ሰው፡- አፈጣጠሩ

ሀ. የሰው ፍጡርነት 

ሰው በዚህ አስደናቂ በሆነ ፍጥረተ ዓለም መካከል በመሆን፥ የዚሁ ፍጥረተ ዓለም ቁንጮ ሆኖ ሲኖር፥ የራሱንና የሌሎቹን ፍጥረታት አጀማመር ለመረዳት ጥረት ያደርጋል። ተፈጥሮ የሰውን አፈጣጠር ስለማይገልጥና በቃል እየተወራረደ የመጣ ትምህርትም የሚያስተማምን መረዳት ስለማያስገኝ፥ እግዚአብሔር ራሱ ስለ ሰው አፈጣጠር በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት የገለጠውን መመልከቱ አስተማማኝ ማረጋገጫ ይሆናል። በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሰው አፈጣጠር በማያሻማ አኳኋን ተገልጧል። 

የሰውን አመጣጥ ማወቅ ለሰው ዘር ሁሉ ሰብእዊ ጥያቄና መላምታዊ ጉዳይ ከመሆኑ የተነሣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ለጥያቄው መልስ ለመሻት የሞከሩ ሁሉ፥ የሰውን አፈጣጠር ለመግለጥ ብዙ ጥረዋል። እነዚህ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሰብአዊ የሙከራ ውጤቶች የሚያመለክቱት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጠው ውጭ ሰው ስለ ራሱ አፈጣጠር የሚያገኘው ማረጋገጫ የሌላ መሆኑን ነው። ትክክለኛውና የማያወላውለው ማረጋገጫ የሚገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው አፈጣጠር ትክክለኛና ብቸኛ ምስክር መሆኑን ከሚጻረሩ አመለካከቶች አንዱ፥ የአዝጋሚ ለውጥ ወይም ኢቮሉሽን (evolution) ፅንሰ-አሳብ ነው። በዚህ ንድፈ-አሳብ መሠረት የመጀመሪያው ሕያው ሕዋስ በአንድ ሁኔታ መጣና በተፈጥሮ ምርጫ ሂደት ከዚያ ሕዋስ ሰው ተገኘ። ይህ ፅንሰ-አሳብ በዓለም ያለውን የሕይወት ውስብስብ አፈጣጠር በዚህ የተፈጥሮ ሂደት መሠረትነት ለመግለጥ ይሞክራል። 

በዚህ ንድፈ-አሳብ መሠረት ዕፅዋት፥ እንስሳትና ሰው ራሱ የተገኙት በድንገተኛ ተፈጥሯዊ ለውጥ ነው። ገላጣው ሌሎች ዝርያዎችንም ይመለከታል። ይሁን እንጂ፥ ድንገተኛ ለውጦች ከጥቅም ይልቅ ጉዳት አላቸው። ድንገተኛ ለውጥ ሲጠቅም፥ ወይም አዲስ ዝርያ ሲያመጣ አልታየም። በሕያዋን ፍጥረታት ዝርያዎች መካከል ልዩነት መኖሩን መጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘግብ፥ እግዚአብሔር እንስሳትን “እንደየወገናቸው” የፈጠራቸው መሆኑንም አረጋግጧል (ዘፍጥ. 1፡21፥ 24-25)። 

ከእንስሳት ጋር ሲነጻጸር ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነው (ዘፍጥ. 1፡26-27)። ንድፈ-አሳብና ቅሪተ-አካላት (fossis) ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ያሉትን ሕልው ነገሮች ለመግለጥ እንደማይችሉ የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ-አሳብ አራማጆች ይረዳሉ። የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ-አሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒነት ሰው ሊረዳው የሚቻለው ብቸኛ ገለጣ ከመሆኑም በላይ፥ ስለ ሰው አመጣጥ አሳሳዊ ባልሆነና በተፈጥሯዊነት ፅንሰ-ሃሳብ ላይ ተመሥርቶ የቀረበ ነው ይላሉ። 

በተመሳሳይ ሁኔታ፥ “መለኮታዊ አዝጋሚ ለውጥን” (theistic evolution) የተሰኘው፥ እግዚአብሔር አዝጋሚ ለውጥን ተጠቅሞበታል የሚለው ንድፈ-አሳብ፥ አስተምህሮውን የሚመሠርተው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚገልጠውን ቀጥተኛ ትርጉም በመካድ ላይ ነው። 

የሰው አፈጣጠር መሠረታዊ ትምህርት በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ተመልክቷል (ዘፍጥ. 1፡1-2፡25፤ ዮሐ. 1፡3፤ ቆላ. 1፡16፤ ዕብ. 11፡3)። እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑ በዘፍጥረት መጽሐፍ መጀመሪያ ምዕራፍ ብቻ አሥራ ሰባት ጊዜ ሲገልጥ፥ በሌሎቹ ክፍሎች ደግሞ ከአምሳ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። አንዳንዶቹ ተፈጥሮን በቀጥታ የሚያስተምሩ ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ደግሞ እግዚአብሔር የአዳምና የሔዋን ፈጣሪ መሆኑን ያመለክታሉ (ዘፀ . 20፡11፤ መዝ. 8፡3-6፤ ማቴ. 19፡4-5፤ ማር. 10፡6-7፤ ሉቃስ 3፡38፤ ሮሜ 5፡12-21፤ 1ኛ ቆሮ. 11፡9፤ 15፡22፥ 45፤ 1ኛ ጢሞ. 2፡13-14)። የፍጥረት መሠረታዊ ፅንሰ-አሳብ፥ ከዘፍጥረት 1፡1 በፊት ስለነበረው ሁኔታ ሳይጠቀስ፥ እግዚአብሔር ዓለምን ከምንም ፈጠረ ይላል። 

የዘፍጥረት መጽሐፍ በግልጥ እንደሚያስረዳው፥ ሰው የእግዚአብሔር ፍጡራን ሁሉ መደምደሚያ ሲሆን፥ እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ያጠናቀቀውም በስድስት ቀናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በእግዚአብሔር ቃልነት በሚቀበሉ ሰዎች ስለ ፍጥረት ቀናት የተለያዩ አመለካከቶች ተሠንዝረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መሆኑን ከሚያምኑ ሰዎች አንዳንዶች ደግሞ ዘፍጥረት 1 ላይ ያለው ገለጣ፥ ቀደም ሲል ከሰይጣንና ከወደቁት መላእክቱ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የጠፋው ዓለም እንደገና መፈጠር ታሪክ ነው ይላሉ። በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 1-2 ከተገለጠው የስድስት ቀን የፍጥረት ሥራ በፊት ሕይወት አልባ የሆነ ዓለም ነበር ለሚለው አመለካከት ይህ እንደማስረጃ የሚቀርብ ነው። 

አንዳንዶች የስድስቱ ቀናት የፍጥረት ጊዜ ዕለታዊ ስሌት፥ ከሀያ አራት ሰዓት ሊበልጥ ወይም ሊያንስ ይችላል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቀን” የሚለው ፅንሰ-አሳብ አንዳንዴ ረዘም ያለ ጊዜን፥ ለምሳሌ “የጌታ ቀን” የሚለውን ዓይነት ያመለክታል ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ በአንደኛው ቀን በሁለተኛው ቀን በሦስተኛው ቀን … በማለት፥ “ቀን” ከሚለው ቃል ጋር የተወሰነ ጊዜን ለማመልከት ቁጥር ስለተጨመረበት፥ 

“ቀን” ማለት ሀያ አራት ሰዓት ነው በማለት አጥብቀው ይከራከራሉ። ስለዚህ በዚህ አመለካከት እግዚአብሔር ሰውንና እንስሳትን ሲፈጥራቸው፥ የተወሰነ ዘመን ያህል የኖሩ በሚመስል መልክ እንደፈጠረ ዓለምንም በዚሁ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑ ታምኖበታል። 

ሌሎች ደግሞ የፍጥረት ጊዜ በዘፍጥረት 1፡11 ላይ ከተጠቀሰው ቃል፥ ማለት ፍሬ የሚሰጠው ዛፍ በምድር በቅሎ ከማደጉ አኳያ ሲታይ፥ ከሀያ አራት ሰዓት በላይ ወስዷል ይሳሉ። እግዚአብሔር ያደገ ዛፍ መፍጠር የማይሳነው መሆኑ ቢታወቅም፥ በቀለ የሚለው ቃል የሚያመለክተው፥ የፍጥረቱ ጊዜ ከሀያ አራት ሰዓት በላይ የወሰደ መሆኑን ነው። 

የፍጥረትን ትክክለኛ ሂደት አስመልክቶ የወንጌል አማኞች እንኳ የተለያየ አመለካከት አላቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን እስትንፋሰ-እግዚአብሔርነትና ስሕተት አልባነት የሚያምኑ የቃሉ ፈቺዎች ወይም ተርጓሚዎች፥ ሰውና እንስሳት ወዲያውኑ አሁን ባሉበት ሁኔታ እግዚአብሔር የፈጠራቸው መሆኑን ያረጋግጣሉ። ፍጡራን በተፈጥሮና በአዝጋሚ ሕግ መለወጣቸውን የሚገልጥ ምንም ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። 

ለ. የሰው አፈጣጠር 

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚመሰክሩት፥ ሰው በአሁኑ ሰብአዊ ቅርፁ የፍጥረታት ሁሉ መደምደሚያና ማሳረጊያ ሆኖ በእግዚአብሔር ተፈጥሯል። አፈጣጠሩም በእግዚአብሔር መልክ፥ እንዲሁም ምሳሌ እንደሆነ (ዘፍጥ. 1፡26) እና እግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስ እፍ እንዳለበት (ዘፍጥ. 2፡7) ተገልጧል። እነዚህ መለያዎች ሰውን በምድር ካሉ ፍጥረታት ሁሉ በላይ ያደርጉታል፤ ሰው እእምሮ። ስሜትና ፈቃድ ያለው ፍጡር መሆኑንም ያመለክታሉ። 

በጠቅላሳው አነጋገር፥ የሰው አፈጣጠር ቁሳዊ የምድር አፈር” እና መንፈሳዊ “የሕይወት እስትንፋስ” ነው። ይህ ጥምር መለያ “ውጫዊ ሰው) እና “ውስጣዊ ሰው” (2ኛ ቆሮ. 4፡16) ወይም “ምድራዊ ሸክላ” እና “መዝገብ” (2ኛ ቆሮ. 4፡7) ተብሏል። የሰው ነፍስና መንፈስ ለዘላለም የሚኖሩ መሆናቸው ሲገለጥ፥ ሥጋ ቀድሞ ወደመጣበት አፈር ይመለሳል (መክ. 12፡7)። በመሆኑም ሰው ሥጋን እንጂ ነፍስን መግደል አይቻለውም (ማቴ. 10፡28)። 

መጽሐፍ ቅዱስ ሥጋዊ ስላልሆነው የሰው አካል ሲገልጥ የተለያዩ ቃላትን በማቀያየር ይጠቀማል (ዘፍጥረት 41፡8ን ከመዝሙር 42፡6 ጋር፥ ማቴዎስ 20፡28ን ከ27፡50 ጋር፥ ዮሐንስ 12፡27ን ከ13፡21 ጋር፥ እንዲሁም ዕብራይስጥ 12፡23ን ከራእይ 6፡9 ጋር ያነጻጽሩ)። እግዚአብሔርን ለማመልከቻም እነዚህን ቃላት ይጠቀምባቸዋል (ኢሳ. 42 ፡1፤ ኤር. 9፡9፤ ዕብ. 10፡38)። ለእንስሳት እንዲሁ (መክ. 3፡21፤ ራእይ 16፡3)። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሰውን ነፍስና መንፈስ ለይቶ ያስቀምጣል (1ኛ ተሰ. 5፡23፤ ዕብ. 4፡12)። 

ቁስ ያልሆነው ሰብአዊ አካል ከፍተኛ ተግባር አንዳንዴ የመንፈስ፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ የነፍስ እንደሆነ ተደርጎ ቢገለጥም (ማር. 8፡36-37፤ 12፡30፤ ሉቃስ 1፡46፤ ዕብ. 6፡18-19፤ ያዕ. 1፡21)። መንፈስ ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው፥ ስለ እግዚአብሔር የሚያሰላስል የሰው እንድ ክፍል ሆኖ ነው። ነፍስ ደግሞ ከሰው አእምሮ፥ ከስሜትና ፈቃድ ጋር የተዛመደ ነው። 

የሰውን ቁሳዊ ያልሆነ ተፈጥሮ ለመግለጥ ሌሎች ቃላት ማለት ልብ (ዘዳ. 7፡23፤ መዝ. 37፡4፤ ሮሜ 9፡2፤ 10፡9-10፤ ኤፌ. 3፡17፤ ዕብ. 4፡7) እንደሚለው ያሉት አገልግለዋል። ሌላው ቃል ስለ ሰው አእምሮ የተጠቀሰው ሲሆን፥ የነፍስ ድነት ስላላገኘ ሰው (ሮሜ 1፡28፤ 2ኛ ቆሮ. 4፡4፤ ኤፌ. 4፡17-18፣ ቲቶ 1፡15) ወይም የታደሰውን የክርስቲያን አእምሮ (ማቴ. 22፡37፤ ሮሜ 12፡2፤ 1ኛ ቆሮ. 14፡15፤ ኤፌ. 5፡17) የሚመለከት ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ “ሕሊና” እና “ፈቃድ” የሚሉት ቃላት የሰውን ኢቁሳዊ ክፍል ለማመልከት አገልግለዋል። 

አንዳንድ ጊዜ በተመሳሳይነት፥ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እርስ በርሳቸው በመነጻጸር የሚገለጡ ልዩ ልዩ ቃላት ከመኖራቸው የተነሣ፥ ብዙ ሰዎች የሰውን በቁስነትና ኢቁስነት መከፈል እንደ መሠረታዊ ክፍፍል ወስደውታል። ነገር ግን “ነፍስ” እና “መንፈስ” የሚሉት ቃላት እንኳን አንዳንድ ጊዜ አካሉን ጨምሮ የሰውን ጠቅላላ እሱነት መግለጫነት አገልግለዋል። 

አንዳንድ አረማዊ ሃይማኖቶች ቁሳዊ ያልሆነው የሰው ክፍል ወይም ነፍስ ከአካሉ መፈጠር በፊት ለዘላለም የነበረና፥ ሰው መኖር ሲጀምር ሥጋ የለበሰ መሆኑን ያምናሉ። ይህ እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገረ አይደለም። በአንዳንድ ወንጌሳውያን የሥነ-መለኮት ሰዎች የቀረበው ሌላ አመለካከት፥ እያንዳንዱ ሰው ሕልውናውን በጀመረበት ወቅት ነፍስ ትፈጠርለታለች የሚል ነው። የሰውን ኃጢአተኛነት በሚመለከት ይህ አመለካከት ችግር አለበት። ከሁሉ የተሻለው አመለካከት ምናልባት የመራባት ጽንሰ አሳብ አራማጆች የሚያቀነቅኑት የኃጢአት ውርስ (traducian theory) የተሰኘው ነው። በዚህ አመለካከት መሠረት ነፍስና መንፈስ በተፈጥሮ ትውልዳዊ ሥርዓት ይገኛሉ። በዚህም መሠረት ሰው ኃጢአተኞች ከሆኑ ወሳጆቹ ኃጢአተኛ ነፍስና መንፈስ ይወርሳል። 

ሰብዓዊ አካል ሰው እስኪሞት ድረስ የነፍስና የመንፈስ ማደሪያ ነው። ከሞት በኋላ የሚበሰብስ ቢሆንም፥ በትንሣኤ ጊዜ ይነሣል። ምንም እንኳን ትንሣኤዎቹ ቢለያዩ ይህ ክንውን ለዳኑትም ሆነ ላልዳኑት የማይቀር እውነት ነው። አንዳንድ ጊዜ አካል “ሥጋ” ተብሏል (ቆላ. 2፡1፥ 5)። የክርስቶስን አካል ለመጥሪያነትም አገልግሏል (1ኛ ጢሞ. 3፡16፤ 1ኛ ጴጥ. 3፡18)። በሌላ ጊዜ ደግሞ ኃጢአተኛ ነፍስንና መንፈስን የሚያጠቃልለውን ኃጢአተኛ ተፈጥሮ ይገልጣል። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሥጋን ስቀሉ” (ገላ. 5፡24) በማለት ያመለከተው ነው። በዚህ መሠረት ሥጋ በሁሉም ምንባቦች ከአካል ጋር አንድ ሆኖ ሊወሰድ አይገባም። ምክንያቱም ቃሉ ድነት ያላገኘ ሰውንም ያመለክት ይሆናል። 

የዳኑ ሰዎች አካል “ቤተ መቅደስ” (ዮሐ. 2:21፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡19፥ ፊልጵ. 1፡20)፥ “የሸክላ ዕቃ” (2ኛ ቆሮ. 4፡7)፥ “የተዋረደ ሥጋ”፥ (ፊልጵ. 3፡21)፥ “ሊገደል የሚገባው” (ሮሜ 8፡13፤ ቆላ. 3፡5)፥ እና መጎሰም ያለባቸው ሥጋዎች (1ኛ ቆሮ. 9፡27) ተብሏል። ዳግም የተወለዱ አማኞች አካል ይለወጣል፥ ይቀደሳል፥ ይድናል፥ በኋላ ይጻድቃል። በመጨረሻም ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያኑ በሚመጣበት ጊዜ ለዘላለም ይከብራል (ሮሜ 8፡11፥ 17፥ 18፥ 23፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡13-20፤ ፊልጵ. 3፡20-21)። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት ፍጹም ሰብአዊ አካል ነበረው። ከትንሣኤው በኋላ ደግሞ አማኞች በትንሣኤ ጊዜ የሚኖራቸው ዓይነት ሥጋና አጥንት የሆነ አካል ነበረው። (“አካል” የሚለው ቃል ክርስቶስ የሞተላትንና እካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በምሳሌ ለመግለጫነት አገልግሏል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.