እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡- በሰው ውስጥ ማደሩና ማተሙ

ሀ. የአሁኑ ዘመን አዲስ ገጽታው 

በብሉይ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ከሰዎች ጋር የኖረና የአዲስ ሕይወታቸው ምንጭ፥ የመንፈሳዊ ድላቸው መገኛ የነበረ ቢሆንም፥ የዚያን ጊዜ አማኞች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ያደረ መሆኑን የሚገልጥ ማረጋገጫ የለም። ይህን አስተምህሮ በተመለከተ ብሉይ ኪዳን የሚጠቅሰው ነገር የለም። ኢየሱስ ክርስቶስም በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረውን ሁኔታ ሰአሁኑ ዘመን ካለው ጋር በማነጻጸር የተለያ ትምህርቱን ሲጠቅስ “ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችሁም ስለሚሆን” ብሏል (ዮሐ. 14፡17)። መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ የማደሩ ጉዳይ የዚህ ዘመን ልዩ ገጽታ ሲሆን፥ በሺህ ዓመት መንግሥት ዘመንም የሚሆን ነው። በሌላ በማንኛውም ጊዜ አይገኝም። 

ለ. የመንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሁሉ ውስጥ ማደር 

ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ኃይልና የመንፈስን ፍሬ በማፍራት ረገድ በጣም የሚለያዩ ቢሆንም፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያድርሰት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። መንፈስ ቅዱስ በሰው ውስጥ ሳያድር የመዘግየቱ ሁኔታ ምሳሌ ሐዋርያት ሥራ ውስጥ ታይቷል (8፡14-17፤ 19፡1-6)። እነዚህ ሁኔታዎች ችካካል ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሽግግር ባሕርይ የተነሣ የተፈጠሩ ናቸው። መንፈስ ቅዱስ ሰዎች ውስጥ የማደሩ እውነት፥ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን የሚቀበል ሰው ጥያቄ በማይሆንበት ሁኔታ በብዙ ስፍራ ተጠቅሷል (ዮሐ. 7፡37-39፤ ሐዋ. 11፡17፤ ሮሜ 5፡5፤ 8፡9፥ 11፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡12፤ 6፡19-20፤ 12፡13፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡5፤ ገላ. 3፡2፤ 4፡6፤ 1ኛ ዮሐ. 3፡24፤ 4፡13)። እነዚህ ጥቅሶች ከጳንጤቆስጤ ዕለት በፊት፥ ማለት በብሉይ ኪዳን አሠራር፥ መንፈስ ቅዱስ በጥቂት ሰዎች ብቻ ያድር የነበረ መሆኑን በግልጥ ያስረዳሉ። ከጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ግን ትክክለኛው የመንፈስ ቅዱስ አሠራር በአማኝ ውስጥ ማደር ነው። 

መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ሁሉ የሚያድር መሆኑ ሮሜ 8፡9 ውስጥ የከርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለምን” ሰሚለው ቃል ተደግፏል። በተመሳሳይ ሁኔታ ይሁዳ 19 ውስጥ እንደተገለጠው፥ የማያምኑ ሰዎች (“መንፈስ የሌላቸው” ተብለዋል። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ የሚኖሩና በቁጣው ሥር ያሉ (የሚቀጡ) ክርስቲያኖች እንኳ አካላቸው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19 ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ ሥጋዊ የሆኑ የቆሮንቶስ ሰዎች አካላቸው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለሆነ፥ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ኃጢአት እንዳይፈጽሙ አስጠንቅቋቸዋል። 

መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነም በተደጋጋሚ ተገልጿል። የስጦታ መሠረታዊ እውነት ከተቀባዩ ምንም አጻፋ አለመፈለጉ ነው (ዮሐ. 7፡37-39፤ ሐዋ, 11፡17፤ ሮሜ 5፡5፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡12፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡5)። በተመሳሳይ ሁኔታ ከጌታ ጋር ለመጓዝ የሚሹ ክርስቲያኖች ለሚጠበቅባቸው የሕይወት ከፍተኛው ደረጃ፥ አስፈላጊውን መለኮታዊ ችሉታ ይሰጣቸው ዘንድ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ማደሩ ተገቢ ነው። ካህናትና ነገሥታት ተቀብተው ለተቀደሰ ሥራ እንደሚለዩ፥ ክርስቲያንም ድነቱን በሚቀበል ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ይቀባና በውስጡ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ፊት ከክርስቶስ ጋር ለሚኖረው አዲስ ሕይወት ይለያል (2ኛ ቆሮ. 1፡21፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡20፥ 27)። መቀባት ድነትን በመቀበያ ጊዜ የሚከናወንና ለሁሉም አማኝ የሚሰጥ ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ውስጥ የማደሩ እውነት ከሚያሳየው አስተምህሮም ጋር ይመሳሰላል። አንድ አማኝ ከዳነ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ይቀባል፥ ይህም የጸጋ ሁለተኛ ክፍል ነው፥ ወይም ከመንፈስ ቅዱስ ሙላት በኋላ ብቻ የሚከናወን ነው የሚለው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። 

ሐ. መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ውስጥ ስለ ማደሩ በሚሰጠው አስተምህሮ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች 

መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ የማደሩ እውነት፥ ከአንዳንድ አከራካሪ ጥቅሶች የተነሣ አጠያያቂ ይሆናል። በብሉይ ኪዳንና በወንጌል ውስጥ ባሉ ሦስት ጥቅሶች (1ኛ ሳሙ. 16፡14፤ መዝ. 51፡11፤ ሉቃስ 11፡13) መሠረትነት አንዳንድ ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው በአንዳንድ ሁኔታዎች የእግዚአብሔርን መንፈስ ያጣል ብለው አምነዋል። ዳዊት በሳዖል እንደተደረገበት ሁሉ (1ኛ ሳሙ. 16፡14) ከእርሱም የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳይወሰድበት የጸለየው ጸሎት (መዝ. 51፡11)፥ በብሉይ ኪዳን እሠራር ላይ የተመሠረተ ነው። በዚያ ወቅት መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ውስጥ ማደሩ የተለመደ አልነበረም። በመሆኑም በጌታ ሉዓላዊነት የተሰጠ መንፈስ በዚሁ ሉዓላዊነት ሊወሰድ ይችል ነበር። 

ሐዋርያት ሥራ ውስጥ ያሉ ሦስት ጥቅሶችም መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ሰው ማደሩን አስመልክቶ የሚከሰትን አንድ ችግር የሚጠቁሙ ይመስላሉ። (1) ሐዋርያት ሥራ 5፡32 ውስጥ መንፈስ ቅዱስ “እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው” ተብሏል። እዚህ ላይ መታዘዝ የተባለው ለወንጌል መታዘዝ ነው፥ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመለከተው በከፊል በማይታዘዙት እንኳን መንፈስ ቅዱስ ያድርባቸዋል። (2) ሰማርያ ውስጥ ፊሊጶስ ወንጌል የሰበከላቸው ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ሳይቀበሉ የመዘግየታቸው ምክንያት፥ ይህን አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ኢየሩሳሌም ከነበሩ ሐዋርያት ተግባር ጋር ለማያያዝ ታስቦ ነበር። ለዚህ ነበር ሐዋርያቱ መጥተው እጃቸውን እስኪጭኑባቸው ድረስ ሰዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ያልተሞሉት (ሐዋ. 8፡17)። ይህ ከቆርነሌዎስ መዳን ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በተለመደው መንገድ የሆነ አልነበረም። እርሱ መንፈስ ቅዱስን የተቀበለው እጅ ሳይጫንበት ነው። (3) ሐዋርያት ሥራ 19፡1-6 ውስጥ የተወቀሰው ሁኔታ በመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት እንጂ፥ ፈጽሞ በኢየሱስ ያሳመኑትን ሰዎች የሚመለከት ነው የሚመስለው። ሰዎቹ ጳውሎስ እጅ በጫነባቸው ጊዜ ነው መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት። 

ይህ ሁኔታም ያልተለመደና ከዚያ ወዲህ ያልተደገመ ነው። 1ኛ ዮሐንስ 2:20 ውስጥ ቅዱሱ ቅባት” የተባለውና 1ኛ ዮሐንስ 2፡27 ውስጥ የተጠቀሰው ቃል በትክክል ከተተረጎመ። መንፈስ ቅዱስ አማኙ ውስጥ መጀመሪያ ከማደሩ ጋር እንጂ፥ በኋላ ከሚሆን የመንፈስ ቅዱስ አሠራርጋር የሚዛመድ አይደለም። 

አዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰው ማንኛውም የመንፈስ ቅዱስ መቀባት፥ ከጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላም ሆነ በፊት፥ ሰው በጌታ እንዳመነ የሚሆን የመጀመሪያ ጊዜ ክንውን ነው (ሉቃስ 4፡18፤ ሐዋ. 4፡27፤ 10፡38፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡21፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡20፡27)። ስለዚህ ይህን አስተምህሮ የተመለከቱ ችግሮች የሚወገዱት። ችግሮቹ የሚነሡባቸውን ጥቅሶች በጥንቃቄ በማጥናት ነው። 

መ. የመንፈስ ቅዱስ ሰሰው ውስጥ ማደር ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር ሲነጻጸር 

አንድ አማኝ አዲስ ልደት በሚያገኝበት ወቅት አንዳንድ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ወዲያውኑ በሕይወቱ ስለሚከናወኑ፥ እነዚህን የተለያዩ ክንውኖች በጥንቃቄ መለየት ይገባል። ሁለቱም በአንድ ጊዜ የሚከናወኑ ቢሆኑም፥ የመንፈስ ቅዱስ በአማኙ ውስጥ ማደርና በመንፈስ ቅዱስ ዳግም መወለድ አንድ አይደሉም። በተመሳሳይ ሁኔታ ዳግም ልደትና የመንፈስ ቅዱስ በአማኙ ውስጥ ማደር በመንፈስ ቅዱስ ከመጠመቅ ጋር አንድ አይደሉም። በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቁ ጉዳይ ወደፊት የምንገልጠው ይሆናል። የመንፈስ ቅዱስ በሰው ውስጥ ማደር በመንፈስ ቅዱስ ከመሞላት ይለያል። ይህም ልዩነት ክርስቲያኖች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ሊያድርባቸው ሲችል፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚሞሉት ሁሉም አለመሆናቸው ነው። የመንፈስ ቅዱስ በአንድ ሰው ውስጥ ማደር ለአንዴና ለዘላለም የሚከናወን ሲሆን፥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ግን ብዙ ጊዜ በክርስቲያን ልምምድ የሚፈጸም ነው። የመንፈስ ቅዱስ በአንድ ሰው ማደር ግን፥ በመንፈስ ቅዱስ ከመቀባትና ከመታተም ጋር ተመሳሳይ ነው። 

የመንፈስ ቅዱስ በሰው ውስጥ ማደር ወይም መቀባት የዚህ ዘመን ክንውን ነው (ዮሐ. 14፡17፤ ሮሜ 7፡6፤ 8፡9፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡19-20፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡21፤ 3፡6፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡20፥27)። መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ከማደሩ የተነሣ አማኝ ይቀደሳል፥ ወይም ለእግዚአብሔር ይለያል። በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረው የቅባት ዘይት በአሁኑ ዘመን ያለው በመንፈስ ቅዱስ የመቀባት ምሳሌ ነው። ዘይት ከሰባቱ የመንፈስ ምሳሌዎች አንዱ ነው። 

1. በዘይት የተቀባ ነገር ሁሉ ወዲያውኑ የተቀደሰ ይሆናል (ዘፀ. 40፡9-15)። በተመሳሳይ ሁኔታ በዚህ ዘመንም መንፈስ ቅዱስ ሰውን ይቀድሳል (ሮሜ 15፡16፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡11፤ 2ኛ ተሰ. 2:13፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡2)። 

2. ነቢዩ በዘይት ተቀድሶ ነበር (1ኛ ነገ, 9፡16)። እንዲሁም ክርስቶስ በመንፈስ ነቢይ ነው (ኢሳ. 61፡1፤ ሉቃስ 4፡18)። አማኝም በመንፈስ ምስክር ነው(ሐዋ. 1፡8)። 

3. ካህን በዘይት ይቀደስ ነበር(ዘፀ. 40፡15)፤ ክርስቶስም እንዲሁ በመሥዋዕቱ በመንፈስ ተቀድሷል (ዕብ. 9፡14)። እማኝም በመንፈስ ይቀደሳል (ሮሜ 8፡26፤ 12፡1፤ ኤፌ. 5፡18-20)። 

4. ንጉሡ ዘይት ተቀድሷል (1ኛ ሳሙ. 16፡12-13)። ክርስቶስም እንዲሁ በመንፈስ (መዝ. 45፡7) እና አማኝም በመንፈስ ይነግሣል። 

5. በዘይት መቀባት ለፈውስ ነበር (ሉቃስ 10፡34)፤ ይህም በመንፈስ ቅዱስ በሚገኝ ድነት አማካይነት የነፍስ ፈውስ የሚገኝ መሆኑን ያመለክታል። 

6. ዘይቱ ፊት እንዲያበራ ያደርጋል፤ እንደ ደስታ ዘይት ነው (መዝ. 45፡7)፤ ለዚህም ንጹሕ ዘይት አስፈልጓል (መዝ. 92 ፡10)። የመንፈስ ፍሬ ደስታ ነው (ገላ. 5፡22)። 

7. ሰማደሪያው ድንኳን የሚያስፈልጉ ነገሮች ሲዘረዘሩ ለመቅረዙ ዘይት የሚያስፈልግ መሆኑ በግልጥ ተጠቅሷል (ዘፀ. 25፡6)። ዘይት መንፈስ ቅዱስን፥ የዘይት ክር ደግሞ አማኝን በማስተላለፈያነት ሲገልጡ፥ ከዘይት የሚገኝ ብርሃን ደግሞ የክርስቶስን ብሩህነት ያመለክታል። በሚገባ ይሰራ ዘንድ ክሩ ዘይቱ ውስጥ መግባት ይኖርበታል፤ አማኝም በመንፈስ መመላለስ አለበት (ገላ. 5፡16)። ክሩ ወደ ዘይቱ ዘልቆ እንዳይገባ ከሚያሰናክለው ከማንኛውም ዓይነት ነገር ነጻ መሆን እንዳለበት ሁሉ አማኝም መንፈስ ቅዱስን መቃወም የለበትም (1ኛ ተሰ. 5፡19)። ክሩ መስተካከል እንዳለበት ሁሉ አማኝም ከኃጢአት ራሱን በንሰሐ ማንጻት አለበት (1ኛ ዮሐ. 1፡19)። 

የተቀደሰው የቅባት ዘይት (ዘፀ. 30፡22-25) ራሱ የሚቀመመው ከአራት የተለያዩ መሠረታዊ ቅመሞች ነበር። እነሱም በክርስቶስ ብቻ የሚገኙትን ባሕርያት ያመለክታሉ። የቅመሞቹ ውህደት የሚያመለክተው፥ መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስን እውነተኛ ሕይወትና ባሕርይ ወስዶ በአማኝ ሕይወት የሚያውለው መሆኑ ነው። 

ሰማደሪያው ድንኳን ውስጥ የሚቀመጥ ዕቃ ሁሉ መቀባትና ለእግዚአብሔር መታየት ነበረበት። ይህ የሚያመለክተው የአንድ አማኝ ለእግዚአብሔር መሰጠት ፍጹም መሆን ያለበት መሆኑን ነው (ሮሜ 12፡1-2)። 

ሠ. በመንፈስ ቅዱስ መታተም 

የመንፈስ ቅዱስ በአማኝ ውስጥ ማደር፥ በአዲስ ኪዳን ሦስት ክፍሎች ውስጥ እንደ እግዚአብሔር ማኅተም ተመስሏል (2ኛ ቆሮ. 1፡22፤ ኤፌ. 1፡13፤ 4፡30)። በምንም ዓይነት መንገድ ብናየው በመንፈስ ቅዱስ የማተሙ ተግባር የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ማንኛውም ክርስቲያን የታተመ ስለሆነ፥ በመንፈስ ቅዱስ መታተምን እንዲሻ ሊነገረው አያሻም። ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ የማተም ሥራ በድነት ጊዜ የሚከናወን ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ በእማኝ ሁሉ ውስጥ እንደሚያድር በመንፈስ መታተምም በሁሉም ዘንድ የሚከናወን ነው። 

የኤፌሶን ክርስቲያኖች “ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ” (ኤፌ. 4፡30) ተብለዋል። ኃጢአት ቢሠሩና መንፈስ ቅዱስን ቢያሳዝኑ እንኳን፥ እስከ ቤዛ ቀን ማለት እስከ ትንሣኤው ወይም እስከ መገለጥ ድረስ የታተሙ ናቸው። ያኔ አዲስ አካል ስለሚሰጣቸው ፈጽሞ ኃጢአት አይሠሩም። 

ልክ መንፈስ ቅዱስ በአማኙ እንደሚያድር ሁሉ፥ መታተምም በእምነት ከእግዚአብሔር የሚገኝ እንጂ፥ ልምምድ አይደለም። በመንፈስ ቅዱስ መታተም አስደናቂ የክርስቲያን ድነት ዋነኛ ክፍል ነው። በመሆኑም አማኙ ድነትና ዋስትና ያለው፥ እንዲሁም የእግዚአብሔር መሆኑን ያመለክታል። ይህም ሙሉ ለሙሉ ለጌታ እንዲሆን የሚያስፈልገው ዋጋ ሁሉ መካፈሉን ያመለክታል። ስለሆነም ክርስቲያን እካሉ በክብር እስከሚለወጥበትና እስከ ቤዛ ቀን ድረስ ታትሟል። ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው መንፈስ ቅዱስ እንደ ማኅተማችን ሆኖ በውስጣችን ማደሩ፥ ይህን ታላቅ እውነት ለሚረዳ ክርስቲያን ልብ ዋስትኖን እና መጽናናትን ያመጣል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: