃጢአት የተቆጠረበት ሁኔታ አልተመለከተም። 

በተቃራኒው ግን በጸጋ ዘመን የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑ አማኞች የሰንበትን ሕግ እንዳይጠብቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። 

ገላትያ 4፡9-10 ቀናትን፥ ወራትን፥ ወቅቶችንና ዓመታትን የማክበሩ ተግባር የማያስፈልግ መሆኑን የሚያሳይ አሳብ አለ። እነዚህ ነገሮች የሚከበሩት በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያስገኛሉ ከሚል አስተሳሰብ ሲሆን፥ አክባሪዎቹም በአንድ ወቅት እግዚአብሔርን የሚያስቡና በሌላ ጊዜ ግን በግዴለሽነት የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። 

ዕብራውያን 4፡1-13 ሰንበት እግዚአብሔር ከሥራው ያረፈበትና አማኝም በሚድንበት ጊዜ የሚገባበት የእረፍት ስፍራ መሆኑን ያስረዳል። 

ቆላስይስ 2፡16-17 ውስጥ የሰፈረው ቃል የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ከሰንበት እከባበር ጋር በተያያዘ ሊፈረድበት የማይገባ መሆኑን በግልጥ ያስረዳል። አሁን አዲስ ፍጥረት ለሆነው አማኝ ክርስቶስ ከሆነለት ሁኔታ አንጻር፥ በሰንበት ላይ የዚህ ዓይነት እመለካከት መያዙ ትክክል ነው (ቆላ. 2፡9-17)። በዚህ ምንባብ ውስጥ የተጠቀሱት የሥርዓታዊ ሕግ አካላት የሆኑት ልዩ ወይም ተጨማሪ ሰንበታት ሳይሆኑ፥ ሳምንታዊዎቹ ሰንበታት ይሆኑ ይሆናል፥ ለምሳሌ (ዘሌዋ. 16፡31)። እንድ እማኝ በራሱ አእምሮ ሲረዳ ቀናትን ሁሉ በእኩልነት ሊመለከት እንደሚችል ሮሜ 14፡5 ውስጥ ተጎልጧል። ይህ ሁኔታ በታማኝነት ማምለክን ገለል የሚያደርግ ሳይሆን፥ እንዲህ ላለው ሰው ቀናት ሁሉ ለእግዚአብሔር በመገዛት የተሞሉ መሆናቸውን ያስረዳል። 

አዲስ ኪዳን ውስጥ ሰንበትን በመጠበቅ ረገድ የክርስቲያንን ሕይወትና አገልግሎትን አስመልክቶ እንደ ሕግ የተሰጠ ነገር የለም። ስለዚህ በሙሴ በተሰጠው የሰንበት ሕግ ፈንታ፥ ሰአዲሱ ፍጥረት የጌታ ቀን ሰሚለው የተተካ መሆኑን መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። ይህ የጌታ ቀን በክብሩ፥ በከፈተው መብትና በረከቶቹ ከሰንበት እጅግ የሚልቅ ነው። 

ሐ. ሰንበት በሚመጣው ዘመን 

ከአዲስ ኪዳን ትምህርት ጋር ሙሉ ለሙሉ በተዛመደ መልኩ፥ አዲሱ የጌታ ቀን የሚሠራው ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው። የሰንበት ሕግ እንደገና በሥራ ላይ እንደሚውል ተተንብዮአል። የቤተ ክርስቲያን መጠራት ከተፈጸመና ከዓለም ከተነጠቀች በኋላ፥ የሰንበት ሕግ የጌታን ቀን በመተካት የሚሠራ መሆኑ ነው የተገለጠው። በዚህ ዘመን ፍጻሜና በእግዚአብሔር መንግሥት መካከል ጣልቃ በሚገባው የታላቁ መከራ አጭር ወቅት እንኳ የሰንበት አሳብ ይንጸባረቃል (ማቴ. 24 ፡20)። ሰንበት የሚመጣው መንግሥት ዘመን ዋነኛ ጉዳይ እንደሚሆንም በትንቢት ተመልከቷል (ኢሳ. 66፡23፤ ሕዝ. 46፡1)። 

መ. የክርስቶስ ትንሣኤና የሳምንቱ መጀመሪያ ዕለት 

ከክርስቶስ ትንሣኤ እንሥቶ እስከዛሬ ድረስ የሳምንቱ የመጀመሪያ ዕለት በቤተ ክርስቲያን በመከበር ላይ ነው። ይህ እውነት በአዲስ ኪዳን ዘገባዎች፥ በቀደምት አባቶች ጽሑፎችና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተረጋገጠ ነው። ከሞላ ጎደል በሁሉም ክፍለ ዘመናት፥ እግዚአብሔር ሰአዲሱ ፍጥረት ሊሠራ ያቅደውን የእሁን ዓላማ ሳይገነዘቡ ሰባተኛውን የሰንበት ዕለት ለማክበር የተነሡ ሰዎች ነበሩ። ሰባተኛውን ቀን ማክበር ያስፈልጋል በማለት የሚያስተምሩት፥ ትምህርታቸው ከቃሉ ውጭ በሆኑ ነጥቦች የተደገፈና ሌላ እምነት ያላቸው ናቸው። በሰንበት ጉዳይ ውዝግብ የሚነሣው የአማኞች አምልኮ በሙሴ የሰንበት ሕግ እንደሚመራ ተደርጎ ሲወሰድ ነው። ይህ ሲሆን አዲስ ኪዳን የሚያስተምረው የአዲስ ፍጥረት” እውነት ይዘነጋል። 

ሠ. አዲሱ ፍጥረት 

የዚህ ሥፍረዘመን የእግዚአብሔር ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን እንደተለየ ሕዝብ የሚጠራት መሆኑን አዲስ ኪዳን ያስተምራል (ሐዋ. 15፡13-18)። በዚህ የእግዚአብሔር ጥሪ የዳኑ ሰዎችም ሰማያዊ ዜጎች የሆኑ አዲስ ፍጥረታት ናቸው። እነዚህ ሰዎች በአጠቃላይ አስደናቂ ክብርና ፍጹምነት የሚሰጣቸው መሆኑ ሲገለጥ (ኤፌ. 5፡25-27)፥ በግለሰብ ደረጃም እጅግ የላቀ መለኮታዊ ተግባርና ለውጥ የሚካሄድባቸው ናቸው። እንዲሁም ጠቅላላው አካል በመሠረቱ ከክርቶስ ጋር እንደተገናኘ ሁሉ (1ኛ ቆሮ. 12፡12)፥ ግለሰብ አማኝም በዋናነት ከጌታ ጋር ተዛምዷል (1ኛ ቆሮ. 6፡17፤ ሮሜ 6፡5፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡13)። 

ግለሰብ አማኝን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ያስተምራል፡- (1) ኃጢአትን በተመለከተ፥ በዚህ አካል ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ አማኝ ከኃጢአቱ ነጽቶና ይቅርታን አግኝቶ ጸድቋል። (2) ስጦታን በተመለከተ፥ ለእያንዳንዱ አማኝ ውስጡ የሚኖር መንፈስ ቅዱስና የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነው ዘላለማዊ ሕይወት ተበርክቶለታል። ከክርስቶስ ጋርም የእግዚአብሔር ሕጋዊ ወራሽ ነው። (3) ሰፍራውን በተመለከተ፥ እያንዳንዱ አማኝ የእግዚአብሔር ጽድቅ ሆኖ ሰውድ ልጁ አማካይነት ለዘላለም ተቀባይነትን አግኝቷል (2ኛ ቆሮ. 5፡21፤ ኤፌ. 1፡6)። ይህ ብቻም አይደለ ከተሰጠው ጽድቅ የተነሣ የክርስቶስ ስውር አካል ክፍል፥ የከበረችው ሙሽራ አካልና ክርስቶስ ራሱ የሆነው የሚያስተዳድረው እዲስ ፍጥረት ሕያው ተካፋይ ለመሆን በቅቷል። “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። ነገር ግን፥ የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው” (2ኛ ቆሮ. 5፡17-18 ገላ. 6፡15፤ ኤፌ. 2፡10፤ 4፡24)። 

ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ አማኞች ሲጽፍ፥ “እናንተ የተመረጣችሁ ትውልድ ናችሁ” (1ኛ ጴጥ. 2:9) ብሏል። ይህም በቀጥታ በእግዚአብሔር ኃይል የተፈጠረና ከሰማይ የተወለደ ልዩ ዘር ወይም ብሔር ማለት ነው። የመጀመሪያው አዳም የራሱ ሰብአዊ ሕይወትና ፍጹማዊነት የጎደለው ሕይወት ተካፋይ የሆነውን የሰው ዘር እንደወለደ ሁሉ፥ የመጨረሻው አዳም ክርስቶስ ደግሞ ዘላለማዊ ሕይወቱንና ፍጹምነቱን የሚካፈል አዲስ ዘር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በመፍጠር ላይ ነው። “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” (1ኛ ቆሮ. 15፡45)። አማኝ በክርስቶስ በመሆኑ የትንሣኤው ተካፋይ የሚያደርገውን ሕይወት ያገኘ መሆኑ ተገልጧል (ሮሜ 6፡4፤ ቆላ. 2፡12-13፤ 3፡1-4)። ይሁን እንጂ፥ አካሉን በተመለከተ አማኙ ገና የክርስቶስን የትንሣኤ እካል የሚመስል የከበረ አካል ሊላብስ ይገባል (ፊልጵ. 3፡20-21)። ክርስቶስ ከሞት እንደተነሣ “እንደበኩራት በሰማይ መታየቱ የሚከተሉት ሁሉ የከበረ አካል ለብሰው እንደርሱ የሚነሡ መሆናቸውን ያመለክታል (1ኛ ዮሐ. 3፡2)። 

እዲሱ ፍጥረት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ፥ በሁሉም ስፍራ ከአሮጌው ጋር ተነጻጽሮ ቀርቧል። ይህ አዲስ ፍጥረት የጀመረው በክርስቶስ ትንሣኤ ሲሆን፥ ዳግም የተወለዱትንና በርሱ የሆኑትን ሰማያዊ ዜጎች ያካትታል። አማኝ የዳነውና ነጻ የወጣው ከዚያ አሮጌና የተበላሸ ፍጥረት መሆኑ ግልጥ ነው። 

ሰንበት አሮጌውን ፍጥረት ለመዘከር እንደተፈጠረ ሁሉ (ዘጸ. 20፡10-11፤ 31፡12-17፤ ዕብ. 4፡4)፥ የጌታ ቀንም እዲሱን ፍጥረት ይዘከረዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ሰንበት እንደ ምድራዊ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በእስራኤላውያን ብቻ ይከበር እንደነበር ሁሉ፥ የጌታ ቀንም የዕማያዊው የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል በሆነችው ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ነው። 

ረ. የጌታ ቀን (እሁድ) 

በጸጋ ሥር ባሉ የእግዚአብሔር ልጆች ላይ የሰንበት (ቅዳሜ) ሕግ ተፈጻሚ የሚሆንበት ድንጋጌ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አይታይም። በአንጻሩ ግን ክርስቲያኖች የሳምንቱን የመጀመሪያ ቀን (እሁድ) የሚያከብሩባቸው ምክንያቶች አሏቸው። 

1. ፀጸጋ ዘመን ስለ አዲስ ቀን ተተንብይዋል፥ ተወስኗልም። መዝሙር 118፡22-24 እና የሐዋርያት ሥራ 4፡10-11 እንደሚነግሩን፥ ክርስቶስ በስቅላቱ ግንበኞች” በተባሉት እስራኤላውያን የተናቅ ድንጋይ ሆኗል። ከሞት በመነሣቱ ግን የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ። ይህ አስደናቂ ነገር የተፈጸመው በእግዚአብሔር ሲሆን፥ የአፈጻጸሙ ዕለትም የደስታና የትፍስሕት ዕለት ይሆን ዘንድ በመለኮታዊ ሥልጣን ተወስኗል። በመሆኑም፥ ክርስቶስ በትንሣኤው ማለጻ ያቀረበው ሠላምታ “ደስ ይበላችሁ የሚል (ማቴ. 28፡9) ነበር። አሳቡ በቀጥታ ሲፈታ (“ታላቅ ደስታ!” ማለት ነው። “እግዚአብሔር የሠራት ቀን” እንደመሆኗ “የጌታ ቀን” መባሏ ትክክል ነው። 

2. የመጀመሪያው ዕለት አከባበር በተለያዩ ሁኔታዎች ተመልክቷል።(ህ) ክርስቶስ ከሞት በተነሣበት ዕለት (ማቴ. 28፡1)። (ለ) በዚያን ዕለት ደቀ መዛሙርቱን በአዲስ ኅብረት አገኛቸው (ዮሐ. 20፡19)። (ሐ) በዚያው ዕለት ትእዛዛትን ሰጣቸው (ሉቃስ 24፡13-45)። (መ) በዚያው ዕለት እንደ “በኩራት” ወይም እንደ በኩራት ነዶ ወደ ሰማይ ዐረገ (ዘሌ . 23፡10-12፤ ዮሐ. 20፡17፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡20፥ 23)። (ሠ) እስትንፋሱን እፍ ያለባቸው በዚያን ዕለት ነው (ዮሐ. 20፡22)። (ረ) በዚያን ዕለት መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ ወረደ። (ሰ) ሐዋርያው ጳውሎስ በጢሮአዳ የሰበከው ያን ዕለት ነው (ሐዋ. 20፡6-7)። (ሸ አማኞች የጌታን እራት ሊወስዱ የተሰበሰቡበት ዕለትም ነው (ሐዋ. 20፡6-7)። (ቀ) እግዚአብሔር እንዳበለጠጋቸው መጠን ገንዘብ ያዋጡትም በዚያን ዕለት ነው (1ኛ ቆሮ. 16፡2)። (በ) ጌታ ለዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት በዚያን ዕለት ተገለጠ (ራእይ 1፡10)። 

3. ስምንተኛው ቀን የግርዘት ቀን ነበር። በዚህ ዕለት የሚፈጸም ግርዘት፥ አማኝ በክርስቶስ ሞት አማካይነት ከሥጋና ከአሮጌው ሥርዓት መለየቱን በምሳሌነት ያሳያል (ቆላ. 2፡11}። ከሳምንቱ ፍጻሜ ቀጥሉ በመጀመሪያው ዕለት የሚውል ስምንተኛ ቀን እንደ መሆኑ የአዲስ ጅማሬ ተምሳሌት ነው። 

4. አዲሱ ዕለት የጸጋ ነው። በሕግ ሥራ አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር ለሚዛመዱ ሰዎች፥ ክሳምንቱ አድካሚ ሥራ በኋላ የእረፍት ቀን ያሰጣቸው ነበር። ሥራዎቻቸው በክርስቶስ ለተጠናቀቀላቸው የጸጋ ዘመን ሰዎች ግን ይህ ቀን እንደ እረፍት ብቻ ሳይሆን፥ የአምልኮ ዕለት ተብሎ ነው የተሰጣቸው። ይህም የሳምንቱ መጀመሪያ ዕለት እንደመሆኑ፥ የሥራ ቀናትን ሁሉ ይቀድማል። አማኝ በመጀመሪያው ዕለት ከሚያገኘው ባርኮት፥ ቀጣዮቹን ስድስት ቀናት ጌታውን ያገለግልበታል። የእረፍት ቀን የሚያስፈልገው፥ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት በሥራዎቻቸው ላይ የተመሠረተ ለሆኑ ነው። የማያቋርጥ አምልኮና አጎልግሎት የሚካሄድበት ዕለት ደግሞ፥ ክርስቶስ በፈጸመው ሥራ አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ላሳቸው ሰዎች ነው። ሰባተኛው ዕለት በማይላቀቁት ሕግ ሲታወቅ፥ የመጀመሪያው ዕለት በጸጋ ምርጫና ነጻነት ይሰያል። ሰባተኛው ቀን ምናልባት አንድ ቀን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አገኝ ይሆናል በሚል ቀቢጸ-ተስፋ ይከበር የነበር ሲሆን፥ የመጀመሪያው ቀን ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ባረጋገብ ሰው ይከበራል። ሰባተኛው ቀን የሚፈጸመው በሥጋ ኃይል ሲሆን፥ የመጀመሪያው ቀን ግን በአማኙ ልብ ውስጥ በሚያድረው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት ይከናወናል። 

5 . አዲሱ ዕለት በእግዚአብሔር ተባርኳል። በዚህ ዘመን፥ መንፈስ ቅዱስ ሙላት ያደረባቸውና የእግዚአብሔር ፈቃድ በግልጥ የታየባቸው እውነተኛ አማኞች የጌታን ቀን ሲጠብቁ ሰባተኛውን ቀን ግን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው አድርጎው አይረዱትም። እነዚህ ወገኖች የሰንበትን ሕግ በመጣስ በደለኞች ቢሆኑ ኑሮ ስለ ኃጢአታቸው ያቀጡ ነበር ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። 

6. አዲሱ ዕለት የተሰጠው ለእማኝ ግለሰብ ብቻ ነው። ላልዳነ ሰው አልተሰጠውም። ያልዳኑ ሰዎች ማንኛውንም ቀን ቢያከብሩ እግዚአብሔር ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት እንደሚያገኙ የሚያስገነዝብ መሠረት መጣሉ እጅግ አደናጋሪ ነው። ምክንያቱም በክርስቶዕ ከሚገኘው ድነት ውጭ ሰዎች ሁሉ የጠፉ ናቸው። የእረፍት ቀን ለሰው ሁሉ ማኅበራዊ ወይም አካላዊ ጠቀሜታ ሊኖረው ቢችልም፥ እንዲህ ዓይነቱ የቀን አከባበር በእግዚአብሔር ፊት ምንም እንደማያስገኝላቸው ያልዳኑ ሰዎች ሊገነዘቡ ይገባል። 

ይህን ዕለት (እሁድ) ትጠብቅ ዘንድ ለቤተ ክርስቲያን እንደ ትእዛዝ አልተሰጣትም። ስለሆነም፥ የመጀመሪያው ዕለት አከባበር ለግለሰብ አማኝ እንጂ፥ ለቤተ ክርስቲያን አለመሰጠቱ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል። አማኝ ይህን ዕለት የሚያከብርበት ሁኔታ ክርስቶስ ከሞት በተነሣበት ጠዋት ሰተናገራቸው ሁለት አባባሎች ውስጥም ተመልክቷል፤ 

“ደስ ይበላችሁ!” እና “ሄዳችሁ ተናገሩ”። ይህ ጥሪ በማንኛውም አምልኮና አገልግሎት ውስጥ የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ማድረግን የሚጠይቅ ሲሆን፥ ከሰባተኛው ቀን እረፍት ጋር ይጻረራል። 

7. የመጀመሪያው ቀን ሰይድ እንዲከበር የተሰጠ ትእዛዝ የለም። የጸጋ ተግባር በመሆኑ፥ ዕለቱን ስለማክበር የተጻፈ ግዴታ የለም። አከባበሩ ሊከናወን የሚገባበት ሁኔታም በዝርዝር አልተመለከተም። ይህ ጥበብ የተሞላበት ልግስና እንደሚያስረዳው፥ ማንም የጌታን ቀን እንደ ግዴታ እንዲቆጥረው የተጠቀሰበት ሁኔታ የለም። ከልብ በመነጨ ፍላጎት ሊከናወን ይገባል። እስራኤል በእግዚአብሔር ፊት ሞግዚቶችና አስተዳዳሪዎች እንደሚያሻቸው ለጋ ሕፃናት ስለነበረች፤ ከሕፃን እንደሚሰጥ ዓይነት ሕግ አስፈለጋት (ገላ. 4፡1-11)። ቤተ ክርስቲያን ግን በእግዚአብሔር ፊት እንደ እዋቂ ልጆች ትታያለች። የአማኙ ሕይወት በጸጋ ዘመን ምን መምሰል እንዳለበት በሚገባ ተገልጧል። እግዚአብሔር ከእማኙ የሚፈልጋቸው ነገሮች በፈቃደኝነት መሆን ያለባቸው መሆኑን በማሰብ ያቀረበው በልመና ነው (ሮሜ 12፡1-2፤ ኤፌ. 4፡1-3)። በሚገባ ቃሉን የተረዳና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ክርስቲያን የክርስቶስ ትንሣኤና የአዲስ ፍጥረት ዕላት በሚከበርበት ጊዜ በሌላ ሥራ ይጠመዳል ብሎ ለመገመት አይችልም። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ለእግዚአብሔር የማይገዛ ከሆነ፥ ያለፈቃደኛነት ቀንን ማክበር ሥጋዊ ልቡን አያስተካክለውም። እንዲህ ዓይነቱ አከባበርም እግዚአብሔርን አያስደስተውም። ስለሆነም፥ በእግዚአብሔርና በሥጋዊ ክርስቲያን መካከል ያለው ጉዳይ ውጫዊ ተግባር ሳይሆን፥ የተሰጠ ሕይወት ነው። 

የጌታ ቀን የሚከበርበት ሁኔታ ወደ ቀናት ሁሉ ሊዛመት ይችላል። ክርስቶስ ለአብ የሚገዛው እንደኛው ዕለት ከሌላው ባነሰ ሁኔታ አልነበረም። የሰንበት እረፍት ለሁሉም ቀናት በዚያው መልኩ ሊቀጥል አይችልም። ዳሩ ግን አማኝ በሳምንቱ መጀመሪያ ዕለት የበለጠ ጊዜና ነጻነት ሊኖረው ቢችልም፥ የጌታ ዕለት አከባበር መለያ የሆኑት እምልኮ፥ ደስታና እገልግሎት በተቻለ መጠን የዕለት ተዕለት ልምምዶቹ ሊሆኑ ይገባል (ሮሜ 14፡5)።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: