ሀ. ታላቁ መከራ ከአጠቃላይ መከራ ጋር ሲነጻጸር
የታላቁን መከራ አስተምህሮ በተመለከተ የተለያዩ ግራ መጋባቶች ታይተዋል። የዚህ ምክንያቱ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያልፍበትን የተለያዩ መከራዎችና ፈተናዎች በታወቀ ጊዜ እንደሚመጡ ብሉይና አዲስ ኪዳናት ውስጥ ከተገለጠው ታላቅ መከራ ለመለየት አለመቻል ነው። መከራ የሚለው አሳብ የሚያመለክተው ጫናን፥ ጉስቁልናን፥ የልብ ስብራትንና ችግር የምንላቸውን ነገሮች ሁሉ ነው። መከራ ስንል በአጠቃላይ ለሰው ዘር እውን ስለሆኑ ችግሮች መናገራችን ነው። ይህ ዓይነት መከራ ከሰው ልጅ ኃጢአትና በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ ሳቢያ ይመጣል። በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል በምድር ከሚከናወን የዓላማ ልዩነት የተነሣ የሚፈጠር ችግርም ነው።
ኢዮብ 5፡7 ውስጥ “የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ክፍ እንዲሉ ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል” ይላል። ክርስቶስም ይህንኑ ዮሐንስ 16፡33 ውስጥ ሰደቀ መዛሙርቱ ሲያረጋግጥ፥ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ” ብሏል። ብሉይ ኪዳን ውስጥ ኢዮብ የደረሰበት መከራና አዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰው የጳውሎስ ሥጋ መውጊያ ችግር በሰው ልጆች ላይ ያለማቋረጥ ለሚደርሰው መከራና ጉስቁልና እንደ ምሳሌ የሚወሰዱ ናቸው። ከአዳም ጀምሮ ይህ የሰው ልጆች መታወቂያ ሆኗል። በሺህ ዓመቱ መንግሥት ጊዜ በአያሌው የሚቃለል ቢሆንም፥ የሰው ልጅ ታሪክ እስኪያበቃ ድረስ ይቀጥላል።
መከራና ሥቃይ በጣምራነት ባጠቃላይ የሰው ዘር ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት አንጻር፥ በዘመኑ መጨረሻም ችግር የሚኖርበት የተለየ ጊዜ መኖሩን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። ይህ የሚሆነው፥ በተለይ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት መዳረሻ በሆነው የአርባ ሁለት ወራት ጊዜ ሰሚኖረው ታላቅ መከራ ነው።
ለ. ስለ ታላቁ መከራ የብሉይ ኪዳን አስተምህሮ
እስራኤል በኋለኛው ዘመኗ መከራ በሚደርስባት ጊዜ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ያለባት ስለመሆኑ ማስጠንቀቂያ የተነገራት ገና መጀመሪያ ዘዳግም 4፡29-30 ውስጥ ነበር። ይህ የተለየ ጊዜ የተነገረው ሰነቢዩ በኤርምያስ ነው። የመከራው ጊዜ የሚጀምረው እስራኤላውያን በከፊል ወደ ምድራቸው ከተመለሱ በኋላ እንደሚሆን ነቢዩ ምዕራፍ 30፡1-10 ውስጥ እንዲህ በማለት ተንብዮአል፡- “እነሆ የሕዝቤኝ የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአባቶቻቸውም ወደሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነሱም ይገዟታል” (ቁ.3)።
ወዲያውኑ በመቀጠል ከቁጥር 4-7 ባለው ክፍል እስራኤላውያን ወደ ምድራቸው ከተመለሱ በኋላ በሚኖረው ጊዜ ስለሚደርስባቸው መከራ ተጎልጧል። ያኔ እስራኤል ልጅ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ይይዛታል። የመከራው ጊዜ በተለይ ኤርምያስ 30፡7 ውስጥ እንዲህ ተገልጧል፡“ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፥ እርሱንም የሚመስል የለምና፤ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፥ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል”
እስራኤል ምንም እንኳን በዚህ ታላቅ መከራ ውስጥ ብታልፍ፥ እግዚአብሔር በመጨረሻ የባርነት ቀንበሯን እንደሚሰብርና አሕዛብን ከማገልገል ነጻ እንደሚያወጣት ተስፋ ሰጥቷታል። ቁጥር 9 ውስጥ እንደተገለጠው፥ “ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም፥ ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ እንጂ ሌሉች አሕዛብ እንደገና አይገዟቸውም”። ይህ ትንቢት ዳዊት ከሞት ተነሥቶ በሺህ ዓመቱ መንግሥት ጊዜ ከክርስቶስ ጋር በእስራኤል ላይ የሚነግሥ መሆኑን ያመለክታል። ለዚህ ነው እስራኤል ተስፋ እንዳትቆርጥ “ያዕቆብም ይመለሳል፥ ያርፍማል፥ ተዘልሎም ይቀመጣል፥ ማንም አያስፈራውም” (ቁ.10) የሚል ዋስትና የተሰጣት።
የያዕቆብ መከራ ጊዜ ወይም ታላቁ ፍዳ፥ ዳንኤል 9፡27 ውስጥ የተጠቀሰው ቃል ኪዳን ከፈረሰ በኋላ እንደሚሆን በዚሁ ክፍል ተመልክቷል። ጊዜው የሰባቱ ዓመት አጋማሽ ወይም ሦስት ዓመት ተኩል እንደሚሆን በማያሻማ ሁኔታ ተገልጧል፥ “የሚመጣውም አለቃ” (ዳን. 9፡26)፥ “ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ** (9፡27)፥ ማለት ለሰባት ዓመት ያደርጋል። ይሁን እንጂ ቃል ኪዳኑን በሱባዔው እጋማሽ፥ ማለት ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ያፈርስና “መሥዋዕቱንና ቁርባኑን ያስቀራል”፥ ቤተ መቅደሱንም ያረክሳል።
ዳንኤል 12:11 ውስጥ እንዲህ ተብሎ ሁኔታው ተብራርቷል፡- “የዘወትሩም መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፥ የጥፋትም ርኩሰት ከቆመ ጀምሮ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠነኛ ቀን ይሆናል”። ይህ ጥቂት ቀናት ተጨምሮበት ሦስት ዓመት ተኩል ይሆናል። ጊዜው የክርስቶስን ዳግም ምጽአትና ከዚያ የሚከተሉትን የመጀመሪያ ፍርዶች የሚያጠቃልል ሳይሆን አይቀርም። ዳንኤል 12፡12 ውስጥ የተገለጠውና ከ1335 ቀናት በኋላ የሚመጣው በረከት ታላቁን የመከራ ጊዜ፥ የክርስቶስን ዳግም ምጽአትና ፍርዶቹን ብቻ ሳይሆን፥ የተባረከውን የክርስቶስ ሺህ ዓመት መንግሥት በምድር መመሥረትን ይጨምራል። በዚሁ መሠረት የታላቁ መከራ ጊዜ አርባ ሁለት ወራት ወይም ሦስት ዓመት ተኩል መሆኑ ታውቋል።
ታላቁ የፍዳ ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ምጽአት ወቅት የሚያበቃ መሆኑ በግልጥ ይታወቃል። ዳንኤል 7፡13-14 ውስጥ በተጠቀሰው ትንቢት መሠረት ጊዜው የሰው ልጅ (ክርስቶስ) ከሰማይ የመምጣቱንና መንግሥታትን በሥልጣኑ ሥር የማድረጉን ክንዋኔ ያጠቃልላል። በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዋዜማ ላይ የሚኖረው ክፉ መንግሥትና ንጉሥ ይደመሰሳሉ (ዳን. 7፡26)። ከዚያም መጀመሪያ የሺህ ዓመቱ የክርስቶስ አገዛዝ፥ ለጥቆም በአዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የሚመሠረተው ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ይመጣሉ። የብሉይ ኪዳን አስተምህሮ በአንጻራዊ መልኩ ያብቃ ቢሆንም፥ ይህን ክንዋኔ በተመለከተ ግን አዲስ ኪዳናዊው ራእይ ሊታከልበት ይችላል።
ዳንኤል 11፡36-39 ውስጥ በተመለከተው ትንቢት መሠረት፥ በመጨረሻው ዘመን የሚኖረው ሃይማኖት የዓለም መሪ ወይም ገዢ ሰሚሆነው ሰውዬ የሚመራና በእግዚአብሔር ሳይሆን፥ በሌሎች አማልክት ላይ የሚመሠረት ይሆናል። እነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እንደተመለከተው፥ ይህ መሪ ቀድሞ የነበሩትን አማልክት ሁሉ የማያከብርና እራሱን ከእግዚአብሔር በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርግ ነው። የሚያከብረው የአምባዎችን አምላክ ማለት የጦርነት አምላክን ብቻ ይሆናል። ቁሳዊነት እንጂ፥ fእምልኮ መንፈስ ያለበት ሰው አይሆንም። የዚህ ሰው መንግሥት የሚያከትመው፥ ከቁጥር 40-45 ባለው ክፍል እንደተመለከተው፥ እጅግ ታላቅ በሆነ ጦርነት ነው። ከደሱብ፥ ከሰሜንና ከምሥራቅ ሠራዊቶች ይመጡበታል። የሚመጣበትን ሠራዊት ለተወሰነ ጊዜ የሚመክት ቢመስልም፥ ታላቁ ፍዳ እንዲያከትም የሚያደርገው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት እስኪሆን ድረስ ጦርነቱ የከፋ ይሆናል።
ሐ. የፍዳው ዘመን በአዲስ ኪዳን አስተምህሮ
ዳግም ምጽአቱና የዓለም ፍጻሜ መቼ እንደሚሆን ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ በተጠየቀ ጊዜ፥ ለእኛ የሚሆኑ የዘመኑን ምልክቶች ነው አስቀድሞ የነገራቸው። ከነዚህ ብዙዎቹ በክርስቶስ ቀዳሚና ዳግም ምጽአቶች መካከል ባለው ጊዜ መከናወን ያለባቸው እንደመሆናቸው ተፈጽመዋል (ማቴ. 24፡3-14)።
ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ስለሚመጡት ምልክቶች በጠየቁት ጊዜ ማቴዎስ 24፡15-29 ውስጥ ሲመልስ የገለጠላቸው ታላቁን መከራ ነው። መከራው የሚጀምረው “በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ” (ቁ.15) ሰዎች ሲመለከቱ፥ እንዲሁም የቤተ መቅደሱን መርከስና ሰሜድትራንያን አካባቢ የሚነሣው መሪ ራሱን በእግዚአብሔር ስፍራ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያኖር መሆኑን ከማስጠንቀቅ ጋር ገለጠሳቸው። አንድ ቀን ራሱን የቻለ ክንውን ሆኖ የሚገለጠው ይህ ዕለት በሚከሠትበት ጊዜ፥ ሕይወታቸውን ለማዳን ወደ ተራራዎች እንዲሸሹም የእስራኤልን ልጆች አስጠነቀቃቸው።
ክርስቶስ ይህንኑ ዕለት ማቴዎስ 24፡21-22 ውስጥ ሲገልጠው እንዲህ ብሏል፡- “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ያልሆነ፥ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። ክርስቶስ ታላቁን የመከራ ጊዜ ከሌሎቹ የመከራ ጊዜያት ሁሉ ጋር በማነጻጸር ነው የሚገልጠው። መከራው፥ ዓለም ከዚያ በፊት የተለማመደቻቸውን ነገሮች ሁሉ እስኪሸፍን ድረስ የገዘፈ ነው።
ይህ መከራ ሳያጥር (ቶሉ ባያበቃ) ኖሮ የሰው ዘር ምድር ላይ ባልተረፈ ነበር። አንዳንድ ሰዎች “ባያጥር” የሚለውን ቃል እንደተገነዘቡት፥ ወቅቱ ከአርባ ሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ መሆኑን ይህ አያመለክትም። ቃሉ የሚያስረዳው፥ የመከራው ጊዜ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ምክንያት ሳያጥር ኑሮ፥ ታላቁ መከራ የሰውን ዘር ሁሉ ያጠፋ የነበረ መሆኑን ነው። “ስለተመረጡት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው፥ የዳኑ እስራኤላውያንን ወይም የዳኑ አሕዛብን ወይም ሁለቱንም ነው። የክርስቶስ መመለስ ዓላማ በዓለም ለመፍረድ ሲሆን፥ በስሙ ያመኑትን ግን ከክፉ ሁሉ ይሰውራቸዋል።
ጌታችን ስለ መከራው ጊዜ አንዳንድ ባሕርያት ቀጥሎ ባሉት ቁጥሮች ገልጧል። ያኔ ሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ ክርስቶሶች ይነሣሉ (ማቴ. 24፡23-24)። ክርስቶስ በምሥጢር መጥቷል የሚል ሐሰተኛ ወሬም ይኖራል (ቁ. 26)። ለዚህ ነው ያን ጊዜ ማንም እንዳይታለል ደቀ መዛሙርቱን ያስጠነቀቃቸው። ምክንያቱም የክርስቶስ ዳግም ምጽአት፥ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ ግልጥ ክንውን ይሆናል (ቁ. 27)። የፍዳው ጊዜ ሁኔታም “ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ” ተብሎ ቁጥር 29 ውስጥ ተገልጧል። ከዚህ በመቀጠል ነው የክርስቶስ ምጽአት የሚሆነው።
ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ታላቁ መከራ ላቀረቡለት ጥያቄ የሰጠው ገለጣ፥ ራእይ ምዕራፍ 6-18 ውስጥ በሰጠው ተጨማሪ መግለጫ ተረጋግጧል። ራእይ 5፡1 ውስጥ የተጠቀሰውና በሰባት ማኅተም የተዘጋው መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ውስጥ ተገልጧል።
እያንዳንዱ ማኅተም ሲፈታ፥ ታላቅ መቅሠፍት በምድር ላይ መውረድ ይጀምራል። የሚጀምረውም የዓለምን መንግሥት በሚገልጠው የመጀመሪያ ማኅተም ነው (ራእይ 6፡1-2)። ከዚያ ቀጥሎ ጦርነት (ቁ.3-4)፥ ረሃብ (ቁ.5-6)፥ የምድር አራተኛዋ እጅ ሕዝብ መሞት (ቁ.7-8) ይሆናሉ። አምስተኛው ማኅተም ያን ጊዜ የሚሞቱትን ሰማዕታት ይወክላል (ቁ.9-11)። የሚለጥቀው፥ በሰማያት ታላቅ ነውጥ መሆኑ፥ የፀሐይ መጥቆር፥ እንዲሁም የጨረቃ ደም መምሰል ነው (ቁ. 12-14)። ይህን የመሰለው አስደናቂ መለኮታዊ ኃይል በምድር መገለጡ፥ በክርስቶስ ባሳመኑ ሰዎች ላይ ፍርሃትን ይለቅባቸዋል። በመሆኑም ሰዎቹ ተራራዎችን በላያችን ውደቁ፥ “ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣ ቀን መጥቷልና”(ቁ. 15-17) ይላሉ።
ሰባተኛው ማኅተም ሲፈታ (8፡1)፥ ሰባት ተከታታይ ሁኔታዎች መለከት ከያዙ ሰባት መላእክት ጋር ይቀጥላል {8፡2-9፡21፤ 11፡15-19)። ከእነዚህ ታላላቅ ፍርዶች አብዛኛዎቹ ብዙ ሕይወት የሚጠፉባቸውና በተፈጥሯዊው ዓለም ላይ የሚወርዱ ናቸው። ፍርዶቹ የምድር አንድ ሦስተኛው ሰእሳት የሚጠፉበት፥ የውቅያኖሶች አንድ ሦስተኛ ወደ ደምነት የሚለወጥበትና ውስጡ ያሉ ፍጡራንም የሚያልቁሰት፥ እንዲሁም በዚሁ የባሕር ክፍል ላይ ከዋክብት ከሰማይ የሚወድቁባቸው ናቸው (8፡7-11)። አራተኛው መለከት ከዋክብትን ይመለከታል። የፀሐይ፥ የጨረቃና የከዋክብት አንድ ሦስተኛ ክፍል ይጨልማሉ። ከዚያ ቀጥሉ በተከታታይ በሚነፉት መለከቶች አማካይነት ስለሚደርሰው አሠቃቂ እልቂቶችም ትንቢት ተነግሯል።
አምስተኛው መለከት (9፡1-12)፥ የሚያመለክተው በክርስቶስ ያላመኑ ሰዎች ለአምስት ወራት በዲያብሎስ መሠቃየታቸውንና ሰዎቹ የገዛ ሕይወታቸውን እንኳ ሊያጠፉ አለመቻላቸውን ነው። ስድስተኛው መሰከት (9፡13-21)፥ የሚገልጠው የኤፍራጥስን ወንዝ አቋርጦ ከወደምሥራቅ ስለሚመጣው ታላቅ ሠራዊት ነው። በመከራው ዘመን ማብቂያ ላይ በሚደረገው ታላቅ ጦርነት ለመሳተፍ ነው ይህ ሠራዊት የሚመጣው። ሰባተኛው መለከት (11፡15)፥ በመከራው ዘመን ማብቂያ አካባቢ የሚነፋ ሲሆን፥ የክርስቶስን መምጣትና የመንግሥቱን በምድር ላይ መመሥረት ይጠቁማል።
ሰባተኛው መለከት በተከታታይና በፍጥነት የሚወርዱ ሌሎች ሰባት ፍርዶችንም ያመለክታል። እነዚህ ፍርዶች ራእይ 16 ውስጥ የእግዚአብሔር ቁጣ ጽዋዎች ተብለዋል። እነዚህ ከመለካት ፍርዶች ይልቅ እውዳሚዎች ሲሆኑ፥ ምድር ላይ የሚወርደውን የመጨረሻ የእግዚአብሔር ፍርድ ያካትታሉ። ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ቅድመ ዝግጅትም ናቸው።
ስድስተኛው ጽዋ አርማጌዶን ሰተባለው ስፍራ ከሚደረገው የእግዚአብሔር ጦርነት ቅድመ ዝግጅት ጋር ይዛመዳል። በራእይ 16፡14 መሠረት የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው ለውጊያ በስፍራው ይከማቻሉ። እነዚህን እርማጌዶን ላይ የሚከማቹ ሠራዊቶች የሚሰበስባቸውም ሰይጣን ይሆናል። ሠራዊቶቹ የሚዋጉት ለዓለም ሥልጣን ይመስላቸዋል፤ እውነቱ ግን ክርስቶስ ወደ ምድር በሚመለስበት ጊዜ የሚያጅበውን ሠራዊት ይቃወሙ ዘንድ በሰይጣን በራሱ የሚመሩ መሆናቸው ነው (ራእይ 19፡14)።
ራእይ 16፡17.21 ውስጥ ባለው ክፍል የተጠቀሰው የመጨረሻ ጽዋ፥ የዓለምን ታላላቅ ከተማዎች እንዳልነበሩ የሚያደርገውን፥ ባቢሎንን ለፍርድ የሚያበቃትን እንዲሁም ደሴቶችንና ተራራዎችን የሚያጠፋቸውን ታላቅ የምድር መናወጥ ያካትታል። በፍጻሜው፥ ክብደቱ እያንዳንዱ 51 ኪሎ ግራም የሚመዝን በረዶ ከሰማይ ሰመውረድ ምድር ላይ የቀረውን ሁሉ ያጠፋል። በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ወቅት ዓለም ነውጥ፥ ጥፋትና ጦርነት በአንድ ላይ ይረባረቡባታል።
ቀስ በቀስ በእግዚአብሔር ቃል ተሸንፈው ለክርስቶስ ታዛዦች ከመሆናቸው በፊት፥ ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሻሻል ላይ ናት ብለው ያስቡ የነበሩ የሥነ-መለኮት ምሁራን ሕልማቸው ምንኛ የተሳሳተ ነበር! መጽሐፍ ቅዱስ ዓለምን የሚጎልማት ኢ አማኒ በሆነ ገዥ እየተመራች አሰከፊ በሆነ ኃጢአትና በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ በደል ወደ ፍጻሜዋ የምታመራ መሆኗን ነው። የመጨረሻ መሪዋ እግዚአብሔርን የሚነቅፍና በእግዚአብሔር የሚያምኑትን ሁሉ የሚያሳድድ ይሆናል።
በጽድቅ የተሞላው የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ምድር የሚመጣው በሰብአዊ ጥረት ሳይሆን ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጋር ነው። ያኔ በዓለም ያሉ ኃጢአተኞች እጅግ ታሳቅ ፍርድ ይሰጣቸዋል፤ በነዚያ አሠቃቂ ጊዜያት እምነታቸውን በክርስቶስ ያደረጉ ደግሞ አስደናቂ ነጻነት ይሆንላቸዋል።
ይህ የፍዳ ጊዚ ለእግዚአብሔር ልጆች ሳይሆን፥ ለነቃፊዎችና ለማያምኑ የተዘጋጀ እስከፊ ወቅት ነው። ከዚህ የተነሣ ቤተ ክርስቲያን አሠቃቂው ጊዜ ከመጀመሩ በፊት ትነጠቃለች በማለት ብዙዎች ያምናሉ፤ ያስተምራሉም። ቤተ ክርስቲያን ከታላቁ መከራ ጋር በተያያዘና በጎላ ሁኔታ አልተወቀሰችም። ምንም እንኳን ጻድቃን ወይም ቅዱሳን ተብለው የተጠቀሱ ሰዎች ወደ ክርስቶስ የሚቀርቡ መሆኑ ቢገለጥ፥ እነዚህን ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚያዛምዳቸው በግልጥ የተጠቀሰ ነገር የለም። ስለ ሰዎቹ የሚታወቀው ነገር፥ በክርስቶስ የሚያምኑ አይሁዳውያንና አሕዛብ መሆናቸው ነው። ከነዚህ ብዙዎቹ ሰማዕታት ይሆናሉ፤ ከፍዳው ጊዚ የሚተርፉት ጥቂት ናቸው።
በአጠቃላይ እንግዲህ፥ የፍዳው ጊዜ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዋዜማ ሲሆን፥ በኃጢአተኞች ላይ ለመፍረድና ቅዱሳንንም ለመቤዠት መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ እንደነበር ያስገነዝባል። በፍዳው ጊዜ የሚኖረውን ጭለማም ቀጥሎ ከሚመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት ክብር ጋር ያነጻጽራል።
ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡