Site icon

ቤተ ክርስቲያን፡- ምእመኖቿ

ሀ. ቤተ ክርስቲያን- የዚህ ዘመን የእግዚአብሔር ዓላማ 

ቤተ ክርስቲያን የዚህ ዘመን የእግዚእብሔር ማዕከላዊ ዓላማ መሆኗ እዲስ ኪዳን ውስጥ ተገልጧል። እግዚአብሔር ለብሉይ ኪዳን ግለሰቦችና አገሮች ከነበሩት ዓላማዎችና ለእስራኤልም ከነበረው ሰፋ ያለ ዓላማ ጋር ሲነጻጸር፥ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ሕዝቦችና ከአይሁዶች የተዋቀረች የአማኞች አንድነት ሆና ተገልጣለች። እነዚህም ከዓለም ተጠርተው በመውጣት በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ሕያው አንድነት የተሳሰሩ ናቸው። 

በአጠቃላይ፥ የቤተ ክርስቲያን ፅንሰ-አሳብ በሁለት ዓበይት ምድቦች ይከፈላል። አዲስ ኪዳን ውስጥ የምንመለከተው የመጀመሪያ ፅንሰ-አሳብ፥ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ውስጥ የሚገኙ እውነተኛ አማኞች ሁሉ ሕያው ጥምረት መሆኗን ነው። ይህም መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ዕለተ ጰንጠቆስጤ አንሥቶ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያኑ ዳግም በመመለሱ የሚደመደም ልዩ እውነት ነው። ጌታ በሚመለስበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ከዓለም መነጠቅ ወደ ሰማይ ትወሰዳለች። 

ሌላው ፅንሰ-አሳብ፥ ስለ አጥቢያ ወይም ስለ ተደራጀች ቤተ ክርስቲያን የተገለጠው ነው። ይህ በአንድ አጥቢያ የሚገኙ አማኞች ወይም ይህን የመሰሉ ጉባኤዎች የአማኞች ስብሰብ ነው (1ኛ ቆሮ. 1፡2፤ ገላ. 1፡2፤ ፊልጵ. 1፡1)። 

ቤተ ክርስቲያን” የሚለው ቃል “ኤክሌዢያ” ከሚለው ግሪክኛ የተተረጎመ ሲሆን፥ ቃሉ ለየትኛውም ዓይነት የሕዝቦች ስብሰባ ወይም ጉባኤ በተደጋጋሚ አገልግሏል። የተሰብሳቢዎቹ ዓላማ ሃያማኖታዊ ወይም ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል። የቃሉ ፍች ደተጠርተው የወጡ” ማለት ነው። በጥንታዊቱ ግሪክ፥ ብዙዎቹ ከተሞች የሚተዳደሩት ነጻ በሆን ዲሞክራሲ ነበር። በመሆኑም፥ እያንዳንዱ ዜጋ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተግባራዊ እርምጃ ሰመውሰድ ይሰበሰባል። ከወትሮው ተግባራቸው ድምፅ ወደሚሰጡበት ስብሰባ ተጠርተው ሲመጡ፥ ቃሉ፥ ተጠርቶ የመውጣት ውጤት ወይም የተሰበሰቡ ሰዎች የሚል ፍች ሊሰጠው በቃ። 

ይህ ቃል የብሉይ ኪዳን የተለያዩ ጉባኤዎችን ለማመልከት የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጓሜ በሆነው ሰፕቱዋጄንት ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። እንደ የሐዋርያት ሥራ 7፡38 እና 19፡32 በመሳሰሉ ምንባቦች ውስጥ የሰዎችን ስብስብ በሚገልጥ መልኩ ተጠቅሶ እናገኛለን። ይሁንና ቃሉ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ክርስቶስ አካል ለማመልከት በሚያገለግልበት ጊዜ ከዓለም ተጠርተው በክርስቶስ ሕያው ኅብረት የፈጠሩ ሰዎችን ለማመልከት ያገለግላል። ምንም እንኳ እስራኤላውያን አንዳንድ ጊዜ ለሃይማኖታዊ ዓላማዎች መሰባሰባቸው ቢታወቅ፥ ይሄ ፅንሰ-አሳብ ብሉይ ኪዳን ውስጥ አይገኝም። ቃሉ የዳኑትን በሚያመለክትበት ጊዜ ደግሞ የሚያመለክተው፥ በአሁኑ ዘመን በምድርም ሆነ ሰሰማይ ድነት ያገኙት ሰዎች ኅብረት ነው። 

ለ. ቤተ ክርስቲያን- የአዲስ ኪዳን መገለጥ 

ዘላሰማዊ ሕይወት በማግኘት የተባበሩ አይሁዳውያንና አሕዛብ ያሉበትን ቤተ ክርስቲያን ፅንሰ-አሳብ ከብሉይ ኪዳን ውስጥ አናገኝም፤ አዲስ ኪዳን ብቻ ነው የዚህን ዋና ጉዳይ መለኮታዊ መገለጥ የሚያስጨብጠን። በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ መጀመሪያ የክርስቶስ መምጣት፥ በመስቀል ላይ መሞት፥ ከሞት መነሣትና ወደ ሰማይ ማረግ የግድ አስፈላጊ ክንውን ነበር። የመንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኀምሳ ዕለት መምጣት ግን፥ እግዚአብሔር በአሕዛብና በእስራኤል መካከል ልዩነት ሳያደርግ ልዩ የአማኞች ኅብረት ለመፍጠር ያለውን ዓላማ እውን አደረገበት። በዚህም መሠረት በእስራኤልና በአሕዛብ መካከል ልዩነት ሳይደረግ ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ ውስጥ ስፍራ አግኝተዋል። 

በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለት ውስጥ እንደተመለከተውና በዚሁ መጽሐፍ ምዕራፍ አሥር ቆርኔሌዎስ ገጠመኝ እንደተረጋገጠው፥ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀው (1ኛ ቆሮ. 12፡13) አንዳቸው የሌላው አባል ሆነዋል። ይህም በመንፈስ ቅዱስ መምጣት የተከናወነ ተግባር ነው። ከዕለተ በዓለ ኀምሳ በመለስ፥ እያንዳንዱ አማኝ ድነትን ሲያገኝ ቀደም ሲል በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ውስጥ እንደተገለጠው የክርስቶስ አካል ክፍል ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን ዘመኗ ተፈጽሞ ወደ ሰማይ በምትነጠቅበት ጊዜ፥ መለኮታዊው ዓላማ በአይሁዶችና ሰአሕዛብ መካከል ወዳለው የተለመደ ልዩነት ይመለሳል። ይህ ከመነጠቅ በኋላ በሚኖረው የመከራ ወቅትና በሺህ ዓመቱ መንግሥት ውስጥ የሚያምኑትን አይሁዶችና አሕዛብ የሚመለከት ነው። 

ሐ. አይሁድ፥ አሕዛብና ቤተ ክርስቲያን 

በአሁኑ ዘመን፥ ሦስት ዓበይት ሰብአዊ ክፍፍሎች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘረዝራል። እነዚህም አይሁዶች፥ አሕዛብና ቤተ ክርስቲያን ናቸው (1ኛ ቆሮ. 10፡32)። እግዚአብሔር ለዚህ ዘመን ያለውን ዓላማ ለመረዳት እነዚህን ልዩነቶች ማጤኑ እጅግ 

እስፈላጊ ነው። 

1. አይሁዶች ወይም እስራኤላውያን ከአብርሃም አብራክ ወጥተው ለይስሐቅና በያዕቆብ የዘር ሐረግ የተዋለዱ ሲሆኑ፥ ከመለኮታዊ ዓላማና የተስፋ ቃል የተነሣ የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ናቸው። የአይሁድ ሕዝብ እስካሁን በተአምራዊ መንገድ ተጠብቆ የቆየ ሲሆን፥ በሚመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት ዘመን በምድር ላይ ኃያልና የተከበረ ሕዝብ እንደሚሆን ትንቢቶች ያስረዳሉ (ኢሳ, 62፡1-12)። 

ያህዌ ለነዚህ ሕዝቦች የገባላቸው ዘላለማዊ የተስፋ ቃላት ሊለወጡ አይችሉም። የተስፋ ቃላቱ ከሚያካትቷቸው ነገሮች መካክል ብሔራዊ ነጻነት (ኤር. 31፡36)፥ መሬት (ዘፍጥ. 13፡15)፥ ዙፋን (2ኛ ሳሙ. 7፡13) ፥ ንጉሥ (ኤር. 33፡20-21) እና መንግሥት (2ኛ ሳሙ. 1፡16) ይገኙባቸዋል። እነዚህ ምድራዊ ባሕርይ ያላቸው የተስፋ ቃላት በእግዚአብሔር ታማኝነት እስካዛሬ በመፈጸም ላይ ናቸው። ተስፋዎቹ ዘላለማዊ በመሆ ናቸው ለዘላለም እንዲሁ ይፈጸማሉ። በነዚህ ሕዝቦች የሚፈጸመውን የመለኮታዊ ዓላማ አሠራር የሚከተሉት አራት ቃላት ይገልጧቸዋል፡- “የተመረጡ”፥ “ተበተኑ”፥ “የተሰበሰቡ” እና “የተባረኩ”። አይሁዶች በእግዚአብሔር መመረጣቸውና አሁን በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል መበታተናቸው ግልጥ ነው። መሰባሰባቸውና መባረካቸው ግን አይቀሬ ነው። የዚህ ሕዝብ ልዩ እገልግሎት ሮሜ 9፡4-5 ውስጥ ተገልጧል (ከዘፍጥረት 12፡3 ጋር ያነጻጽሩት)። 

አሕዛብ እስራኤላውያንን ሳይጨምሩ ከአዳም ዘመን እሰከ ዛሬ የኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ሲሆንተቆጥረው እስከማይለቁ ድረስ እጅግ ብዙ ናቸው። ከተወሰኑ ግለሰቦች በስተቀር፥ ከአዳም እስከ ክርስቶስ ዘመን በነበረው የጊዜ ገደብ እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ምን ዓይነት ልዩ ግንኙነት እንዳደረገ ወይም ምን ዓይነት የቅርብ የተስፋ ቃላት እንዳደረገ የሚያመለክት ዘገባ አናገኝም። ወደፊት በምድር ላይ በሚመሠረተው መንግሥት ውስጥ ግን፥ አሕዛብ ታላቅ ምድራዊ በረከቶችን እንደሚያገኙ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ያመለክታሉ። በአሁኑ ዘመንም አሕዛብ ከእይሁዳውያን ጋር የወንጌሉ ዕድል ተካፋዮች ናቸው። 

3. ቤተ ክርስቲያን ሚያመለክተው፥ የተደራጀችን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እባልነት ሳይሆን፥ በአሁኑ ዘመን ያሚድኑትን ሰዎች አጠቃላይ ኅብረት ነው። እነዚህ ሰዎች የሚከተሉት ነጥቦች ምክንያት የተለዩ ናቸው። 

ሀ) በዚያ ኅብረት ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ሁሉ ዳግም የተወሰዱ በመሆናቸው፥ ወዷ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባሉ (ዮሐ. 3፡5)። ክርስቶሰን ይመስሉ ዘንድም ከቀድሞው የተወሰኑ ናቸው (ሮሜ 8፡29)። 

(ለ) ከእንግዲህ አዳምን ተከትለው የእሮጌውን ተፈጥሮ ውድቀት የሚካፈሉ አይሆኑም (2ኛ ቆሮ. 5፡17)። ይልቁንም ክርስቶስን ተከትለው እርሱ በትንሣኤው ሕይወትና ክብር የሆነውን ሁሉ የሚሆኑ እና የአዲሱ ተፈጥሮ ተካፋዮች ናቸው (ኤፌ. 1፡3፤ ቆላ. 2፡10)። 

(ሐ) በእግዚአብሔር እይታ ዜግነታቸው ተለውጧል፤ ምክንያቱም ሰዎች አይሁዳዊ ወይም እሕዛብ ተብለው ወደማይለዩበትና ክርስቶስ ሁሉ በሁሉም ወደሆነበት አዲሰ ሕይወት መጥተዋልና(ቆላ. 3፡11)። 

(መ) አሁን የሰማይ ዜጎች ስለሆኑ (ፊልጵ. 3፡20፤ ቆላ. 3፡3)፥ የተስፋ ቃላቶቻቸው፥ ሀብቶቻቸውና ሰፍራቸው ሰማያዊ ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡17-18)። እነዚህ ሰማያዊ ዚጎች ከምድራውያኑ በብዙ አኳኋን ይለያሉ። 

መ. ከአይሁድና ከአሕዛብ የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን 

የአይሁዶችና የአሕዛብ ምድራዊ ስፍራ ቀደም ብሎ ተገልጧል። በተጨማሪም እግዚአብሔር በአሁኑ ዘመን ለጸጋው ዓላማዎች አሕዛብንም ሆነ አይሁዶችን በእንድ ዓይነት መሠረት ላይ ያስቀመጣቸው መሆኑን መገንዘቡ ተገቢ ነው (ሮሜ 3:9)። ሁሉም “ከኃጢአት በታች” መሆናቸውና መዳን የሚችሉት ሰጸጋ ብቻ መሆኑ ተገልጿል። 

መለኮታዊው ፕሮግራም በክርስቶስ ሞት ተለውጧል። ይሄውም ከእንድ የተመረጠ ሕዝብ ይልቅ፥ አይሁድ ወይም አሕዛብ ሳይል ግለሰቦችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መቀበሉ ነው። ይህ መለኮታዊ አሠራር አይሁዶች ሊገነዘቡ ያልቻሉት ነገር ነበር። ቃል ኪዳኖቹ ለጊዜው ወደ ጎን የተደረጉ እንጂ ያልተሻሩ መሆናችውን አልተረዱም። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እይሁዶች ይህን አለመረዳታቸውን የሚያሳይ አሳብ እናነባለን። 

አይሁዶች ካላቸው የተሳሳተ መረዳት የተነሣ በዚህ ዘመን ያለውን የእግዚአብሔር ፕሮግራም እይቀበሉትም። ቤተ ክርስቲያን እስክትነጠቅ ድረስ አይሁዶች በዚህ አስተሳሰባቸው እንደሚቆዩም ትንቢት ተነግሯል (ሮሜ 11፡25)። ከዚያ በኋላ ነጻ አውጪው ከፅዮን ስመምጣት፥ አለማመንን ከያዕቆብ ቤት ያስወግዳል። እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን እንደሚያስወግድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን የገባበት ጉዳይ መሆኑን ይህ ያመለክታል (ሮሜ 11፡26-27)። ያም ሆነ ይህ፥ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ በወንጌል ስብከት በመዳን ላይ ናቸው። ቤተ ክርስቲያንም በዚህ በመሟላት ላይ ነች። ሐዋርያው ወንጌሉ መጀመሪያ ለአይሁዶች እንዲሰበክ ያስታወቀ ሲሆን (ሮሜ 1፡16)፥ የርሱም አገልግሎት ከዚሁ ፕሮግራም አኳያ የተዋቀረ ነው (ሐዋ. 17፡1-3)። 

ቀደም ሲል እንደተገለጠው፥ ለሐዋርያው ጳውሎስ ሁሰት መገለጦች ተሰጥተውት ነበር። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር የጸጋ ወንጌል ነው። ይህን መገለጥ የተቀበለው ምናልባት በአገልግሎቱ መጀመሪያ አካባቢ ዓረቢያ ውስጥ እያለ ሳይሆን እይቀርም (ገላ. 1፡11 -12)። ሌላው የክርስቶስ አካል ስለሆነችው ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መገለጥ ሲሆን፥ የተቀበለው በወኅኒ ቤት እያለ ሳይሆን አይቀርም (ኤፌ. 3፡3-6)። የሁለተኛው ምሥጢር ዋንኛ ጕዳይ እግዚአብሔር ከሁላት ምንጮች፥ ማለትም ከአይሁድና ከአሕዛብ አንድ ፡አካል በመሥራት ላይ መሆኑን የሚያመለክት ነው (ኤፌ. 2፡15)። ይህ ተሰውሮ የኖረ መለኮታዊ ምሥጢር ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤል ወይም ላአሕዛብ ዓላማዎች እንዳሉት የብሉይ ኪዳን ትንቢት በግልጥ ያመለክታል። ይህም ከአይሁዶችና አሕዛብ እዲስ ሰማያዊ ፍጥረትን የመሥራት ምሥጢር ነው። 

ሠ. የቤተ ክርቲያን አባልነት 

“አንድ ሰው ከዳነ በኋላ የቤተ ክርስቲያን አባል ላይሆን ይችላልን?” የሚለው ጥያቄ መልስ፥ “ቤተ ክርስቲያን” ለተባለው ቃል በሚሰጠው ፍች ላይ ይደገፋል። አንድ ሰው ድነት ካገኘ በኋላ በአጥቢያ ደረጃ የተዋቀረች ቤተ ክርስቲያን አባል ላይሆን እንደሚችል እውነት ነው። ሰዎች ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አባል ከመሆናቸው በፊት በክርስቶስ አምነው መዳን አለባቸው። ከዳኑ ደግሞ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ኅብረት ማድረግን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መሻታቸው ተፈጥሮአዊ ነው። 

በሌላ በኩል፥ ድነትን አግኝቶ የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን አባል አለመሆን የማይቻል ነገር ነው። ምክንያቱም በድነት ውስጥ መለኮታዊው የሥራ ድርሻ የዳነውን ሰው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የክርስቶስ አካል ማድረግ በመሆኑ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡13)። ከመንፈስ ቅዱስ አሠራር ጋር በተገናኘ መልኩ እንዳገለገለው፥ ያረማጥመቅ የሚለው ቃል ከውጫዊው የውኃ ጥምቀት ሥርዓት አልፎ፥ መንፈስ ቅዱስ ለአማኝ የሚሰጠውን አገልግሎት የሚወክል ሰፋ ያለ ትርጉም አለው። ይህም የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ሰድነት ውስጥ ከሚከናወኑ ሌሎች መለኮታዊ ተግባራት ሁሉ የላቀ ውጤት ያስገኛል። ሰይጣን የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀትና፥ ጥምቀቱ የሚወክለውን መለኮታዊ አገልግሎት ግልጥ ትርጉም ማዛባቱ አስገራሚ አይሆንም። ምክንያቱም የመለኮታዊውን ጸጋ ባለጠግነት ለመረዳት ወይም ወደ ሰማያዊ ደስታ ለመግባት የምንችለው፥ በዚህ አገልግሎት ላይ በመመሥረት ብቻ በመሆኑና ከነዚህ ጸጋዎች ወደሚገኘው የተቀደሰ ሕይወት የሚገፋፋን በመሆኑ ነው። 

በምድር ላይ ቤተ ክርስቲያን ወደ ቅድስት አገር የምትጓዝ የምስክርነት ቡድን ሆና ነው የምትታየው። ክርስቶስ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ ሁሉ፥ ክርስቲያኖችም ከዚህ ዓለም አይደሉም (ዮሐ. 17፡16)። አብ ወልድን ወደ ዓለም እንደ ላከው፥ ወልድም እነዚህን ምስክሮች ወደ ዓለም ልኳቸዋል። በጸጋው ባለጠግነት የሚኖራቸው እውነተኛ ማንነት ገና አልታወቀም (ቆላ. 3፡4፤ 1ኛ ዮሐ. 3፡2)። ቤተ ክርስቲያን፥ ማለት ቅዱሳን በሰማያዊ ስፍራ እንደ በጉ ሙሽራ፥ ከንጉሡ ጋር አብራ የምትገዛና ከዘላለማዊው የእግዚአብሔር ልጅ ክብር ዘላለማዊ ተካፋይ ሆና ትገለጣለች።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Exit mobile version