እግዚአብሔር ሥሉስ

ሀ. በእግዚአብሔር ሕልውና ማመን 

ከሰው የሚልቅና መለኮታዊ ሕልውና ያለው አካል መኖሩን ማመን በማንኛውም ባሕልና ሥልጣኔ ያለ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት፥ ባንድ ወገን፥ ሰው ስለ ዓለማችንና ስለ ሰብአዊ ልምምድ የሚገለጥ አንድ ነገር መኖር አለበት፥ ይህን ለመግለጥም፥ ያ ከሰው የሚልቅ አካል ይቻለዋል ብሎ ስለሚመራመር ነው። ሰው በተፈጥሮ አስተዋይነቱ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ተፈጥሮው ከርሱ የሚልቅ ሕልውና ወዳለው አካል የመድረስ ፍላጎት አለው። ይህ ፍላጎቱ በትምህርተ መለኮት ለሁሉም የሚሆን ጸጋ በመባል ከሚታወቅ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጋር በመያያዝ ሊገለጥ ይችላል። ይህ ከሰዎች ድነት ጋር ከተያያዘው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የተለየ ነው። እግዚአብሔር የለም የሚሉ ብዙ ሰዎች ዘመናዊ ክሥተት የሚመነጨው፥ ከተዛባ አስተሳሰብ እና በማንኛውም አቅጣጫ በሚደረግ ምርምር ዓለምን ለመግለጥ ይቻላል ከሚል አመለካከት ነው። እግዚአብሔር የለም የሚለውን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ሞኝ* ይለዋል(መዝ. 14፡1)።

*እዚህ ላይ የተጠቀምነው የ1980ውን ትርጉም ነው። ምክንያቱም ዩናባል ለሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተሻለ ትርጉም ይሰጣል ብለን ስለምናምን ነው።  በተለያዩ አገባቦች “ናባል” የሚለው ቃል ብሉይ ኪዳን ውስጥ 36 ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል። አምስት ጊዜ የአእምሮ ችግርን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል። ነገር ግን በአብዛኛው “ናባል” በሕብረተሰብ ያለውን ሕግ ወይም የእግዚአብሔርን ሕግ በድፍረት የሚጥስ ሰው አስተሳሰብን ይገልጣል። ለምሳሌ “ናባል” ሴኬም ዲናን አስገድዶ መድፈሩን ለመግለጥ (ዘፍጥ. 34፡7)፥ አምኖን ትዕማርን አስገድዶ መድፈሩን (2ኛ ሳሙ. 13፡12-13)፥ ከጎረቤት ሚስት ጋር ማመንዘርን (ኤር. 29፡23) ለመግለጥ ጥቅም ላይ ውሏል። አካን ከኢያሪኮ ድል በኋላ የፈጸመው የምርኮ ዕቃዎች ስርቆት “ናባል’ ነበር (ኢያሱ 7፡15)። የኢዮብ ጓደኞች “ናባል” ተብለው ተጠርተዋል። ምክንያቱም አስተሳሰባቸውና ድምዳሜያቸው ከእግዚአብሔር አልነበረምና (ኢዮ. 42፡8)። የእስራኤል መሪዎችም እርኩሰትን ሲለማመዱ፥ ዓመጽን ሲያቅዱ፥ ሰዎችን ሲያስርቡ ናባል ተብለው ይጠሩ ነበር (ኢሳ. 32፡5-7)።  ሐሰተኛ ነቢያት አክአብና ሴዴቅያስ “ናባል” ነበሩ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን እውነት አልተናገሩም (ኤር. 29፡23)። የእስራኤል ሕዝብ ናባል ነበር (ዘዳ. 32፡6፥ 15፥ ኤር. 14፡1)። ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ክብርና ታላቅነት እያወቀ ከእርሱ ይርቅ ነበር። ናባል የእግዚአብሔርን መኖር የሚክድና (መዝ. 14፡1፥ 53፡2)፥ በእግዚአብሔር በሚታመኑት ላይ የሚሳለቅ ነው (መዝ፡39፥9፥ ኢዮ. 2፡10)።  

በተለምዶ ሰዎች ስለ ራሳቸው ሕልውናም ሆነ፥ በስሜት ሕዋሶቻቸው አማካይነት ሊረዱአቸው ስለሚችሉአቸው ቁሳዊ ነገሮች ሕልውና ማረጋገጫ አይጠይቁም። እግዚአብሔር በአካለ ሥጋ ባይታይም ሕልውናው የተረጋገጠ በመሆኑ፥ በአብዛኛው ሰዎች ስለ መኖሩ ምንም ማስረጃ አይጠይቁም። የእግዚአብሔርን ሕልውና መጠራጠር የሚመጣው፥ ሰው ራሱ ትክክለኛውን መንገድ ከመሳቱና መንፈሳዊ ዓይኑ በመታወሩ፥ እንዲሁም ከሰይጣናዊ ተጽዕኖ የተነሣ ነው። የእግዚአብሔር ሕልውና በተፈጥሮ አማካይነት በሚገባ ተገልጧል። ስለ ወንጌል ያልሰማው የማያምን ዓለም የፍርድ መሠረትም ይህን በተፈጥሮ የተገለጠ የእግዚአብሔር ሕልውና አለማመኑ ነው። በመሆኑም ሮሜ 1፡19-20 ውስጥ፥ “እግዚአብሔር ስለገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና”፥ በሚለው ቃል መሠረት ይፈረድባቸዋል። 

መጽሐፍ ቅዱስ ከመጻፉ በፊት በነቢያት በኩል የተላለፈውን እና በመጽሐፉ የተላለፈውን የእግዚአብሔር መገለጥ ዛሬ በተወሰነ ደረጃ አብዛኛው ሰው ያውቀዋል። ዓለም በጠቅላላው ሲታይ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተላለፈው መገለጥ መሃይም ቢሆንም፥ በመጠኑም ቢሆን ስለ እግዚአብሔር እንዲያሰላስል መገለጡ የዓለምን ሁሉ አሳብ ይዞታል። ስለዚህ በአንድ ሉዓላዊ በሆነ አካል ማመን መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ባልደረሳቸው ሰዎች ዘንድ እንኳ አለ። 

ጥንታዊ የግሪክ ፈላስፋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊውን መገለጥ ባያውቁትም፥ አንድ ሉዓላዊ አካል አለ በሚል አስተሳሰብ ላይ በመመሥረት ዓለማትን ለመግለጥ ሞክረው ነበር። በዚሁ መሠረት የተለያዩ የአስተሳሰብ ዘዴዎች ቀርበዋል። እነሱም፦ 

1. በብዙ አማልክት ማመን (Polytheism)፤ 

2. ኃይሎኮይዝም (Hylozoism) በእያንዳንዱ ተፈጥሮ ውስጥ የሚገኘው የሕይወት ሥርዓት ራሱ እግዚአብሔር ነው የሚል እምነት፤ 

3. ቁስ-አካላዊነት (Materialism)፥ ቁስ-አካል በራሱ የተፈጥሮ ሕግ መሠረት የሚሠራ ስለሆነ፥ ለማንኛውም እንቅስቃሴው ምንም አምላክ አያስፈልገውም። ይህ ትምህርት የአዝጋሚ ለውጥን (Evolution) አሳብ የሚደግፍ ነው፤ 

4. “ፖንቴይዝም” (Pantheism) የሚባለው ደግሞ እግዚአብሔር ስብእና የሌለውና ከተፈጥሮ ጋር አንድ የሆነ ነው፥ ስለዚህም እግዚአብሔር አብሮ ያለ፥ የቅርብና እኩያ እንጂ የበላይ የሆነ ወይም አእምሮን የሚያልፍ አይደለም ይላል። ስለ እግዚአብሔር ይህን የመሳሰሉ ብዙ አስተሳሰቦች አሉ። 

ስለ እግዚአብሔር መኖር ከቃሉ ከሚገኘው መገለጥ ውጪ፡ከተፈጥሮ እውነት አንጻር ብቻ ሲታይ እንኳን የሚከተሉት አራት ዋና ዋና አሳቦች ወይም ምክንያቶች ሊስተዋሉ ይችላሉ። እነርሱም፡

1. እግዚኣብሔር አለ ብሎ ሰው ሁሉ ስለሚያምን እግዚኣብሔር መኖር አለበት የሚለው አሳብ ነው። ይህ አስተሳሰብ “አንተሎጂካል ተሐስቦ” (Ontological argument) ይባላል። 

2. የዓለማት አፈጣጠር ተሐስቦ (Cosmological argument) የተሰኘው አመለካከት፥ ማንኛውም ውጤት ምክንያት ወይም መነሻ ሊኖረው ይገባል፤ ስለሆነም ውጤት የሆኑት ዓለማት መነሻ የሆን ፈጣሪ ሊኖራቸው ይገባል ይላል። በዚህም አሳብ የተካተተው ሌላ አመለካከት በአጋጣሚ ሊመጡ የማይችሉት ዓልማት ሥርዓት ውስብስብነት ነው። 

3. ማንኛውም ውጥን ወይም ዕቅድ ያለ አድራጊና ያለ ዓላማ ሊከናወን አይችልም የሚለው “ቴሌሎጂካል ተሐስቦ” (Teleological argument) አስተሳሰብ፥ ተፈጥሮ ባጠቃላይ በረቀቀ ሁኔታ የታቀደና አንዱ ከሌላው የተዛመደ እንደ መሆኑ እንድ ታላቅ ሠሪ ሊኖረው ይገባል ይላል። ነገሮች ሁሉ በአንድነትና በኅብረት የመሥራታቸው እውነት፥ እነሱን የሠራ ፈጣሪ ፍጹም ኃይልና ጥበብ ያለው መሆኑን ያመለክታል። 

4. ሥነ-ሰብአዊ (Anthropological argument) አመለካከት፥ የሰው ተፈጥሮ በአምሳያው ከፈጠረው፥ ነገር ግን ከርሱ እጅግ ከሚልቀው ከእግዚአብሔር ባሕርይ ተለይቶ ሊገለጥ አይችልም ይላል። ከዚሁ ጋር ሰው አእምሮ (የማሰብ ችሎታ)፥ ስሜት (በስሜት የመገንዘብ ችሎታን)፥ ፈቃድ (ምርጫ የማድረግ ችሎታ) አለው። እንዲህ ያሉት ልዩ ችሎታዎች ተመሳሳይ ነገር ግን የላቀ ባሕርይ ወዳለውና ሰውን ወደፈጠረ አምላክ ያመለክታሉ። 

የእግዚአብሔርን ሕልውና አስመልክቶ የተነሡ እነዚህ አስተሳሰቦች በቀላሉ የማይገመት ጠቀሜታ አላቸው። ሰውም እነዚህን አሳቦች ባለመቀበሉ የተፈረደበት መሆኑ ትክክል ቢሆንም (ሮሜ 1፡18-20)፥ ሰው በትክክል ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ አልረዳውም፤ ወይም ያለ መጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ በእግዚአብሔር እውነተኛ እምነት እንዲኖረው አልረዳም። የእግዚአብሔር ሙሉ መገለጥ የተሰጠው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመሆኑም ተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን እውነታዎች እና በርሱም ላይ ተፈጥሮ ሊገልጣቸው የማይቻለው ብዙ እውነቶች ታክለዋል። 

ለ. የሥላሴ መለኮታዊ አንድነት 

ብሉይ ኪዳን በአጠቃላይ የእግዚአብሔርን ውሑድነት ወይም አንድነት ይገልጣል (ዘፀ. 20፡3፤ ዘዳ. 6፡4፤ ኢሳ. 44 ፡6)። ይህን እውነት አዲስ ኪዳንም ያስተምራል (ዮሐ. 10፡30፤ 14፡9፤ 17፡11፤ 22፡23፤ ቆላ. 1፡15)። ብሉይ ኪዳን፥ በይበልጥም አዲስ ኪዳን፥ እግዚአብሔር በሥሉስነት ማለት፥ እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሆኖ እንደሚኖር ያስገነዝባሉ። ብዙ ሰዎች የሥላሴ ትምህርት ኤሎሂም በሚለውና የእግዚአብሔርን ሥሉስነት ያመለክታል ተብሎ በሚታመነው ስም ውስጥ ይጠቃለላል ይላሉ። ይህንንም የሚሉበት ምክንያት ኤሎሂም የሚለው ቃል የብዙ ቁጥር በመሆኑ ነው። 

በዘፍጥረት መጀመሪያ ክፍሎች ስለ እግዚአብሔር መንፈስ የሚገልጥና እግዚአብሔርን በብዙ ቁጥር የሚያመለክት ተውላጠ ስም ይገኛል (ዘፍጥ. 1፡26፤ 3፡22፤ 11፡7)። የአብን፥ የወልድንና የመንፈስ ቅዱስን ባሕርይ በተመለከተ፥ ብዙ ጊዜ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ልዩነቶች አሉ። ኢሳይያስ 7፡14 ላይ ወልድን አማኑኤል “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” በማለት ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ለየት አድርጎ ያቀርበዋል። ኢሳይያስ 9፡6 ላይ ደግሞ፥ ይሄው ወልድ “ኃያል አምላክ፥ የዘለአለም አባት፥ የሠላም አለቃ” ተብሏል። 

መዝሙረ ዳዊት 2፡7 ውስጥ “እኔ” ተብሎ የተጠቀሰው እግዚአብሔር አብ፥ ዓሳማው ልጁን የዓለም ልዑል ገዢ ማድረግ መሆኑ ተገልጧል። አብና ወልድ እንደተለያዩ ሁሉ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን መላኩ በተገለጠበት መዝሙረ ዳዊት 104፡30 ውስጥ፥ አብ ከመንፈስ ቅዱስ የሚለይ መሆኑ ተመልክቷል። በዚህ ላይ የሚታካሉት ሌሎች ማስረጃዎች፥ የእግዚአብሔርን ልጅ መገለጥ በሚያመለክተው ብሉይ ኪዳን ውስጥ “የያህዌህ መልአክን” መታየት የሚያሳዩት ታሪኮች ናቸው። የእግዚአብሔር መንፈስ፥ መንፈስ ቅዱስ መሆኑና እርሱም ከአብና ከወልድ የተለየ መሆኑ መገለጡም ከዚሁ ጋር የሚዳመር ነው። 

ለነዚህ የብሉይ ኪዳን ማስረጃዎች እዲስ ኪዳን ተጨማሪ መገለጥ ይሰጣል። ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ የተፀነሰና የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ፥ ማለት ሥጋ የለበሰ አምላክ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ሥርዓተ ጥምቀት ጊዜ፥ እግዚእብሔር አብ ከሰማይ ሲናገር፥ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል ወርዶ በላዩ ሲያርፍበት እና፥ ኢየሱስ እራሱ ሲጠመቅ፥ በሥላሴ ውስጥ ያለው ልዩነት ተገልጧል (ማቴ. 3፡16-17)። ይህ የሥላሴ ልዩነት ዮሐንስ 14፡16 በመሳሰሉ ክፍሎችም ታይቷል። በነዚህ ምንባቦች አብና አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ከክርስቶስ ተለይተው ተገልጠዋል። ማቴዎስ 28፡19 ውስጥ ደቀ መዛሙርት “በአብ፥ በወልድ፥ በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንዲያጠምቁ በታዘዙበትም ልዩነቱ ተመልክቷል። 

እግዚአብሔር በሥሉስነት የሚኖር መሆኑን በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን የሚያመለክቱት ክፍሎች፥ የሥላሴን ትምህርት በመግለጥ ረገድ ከጥንት እስከዛሬ የትክክለኛው እምነት ማዕከላዊ እውነት ናቸው። በመሆኑም ይህን አለመቀበል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዳለመቀበል ተቆጥሯል። “ሥላሴ” የሚለው ቃል መጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም፥ የእግዚአብሔር ቃል መገለጥ እውነቶች ይህንኑ ብቻ የሚያሳዩ ናቸው። 

የሥላሴ ትምህርት የክርስትና እምነት ትምህርት ማዕከላዊ እውነት ሲሆን፥ ከሰብአዊ ግንዛቤ በላይና በሰው ልምምድ ውስጥ አምሳያ የሌለው ነው። እግዚአብሔር አንድ ሲሆን፥ በሦስት አካልነት ይኖራል የሚለው አገላለጥ ከሁሉ የተሻለ ነው። እነዚህ አካላት አቻ ናቸው፥ አንድ ባሕርይ አላቸው፤ እኩል ክብር፥ አምልኮና መታመን ይገባቸዋል። ያም ሆኖ ስለ እግዚአብሔር አምላክ ውሑድነት ያለው መሠረታዊ ትምህርት እነዚህ አካላት እንደተለያዩ ሰዎች ማለት፥ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ዮሐንስ እንደ ማለት የተለያዩ ሦስት አማልክት አለመሆናቸውን በግልጥ ያስረዳል። በመሆኑም እውነተኛው የክርስትና እምነት የሦስት አማልክት እምነት አይደለም። በሌላም በኩል ሥላሴ እግዚአብሔር እራሱን የገለጠበት ሦስት መንገዶች እንደሆነ ሊታሰብ አይገባም። ሥላሴ ማለት ስለ እግዚአብሔር ሕላዌና ማንነት የሚናገር እንጂ፥ ራሱን የገለጠበትን ሦስት መንገዶች የሚያሳይ አይደለም። ስለሆነም የሥላሴ ትምህርት ስለ እግዚአብሔር ባለ ትምህርት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ነው። 

የሥላሴ አካላት በሕላዌ አቻ ባሕርይ ቢኖራቸውም፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች ይለያያሉ። በዚሁ መሠረት የመጀመሪያው አካል እግዚአብሔር አብ ይባላል። ሁለተኛው በአብ የተላካውና እግዚአብሔር ወልድ ተብሎ የሚጠራው ነው። ሦስተኛው አካል ደግሞ፥ በአብና በወልድ የተላከው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ በትምህርተ-መለኮት ገላጣ ሥርፀት የሚባል ሲሆን፥ ፈጽሞ አይዛባም፤ ማለት ወልድ በምንም ሁኔታ አብን፥ ወይም መንፈስ ቅዱስ ወልድን አይልክም። የአምላክን ልዩ ባሕርይ በተመለከተ፥ ለሰብአዊ አእምሮ የሚገባ ተምሳሌት የለም። ስለሆነም ምንም እንኳ ከሰብአዊ ግንዛቤና ቋንቋ በላይ ቢሆን፥ በእግዚአብሔር ቃል መገለጥ ላይ በመመሥረት ትምህርቱን በእምነት መቀበል ይገባል። 

ሐ. የእግዚአብሔር ስሞች 

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር በሦስት ዋና ዋና ስሞች ተጠርቷል። የመጀመሪያው “ያህዌህ” የሚለው ሲሆን፥ የእውነተኛው አምላክ መጠሪያ ስም ነው። ይህ ስም ዘፍጥረት 2፡4 ላይ እንደተመለከተው፥ ከፍጥረት ጋር ተያይዞ የቀረበ ሲሆን፥ የስሙም ትርጉም ዘዳግም 3፡13-14 ላይ እንደተመለከተው “ያለና የሚኖር እኔ ነኝ” ተብሎ ተገልጧል። የዚህ ፍቺው በራሱ የሚኖር ዘላለማዊ አምላክ ማለት ነው። 

በብሉይ ኪዳን የተለመደው የእግዚአብሔር ስም “ኤሎሂም” የሚለው ሲሆን፥ ለእውነተኛው አምላክና ለአሕዛብ አማልክት መጠሪያነት አገልግሏል። ስሙ መጀመሪያ የተገለጠው ዘፍጥረት 1፡1 ውስጥ ነው። የዚህ ስም ትርጉም ወይም ፍቺ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል። ቢሆንም “ብርቱው” ሊፈራና ሊከበር የተገባው የሚሉትን አሳቦች ያካተተ ይመስላል። የብዙ መጠሪያነትም ስላለው የሥላሴ አካላትን ያካተተ ይመስላል፤ የሥላሴን አካላት በተናጠል ለመጥራትም ያገለግላል። 

ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኝ የእግዚአብሔር ሦስተኛ ስም፥ “አዶናይ” የሚለው ሲሆን፥ ትርጉሙም በተለምዶ “ጌታ” ማለት ነው። ይህ እግዚአብሔር ጌታችን መሆኑን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን፥ በአገልጋዮቻቸው ላይ ጌታ ለሆኑ ሰዎች መጠሪያነትም ያገለግላል። ዘፍጥረት 15፡2 ውስጥ እንደተመለከተው፥ ይህ ቃል ኤሎሂም ከሚለው ስም ጋር በተደጋጋሚ ይያያዛል። እንዲያ ተያይዞ ሲጠቀስ እግዚአብሔር ጌታችን መሆኑን ያመለከታል። ብሉይ ኪዳን ውስጥ ብዙ የነዚህ ስሞች ጥምሮች አሉ። ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ግን፥ ያህዌህ፥ ኤሎሂም ወይም አዶናይ ኤሎሂም የሚለው ነው። 

ከነዚህ ሦስት ዋና ዋና ስሞች ጋር ተያያዥ ወይም ተዋሐጅ የሆኑ ብዙ ቃላት ኣሉ። እነዚህም፥ ያህዌህ-ይርኤ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል”፥ (ዘፍጥ. 22፡13-14)፥ ያህዌህ-ራፋ “እግዚአብሔር ፈዋሽ” (ዘጸ. 15፡26)፥ ያህዌህ-ንሲ “እግዚኣብሔር ዓላማዬ” (ዘጸ. 17:8-15)፥ ያህዌህ-ሻሎም “እግዚእብሔር ሰላማችን” (መሳ. 6፡24)፥ ያህዌህ-ጽድቅኒ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” (ኤር. 23፡6)፥ ያህዌህ- ሻማ “እግዚኣብሔር እዚህ አለ” (ሕዝ. 48፡35) የሚሉ ናቸው። 

አዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉ ተጨማሪ የእግዚአብሔር ስሞች፥ የመጀመሪያው አካል “አብ”፥ ሁለተኛው አካል “ወልድ”፥ እና ሦስተኛው ኣካል “መንፈስ ቅዱስ” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ስሞች አዲስ ኪዳን ውስጥ ይበልጥ የተለመዱ ይሁኑ እንጂ፥ ብሉይ ኪዳን ውስጥም አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረገው ውይይት ሦስቱን የሥላሴ አካላት ኣስመልክቶ በሚቀርቡት ምዕራፎች ውስጥ ይቀጥላል። 

መ. የእግዚአብሔር ባሕርያት 

በእግዚአብሔር ዋና ሕልውና ውስጥ እንዳንድ ተወራራሽ ወይም መሠረታዊ ባሕርያት አሉ። እነዚህ ባሕርያት፥ ለዘላለም የሥላሴ የሆኑና በሁሉም የሥላሴ አካላት ውስጥ በእኩል የሚኖሩ ናቸው። ከባሕርያቱ ውስጥ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ነው (ዮሐ. 4፡24)፤ ሕይወት ነው (ዮሐ. 5፡26)፤ ኗሪ ነው (ዘጸ . 3፡14)፤ ገደብ የለውም (መዝ. 145፡3)፤ አይለወጥም (መዝ. 102፡27፤ ሚል. 3፡6፤ ያዕ. 1፡17)፤ እውነት ነው (ዘዳ. 32፡4፤ ዮሐ. 17፡3)፤ ፍቅር ነው (1ኛ ዮሐ. 4:8)፤ ዘለአለማዊ ነው (መዝ. 90፡2)፤ ቅዱስ ነው (1ኛ ጴጥ. 1፡16፤ 1ኛ ዮሐ. 1፡5)፤ በሁሉም ስፍራ አለ (መዝ. 139፡8፤ ኤር. 23፡23-24)፤ ሁሉን የሚያውቅ ነው (መዝ. 147፡4-5)፤ ሁሉን ቻይ ነው (ማቴ. 19፡26)፤ የሚሉት ይገኙባቸዋል። 

የእነዚህ ባሕርያት የተለያዩ ገጽታዎች፥ በእግዚአብሔር መልካምነት፥ መሐሪነትና ልዕልና ውስጥ ይታያሉ። ፍጹምነት ለዘላለም የእግዚአብሔር ሲሆን፥ ሥራዎቹና ሕልውናውም ፍጹም ናቸው። የዓለማት ዕቅድና ዝርዝር ሥራዎቹ የልዑልነቱ፥ የኃይሉና የጥበቡ ማረጋገጫዎች ናቸው። በቃሉ እንደተነገረው፥ የመገለጡ ዕቅድ፥ የፍቅሩ፥ የጽድቁ እና የጸጋው ማረጋገጫዎች ናቸው። ከርሱ ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ተፈጥሮ የለም፤ የድንቢጥን ያህል ያነሰ ነገር እንኳን በልዑላዊ ዕቅዱ ውስጥ አይዘነጋም። 

ሠ. የእግዚአብሔር ልዕልና 

እግዚአብሔር ከሁሉ የላቀ መሆኑን ባሕርያቱ ይገልጣሉ። ለምንም ኃይል፥ ሥልጣን ወይም ከብር እንዲሁም ከርሱ ለበለጠ ፍጹም ትልቅ አካል የሚገዛ አይደለም። በሕልውናውና በማንኛውም ሁኔታ ፍጹም ነው። ድንገት ድል መሆንና ያልተረጋገጠ ነገር በርሱ ዘንድ የለም። ይሁን እንጂ ሥልጣኑን ሳይተው ወይም ፍጹም የሆነ ፍቃዱን ከማከናወን ሳይገታ፥ የተወሰነ የምርጫ ነጻነት ለሰዎች ወድዶ ሰጥቷል። በዚሁ መሠረት በምርጫው በመገልገሉ ረገድ እግዚአብሔር ሰውን ተጠያቂ ያደርገዋል። 

ሰው ከአምላክ ጸጋ በመወገዱ ሳቢያ፥ ለእግዚአብሔር ሥራ ዕውርና ስሜቱም የደነዘዘ በመሆኑ፥ እግዚኣብሔር ራሱ በመንፈሱ አማካይነት ካላነሣሣው በቀር፥ ወደ እግዚኣብሔር እንደማይመለስ ከመጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ለመረዳት ይቻላል (ዮሐንስ 6፡44፤ 16፡7-11)። ይሁን እንጂ ሰውም በበኩሉ ባለማመኑ በኃላፊነት ተጠያቂ ስለሆነ፥ ይድን ዘንድ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምን ታዟል (ሐዋ. 16፡31)። እንዲሁም እግዚአብሔር በሰዎች፥ በተለይም በክርስቲያኖች ጉዳይ ወይም ነገር አማካይነት ፍቃዱን ለመፈጸም ይሠራል (ፊሊጵ. 2፡13)። ቢሆንም በፈቃደኝነታቸው እንጂ ሰዎችን በኃይል እያስገድዳቸውም (ሮሜ 12፡1-2)። 

እግዚአብሔር ለሰው የተወሰነ ነጻነት መስጠቱ በዓለማት ውስጥ እርግጠኛነት የለም እያሰኝም። እግዚአብሔር፥ ሰው ከመለኮትና ከመሰሉ ከሰው ለሚደረግበት ተጽዕኖ የሚመልሰውን አጸፋ ሁሉ አስቀድሞ ያውቃል። ስለሆነም ልዕልናው እስከ ማንኛውም ድርጊት፥ እርሱ የሚከብርበት ከሆነ፥ ክፉ ነገርን ለጊዜው እስከ መፍቀድም ይደርሳል። 

ረ. የእግዚአብሔር ድንጋጌ 

የእግዚአብሔር ልዑላዊ ዓላማና ዕቅድ በትምህርተ-መለኮት የእግዚኣብሔር ድንጋጌ ተብሏል። ይህ ስያሜ ወደፊት የሚሆኑትን ክንውኖች ሁሉ የሚጨምረውን ጠቅላላ ዓላማና ዕቅድ ያመለክታል። የእግዚአብሔር ድንጋጌ እርሱ ራሱ የሚያደርጋቸውንና በተፈጥሮ ሕግ በኩል የሚያከናውናቸውን ይጨምራል። እነዚህን ሁሉ በፍጹም ሉዓላዊነቱ የሚቆጣጠራቸው እርሱ ነው። የሰው ድርጊቶች እንዴት በዘላለማዊ ዕቅዱና ድንጋጌው ውስጥ እንደተካተቱ ለመረዳት እጅግ ያዳግታል። 

የማይገባን ቢሆን እንኳ፥ የጥበብ አምላክ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የወደደውን እንዲያደርግ ነጻነት ሲሰጠው፥ በተሰጠው ነጻ ፍቃድ ምን እንደሚያደርግ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ፥ እርግጠኛ ያለመሆን ነገር በድንጋጌው ውስጥ የለም። በዚሁ መሠረት፥ መለኮታዊው ዕቅድ፥ አዳምና ሔዋን እንዳደረጉት ሰው ኃጢአትን እንዲያደርግ መፍቀድን ይጨምራል። ይህ ፍቃድ፥ በክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞትና ሰዎችን ወደ ንስሐና እምነት በሚያመጣው የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ሁሉ ውጤት የሆነው መለኮታዊ ፈውስንም ይጨምራል። 

እግዚአብሔር በሰዎች ልብ የሚያከናውነው ተግባር የማይመረመር ቢሆንም፥ ሰው በአንድ በኩል ድርጊቱ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ድንጋጌ ውስጥ መታከሉ፥ በሌላ በኩል ደግሞ በነጻ ምርጫው የሚኖርና፥ ለዚህ ምርጫውም ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያስረዳል። የእግዚአብሔር ድንጋጌ ባወጣው ያውጣው የሚል፥ ጭፍንና እንደ ግዑዝ መሣሪያ ነገራትን የሚቆጣጠር ሳይሆን፤ በማስተዋል በፍቅርና በጥበብ የተሞላ ነው። ስለሆነም ከሰው ምርጫ በመነሣት ክፉውን ይቀጣል መልካሙን ደግሞ ይሸልማል። 

የእግዚአብሔርን ድንጋጌ በንዑሳን ክፍሎች፥ ማለት የመፍጠር ድንጋጌ፥ ዓለምን የማጽናት ድንጋጌ፥ የጥበቃና ክብካቤ ድንጋጌ እና ዓለማትን የመምራት ብልህ አመራር ብሎ ለመመደብ ይቻላል። ድንጋጌው የእግዚአብሔርን ተስፋ ወይም ቃል ኪዳን፥ የዓላማውን መፈጸም እና ለሰዎች የተገለጠውን ልዑል ዓላማ ይጨምራል። እንዲህ ባለው ልዑል አምላክ ፊት ሰው ሊያደርግ የሚችለው፥ በመገዛት፥ በፍቅርና በአክብሮት መንበርከክ ነው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: