ኃጢአት፡- ባሕርዩና ሁሉን አቀፍነቱ

ሀ. ሰው ስለ ኃጢአት ያለው አስተሳሰብ። 

ኃጢአት በሰው ሕይወት ውስጥ ዋና እውነታና የመጽሐፍ ቅዱስ ታላቅ ጉዳይ በመሆኑ፥ የማያቋርጥ የውይይት ርዕስ ሆኖ ቆይቷል። መንፈሳዊ መገለጥን የማይቀበሉ ክፍሎች ስለ ኃጢአት በቂ ያልሆን ፅንሰ-አሳቦችን በመደጋገም ሰንዝረዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውና የተለመደው አመለካከት፥ ኃጢአት በዓለም መልካምና ክፉ አለ በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ላይ በመመሥረት የሚመጣ የተሳሳተ እምነት ነው ብለውታል። ይህ ፅንሰ-አሳብ የሕይወትን እውነታና፥ የኃጢአትን ክፉነት መመልከት ይሳነዋል። የመልካም ሥነ ምግባር አምላክና ሕግጋት መኖራቸውንም አይቀበልም። 

ኃጢአትን በተመለከተ ሌላውና ጥንታዊው አመለካከት፥ ኃጢአትን ከእግዚአብሔር ተጻራሪና ከቁሳዊው ዓለም ጋር የሚዛመድ አድርጎ የሚያየው ነው። ይህ በምሥራቃውያን ፍልስፍናና በግሪክ ኖስቲካዊነት ውስጥ የሚገኝ አመለካከት ነው። ይህ አመሰካካት በመናኝነት ትምህርት (Atheism/ኤቲይዝም) ራስን የመካድና ለሥጋ ፈቃድ እምቢ የማለት አስተሳሰብ መሠረትነው። ከዚያም ሌላ የትምህርቱ ታላቅ ትኩረት፥ ሥጋን ማስደሰት ነው ለሚሰው ሌላ አስተምህሮ (Epicurianism/ኤፒኪዩሪየኒዝም) መሠረት ሆኗል። ያም ሆነ ይህ የአመለካከቶቹ መሠረታዊ አሳብ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑንና ለሚሠራውም ኃጢአት በእግዚአብሔር ተጠያቂ መሆኑን መካድ ነው። ኃጢእት ራስ ወዳድነት ነው የሚል፥ የተለመደ ግን በቂ ያልሆነ አመለካከትም አለ። ኃጢአት ራስ ወዳድነት መሆን እርግጥ ሲሆንም፥ ይህ አመለካከት ሌሎችንም ሁኔታዎች የሚያጠቃልል አይደለም። 

ምክንያቱም ሰው አንዳንዴ በራሱም ላይ ኃጢአት ይሠራል። 

እነዚህ ሁሉ ፅንሰ-አሳቦች የኃጢአትን ምንነትና ሁለንተናዊነት አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን መገለጥ የማይቀበሉ እንዲሁም ደረጃቸውን ያልጠበቁ ናቸው። 

ለ. ስለ ኃጢአት መጽሐፍ ቅዱሳዊው አስተምህሮ 

በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት ኃጢአት በድርጊት፥ በሁኔታና በዝንባሌ ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር የማይመሳሰል አኗኗርን ነው የሚያመለክተው። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተለያዩ ኃጢአቶች ተገልጠዋል። ለምሳሌ ለእስራኤል በተሰጡት በአሥርቱ ትእዛዛት ተገልጧል (ዘፀ. 20፡3-17)። ኃጢአት ምንጊዜም ከእግዚአብሔር ማንነትና ከዘላለማዊ ቅድስና የተለየ ነገር ነው። ምንም እንኳን በሰዎች ላይ የሚፈጸም ቢሆን፥ ኃጢአት ምን ጊዜም የእግዚአብሔር ተፃራሪ ነው (መዝ. 51፡4፤ ሉቃስ 15፡18)። ስለዚህ ኃጢአትን የሚሠራ ሰው በድርጊቱ እንደ እግዚአብሔር አይደለም፤ ስለሆነም ከጌታ ፍርድ አያመልጥም። ስለ ኃጢአት የሚሰጠው አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእራት መንገዶች ቀርቧል። 

1. የግል ኃጢአት (ሮሜ 3፡23)፥ በዕለታዊ ሕይወት የሚደረግ፥ ከእግዚአብሔር ፈቃድና ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር የማይስማማን ማንኛውንም ድርጊት ያጠቃልላል። 

ሰዎች ብዙ ጊዜ የግል ኃጢአታቸውን ያውቃሉ። የግል ኃጢአቶች ደግሞ በዓይነታቸው የተለዩ ናቸው። በአጠቃላይ ሲታይ የግል ኃጢአት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተሰጠን የተለየ ትእዛዝ ካለማክበር ጋር ይዛመዳል። የዓመፅን ወይም ያለመታዘዝን ፅንሰ- አሳብ የሚያካትትም ነው። ምንም እንኳን ብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ ኃጢአት የተጠቀሱት ስምንት ያህል ቃላት፥ አዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ አሥራ ሁለት ያህል ቢሆኑ፥ መሠረታዊው ነገር በማድረግ ወይም ባለማድረግ ከእግዚአብሔር ባሕርይና ፈቃድ ያላመስማማት ጉዳይ ነው። የኃጢአት መሠረታዊ አሳብ፥ ሰው ከእግዚአብሔር ቅዱስ ባሕርይ አንጻር ሲታይ የተወሰነለትን ግብ አለመምታት፥ የተከለለለትን መሥመር መጣስ እና ከጌታ ቅድስና መጉደል ነው። 

2. ኃጢአታዊ ተፈጥሮ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው እንደ ኃጢአት ነው (ሮሜ 5፡19፤ ኤፌ. 2፡3)። የአዳም ኃጢአት ለውድቀት አብቅቶታል። በዚህም ሳቢያ ሰው ከእግዚአብሔር የተለየ፥ ጸጋው የተገፈፈና ኃጢአትን ለትውልዱ የሚያወርስ ሆነ። በመሆኑም ከአዳም የተወለዱ ሁሉ በአዳማዊ ተፈጥሮ ነው የተወሰዱት። የኃጢአት ዝንባሌ አላቸው። ምንም እንኳ ይህ ተፈጥሮ በክርስቶስ አማካይነት መስቀል ላይ የተፈረደበት ሲሆን (ሮሜ 6፡10)በማንኛውም ክርስቲያን ሕይወት የሚሠራ ኃይል ነው። ኃጢአት በአሁኑ ጊዜ ፍጹም ይወገዳል ወይም ይጠፋል አልተባለም። ክርስቲያን ግን ውስጡ በሚኖር መንፈስ ቅዱስ አማካይነት ኃጢአትን የማሸነፍ ኃይል አሰው (ሮሜ 8፡4፤ ገላ. 5፡16-17)። 

ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህን ጠቃሚ ጉዳይ ያነሡታል። ኤፌሶን 2፡3 ውስጥ ሰዎች፥ ጥፍጥረታቸው የቁጣ ልጆች” ተብለዋል። የሰው አጠቃላይ ተፈጥሮም ተበላሽቷል። አጠቃላይ መበላሸት ወይም መበከል የሚለው ፅንሰ-እሳብ ሰው ፍጹም ክፉ ነው ማለት ሳይሆን፥ በተፈጥሮው በኃጢአት ተበክሏል (ሮሜ 1፡8-3፡20) ማለት ነው። በመሆኑም የሰው ፈቃዱ (ሮሜ 1፡28)፥ ሕሊናው (1ኛ ጢሞ. 4፡2) እና አእምሮው (ሮሜ 1፡28፤ 2ኛ ቆሮ. 4:4)። ተበክሏል፤ ልቦናው ታውሯል (ኤፌ. 4፡18)። 

ባለፈው ጥናታችን እንደተመለከትነው፥ ሰዎች ኃጢአታዊ ተፈጥሮ የኖራቸው ከወላጆቻቸው ስለወረሱት ነው። በዓለም ከተወለዱት ሕፃናት ማንም ቢሆን ልዩ ከሆነው የኢየሱስ ማዳን ካልሆነ በቀር ከዚህ ኃጢአታዊ ተፈጥሮ ነጻ አይደለም። ሰዎች ኃጢአተኛ የሚሆኑት ኃጢአት በመሥራታቸው አይደለም፤ በኃጢአታዊ ተፈጥሯቸው ሳቢያ ኃጢአት ይሠራሉ እንጂ። ለዚህና ለግል ኃጢአት ፈውሱ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተሰጠው ድነት ነው። 

3. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጠው ኃጢአት በተፈጥሯችን የሚተላለፍ ነው (ሮሜ 5፡12-18)። ከሰው በኃጢአት መውደቅ ጋር ተያይዞ ባለው ምዕራፍ እንደተገለጠው፥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰው በራሱ ኃይል የማያገኛቸው ግን የሚተላላፉ ሦስት ነገሮች አሉ፡- (ሀ) ኃጢአትን የተመለከተው አስተምህሮ የተመሠረተበትና ከአዳም ወደ ትውልዶቹ በውርስ የተላለፈው፥ (ላ) የሰው ኃጢአት ወደ ክርስቶስ የተላለፈበትና የድነት ትምህርት የተመሠረተበት (ሐ) የእግዚአብሔር ጸጋ በክርስቶስ ወደአመኑት የተላለፈበትና የጽድቅ ትምህርት የተመሠረተበት። 

ይህ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፈው ሀ. በውርስ ወይም ለ. በሕግ ሊሆን ይችላል። የውርስ የሚሆነው፥ አንድ ሰው ከቀደሙት አባቶቹ የሚተላለፍለት መሆኑን ሲገነዘብ ነው። ሆኖም ከክርስቶስ የማስታረቅ ሥራ የተነሣ እግዚአብሔር አሁን ሰውን የውርስ ኃጢአት ባለ ዕዳ አያደርገውም (2ኛ ቆሮ. 5፡19)። 

ሕግን ካለመፈጸም የሚመጣ የኃጢአት መተላለፍ በውርስ ከሚመጣው ይለያል (ፊሊሞና 18)። ከአዳም ለዘሮቹ የተሳለፈው ኃጢአት የውርስ ነው ወይስ የሕግ መተላለፍ ለሚለው ጥያቄ በሚሰጠው መልስ አለመግባባት ቢኖርም፥ ሮሜ 5፡12 ውስጥ የተጠቀሰው ቃል በግልጥ እንደሚያስረዳው የተላለፈው በውርስ ነው። የሁሉ አባት የሆነው አዳም ኃጢአት በሠራ ጊዜ፥ ትውልዱ ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋል። 

ቀጥሎ ያሉት ሁለት ጥቅሶች (ሮሜ 5፡13-14) የተጻፉት፥ ይህ ዓይነቱ ኃጢአት የግል አለመሆኑን ለማመልከት ነበር (ዕብ. 7፡9-10ን ይመልከቱ))። ይሁን እንጂ ሮሜ 5፡17-18 እንደሚያመለክተው፥ ማለት በአንድ ሰው ኃጢአት ፍርድ በሰዎች ሁሉ ላይ መጣ፥ ስለሚል የውርስ ኃጢአት የሕግ መተላለፍም ነው። አጠያያቂ የሚሆነው፥ የመጀመሪያው የአዳም ኃጢአት ብቻ ነው። ለአዳምም ሆነ በቀጥታ ለሚተላለፍላቸው ዘሮቹ ውጤቱ ሞት ነው። ለተላሳፊ ወይም ለውርስ ኃጢአት የተለገሰ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ስጦታ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት ነው። 

4. የኃጢአት መተላለፍ በሰው ዘር ሁሉ ላይ ያመጣው ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጧል። ዓለም ሁሉ፥ አይሁድና ሌሎች ሕዝቦችንም ጨምሮ፥ በእግዚአብሔር ፊት “ከኃጢአት በታች” ናቸው (ሮሜ 3፡9፤ 11፡32፤ ገላ. 3፡22)። “ከኃጢአት በታች” መሆን ማላት፥ በመለኮት እይታ ከድነት ጸጋ ውጭ መሆን ማለት ነው። ድነት በጸጋ ብቻ የሚገኝ እና በሰዎች መልካም ሥራ የማይደገፍ መሆኑን ስለሚገልጥ፥ እግዚአብሔር ሁሉንም (“ከኃጢአት በታች ወይም ጸጋ የጎደላቸው ብሏቸዋል። ይህ ከኃጢአት በታች የመሆን ፍርድ ፈውስ የሚያገኘው፥ ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ ሥራ አማካይነት በምሕረቱ ባለ ጸጋ በሆነው እግዚአብሔር ፊት ሲቆም ነው። 

በአጠቃላይ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያመለክተው፥ ኃጢአት በሰው ላይ የሚያመጣውን እሠቃቂ ውጤትና፥ ሰው የራሱን የኃጢአት ችግር ለማስወገድ ተስፋ የሌለው መሆኑን ነው። በመሆኑም የኃጢአትን ትክክለኛ ትምህርት መረዳቱ እግዚአብሔር ለኃጢአት የሰጠውን መፍትሔ ለመረዳት መሠረታዊ ነገር ነው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: