ቤተ ክርስቲያን፡- አደረጃጀትና ሥርዓቷ

ሀ. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር 

ቤተ ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ አካልነቷ፥ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት የአካሉ ራስ ከሆነው ክርስቶስ ጋር የተባበረውን ማንኛውንም ክርስቲያን ታካትታለች። አካል እንደ መሆኗ፥ የዕውን የአካል ክፍል በሚመስል አኳኋን ተዋቅራለች። እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ከሌላው ጋር ይገናኝና፥ ጠቅላላውን አካል ከሚመራው ራስ ጋር ይዛመዳል። የክርስቶስ አካል የሆነችው እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት መንፈሳዊና መለኮታዊ እንደ መሆኑ፥ ድርጅታዊነትን እንደ ዋና ነገር አድርገን መውሰድ እንችልም። 

ይህም ሆኖ፥ በቀደመው ዘመንም ሆነ ዛሬ፥ ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ አደረጃጀት አስፈላጊ ይመስላል። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሦስት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዓይነቶች ይገኛሉ። እነዚህ የአስተዳደር ዓይነቶች ከሐዋርያት ዘመን ጋር የተያያዙ ናቸው። 

1. በኤጵስቆጶሳዊ” የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለጵጵስና ወይም ሌላ ዓይነት የማዕረግ ስያሜ ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪ ይሰጣል (1ኛጢሞ. 3፡1)። ይህ ዓይነቱ የቤተ ክርስቲያን ተሰያሚ በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቱን ይመራል። እንዲህ ያለው አደረጃጀት ወደ ከፍተኛ ድርጅታዊነት በማደጉ፥ ጳጳሳት በተወሰኑ እካባቢዎች የአብያተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴዎች በበላይነት ለመቆጣጠር ይሾማሉ። እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፥ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንና በሜተዲስት ቤተ ክርስቲያን የተላመደ ነው። 

2. ቀተወካዮች” የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በአግባቡ የሚወከሉ ግለሰቦችን ሥልጣን ይቀበላል። እነዚህ ተወካዮች በአብዛኛው በመልክዓ-ምድራዊ ክልል የሚወሰኑ ሲሆን፥ በፕሬስቢቲሪያንና ሪፎርምድ አብያተ ክርስቲያን ውስጥ የተለመዱ ናቸው። ብዙውን ጊዜ አንድ አካባቢ ያለ የአብያተ ክርስቲያን የተወካዮች ቡድን ከርሱ በበለጠ አካል ወይም ሲኖዶስ ሥር የሚንቀሳቀስ ይሆናል። ሲኖዶሱም በበኩሉ ከርሱ ስላቀ አጠቃላይ ጉባኤ ይገዛል። ምንም እንኳ ደንቦችና የሥልጣን ደረጃዎች ቢለያዩ፥ ዋናው አሳብ በተገቢው መንገድ የተመረጡ ተወካዮች የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን የሚይዙ መሆናቸው ነው። 

3. በጉባኤያዊ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዓይነት ሥልጣኑን የሚይዘው የእግቢያ ጉባኤ ነው። በዚህ የአስተዳደር ዓይነት ለዋነኞቹ ጉዳዮች ውሳኔ የሚሰጠው፥ የሌሎቹን አብያተ ክርስቲያን ወይም ባለሥልጣናት ሥልጣን ከግንዛቤ ሳያስገባ ጉባኤው ብቻ ነው። ይህን ዓይነቱ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንደ ባፕቲስት አብያተ ክርስቲያን በመሳሰሉት ይዘወተራል። ምንም እንኳ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ለበላይ አካላት፥ ኮሚቴዎች ወይም ኃላፊዎች በተወሰነ ደረጃ ሊገዙ የተገባ ቢሆንም፥ የዚህ ዓይነቱ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዋነኛ አሳብ፥ ጉባኤዎች የራሳቸውን ጉዳዮች የሚወስኑ አገልጋዮች የሚሾሙና የራሳቸውን መዋዕለ ንዋይ አጠቃቀም የሚመሩ መሆኑን ነው። 

በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ቅርፆች በተወሰነ ደረጃ አገልግለዋል። ሐዋርያት ቀዳሚ ሥልጣን የነበራቸው መሆኑን ብዙዎቹ የቀድሞ አብያተ ክርስቲያን ተገንዝበዋል። ይሁንና፥ ይህ ከመጀመሪያው ክርስቲያን ትውልድ ጋር ያለፈ ይመስላል። ሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ውስጥ እንደተገለጠው፥ ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የሚገኙ ሽማግሌዎች፥ አብያተ ክርስቲያን ላነሱዋቸው የአስተምህሮ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ ተወካዮች ነበሩ። ይህን ካለንበት ዘመን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አሠራር አንጻር ስናየው ግን፥ እነዚህ ሰዎች ተመራጮች ወይም የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች አልነበሩም። አብያተ ክርስቲያን እየበሰሉ መጥተው የሐዋ ርያትን ተቆጣጣሪነት ከማይፈልጉበት ደረጃ ላይ በደረሱ ጊዜ፥ የአብያተ ክርስቲያን አስተዳደር ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የተላለፈ ይመስላል። ራእይ 2-3 ውስጥ የተጠቀሱትን ሰባት የእስያ አብያተ ክርስቲያን በተመለከተ እውን የነበረ ይመስላል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያን ከራሱ ከክርስቶስ በቀር ለማንኛውም ሰብአዊ ሥልጣን አይገዙም ነበር። ከዚህ አንጻር ሲታይ፥ በአሁኑ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው የረቀቀና የተወሳሰበ አስተዳደር በመጽሐፍ ቅዱስ የሚደገፍ መሆኑ አጠራጣሪ ስለሆነ፥ ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ግንዛቤ መመለሱ ተገቢ ነው። 

ለ. የቤተ ክርስቲያን መሪዎች 

በመጀመሪያው ዓመተ ምህረት የነበሩ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ “ኤጲስ ቆጶስ” ወይም “ሽማግሌዎች ተሰይመው እጥቢያይቱን የሚመሩት ሰዎችን ያካትታል። ምንም እንኳ ስሞቻቸው በመጠኑ ቢለያይ፥“ኤጵስ ቆጶሳትን እና “ሽማግሌዎች” አንድ ዓይነት ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። 

ምናልባትም የአዲስ ኪዳን የሽማግሌዎች ፅንሰ-አሳብ የተወሰደው፥ በእስራኤል ላይ ሥልጣን ከነበራቸው ሽማግሌዎች አሠራር ሆኖ (ማቴ. 16፡21፤ 26፡47÷ 57፤ ሐዋ. 4:5፥ 23)፥ በአስተሳሰቡ የበሰለና ሥልጣን ሊይዝ የሚገባውን ሰው ያመለክት ነበር። ስለሆነም፥ ሽማግሌ ለመሪነት የሚያበቁትን መመዘኛዎች የሚያሟላ ሰው እንደነበረ እንረዳለን። “ኤጲስ ቆጶስ” የሚለው ቃል የሰውን ሥልጣን ወይም አገልግሎት የሚገልጥ ነው። ኤጲስ ቆጶስ ሁልጊዜ ሽማግሌ ሲሆን፥ ሽማግሌ ግን በተወሰኑ ሁኔታዎች ምክንያት ኤጲስ ቆጶስ ሊሆን አይችል ይሆናል። ማለት ሥልጣ ሳይኖረው ብቃቱ ሲኖረው ይችላል። በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ሁለቱም ቃላት በተመሳሳይነት ያገለገሉ ይመስላል (ቲቶ 1፡5፥ 7)። 

ኤጲስ ቆጶስና ሽማግሌዎች ቤተ ክርስቲያንን የማስተዳደር (1ኛ ጢሞ. 3፡4-5፤ 5፡17)፥ ቤተ ክርስቲያንን ከግብረ ገባዊ ወይም ሥነ-መለኮታዊ ስሕተት የመጠበቅ (ቲቶ 1፡9) እና እረኛ መንጋውን እንደሚንከባካብ ቤተ ክርስቲያንን የመንከባከብ ወይም የመቆጣጠር የመሳሰሉ ኃላፊነቶችን መወጣት ነበረባቸው (ዮሐ. 21፡16፤ ሐዋ. 20፡28፤ ዕብ. 13፡17፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡2)። የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሐዋርያት የተሾሙ ቢመስልም፥ አብያተ ክርስቲያኑ እየበሰሉ ሲመጡ የመሾሙን ተግባር ራሳቸው ሳያካሂዱት አልቀሩም። ሹመቱ የሰዎቹን የመሪነትና መንፈሳዊ ብቃት ያገናዘበ ነበር (ሐዋ. 14፡23፤ 20፡28፤ ቲቶ 1፡5፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡2)። 

ከሽማግሌዎችና ኤጲስ ቆጶሳት ባሻገር ሌሎች አገልጋዮች ዲያቆናት ተብለው ይሾሙ ነበር። ዲያቆናት በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳ መንፈሳዊ ስጦታዎች ሊኖራቸው ቢችል፥ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጡት ግን ችግረተኞችን በመርዳቱና ቁሳዊ አገልግሎት በማበርከቱ ተግባር ላይ ነበር (ሐዋ. 6፡1-6፤ 1ኛ ጢሞ. 3፡8-13)። እንደ ሽማግሌዎቹ ሁሉ ዲያቆናት በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት (ሐዋ. 6፡6፤ 13፡3፤ 1ኛ ጢሞ. 1፡6) ወይም በሽማግሌዎች ሳያሾሙ አይቀሩም (1ኛ ጢሞ. 4፡14)። በኤጲስ ቆጶስና ሽማግሌዎች አገልግሎት እንደሚደረገው፥ በድቁና ሹመትና ዲያቆኑ በሚያበ ረክተው አገልግሎት መካካል ልዩነት ሊደረግ ይገባል። ፊልጶስ በመንፈሳዊ ስጦታው ወንጌላዊ ቢሆንም፥ የድቁና ሥልጣን ነበረው (ሐዋ. 6፡5፤ 21፡8)። 

ዛሬ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያን መጋቢውን እንደ አንድ ብቸኛ ሽማግሌ፥ እድርገው ይመለከቱታል። በመንፈሳዊ ጉዳዮች የሚረዱትን ሌሎች ሰዎች ደግሞ እንደ ዲያቆናት ይመለከቷቸዋል። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልምምድ አይመስልም። 

ሐ. የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች 

አብዛኛዎቹ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያን ሁለት ሥርዓቶችን፥ ማለት ጥምቀትንና የጌታ እራትን ብቻ ነው እንደ ሥርዓት የሚቀበሉት። ከነዚህ አብያተ ክርስቲያን አንዳንዶቹ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበትን ምሳሌ (ዮሐ. 13)፥ እንደ ሥርዓት አድርገው በመውሰድ በተግባር ይፈጽሙታል። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በነዚህ ላይ ሌሎች ጥቂት ሥርዓቶችን ይጨምራሉ። ከሞላ ጎደል በሁሉም የተለመዱ ሥርዓቶች ጥምቀትና ቅዱስ ቁርባን ብቻ ናቸው። 

1. በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፥ የውኃ ጥምቀት ሥርዓት ከፍተኛ ውዝግብ ያስከተለ ሲሆን፥ ለቤተ ክርስቲያን ክፍፍልም እስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የሚነሡ ክርክሮች በአጠቃላይ ሁለት ዓበይት ችግሮችን ያካትታሉ፤ () የውኃ ጥምቀት ሥርዓት ብቻ ነው? ወይስ ለተጠማቂው የሚያበረክተው መለኮታዊ ጥቅም አለ? (2) አፈጻጻምን በተመለከተ፥ የውኃ ጥምቀት የሚከናወነው በመጥለቅ ብቻ፥ ወይስ በተጠማቂው ላይ ውኃ በማፍሰስና በመረጨትም ሊሆን ይችላል? 

የውኃ ጥምቀት፥ ሥርዓት ብቻ መሆኑን የሚያምኑ ሰዎች ድርጊቱ መንፈሳዊ እውነትን እንደሚያካትት፥ ነገር ግን ለተጠማቂው የሚያስተላልፈው ምንም ዓይነት ጸጋ ወይም ሕይወት እንደሌለ ያስረዳሉ። የውኃ ጥምቀት ሥርዓት ብቻ መሆኑን የሚያመለክተው ገለጣ የተሻለ አተረጓጎም ነው። የውኃ ጥምቀት አንዳች ልዩ ጸጋ እንደሚያስገኝ የሚያምኑ ሰዎች ድርጊቱ ለተጠማቂው የሚያስገኘውን የበረከት መጠን በተመለከተ በእጅጉ ይለያያሉ። አንዳንዶች ጥምቀትን ከዳግም ልደት ጋር በማነጻጸር፥ በአንድ ሰው ዳግም ልደት ውስጥ ድርሻ እንዳለው ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲሁ ጸጋን እንደሚያስገኝ ወይም ወደ እምነትና ለወንጌሉ ወደ መታዘዝ እንደሚመራ ያምናሉ። ጥምቀት ሥርዓት ብቻ የመሆኑን አሳብ የሚቃወሙ ወገኖች የውኃ ጥምቀት፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ከአማኙ ዳግም ልደት ጋር በማይነጣጠል መልኩ የተጣመረ መሆኑን ይገልጣሉ። 

ባፕቶ” የሚለው የግሪኩ ቃል “አንድን ነገር ፈሳሽ ውስጥ መንከር” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሦስት ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን በአማርኛ “ነከረ” (ሉቃስ 16:24)። “አወቀሰ” (ዮሐ. 13:26)፥ “ተረጨ” (ራዕይ 19፡13) በሚል ተተርጉሟል። 

“ባፕቲዞ የሚለው የግሪኩ ቃል ባፕቶ” ከሚለው የመጣ ሲሆን በአዲስ ኪዳን የተለያየ ትርጉም አለው። “ማጥመቅ” የሚለው የግሪክ ቃል ባፕቲዞ” ሲሆን፤ ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን የተለያየ ትርጉም ይዞ እናገኘዋለን።* [* በግሪኩ ጥምቀት መጠመቅ የሚል ቀጥተኛ አባባል (ማቴ. 20፡22-23፤ ሉቃስ 12፡50፤ 1ኛ ቆሮ. 10፡2) ተጠቅሷል። ውኃ የሚል ቃል በነዚህ ክፍሎች ስለሌለ አንዳንዶች ለጥምቀት ውኃ አያስፈልግም የሚል ትምህርት ያስተምራሉ። ይህ የአባባል ጕዳይ መሆኑን ልንገነዘብ ይጎዳል። አሳሳሉ የሚሰጠው ትርጉም በአስቸጋሪ ልምምድ ወይም መከራ ውስጥ” መግባትን ነው። ስለዚህ ውኃንም ሆነ ምንም ዓይነት የሃይማኖት ሥርዓተ ትምህርትን የሚያመለክት አይደለም።] (1) የመንፃትን ሥርዓት አስመልክቶ አጥባቂ አይሁዳውያን የሚያደርጉትን የመታጠብ ሥርዓትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል (ማር 7፡4፤ ሉቃስ 11፡38)። (2) ቃሉ የአንድ ሰውን ወደ እንድ የሃይማኖት ቡድን መግባቱን በጉባዔ ማስታወቅን በማመልከት ረገድ ጥቅም ላይ ውሏል።* [*የጥምቀት ሥርዓት በተለያየ መልኩ በብዙ የሃይማኖት ክፍሎች ይከናወናል። ለምሳሌ ወደ አይሁዳዊነት የተለወጡ አሕዛብ በመጀመሪያ መገረዛቸው፥ ከዚያም ሁለት ካህናት ከሕግ መጻሕፍት እያነበቡላቸው መጠመቂያ ገንዳ መታጠባቸው የተለመደ ነበር።] ለምሳሌ መጥምቁ ዮሐንስ የንስሀን ጥምቀት” ሰብኳል። በዚህ ስብከቱም ብዙዎች ንስሀ በመግባት የንስሀቸውን ፍሬ ያሳዩ ዘንድ በውኃ ተጠመቁ(ማር. 1፡4)። 

ጴጥሮስም በጰንጠቆስጤ ቀን በሰበከው ስብከት ያመኑትን ይጠመቁ ዘንድ አሳስቧቸዋል (ሐዋ. 2፡38)። በጥምቀታቸው የኢየሱስ ክርስቶስን መሢሕነት በመመስክር ከክርስቲያኖች ጋር አንድነታቸውን የሚመሰከሩበት ሥርዓት ነበር። 

ክርስቶስ የሞት ሥቃዩን እንደ ጥምቀት የጠቀሰ ሲሆን፥ በቀይ ባሕር ውስጥ ውኃ ሳይነካቸው (ማቴ. 20፡22-23) ያለፉ እስራኤላውያንም በደመናና በባሕር እንደተጠመቁ ተገልጧል (1ኛ ቆሮ. 10፡2)። ስለሆነም፥ ውኃ ውስጥ በአካል መግባቱ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥምቀት አስፈላጊ አይደለም የሚል ክርክር አለ። 

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደታየው፥ ለሚጠመቀው ሰው ላይ ውኃ የማፍሰስ ተግባር ይከናወን ነበር። ድርጊቱ ያገለግል የነበረው፥ በጅነት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ በተምሳሌትነት ለማመልከት ሲሆን፥ መጠነኛ ውኃ “በመርጨት” ብቻም ጥምቀቱ ይከናወን ነበር። በጥምቀት አስተምህሮ ዙሪያ የተነሡ ውዝግቦች መቋጫ አልነበራቸውም። በአንዳንድ አጋጣሚዎች፥ ለምሳሌ የክርስቶስን ጥምቀት ዕንመለከት፥ ሥርዓቱ ተግባራዊ የሆነው በመንከር የነበረ ይመስላል። የፈልጵስዩስን የወኅኒ ቤት ጠባቂ ዓይነቶቹን ሌሎች አጋጣሚዎች ስንመለከት ግን (ሐዋ. 16፡33)፥ ጠባቂውና ቤተሰቦቹ በዚያ ጽልመታም ጠዋት ውኃ ውስጥ ተነክረዋል ማለቱ እዳጋች ስለሚሆን፥ ጥምቀቱ ሊካሄድ የሚችለው ቤት ውስጥ በተጠማቂዎቹ ላይ ውኃ በማፍሰስ እንደሆነ ይገመታል። 

በመንከር ማጥመቁ ሥርዓታዊ ተደርጎ ስለሚወሰድ፥ የብዙዎቹ ወንጌል አማኝ አብያተ ክርስቲያን ዝንባሌ፥ መርጨት ተገቢ የጥምቀት አፈጻጸም በመሆኑ ጉዳይ ላይ ከመከራከር ይልቅ የመንከሩን ሥርዓት መከተልን፥ ይመርጣሉ። ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ግለሰቡ ዳግም ተወልዶ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ክርስቶስ አካል የመጣበቁ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ለውኃ ጥምቀት አፈጻጸም ክርክር መፍጠር ተገቢ አይደለም። 

በዚህ ትምህርት ዙሪያ የሚነሣው ሌላ ውዝግብ ሕፃናትን የማጥመቁ ጉዳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሕፃናት ጥምቀት የሚገኘው መረጃ አነስተኛ ነው። ሕፃናትን የሚያጠምቁ ወጎኖች እንደ እስራኤላውያኑ የግርዘት ሥርዓት ልጆችን ለእግዚአብሔር የሚለዩበት የዚህ ዘመን አሠራር እንደሆነ ያስባሉ። ሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 16 ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ ምንም እንኳ የቤተሰቡ አባላት ሲጠመቁ ሕፃናትም ቢኖሩበት፥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሌላ ስፍራ ስለ ሕፃናት ጥምቀት በግልጥ የተጠቀሰ ነገር የለም። ከዚህም የተነሣ፥ አብዛኛዎቹ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን፥ የውኃ ጥምቀትን በክርስቶስ ላይ ለተጣለ እውነተኛ እምነት ውሳኔ ለመስጠት ከሚያስችል ዕድሜ ላይ ለደረሱት ብቻ በማቆየት፥ ልጆችን ለእግዚአብሔር አሳልፎ የመስጠትን ሥርዓት መከተሉን ይመርጣሉ። 

ልጆችን ማጥመቅ ወላጆች የኋላ ኋላ ልጃቸው እንደሚድን ያላቸውን እምነትና ተስፋ የሚገልጡበት ሥርዓት ከመሆን አያልፍም። የአዋቂዎች ጥምቀት በማንኛውም መልኩ በክርስቶስ ላይ የሚጣለውን እውነተኛ እምነት ተከትሎ ሊፈጸም ይገባዋል። ምንም እንኳን የጥምቀት አፈጻጸም ከሕፃናት ጥምቀት ጋር የግድ ባይተሳሰር፥ በአጠቃላይ አነጋገር ልጆች የሚጠመቁት ከመንከር ይልቅ በመርጨት ነው። ጥምቀት በመንከር ብቻ መፈጸም እንዳለበት የሚያምኑ ወገኖች በአጠቃላይ፥ ከልጆች ይልቅ አዋቂዎች ወይም አማኞች ብቻ መጠመቅ እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። 

የጥምቀት አፈጻጸም ሥርዓት እንዴትም ይሁን እንዴት፥ ዋነኛ ትርጉሙ፥ አማኝ ያለ ክርስቶስ ከነበረበት ሕይወት ተለይቶ አሁን የክርስቶስ ሞትና ሕይወት በረከቶች ተጠቃሚ መሆኑ ነው። የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀትን ሥርዓት ባለማቋረጥ ታከናውን ነበር፤ ዛሬም ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የውኃ ጥምቀትን ይፈጽማሉ። 

2. የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት የተጀመረው በክርስቶስ ምት ዜማ ምሽት ሲሆን፥ እማኝ በርሱ ምት አማካይነት የሚካፈላቸው በረከቶች ተምሳሌት ሆኖ ነው የቀረበው። ሥርዓቱ አይሁዶች ከግብፅ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ የሚያከብሩትን የፋሲካ በዓል ተክቷል። 

1ኛ ቆሮንቶስ 11፡23-29 ውስጥ እንደተተነተነው፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራውን እንዲቆርሱ ሲያስተምራቸው፥ እንጀራው ለነርሱ የሚሠዋ ሥጋውን እንደሚወክል ነግሯቸዋል። ይህንንም ሥርዓት እርሱ ከተለያቸው በኋላ ለመታሰቢያ ሊያደርጉት ይገባ ነበር። የወይን ጠጁን ደግሞ የአዲስ ኪዳን ደሙ እንደሆነ ክርስቶስ ገልጧል። ከጽዋው ሲጠጡ የክርስቶስን ሞት ያስታውሱ ነበር። ስለሆነም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ይህንኑ ሥርዓት ማክበር ነበረባቸው። 

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በቅዱስ ቁርባን የተለያዩ አመለካከቶች ላይ ማክተሚያ የሌላቸው ውዝግቦች ሲከሰቱ ኖረዋል። በዚህ አሳብ ዙሪያ በአጠቃላይ ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ነበሩ የተነሡት። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፥ እንጀራውና 8ይኑ ወደ ክርስቶስ ሥጋነትና ደምነት እንደሚለወጡ ታስተምራለች። ይህ ትምህርቷ “ትራንሰብስታንሺዬሽን/transubstantiation” በመባል ይታወቃል። በአስተምህሮው መሠረት እንግዲህ ምንም እንኳ የስሜት ሕዋሳቶቹ ተራ እንጀራና ወይን እንደሚወስድ ቢነግሩትም፥ ቅዱስ ቁርባኑን የሚወስደው ሰው በቀጥታ የክርስቶስን ሥጋና ደም እንደሚቋደስ ይታመናል። ሁለተኛው የሉተራን ቤተ ክርስቲያን እመለካከት ነው። ይህ ትምህርቷ ካንሰብስታንዬሽን/consubstantiation” በመባል ይታወቃል። በዚህ አመለካከት መሠረት እንጀራው በእንጀራነቱ፥ ወይኑም ሰወይንነቱ፥ የሚቆይ ሲሆንም፡የክርስቶስ ሕላዊ እንጀራውም ሆነ ወይኑ ውስጥ ስለሚገኝ፥ ቅዱስ ቁርባንን የሚወስድ ሰው የክርስቶስ አካል ተካፋይ ይሆናል። 

ሦስተኛው አመለካከት ዝዊንግሊ የተባለው የሥነ-መለኮት ምሁር ያቀረበው ሲሆን፥ እንጀራውና ወይኑ መለኮታዊ ለውጥ ሳይካሄድባቸው ድርጊቱ ለመታሰቢያነት ነው የሚያገለግለው ይላል። ጆን ካልቪን የተባለ ሌላ ሰው ደግሞ፥ ይህን አመለካከት በመጠኑ ለወጥ በማድረግ፥ በቅዱስ ቁርባኑ ሥርዓት ጊዜ ክርስቶስ በመንፈስ በእንጀራውና በወይኑ ውስጥ ይገኛል በማለት አስተምሯል። 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቅዱዕ ቁርባን የሚያስተምረው ዝዊንግሊ ያለውን የመታሰቢያነት አሳብ በሚደግፍ መልክ ይመስላል። እንጀራውና ወይኑ የክርስቶስን መገኘት የሚያመለክቱ ወይም የሚወክሉ ሳይሆን፥ የርሱን አለመኖር የሚያሳዩ ይመስላል። ለዚህ ነው የጌታ እራት እርሱ “እስኪመጣ ድረስ” መካሄድ የሚኖርበት። 

ተገቢው የቅዱስ ቁርባን አከባበር 1ኛ ቆሮንቶስ 11፡27-29 ውስጥ በጥንቃቄ የቀረበውን የሐዋርያው ጳውሎስን ትምህርት ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። ቅዱስ ቁርባን በሚወሰድበት ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያከብር ፍርሃትና መንቀጥቀጥ ደግሞም ራስን መመርመር አስፈላጊ ነው። የጌታን እራት ይወስድ ዘንድ የማይገባው ወይም በግድየለሽነት የጌታን እራት የሚወስድ ሰው በራሱ ላይ ፍርድ ያመጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ፥ “ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ” (1ኛ ቆሮ. 11፡28) ብሏል። 

ቅዱስ ቁርባን፥ በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የክርስቶስን ሞት የሚያስቡበት የተቀደሰ ጊዜ እና ለእያንዳንዱ አማኝ ልዩ የሆነ ትርጉም የሚሰጥ ተደርጎ ይወሰዳል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳስተማረው፥ ቅዱስ ቁርባን ልባችንን የምንፈትንበት፥ ኃጢአታችንን የምንናዘዝበትና የምንታደስበት ጊዜ ሊሆን ይገባል። እያንዳንዱ ክርስቲያን በክርስቶስ ሞት አማካይነት ያገኛቸውን ድንቅ በረከቶች የሚያስብበትም ጊዜ ነው። 

ቅዱስ ቁርባን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ታሪካዊውን የክርስቶስ የመጀመሪያ ምጽአትና የመስቀል ላይ ሞትን እንደሚያመለክት ሁሉ፥ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት የሚያበቃበትን የክርስቶስ ዳግም ምጽአትም ይጠቁማል። ቅዱስ ቁርባን የሚወሰድበትን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጥ ባይቀመጥም፥ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በተደጋጋሚ ሲያከናውኑት የቆዩ ይመስላል። ይህም በሳምንቱ የመጀመሪያ ዕለት የክርስቶስን ትንሣኤ ለማክበር ሲሰባሰቡ የቅዱስ ቁርባኑን ሥርዓትም ያካሂዱ የነበረ ይመስላል። ያም ሆነ ይህ፥ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት መደበኛ ሆኖ ሊቀጥልና፥ ዳግም እስኪመጣ ድረስ ለመታሰቢያው እንድናደርገው ክርስቶስ እንዳዘዘን፥ ሰአግባቡና አክብሮት ባልተለየው ታዛዥነት ሲካሄድ ይገባል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.