እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አካልነቱ

ሀ. የአካልነቱ አስፈላጊነት 

መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ ሰሚሰጥ ትምህርት ውስጥ እበይት ከሆኑት እውነቶች መካከል በማንነቱ ሳይ ልዩ ትኩረት ሊደረግ ይገባል። ይህ የሚያስፈልግበት ምክንያት በአሁኑ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የሚሰማውን እንጂ (ዮሐ. 16፡13፤ ሐዋ. 13፡2) ከራሱ ወይም ስለ ራሱ የማይናገር መሆኑና ወደ ዓለም የመጣውም ክርስቶስን ሊያከብር በመሆኑ ነው (ዮሐ. 16፡14)። ከዚህ ጋር ሲነጻጸር አብም ሆነ ወልድ ከራሳቸው እንደሚናገሩ አድርጎ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርበው። ይህ ሲሆን አብና ወልድን የሚያቀርባቸው በልዑላዊ ሥልጣንና እኔ በሚለው ተውላጠ ስም ብቻ ሳይሆን፥ እርስ በርሳቸው ቀጥተኛ መስተጋብር፥ ኅብረትና መስማማት እንዳላቸው በማረጋገጥ ነው። ከራሱና ስለ ራሱ አለመናገሩ ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ያላን መረዳት ውሱን ያደርገዋል። በዚሁ መሠረት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመንፈስ ቅዱስ አካልነት ለብዙ መቶ ዓመታት እንደቀላል ነገር የታየ ጉዳይ ነበር። በ325 ዓ.ም. በኒቅያ የእምነት መግለጫ አብና ወልድ በዝርዝር በተገለጡ ጊዜ ነው መንፈስ ቅዱስም እንደ አካል እውቅና ያገኘው። 

በትክክለኛው አስተምህሮ በኋላ እንደተገለጠው፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት እግዚእብሔር በሦስት አካል ይገለጣል የሚል ነው። ይሄውም አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ተቀባይነት አግኝቷል። መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና እንደወልድ አካል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያስተምራል። ከዚህ የሥላሴ አስተምህሮ ጥናት የምንረዳው፥ ሦስቱ አካላት አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አለመሆናቸውን ነው። 

ለ. ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተገለጠው የመንፈስ ቅዱስ አካልነት 

1. መንፈስ ቅዱስ አካል ያለው ብቻ ሊሠራ የሚችለውን እንደሚሠራ ተገልጿል። 

(ሀ) ዓለምን ይወቅሳል፡- “እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ጽድቅም፥ ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል” (ዮሐ. 16፡8)። 

(ለ) ያስተምራል፡- “እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል” (ዮሐ. 14፡26፤ ህ. 9፡20፤ ዮሐ. 16፡13-15፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡27)። 

(ሐ) ይናገራል፡- “ልጆችም ስለሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሉ የሚጮህ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ” (ገላ. 4፡6)። 

(መ) ይማልዳል፡- “ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል” (ሮሜ 8፣ 26)። 

(ሠ) ይመራል፡- “በመንፈስ ብትመሩ” (ገላ. 5፡18፤ ሐዋ. 8፡29፤ 10፡19፤ 13፡2፤ 16፡6-7፤ 20፡23፤ ሮሜ 8፡14)። 

(ረ) ምዕመናንን ለአገልግሎት ይሾማል፡- “መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ” (ሐዋ. 13፡2፤ 20፡28)። 

(ሰ) መንፈስ ቅዱስ ራሱ ለአገልግሎት ይላካል፡(ዮሐ. 15፡26)። 

ሸ መንፈስ ቅዱስ ያገለግላል፥ ዳግም ልደትንም ይሰጣል፡- (ዮሐ. 3፡6)፤ ያትማል (ኤፌ. 4፡30)፤ ያጠምቃል (1ኛ ቆሮ. 12፡13)፤ ይሞላል (ኤፌ. 5 ፡18)። 

2. እካል እንደመሆኑ መጠን በሌሉች ተጽዕኖ ይነካል። 

(ሀ) አብ ወደ ዓለም ይልከዋል (ዮሐ. 14፡16፥ 26)። ወልድም ይልከዋል (ዮሐ. 16፡7)። 

(ለ) ሰዎች ያስቆጡታል (ኢሳ. 63፡10)፥ ያሳዝኑታል (ኤፌ. 4፡30)፥ ያጠፉታል (ማዳፈን)፥ (1ኛ ተሰ. 5፡19)፥ ይሰድቡታል (ማቴ. 12፡31)፥ ይዋሹታል (ሐዋ. 5፡3)፥ ያክፋፉታል (ዕብ. 10፡29)፥ ቃል ይናገሩበታል (ማቴ. 12፡32)። 

3. መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ መጽሐፉ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አባባሎች ሁሉ አካልነቱን ያመለክታሉ። 

(ሀ) “ሌላው አጽናኝ” ተብሏል። ይህም የክርስቶስን ያህል አካልነት ያለው መሆኑን ያመለክታል (ዮሐ. 14፡16-17፥ 26፤ 16፡7፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡1-2)። 

(ለ) እግዚአብሔር መንፈስ እንደተባለ፥ መንፈስ ቅዱስም እንደአካል በዚሁ ስም ተጠርቷል (ዮሐ. 4፡24)። 

(ሐ) ለመንፈስ ቅዱስ መጠሪያነት ያገለገሉ ተውላጠ ስሞች አካልነቱን ያመለክታሉ። በግሪክ “መንፈስ” የሚለው ቃል ጾታ የማይለይ ስም ሲሆን፥ በጾታ ለማይለይ አካል መጥሪያነት ያገለግላል። ይህ ጾታ የማይለይ ተውላጠ ስም በአንዳንድ ሁኔታዎች ተጠቅሷል (ሮሜ 8፡16፥ 26)። ብዙ ጊዜ ግን የተባዕታይ ጾታ ተውላጠ ስም የመንፈስ ቅዱስን አካልነት በሚገልጥ መልኩ አገልግሏል (ዮሐ. 14፡16-17፤ 16፡7-15)። 

ሐ. መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር አካል እንደመሆኑ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል ነው 

1 እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል። ኢሳይያስ 6፡8-9 ውስጥ ያለውን ክፍል ከሐዋርያት ሥራ 28፡25-26፥ ኤርምያስ 31፡31-34ን ከዕብራውያን 10፡15-17 ጋር በማነጻጸር ይህን እውነት ለመረዳት ይቻላል። (2ኛ ቆሮ. 3፡18 እና ሐዋ. 5፡3-4 ውስጥ ይህን ቃል ልብ ይበሉ፡- “መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱም ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ሰለምን ሞላ? እግዚአብሔር እንጂ ሰውን አልዋሸህም።” ምንም እንኳን መንፈስ ቅዱስን ባታልሉት ላይ እግዚአብሔር ጠበቅ ያለ ፍርዱን ቢያወርድባቸውም (ሐዋ. 5፡3)፥ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳይምሉ ቢከለከሉና መንፈስ ቅዱስ በመባል ቢጠራም፥ ከአብና ከወልድ ይበልጥ ቅዱስ ነው ማለት አይደለም። ፍጹም ቅድስና የሥላሴ ዋና ባሕርይ ነው። 

2. መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ባሕርያት አሉት(ዘፍጥ. 1፡2፤ ኢዮብ 26፡13፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡9-11፤ ዕብ. 9፡14)። 

3. የእግዚአብሔርን ሥራዎች ያከናውናል(ኢዮ. 33፡4፤ መዝ. 104:30፤ ሉቃስ 12፡11-12፤ ሐዋ. 1፡5፤ 20፡28፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡11፤ 2፡8-11፤ 2ኛ ጴጥ. 1፡21)። 

4. ከላይ እንደተጠቀሰው መንፈስ ቅዱስን ለማመልከት ያገለገሉት ሰብዓዊ ተውላጠ ስምች ማንነቱን ያረጋግጣሉ። 

5. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ መንፈስ ቅዱስ ሊታመንበት የሚገባ አካል ሆኖ ቀርቧል (መዝ. 51፡11፤ ማቴ. 28፡19፤ ሐዋ. 10፡19-21)። የሚታመንበት አካል እንደመሆኑ፥ ሊታዘዙትም የሚገባው ነው። በክርስቶስ ያመነ ሰው፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሕብረት ስለሚጓዝ፥ ኃይሉን፥ መሪነቱን፥ ትምህርቱን፥ እና ሙሳቱን (ብቃቱን) በመለማመድ፥ የመንፈስ ቅዱስን አካልነት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ታላቅ የአስተምህሮ እውነት ይረዳል። 

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: