ሀ. አገልግሎቷ ለእግዚአብሔር
ለሌላው ይጠቅም ዘንድ የሚከናወን ማንኛውም ተግባር አገልግሎት ይባላል። ይህን ጉዳይ ከመጽሐፍ ቅዱስ በምናጠናበት ጊዜ፥ በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል አያሌ ተመሳሳይና ተነጻጻሪ ሁኔታዎች እንመለከታለን። የአዲስ ኪዳን አብዛኛው አስተምህሮ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የተተነበየ ስላሆነ፥ በአዲሱ እስኪፈጸም ድረስ የብሉይ ኪዳን እስተምህሮ ጎደሎ ነው። የአገልግሎትንም ጉዳይ ስንወስድ ከዚህ የተለየ አይደለም። ስለ አገልግሎት ስናጠና በአብዛኛው የብሉይ ኪዳኑ አባባሎች እንደ ጥላ የነበራቸው ትርጉሞች በአዲስ ኪዳን ፍጻሜ ሲያገኙ እናያለን።
በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ሥርዓት ከእግዚአብሔር የሆነ አገልግሎት ከህነት ግንኙነት የሚጠቀላል ነው። በብሉይ ኪዳን ሥርዓት ከህነት በተዋረድ የሚካሄድ ሲሆን፥ ካህናቱ በሊቀ ካህኑ ሥልጣን ሥር ያገለግሉ ነበር። በአዲስ ኪዳን ሥርዓት ግን እያንዳንዱ አማኝ ለእግዚአብሔር ካህን ነው (1ኛ ጴጥ. 2፡5-9፤ ራእይ 1፡6)። የአዲስ ኪዳን ክህነት ጠቅላላ የአጎልግሎት እውነተኛ ሊቀ ካህን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ሥር የሚካሄድ ነው። ሌሎች ሊቀ ካህናት እውነተኛ ሊቀ ካህን ወደሆነው ክርስቶስ የሚያመለክቱ ጥላዎች ብቻ ነበሩ። ስለሆነም በአዲስ ኪዳን ሥርዓት መሠረት፥ አማኞች ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው የክህነት ግንኙነት ላይ በመመሥረት በተመሳሳይ ደረጃ ያገለግላሉ። በክህነት አገልግሎታቸው፥ እንደ ብሉይ ኪዳን ክህነት ሁሉ የአዲስ ኪዳን ካህናትም እግዚአብሔርንና ሰውን እንዲያገለግሉ ተሹመዋል።
በብሉይ ኪዳን ዘመን ለአሕዛብ የሚሰበክ ወንጌል ሰላልነበረ፥ አገልግሎቱ የሚያካትተው ከእግዚአብሔር የተሰጡትን ሥርዓቶች በመገናኛው ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ ውስጥ ማከናወንን ብቻ ነበር። ከዚህ ጋር ሲነጻጸር፥ የአዲስ ኪዳን የክህነት አገልግሎት በደረጃው የላቀና ሰፊ ነው። ይኸውም እግዚአብሔርንና ሌሎች አማኞችን ብቻ ሳይሆን፥ በሁሉም ስፍራ የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ የሚያጠቃልል መሆኑ ነው።
1. የመሥዋዕት አገልግሎት በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ተመሳሳይ ነበር። አንድ የብሉይ ኪዳን ካህን የሚቀደሰው ወይም የሚለየው፥ በሌዊ የካህንነት ቤተሰብ ውስጥ በመወለድና በተገቢው ሥርዓት ለክህነት አገልግሎት በመሾም ነበር። ሹመቱም ተሿሚው በሕይወት እስካለ ድረስ የጸና ነው። ካህኑ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ አንድ ጊዜ ለዘላለም በመታጠብ እንዲነጻ ይደረጋል (ዘጸ. 29፡4)።
የብሉይ ኪዳኑ ካህናት አገልግሎታቸውን በመንጻት እንደሚጀምሩ፥ በአማናዊነት የሚፈጽም የአዲስ ኪዳን አማኝ ካህን” ድነትን ሲያገኝ ለአንዴና ለዘላለም በመንጻት ነው እገልግሉቱን የሚጀምረው (ቆላ. 2፡13፤ ቲቶ 3፡5)። ከድነቱም የተነሣ ለእግዚአብሔር ተለይቷል። እንደዚሁም በአዲስ ልደት አማካይነት እግዚእብሔር ቤተሰብ ሆኗል። ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ፥ የአዲስ ኪዳን ካህን በፈቃደኝነት ራሱን ለእግዚአብሔር መስጠቱ የተለየ መመዘኛ ሆኖ የሚታይ ነው።
ራስን ስለ መስጠት፥ “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ” (ሮሜ 12፡1) የሚል ቃል እናነባለን። በእግዚአብሔር ርኅራኄ” የሚለው ሐረግ ሮሜ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ብሎ የተጠቀሱትን ታላላቅ የድነት እውነታዎች ያመለክታል። እያንዳንዱ እማኝ ድነት በሚያገኝበት ቅፅበት ይህንኑ ምሕረት ያገኛል። ሰውነትን እንደ ሕያው መሥዋዕት ማቅረብ የሚለው ቃል፥ አማኝ ራሱንና ያለውን ሁሉ ሰውዴታው ለእግዚአብሔር ፈቃድ መስጠቱን ያመለክታል። እግዚአብሔርም አማኙ የሚሰጠውን ሁሉ ተቀብሎ በፈቀደበት ስፍራ ላአገልግሎት ያስቀምጠዋል (ኤፌ. 2፡10)።
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጥ፥ ይህ የመቀበልና ስፍራ የመስጠት ተግባር መቀደስ ነው። ስለሆነም፥ አማኝ-ካህን ራሱን ለእግዚአብሔር የመስጠት እንጂ፥ ራሱን ለእግዚአብሔር የመቀደስ ብቃት የለውም። የሚቀድስ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ከመለኮታዊ የመቀደስ ተግባር ጋር በተያያዘ፥ በአሁኑ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ የአማኞችን አገልግሎት እንደ ሊቀ ካህን በመቀበል የተቀደሰ ያደርገዋል፥ ይህ በመምራትና ሰማዕተዳደር የሚያከናውነው ተግባር፥ የብሉይ ኪዳን ካህን የሌዊን ልጆች ሰሚቀድስበት አገልግሎት ውስጥ በጥላነት የተመለከተ መሆኑ ሊጤን ይገባል።
አማኝ-ካህን ራሱን ለእግዚአብሔር በመስጠትና ወደፊት ይህን ዓለም ሳለመምሰል፥ በውስጡ ሰሚያድረው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት የተለወጠ ሕይወት ይኖረዋል። በዚያውም ኃይል አማካይነት “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ” ፈጥኖ ሊያውቅ ይችላል (ሮሜ 12፡2)።
ሰእዲስ ኪዳን ሥርዓት፥ ሰመሥዋዕትነት ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የክህነት አገልግሎት አራት ገጽታዎች አሉት፡- (ሀ) “ሰአእምሮ የሚመች አገልግሎት” (ሮሜ 12፡1) ወይም ደግሞ ይበልጥ በቀጥተኛ ትርጉም “መንፈሳዊ አምልኮ” የተባለው ራስን የመስጠት ተግባር። ራሱ ክርስቶስ መሥዋዕት አቅራቢና መሥዋዕት እንደነበረ ሁሉ፥ አማኙም ሰውነቱን በሙሉ ለእግዚአብሔር እንደ ሕያው መሥዋዕት በማቅረብ ሊያስከብረው ይችላል፤ (ለ) የከንፈር መሥዋዕት ማለትም የምሥጋና ድምፅ ባለማቋረጥ ሊቀርብ ይገባል (ዕብ. 13፡15)፣ (ሐ) የቁሳዊ ነገር መሥዋዕት (ፊልጵ. 4፡18)፣ (መ) የሰናይ ምግባራት መሥዋዕት (ዕብ. 13፡16)።
የካህናትን መንጻት አስመልክቶ፥ የብሉይ ኪዳን ካህን ወደ ቅዱስ አገልግሎቱ በሚገባበት ጊዜ ጠቅላሳ ሰውነቱን በመታጠብ አንድ ጊዜ ለዘላለም ይነጻ እንደነበር በድጋሚ መገንዘቡ አስፈላጊ ነው። ይህም የመታጠብ ተግባር በራሱ በካህኑ ሳይሆን በሌላ ሰው ይከናወን ነበር (ዘዳ. 29፡4)። ከዚያ በኋላ፥ ምንም እንኳን ሰውነቱን ሁሉ የታጠበ ቢሆን፥ በተደጋጋሚ ከፊል የመታጠብ ተግባሩን ሐስ ሳህን ላይ እንዲያከናውን ይጠየቃል። ይህም የትኛውንም የክህነት አገልግሎት ከማበርከት አስቀድሞ ይከናወናል። የዚህን ምሳሌያዊ ጠቀሜታ ለመፈጸም፥ የአዲስ ኪዳን ካህን ምንም እንኳ ድነትን ባገኘ ጊዜ የነጻና ይቅርታ የተደረገለት ቢሆን፥ ሁልጊዜ ልቡ የሚያውቃቸውን ኃጢአቶች መናዘዝ ይኖርበታል። ይህ የሚሆንበት ምክንያቱ ለመንጻትና ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የማድረግ ብቃት ይኖረው ዘንድ ነው (1ኛ ዮሐ. 1፡9)። የብሉይ ኪዳን ካህን ሹመት ለዘላለም እንደሆነ ሁሉ፥ የአዲስ ኪዳን ካህንም ለዘላላም የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው።
2. የአምልኮ አገልግሎት በቀጣዩ ምዕራፉ ውስጥ በስፋት ይቀርባል)፥ በአሁኑ ዘመን የእያንዳንዱ አማኝካህን የአገልግሎት ሕይወት ክፍል እንደን መመልከት ይቻላል። በብሉይ ኪዳን የሁሉም ካህን አገልግሎት እንደነበረው ማለት ነው። የተቀደሰው ስፍራ አሠራሮች በብሉይ ኪዳን ሥርዓት የካህኑን እምልኮ ሰተምሳሌትነት እንደሚያመለክቱና፥ የስፍራው ገጽታና አሠራር ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደሚናገር፥ የእማኝም አምልኮ በክርስቶስ አማካይነት ብቻ የሚሆን ነው። አሁንም በአገልግሎት መልክ ለእግዚአብሔር የሚቀርሰው የአማኝ አምልኮ፥ ራስን ለእግዚአብሔር ማቅረብ (ሮሜ 12 ፡1)፥ ከልብ የመነጨ ምስጋናና ውዳሴ ለእግዚአብሔር መሠዋት (ዕብ. 13፡15)፥ ወይም የመሥዋዕትነት ስጦታዎችን ለርሱ ማቅረብ ሊሆን ይችላል።
ከብሉይ ኪዳን ካህናት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ሁለት የተከለከሉ ነገሮች ተመዝግበዋል። እነዚህም ተምሳሌታዊ ፍች አላቸው። “እንግዳ” ወይም ሌላ ዕጣን ማቅረብ አይቻልም (ዘዳ. 30፡9)። ይህም ለእግዚአብሔር በሚቀርብ አገልግሎት ውስጥ ልባዊ ያልሆነ ሥርዓትን ያመለክታል። “እንግዳ” ወይም ሌላ እሳት ማቅረብም አይቻልም (ዘሌዋ. 10፡1)። ይህ ደግሞ ለክርስቶስ በመንፈስ አማካይነት እውነተኛ መሰጠት ሊኖረን ሲገባ፥ ሥጋዊ ስሜቶችን መተካትን ወይም ለክርስቶስ ልንሰጠው የሚገባንን ፍቅር በተራ ነገሮች መሸፈንን በተምሳሌትነት የሚያሳይ ነው (1ኛ ቆሮ. 1፡11-13፤ ቆላ. 2፡8፥16-19)።
3. በቀጣዩ ምዕራፍ ውስጥ የምንመለከተው የምልጃ አገልግሎትም ካህን የተሳለው እማኝእስፈላጊ ተግባር ነው። ነቢይ ለሕዝቡ የእግዚአብሔር ወኪል እንደሆነ ሁሉ፥ ካህን ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ የሕዝብ ወኪል ነው። ክህነት መለኮታዊ ሹመት እንደመሆኑ፥ ሁልጊዜም ወደ እግዚአብሔር የመቅረቢያው መንገድ ነበር። ቢሆንም በብሉይ ኪዳን ዘመን ካሊቀ ካህናቱ በቀር የትኛውም ካህን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንዲገባ አይፈቀድለትም ነበር። እርሱም ቢሆን በዓመት አንድ ጊዜ የመሠዊያ ደም ይዞ ነበር የሚገባው (ዕብ. 9፡7)።
በዚህ ሥፍረ-ዘመን ክርስቶስ እንደ ሊቀ ካህን በራሱ ደም ወደ ሰማያዊቷ መቅደስ ገብቷል (ዕብ. 4፡14-16፤ 9፡24፤ 10፡19-22)። ስለሆነም የርሱ ለሆኑትና በዓለም ለሚገኙት በመማለድ ላይ ነው (ሮሜ 8፡34፤ ዕብ. 7፡25)። ክርስቶስ በሞተበት ቅፅበት የቤተ ክርስቲያን መጋረጃ ለሁላት ተቀዷል። ይህም ለዓለም ሳይሆን በፈሰሰው የክርስቶስ ደም በኩል ወደ እግዚአብሔር ለሚመጡ ሁሉ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ እንደተካፈተ ያመለክታል (ዕብ. 10፡19-22)።
የአዲስ ኪዳን ካህን ከክርስቶስ ደም የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ስለሚችል፥ በምልጃ የማገልገል ዕድል አለው (ሮሜ 8፡26-27፤ ዕብ. 10፡19-22፤ 1ኛ ጢሞ. 2፡1፤ ቆላ. 4 ፡12)።
ለ. የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለሰው
ሮሜ 12፡1-8 ውስጥ የተጠቀሰው እውነት በመለኮት የተደረገ የቅደም ተከተል እቀማመጥ አለው። በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደተመለከተውና፥ በዚህ ክፍልም እንደተጠቀሰው፥ የመሰጠትና የቅድስና ሕይወት እስካልታዩ ድረስ ክርስቲያናዊ አገልግሎት የተባለ ነገር አይኖርም። እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች ተከትሎ መለኮታዊ ጸጋ ስጦታዎች ለአገልግሎት ተሰጡ። ከዚሁ ጋር በተገናዘበ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ “ስጦታ” የሚለውን ቃል በሚጠቀምበት መንገድና በተለመደው አገላለጥ መካከል ያለውን ሰፈ ልዩነት መገንዘቡ መልካም ነው። ስጦታ በትውልድ ወይም በዘር የሚተላለፍ እና የተለየ ነገር ለማድረግ የሚያስችል ነገር አድርጎ የመቁጠር ግንዛቤ አለ። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም “ስጦታ፡፡አማኝ ውስጥ የሚያድረው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ነው።
መንፈስ ቅዱስ አማኙን በመሣሪያነት በመጠቀም አገልግሎት ይሰጣል። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በማንኛውም መልኩ በአማኙ ጥረት፥ ወይም የርሱ ጥረት ታክሎበት የሚመጣ ነገር አይደለም። ክርስቲያናዊ ባሕርይ የመንፈስ ፍሬ” እንደሆነ ሁሉ (ገላ. 5፡22-23)፥ ክርስቲያናዊ አገልግሎትም <<መንፈስ ቅዱስን መግለጥ” ወይም የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ እንደሆነ ተመልክቷል (1ኛ ቆሮ. 12፡7)።
እያንዳንዱ አማኝ አንዳንድ መለኮታዊ ስጦታዎች ቢኖሩትም (1ኛ ቆሮ. 12፡7፤ ኤፌ. 4፡7)፥ የስጦታዎቹ ዓይነት የተለያየ ነው (ሮሜ 12፡6፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡4-11፤ ኤፌ. 4፡11)። ክርስቲያኖች ሁሉ ተመሳሳይ ሥራ እንዲያከናውኑ አይመረጡም። በዚህ ረገድ አማኞች ሁሉ ከሚሠዉበት፥ ከሚያመልኩበትና ከሚያማልዱበት የክህነት አገልግሎት ጋር “ስጦታ” ልዩ መሆኑን መገንዘቡ ተገቢ ነው። እነዚህን የሚያደርጉት ስጦታ ስላላቸው ሳይሆን ካህናት ስለሆኑ ነው። ምንም እንኳ አጠቃላይ የሆኑ የጸጋ ስጦታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢዘረዘሩ (ሮሜ 12፡6-8፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡8-11፤ ኤፌ. 4፡11)፥ እና ከነዚህም መካከል አንዳንዶቹ መሥራት ቢያቆሙ (1ኛ ቆሮ. 13፡8)፥ በአማኞች አማካይነት የሚከናወነው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎትና አማኞቹ እንዲያገለግሉ የተጠሩባቸው ሁኔታዎች እንዳሉባቸው ስፍራዎች ይለያያሉ።
ስጦታዎች የሚሰጡት የእግዚአብሔር አገልጋይ “ጠቃሚ” ይሆን ዘንድ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡7)። በሥጋ ጉልበት የሚሠራ አገልግሎት ጠቃሚ ያለመሆኑን ይህ ያመለክታል። በስጦታው ልምምድ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ እንደ የሕይወት ውኃ ወንዝ” (ዮሐ . 7፡37-39) መፍሰስ እና “እግዚአብሔር እናደርገው ዘንድ አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ” (ኤፌ. 2፡10) ማከናወን ነው።
በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ አማኞች ማንም ሳይገፋፋቸው ስጦታዎቻቸውን ባለማቋረጥ ከሥራ ላይ ያውላሉ። ሥጋዊ እማኞች ስጦታው ቢኖራቸውም፥ በትጋት የማገልገልም ሆነ ሰዎች ስጦታቸውን እንዲጠቀሙ ሲያበረታቷቸው የመንቃት ዝንባሌ አይታይባቸውም። ይሁንና ኃጢአታቸውን በመናዘዝ፥ ሕይወታቸውን በመስጠትና በውስጣቸው በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ላይ በመደገፍ ከእግዚአብሔር ጋር በሚስማሙ ጊዜ፥ ወዲያውኑ በመንፈስ ቅዱስ ይሞሉና የእግዚአብሔርን ፈቃድ የመፈጸም መሻት ያድርባቸዋል። ሰመሆኑም፥ በውስጣቸው በሚሠራው የእግዚአብሔር ኃይል አማካይነት ቀደም ሲል እግዚአብሔር ለሰጣቸው አገልግሎት ጠቃሚ መሣሪያዎች ይሆናሉ። ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ የሚሞሉት ትጉህ አገልጋዮች በመሆናቸው አይደለም። ይልቁንም፥ በመንፈስ ቅዱስ በመሞላታቸው ትጉህ አገልጋዮች ይሆናሉ። አንዳንድ ጊዜ የዛለ አገልጋይ እንቅስቃሴውን ሁሉ በግቆም እንዲያርፍ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “ብቻችሁን…ሁኑ እረፉ” ያላቸው ወቅት ነበር።
ሐ. የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ አወቃቀሟ
የክርስቲያን የገንዘብ አስተዳደር ወይም አያያዝ በሦስት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡- (1) ገንዘብን ማግኘት፥ (2) ገንዘብን በንብረትነት መያዝ፥ (3) ገንዘብን መስጠት። ገንዘብን ማግኘት በማንም ሰው ዕለታዊ ሕይወት ያለ ቢሆንም፥ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚያገኙት ገንዘብ አጠቃቀም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት በሚቀርቡበት ጊዜ መልስ ይሰጥበታል (ሮሜ 14፡16-12)። ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ ገንዘብ ያገኛሉ፥ ይይዛሉ፥ ያጠፋሉ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖራቸው የሚገባ ግንኙነት ግን አያጤኑትም።
1. ክርስቲያን ገንዘብ የማግኘቱ ተግባር ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ግንኙነት ጋር ሰሚስማማ መልኩ ሊሆን ይገባል። ይህም “የምታደርጉትን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ኛ ቆሮ. 10፡31) ከሚለው ትእዛዝ አንጻር ተግባራዊ መሆን አለበት። ሁሉም በወዙ እንዲያድር መለኮታዊ ዕቅድ ነው (ዘፍጥ. 3፡19፤ 2ኛ ተሰ. 3፡10)፤ ክርስቲያንም ከዚህ የተለየ አይደለም። መንፈሳዊ ለሆነና ለሚያስተውል አማኝ ግን፥ ሥራ የኑሮ ማሸነፊያ መንገድ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግም ነው። የቱንም ያህል አድካሚ ቢሆን፥ ማንኛውም ሥራ ከእግዚአብሔር እንደተሰጠ ተደርጎ ለርሱ ክብር ሊከናወን ይገባል። ይህ ካልሆነ ባይሠራ ይሻላል።
እግዚአብሔር በዕለታዊ ሥራ አማካይነት ለልጆቹ ምግብና ልብስ በመስጠት ደስ መሰኘቱ፥ በፍጹም ፍቅሩ ለልጆቹ የሚያስብላቸው የመሆኑን የላቀ እውነት ሊያደበዝዘው እይገባም (ፊልጵ. 4፡19፤ ዕብ. 13፡5)። “እግዚአብሔር የሚሰጠው ለራሳቸው ምንም ለማድረግ ለማይችሉ ብቻ ነው” የሚለው አባባል እውነት አይደለም። የእርሱ ለሆኑት ሁልጊዜ ይጠነቀቅላቸዋል፤ ያላቸው ነገር ሁሉ ከርሱ ነውና(1ኛ ሳሙ. 2፡7)።
“ለሠራተኛ ደመወዙ ስለሚገባው” (ሉቃስ 10፡7)፥ በሰዎች መካከል በሚኖሩ ግንኙነቶች ውስጥ ስምምነቶችና ደመወዞች ተለይተው ይታወቃሉ። ክርስቲያን ግን አባቱ ከሆነው እግዚአብሔር ያለው ግንኙነት ምንም ሲያደርግ ለአባቱ ፈቃድና ለርሱ ሲል የሚያከናውነው ነው። የሚያከናውነው ሥራም ራሱን ለእግዚአብሔር መስጠቱን የሚገልጥበት ይሆናል። በተመሳሳይ ሁኔታ ክርስቲያን የሚያገኘው ነገር ሁሉ ከሥራው የሚገኝ ሳይሆን፥ የአባቱ የፍቅር መግለጫ ነው። የዚህ ዓይነቱ አመለካከት ስሜታዊ ወይም ከተግባራዊነት የራቀ አይደለም። ይልቁንም፥ እማኝ ድካሙን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር በማዋል የሚቀድስበት ወይም በሕይወት ጫና ውስጥ እንኳ ቢኖር ለዘላለሙ የሚደሰትበት (1ኛ ተሰ. 5፡16) ብቸኛ መሠረት ነው።
2. ለማንኛውም ታማኝ ክርስቲያን የገንዘብ እያያን ከፍተኛ ኃላፊነት ነው። ከየአቅጣጫው ከሚመጣው የእርዳታ ጥያቄና ገንዘብ ከሚያከናውነው ብዙ በጎ ተግባር አንጻር፥ እያንዳንዱ መንፈሳዊ ክርስቲያን ያለውን ገንዘብ “ልስጥ ወይ አልስጥ” የሚል ጥያቄ ይገጥመዋል። ንብረትን ባለማባከን መያዝ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑ እያጠራጥርም። ራሱን ለጌታ የሰጠ አማኝ ንብረቱን ልስጥ አልዕጥ ሰማላት ሊጠይቅ ይገባል። እውነተኛ ክርስቲያን ንብረቱን እግዚአብሔር እንደመራው የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ተቆጣጣሪውም እግዚአብሔር ነው። ሀብታሞችንም ሆነ ድሆችን የሚያነሣሡ ውስጣዊ ዓላማዎች፥ ማለትም የሳለጠግነት መሻት (1ኛ ጢሞ. 6፡8-9፥ 17-18፤ ያዕ. 1፡11፤ ዕብ. 13፡5፤ ፊልጵ. 4፡1)፥ ለነገ በመጨነቅ የማስቀመጥ ፍላጎት (ማቴ. 6፡25-34) እና ለሌሎች የመስጠት ፍላጎቶች ተገቢ የሚሆኑት፥ በእያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት የተገለጠውን የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚፈጽሙ ሲሆኑ ብቻ ነው።
3 ክርስቲያን ሥርቶ ካገኘው ገንዘብ የመስጠቱ ጉዳይ ለእግዚአብሔር የሚያስ ረክተው ፆናና አስፈላጊ አገልግሎት ነው። እኔነትና ገንዘብ የክፋት ሥሮች ናቸው። በመሆኑም ገንዘብን በማግኘቱና በመጠቀሙ ረገድ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ባለው የጸጋ ግንኙነት ላይ መቆም ይጠበቅበታል። ይህም ግንኙነት አማኝ በቅድሚያ ራሱን ለእግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ የሰጠ መሆኑን ያመለክታል (2ኛ ቆሮ. 8፡5)። አንድ ሰው በእውነት ራሱን ለእግዚአብሔር ከሰጠ ራሱም ሆነ ያለው ንብረት ሁሉ (1ኛ ቆሮ. 6፡20፤ 7፡23፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡18-19)፥ ማለትም ሕይወቱ፥ ጊዜው፥ ብርታቱ፥ ችሎታው፥ ዓላማና ንብረቱ የእግዚአብሔር ይሆናሉ።
ከገንዘብ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ፥ የጸጋ መርሆ የሚያካትተው፥ ክርስቲያን ባለው ነገርና በራሱም ማንነት ላይ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ ሥልጣን የሚገነዘብ መሆኑን ነው። ይህ ሕጉ እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ የሕጉ አካል ሆኖ ይሠራበት ከነበረው የብሉይ ኪዳን የአሥራት አወጣጥ መንገድ ይለያል (ዮሐ. 1፡16-17፤ ሮሜ 6፡14፤ 7፡1-6፤ 2ኛ ቆሮ. 3፡1-18፤ ገላ. 3፡19-25፤ 5፡18፤ ኤፌ. 2፡15፤ ቆላ. 2፡14)። ምንም እንኳን አንዳንድ የሕግ መመሪያዎች በጸጋ ሥር እንደገና ቢገሰጡ፥ ሰንበትን እንደማከበር ሁሉ አሥራትም በዚህ ሥፍረ-ዘመን በአማኙ ላይ የተጣሉ አይደሉም። የጌታ ቀን ሕጋዊውን የሰንበት አከባበር ስለተካና ከጸጋ መመሪያዎች ጋር እንደተስማማ፥ አሥራትም በሌላ የመስጠት ዘዴ ተተክቷል። ይህም ከጻጋ ትምህርት ጋር የሚስማማ የእሰጣጥ መንገድ ነው።
በቆሮንቶስ ቅዱሳኝ ልምምድ እንደተብራራው፥ ክርስቲያናዊ ስጦታ በጸጋ ዘመን 2ኛ ቆሮንቶስ 8፡1-9፡15 ውስጥ ተጠቃሎ ቀርቧል። በዚህ ክፍል የሚከተሉትን ነጥቦች እንመለከታለን፡-
(ሀ) ክርስቶስ ለቆሮንቶስ ቅዱሳን ምሳሌያቸው ነበር። በጻጋ ዘመን ለሁሉም ዓይነት መስጠት ምሳሌ የሚሆነው፥ ክርስቶስ ራሱን መስጠቱ ነው (2ኛ ቆሮ. 8፡9)። እርሱ የሰጠው አሥር ከመቶውን ብቻ ሳይሆን፥ ሁሉንም ነው።
(ለ) የሰጡት ከከፍተኛ ድህነታቸው ነበር። የቆሮንቶስ አማኞች በመስጠት አገልግሎታቸው የጎጠማቸው ነገር በአስገራሚ ቃላት ነው የተገለጠው (2ኛ ቆሮ 8፡2)፡“በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ፥” “የደስታቸው ብዛት፥” (“የድህነታቸው ጥልቅነት፥” “የልግስናቸው ባለጠግነት”። በተመሳሳይ ሁኔታ በትልቅ ድህነት ውስጥ በልግስና መስጠትን በተመለከተ የጌታችንን ምስጋና ያተረፈው የመበለቲቱ ሣንቲም (ሉቃስ 21፡1-4)፥ “የነበራት ሁሉ” እንጂ ከነበራት ተከፍሎ የተሰጠ አለመሆኑን መገነዘቡ አስፈላጊ ነው።
(ሐ) ገንዘባቸውን የሰጡት በትእዛዝ ወይም በግዴታ አልነበረም። በሕግ ዘመን አይሁዶች ከገቢያቸው አሥር እጅ እንዲከፍሉ የታዘዙ ሲሆን፥ ያም የግድ መከፈል ነበረበት። በጸጋ ዘመን ግን እግዚአብሔር የሚፈልገው ስጦታውን ሳይሆን፥ የሰጪውን ፍቅርና ታማኝነት ነው። በጸጋ ዘመን የሕግ ጫና የለም። ሊሰጥ የሚገባው መጠንም አልተጠቀሰም። እግዚአብሔር በጎ ፈቃዱን ለመቀበልና ደስ የሚያሰኘው ለማድረግ የተሰጠ ልብ የሚሠራ መሆኑ እውነት ቢሆንም (ፊልጵ. 2፡13)፥ ይበልጥ ደስ የሚሰኘው ግን፥ በልግስና በሚቀርብለት ስጦታ ነው (2ኛ ቆሮ. 9፡7)።
ሰው ሊለግስ የሚገባውን የስጦታ መጠን የሚደነግግ ሕግ ቢኖር ኑሮ፥ ከበጎ ፈቃዳቸው ውጭ ቢሆንም እንኳ ትእዛዛትን የሚፈጽሙ ሰዎች መኖራቸው አያጠራጥርም። ይህም ቢሆን ስጦታቸው “በቅሬታ” ወይም “ሰግዴታ” የተሰጠ ይሆን ነበር። የወንጌሉን ሥራ ለመደገፍ በልግስናም ይሁን ያለ ልግስና የተሰጠ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የምንናገር ከሆነ፥ የሚፈለገውን ውጤት የሚያስገኘው በስጦታ የተገኘው የገንዘብ ቁጥር ሳይሆን፥ በስጦታው ላይ የሚያርፈው መለኮታዊ በረከት መሆኑን ልንረዳ ይገባል።
ክርስቶስ በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ሰዎችን መግቧል። የእግዚአብሔር ልጆች ሰጸጋ የመስጠት ዕድላቸውን ተግባራዊ በሚያደርጉበት ስፍራ ሁሉ በረከት ይክተሳቸዋል። “እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል” (2ኛ ቆሮ. 9፡8) የሚለው ቃል እውነት ለመሆኑ ማረጋገጫ አለ።
(መ) የመጀመሪያው ምእተ ዓመት ክርስቲያኖች ከሁሉም በፊት ራሳቸውን ነበር የሰጡት። ትክክለኛ የሆነ ስጦታ የሚቀድመው ራስን በመስጠት ነው (2ኛ ቆሮ. 8፡5)። ይህ የሚያመለክተው፥ የጸጋ ዘመን መስጠት፥ እንደ ሕግ ዘመን፥ ሰው ሁሉ የሚያደርገው ሳይሆን፥ በተወሰኑ ስዎች የሚከናወን መሆኑን ነው። አሥራትን እንዲከፍሉ እግዚአብሔር የጠየቃቸው እስራኤላውያንን እንጂ ሌሉች ሕዝቦችን አልነበረም። ስለሆነም፥ ክርስቲያናዊ መስጠት ለክርስቲያኖች ብቻ የተወሰነ ሲሆን፥ ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ከሰጡት አማኞች የሚመጣው ነው።
(ሠ) የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን አማኞች የአሰጣጥ ሥርዓት ነበር። እንደ አሥራት ሁሉ፥ በጸጋ ዘመንም የሚከናወን መደበኛ የአሰጣጥ ሥርዓት እንዳለ እንመለከታለን። “እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ” (1ኛ ቆሮ. 16፡2)። ይህ ትእዛዝ “ለእያንዳንዱ” ክርስቲያን በመሆኑና የሚሰጠውም “ከተቀማጩ” በመሆኑ ማመኻኛ ማቅረብ አይቻልም።
(ረ) የሚሰጥን አማኝ እግዚአብሔር ይደግፈዋል። በጸጋ መስጠትንም ወሰን በሌላቸው ጊዜያዊ ሀብቶች ይደግፋል (2ኛ ቆሮ. 9፡8-10፤ ሉቃስ 6፡38)። በዚህ መሠረት አሥር በመቶ ያህል የሚሰጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በጊዜያዊ ነገሮች የሚበለጥጉ መሆናቸውን ለመመልከት ይቻል ይሆናል። ይሁንና፥ እማኝ ካሕግ ጋር ግንኙነት ስለሌለው (ገላ. 5፡1)። ይህ የብልጥግና ተስፋ የጻጋ እንጂ የሕግ የተስፋ ቃል ፍጻሜ አይደለም። ስለሆነም፥ በአሥራት መጠን ላይ የሚደገፍ በረከት አይኖርም።
በረከቶቹ የሚገኙት፥ በስጦታ አማካይነት ልክ ራሱን ስለገለጠ ነው። እግዚእብሔር በቸርነቱ የማይቀበለው ከልብ ሆኖ የቀረበ ስጦታ አይኖርም። እዚህ ላይ በመስጠት የመበልጠግ ዕቅድ ሊነደፍ አይችልም። ስጦታው ከልብ የመነጨ ሊሆን ይገባል። እግዚአብሔርም ልጁ ለሆነ አማኝ የሚሰጠው መልስ፥ ካለው ፍጹም ፈቃድ አኳያ የሚፈጸም ነው። እርሱ እንደመረጠ መንፈሳዊ ወይም ምድራዊ በረከት ሊሰጥ ይችላል።
(ሰ) እውነተኛ ብልጥግና የሚመጣው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ብልጥግና ተሰጥቷቸው ነበር። በዚህ ዓለም ነገሮች በልጥጎ በእግዚአብሔር ፈት መደህየትም አለ (ሉቃስ 12፡21)። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በእሳት የነጠረውን ወርቅ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲገዙ ተጋብዘዋል (ራእይ 3፡18)። በክርስቶስ ሞት አማካይነት ሰዎች ሁሉ ሊበለጥጉ የሚችሉበት በር ተከፍቷል (2ኛ ቆሮ. 8፡9)። በእምነት (ያዕ. 2፡5) እና በሰናይ ምግባራት (1ኛ ጢሞ. 6፡18) መበልጠግም ይቻላል። አማኝ በኢየሱስ ክርስቶስ የጌታን “የጸጋውን ባለጠግነት” (ኤፌ. 1፡7) እና “የክብሩን ባለጠግነት” (ኤፌ. 3፡16) ይቀበላል።
ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡