እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡- የዳግም ልደት ሥራ

የክርስትና እምነት ሕይወት ከዳግም ልደት የሚጀምር ስለሆነ፥ ከድኅነት ጋር በተዛመደ መልኩ ሲታይ ዳግም ልደት መሠረታዊ ከሆኑት አስተምህሮዎች አንዱ ነው። ስለዚህ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ተገቢ መረዳትና ከአጠቃላዩ የክርስትና ሕይወት ጋር ያለውን ድንቅ ግንኙነት መገንዘቡ፥ ውጤት ላለው የወንጌል ሥራና ለመንፈሳዊ ብስለት ጠቃሚ ነው። 

ሀ. የዳግም ልደት ትርጉም 

“ዳግም ልደት” የሚለው ቃል ጽንሰ አሳብ አዲስ ሕይወት፥ አዲስ ልደት፥ መንፈሳዊ ትንሣኤ፥ አዲስ ፍጡር፥ ባጠቃላይ አማኞች እንደ እግዚአብሔር ልጅነታቸው የሚያገኙትን ከሁሉ የላቀ ወይም ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ሕይወትን ለመግለጫነት በሥነ-መለኮት ሰዎች የተመረጠ ነው። ይህ ቃል በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ብዙ ጊዜ ትክክለኛ ትርጉሙን አላገኘም። ትክክለኛ ግንዛቤ ቢያገኝ ግን ትርጉሙ እንድ ሰው በክርስቶስ ባመነ ጊዜ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ ማለት በቅጽበት ከመንፈሳዊ ሞት ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ተሸጋገረ ማለት ነው። 

ለ. በመንፈስ ቅዱስ ዳግም መወለድ 

ዳግም ልደት ከመሠረቱ የእግዚአብሔር ሥራ የመሆኑ እውነት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታ ላይ ተጠቅሷል (ዮሐ. 1፡13፤ 3፡3-7፤ 5፡21፤ ሮሜ 6፡13፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡17፤ ኤፌ. 2፡5፥ 10፤ 4፡24፤ ቲቶ 3፡5፤ ያዕ. 1፡18፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡9)። በዮሐንስ 1፡13 መሠረት ዳግም ልደት ያገኘ ሰው፥ ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።”። ዳግም ልደት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታ ላይ ከመንፈሳዊ ትንሣኤ ጋር ተነጻጽሯል (ዮሐ. 5፡21፤ ሮሜ 6፡13፤ ኤፌ. 2፡5)። የእግዚአብሔር የመፍጠር ሥራም ስለሆነ ከተፈጥሮ ጋር ተነጻጽሯል (2ኛ ቆሮ. 5፡17፤ ኤፌ. 2፡10፤ 4፡24)። 

ለአማኝ ዳግም ልደትን በመስጠቱ ተግባር ሦስቱም የሥላሴ አካላት ይሳተፋሉ። ያዕቆብ 1፡17-18 ውስጥ አብ ከዳግም ልደት ተግባር ጋር ተዛምዷል። ኢየሱስም በዚህ ተግባር መሣተፉ በተደጋጋሚ ተገልጧል (ዮሐ. 5፡21፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡18፤ 1ኛ ዮሐ. 5፡12)። ይሁን እንጂ ሦስቱም አካላት የተሣተፉባቸው ሌሎች የእግዚአብሔር ሥራዎች ቢኖሩም፥ በዮሐንስ 3፡3-7 እና ቲቶ 3፡5 ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እንደ ዳግም ልደት ሰጭ ሆኖ ተገልጧል። መንፈስ ቅዱስ በዳግም ልደት ውስጥ ባለው ተግባር መሠረት በክርስቶስ መጸነስ ሁኔታ ተሳትፏል። በክርስቶስ ልደት እግዚአብሔር አብ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሲሆን፥ የወልድ ሕይወት በክርስቶስ ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ ተፀነሠ። 

ሐ. በዳግም ልደት የተገኘ የዘላለም ሕይወት 

የዳግም ልደት ዋና አሳብ፥ በመንፈስ ሞቶ የነበረ አማኝ አሁን የዘላለም ሕይወት ማግኘቱ ነው። ይህን አሳብ ለማገናዘብ ሦስት መግለጫዎች ተጠቅሰዋል። አንዱ ዳግም የመወለድ አሳብ ነው። ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ “ዳግም ልትወለድ ይገባል” ወይም አንዳንዴ እንደሚተረጎመው “ከላይ ልትወሰድ ይገባል” ብሎታል። ዮሐንስ 1፡13 ውስጥ እንደተጠቀሰው ዳግም ልደት ከሰብዓዊ ልደት ጋር በመነጻጸር ተገልጧል። ሁለተኛውና መንፈሳዊ ትንሣኤን የሚመለከተው እሳብ፥ በክርስቶስ ያመነ ሰው ከሙታን ተለይቶ በሕይወት እንደሚኖር…” (ሮሜ 6፡13) ያስረዳል። ኤፌሶን 2፡5 ውስጥ በበደላችን ሙታን እንኳን በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን” ይላል። ቀጥታ አባባሉ “ከክርስቶስ ጋር ሕያው አደረገን” ማለት ነው። ሦስተኛው አሳብ አዲስ ፍጥረትን የሚያመለክት ሲሆን፥ አማኞች “ለእውነትም በሚሆን ጽድቅና ቅድስና በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” (ኤፌ. 4፡24) ተብለዋል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17 ውስጥ አሳቡ ይበልጥ ግልጥ ተደርጓል። “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፥ አሮጌው ነገር አልፎአል፥ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል”። ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ምሳሌዎች በክርስቶስ በማመን ስለሚገኘው አዲስ ሕይወት ነው የሚናገሩት። 

ከአዲስ ልደት፥ ከመንፈሳዊ ትንሣኤና መፈጠር ሁኔታ በግልጥ የምንረዳው ነገር፥ ዳግም መወሰድ በማንኛውም ሰው መልካም ሥራ የማይገኝ መሆኑን ነው። የሰው በጎ ፈቃድ ሥራ ወይም የማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አይደለም። ማለትም እንደ ጥምቀት የመሳሰሉ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች ውጤትም አይደለም። ሙሉ ለሙሉ እግዚአብሔር ለሰው እምነት የሚመልሰው ፍጹም መለኮታዊ አጸፋ ነው። 

በመሆኑም ዳግም ልደት ቀጥሎ ካሉት ልምምዶች ሊለይ ይገባል። ዳግም ልደት ቅጽበታዊ ክንውንና ከድኅነት የማይለይ ነው። በትክክለኛው መንገድ ድኅነትን ያገኘ ሰው ተከታታይ መንፈሳዊ ልምምድ ይኖረዋል። ይህ ልምምድ ግን የዳግም ልደት ማረጋገጫ እንጂ ራሱ ዳግም ልደት አይደለም። ለነገሩ አዲሱን ልደት በመለማመድ ላይ ነን በማለት ለመናገር እንችላለን፤ የዚህ አባባላችን ትክክለኛ ትርጉም ግን የአዲስ ልደትን ውጤቶች በመለማመድ ላይ መሆናችንን ነው የሚያመላክተው። 

መ. የዳግም ልደት ውጤት 

ዳግም ልደት በብዙ ሁኔታው ድኅነታችን የተገነባበት መሠረት ነው። በክርስቶስ የሆነ አዲስ ሕይወት ካልተገኘ፥ መንፈስ ቅዱስን፥ ጽድቅን ወይም ሌሎች ተከታታይ ውጤቶችን የማግኛ መንገድ የለም። በዳግም ልደት ወዲያውኑ እውን የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች ግን አሉ። 

አንድ እማኝ ክርስቶስን በእምነት ሲቀበል፥ አዲስ ልደትን ያገኛል፤ በዚያም አማካይነት አዲስ ፍጡር ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እዲሱ ሰው” (ኤፌ. 4:24) የሚለው ይህን ነው። አዲሱ ሰው፥ ለአዲሱ እኛነታችን ይጠቅመን ዘንድ “እንድንለብሰው> የተነገረን ነው። በክርስቶስ የሚያምን እንድ እማኝ ከሚኖረው አዲስ ባሕርይ የተነሣ ድንቅ የሆነ ለውጥ በሕይወቱ ይሆናል። ይህን ለውጥ ያገኘ አማኝ ስለ እግዚአብሔር ያለው እመለካካትና፥ ኃጢአትን ላለማድረግ ያለው ጽናት ከቀድሞው የተለየና የበረታ ነው። ዳግም የተወለደ ሰው አዲስ ተፈጥሮ በእግዚአብሔር ባሕርይ አምሳል የተለወጠ ሲሆን፥ ይህ ተፈጥሮ አዳም ከመውደቁ በፊት ከነበረው ተፈጥሮ ለየት ያለ ነው። አዲሱ ተፈጥሮ መለኮታዊ ባሕርይ ዕላላው የእግዚአብሔር የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ይሻል። ያለመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የራሱን ፍላጎት ለመፈጸም ኃይል ባይኖረውም፥ ለሕይወት እዲስ አቅጣጫን፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ደግሞ አዲስ ምኞትን ይሰጣል። 

ዳግም ልደት የሂደት ልምምድ ሳይሆን ቅጽበታዊ ነው። ቢሆንም ዳግም የተወለደ ሰው የሚቀበለው አዲስ ሕይወት አንዳንድ ልምምድን ለመለማመድ የሚረዳ ብርታትን ይሰጠዋል። አዲሱ አማኝ ቀድሞ ዐይነ ሥውር ነበር። አሁን ግን ያያል። ቀድሞ ሙት ነበር፥ አሁን ግን ለመንፈሳዊ ነገሮች ሕያው ነው። ቀድሞ ከእግዚአብሔር የተለየና አንድነት የሌለው ነበር። አሁን ግን የአንድነት መሠረት ስላለው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ያገኛል። አማኝ ራሱን ለጌታ በሰጠ መጠን የጌታን ድንቅ ስጦታዎች ይላማመዳል። ይህ ልምምድ ጌታ በአንድ ራሱን የሰጠ ሰው ሕይወት የሚያደርገው ድንቅና ሉዓላዊ ሥራ መግለጫ ነው። 

የዘላለም ሕይወት የማግኘቱ ሌላ ጠቃሚ ነገር፥ የዘላለም ዋስትና መሠረትነቱ ነው። አንዳንዶች፥ ሰው ከእምነቱ ቢያፈነግጥ ድኅነቱንና የዘላለም ሕይወትን ያጣል ብለው ቢያስተምሩም፥ የዘላለም ሕይወትና የአዲስ ልደት ባሕርይ ራሱ ይህን የእግዚአብሔርን ሥራ የመሻር ሁኔታ ይከለክላል። ድኅነት በመጀመሪያ የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ ነው፤ በሰው ሥራ ብቁዕነት የሚገኝም አይደለም። እምነት አስፈላጊ ቢሆንም ድኅነት የሚያስገኝ መልካም ሥራ ሆኖ ሊቆጠር አይገባም። እምነት እግዚአብሔር በአማኙ ሕይወት እንዲሠራ በር ይከፍታል። ተፈጥሯዊ ልደት ወደነበረበት እንደማይመለስ፥ መንፈሳዊ ልደትም እንዲሁ ነው። አንዴ ከተከናወነ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ሰማያዊ አባቱ እንደሆነ ለአማኙ ያረጋግጥለታል። 

የትንሣኤ ክንውን ወደነበረበት አይመለስም። በተመሳሳይ ሁኔታም በእግዚአብሔር አሠራር ወደ አዲስ ሕይወት ስለተሸጋገርን ይህን ሕይወት መቀየር አይቻልም። አዲስ ልደት ልክ እንደ ፍጥረት አሠራር አንዴ ከተከናወነ ለዘላለም የሚቀጥል መሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ነው። ሰው ከተፈጠረ በኋላ ራሱን ወዳልተፈጠረበት ሁኔታ መመለስ እይችልም። እንዲሁም የዘላለም ዋስትና አስተምህሮ በሚከተሉት ትምህርት ጥያቄዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡- ድኅነት የእግዚአብሔር ወይስ የሰው ሥራ፥ ሙሉ በሙሉ በጸጋ ላይ ወይስ በሰው ሥራ ላይ የተመሠረተ ነው? ምንም እንኳን በክርስቶስ አዲስ የሆነ ሰው እንደ እግዚአብሔር ልጅነቱ መሆን እንደሚገባው ሊሆን ባይችል፥ ልክ በሰብዓዊ ቤተሰብ የአንድ ሰው ልጅ ባደረገው ጥፋት ልጅነቱ እንደማይሻር፥ እማኝም ያገኘውን የዘላለም ሕይወት አያጣም። አሁን ያለን የዘላለም ሕይወት በመንፈሳዊ ልምምድ የተገለጠው በከፊል ብቻ መሆኑም እውነት ነው። የዘላለም ሕይወት ደስታ ፍጹም የሚሆነው፥ እግዚአብሔር ባለበት በሰማይ ነው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.