እግዚአብሔር ወልድ፡ትንሣኤው

ሀ. ትንሣኤ በብሉይ ኪዳን 

የሰዎችን ሁሉ ትንሣኤና የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚያመለክት አስተምህሮ ብሉይ ኪዳን ውስጥ አለ። አስተምህሮው ቀደም ሲል ምናልባት በአብርሃም ዘመን ይኖር እንደነበር በሚገመተው ከኢዮብ ጊዜ ጀምሮ ነበር፤ ኢዮብ ሰእምነት መግለጫው እንዲህ ብሏል። “እኔን የሚቤዠኝ ሕያው እንደሆነ፥ ሰመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ፥ እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመልከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል” (ኢዮብ 19፡25-27)። ኢዮብ በዚህ ቃሉ የሚያረጋግጠው የራሱን ትንሣኤ ብቻ ሳይሆን፥ አዳኝ የሆነ ጌታው ሕያው እንደሆነና ሰኋላም በምድር ላይ የሚቆም መሆኑን ጭምር ነው። ሰዎች ሁሉ በዘመን ፍጻሜ የሚነሡ የመሆኑ ትምህርት ዮሐንስ 5፡28-29 እና ራእይ 20፡4-6፥ 12-13 ውስጥ ይገኛል። 

ብሉይ ኪዳን ውስጥ የተለያዩ ትንቢቶች ስለ ሰው አካል ትንሣኤ ይናገራሉ (ኢዮብ 14፡13-15፤ መዝ. 16፡9-10፤ 17፡15፤ 49፡15፤ ኢሳ. 26፡19፤ ዳን. 12፡2፤ ሆሴዕ 13፡14፤ ዕብ. 11፡17-19)። የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ መዝሙረኛው ዳዊት፥ “ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም” (መዝ. 16፡9-10) ባለው ክፍል በግልጥ ተነግሯል። ዳዊት በዚህ ክፍል የሚገልጠው፥ በተስፋ ስለሚጠብቀው የግል ትንሣኤው ብቻ ሳይሆን “ቅዱስህን” ብሎ የሚጠራው ኢየሱስም 

መበስበስን እንደማያይ ያረጋግጣል። ይህ የዳዊት ቃል የክርስቶስን ትንሣኤ በሚያመለክትበት ሁኔታ ሰጴጥሮስ ስብከት ውስጥ (ሐዋ. 2፡24-31)፥ እንዲሁም በጳውሎስ ስብከት ውስጥ (ሐዋ. 13፡34-37) ተጠቅሷል። 

የክርስቶስ ትንሣኤ መዝሙረ ዳዊት 22፡22 ውስጥም ክርስቶስ ራሱ ከሞቱ በኋላ ስሙን “ለወንድሞቹ” የሚገልጥ መሆኑን ባስገነዘበበት ሥፍራም ተመልክቷል። ክርስቶስ ከፍ ከፍ ብሎ የማዕዘን ራስ እንደሚሆን መዝሙረ ዳዊት 118፡22-24 ውስጥ የተገለጠው፥ በሐዋርያት ሥራ 4፡10-11 ላይ የኢየሱስን ትንሣኤ በማጉላትና በማብራራት ተጠቅሷል። የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ብሉይ ኪዳን ውስጥ በመልከ ጼዴቅ ተምሳሌትነት የተተነበየ ይመስላል (ዘፍጥ. 14፡18፤ ዕብ. 7፡15-17፥ 23-25)። በተመሳሳይ ሁኔታ ዘሌዋውያን 14፡4-7 ውስጥ ስለ ለምጻሙ ሰው ክሚቀርቡት ሁለት ወፎች ውስጥ የሚለቀቀው ወፍ እና የመከሩ በኩራት (ዘሌ. 23፡10-11) ተምሳሌቶች ክርስቶስ የትንሣኤ በኩራት እንደሆነ ያመለክታሉ። ያቆጠቆጠችው የአሮን በትርም (ዘኁ. 17፡8) ስለ ትንሣኤ ታመለክታለች። ስለዚህ የሰው ሁሉና የክርስቶስ ትንሣኤ ብሉይ ኪዳን ውስጥ በሚገባ ተረጋግጧል። 

ለ. ክርስቶስ ስለራሱ ትንሣኤ፥ የተናገራቸው ትንቢቶች 

ክርስቶስ በወንጌሎች ውስጥ ስለ ሞቱና ትንሣኤው በተደጋጋሚ አስቀድሞ ተናግሯል (ማቴ. 16፡21፤ 17፡23፤ 20፡17-19፤ 26፡12፥ 28-29፥ 31-32፤ ማር. 9፡30-32፤ 14 ፡28፤ ሉቃስ 9፡22፤ 18፡31-34፤ ዮሐ. 2፡19-22፤ 10፡17-18)። ትንቢቶቹ በጣም የተደጋገሙ፥ ግልጥ እና ክርስቶስ የራሱን ሞት እራሱ የተነበየ ለመሆኑ በማያጠያይቅ ሁኔታ በብዙ ተዛማጅ ሁኔታዎች የተገለጡ ናቸው። የእነዚህ ትንቢቶች መፈጸምም ትክክለኛነታቸውን ያረጋግጣል። 

ሐ. የክርስቶስ ትንሣኤ ማረጋገጫዎች 

አዲስ ኪዳን የክርስቶስን ትንሣኤ እስመልክቶ እጅግ ብዙ ማረጋገጫዎችን ያቀርባል። ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ቢያንስ ለአሥራ ሰባት ጊዜ ታይቷል። እነዚህም፡(1) ለማርያም መግደላዊት (ዮሐ. 20፡11-17፤ ማር. 16፡9-11)፥ (2) ለሴቶች (ማቴ. 28፡9-10)፥ (3) ለጴጥሮስ (ሉቃስ 24፡34፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡5)፥ (4) በኤማሁስ መንገድ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ (ማር. 16፡12-13፤ ሉቃስ 24፡13-35)፥ (5) ለአሥሩ ደቀ መዛሙርት (እዚህ ላይ “አሥራ አንዱ” ይላል፥ ግን አሥር ናቸው።) ምክንያቱም ቶማስ በወቅቱ በቦታው አልነበረም (ማር. 16፡14፤ ሉቃስ 24፡36-43፤ ዮሐ. 20፡19-24)፥ (6) ከትንሣኤው ከአንድ ሳምንት በኋላ ለአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት (ዮሐ. 20፡26-29)፥ (7) በገሊላ ባሕር አጠገብ ለሰባቱ ደቀ መዛሙርት (ዮሐ. 21፡1-23)፥ (8) ለአምስት መቶ ሰዎች (1ኛ ቆሮ. 15፡6)፥ (9) ለያዕቆብና ለጌታ ወንድም ለዮሐንስ (1ኛ ቆሮ. 15፡7)፥ (10) በገሊላ ተራራ ላይ ለአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት (ማቴ. 28፡16-20፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡7) ፥ (11) በደብረ ዘይት ተራራ በዕርገቱ ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ (ሉቃስ 24፡44-53፤ ሐዋ. 1፡3-9)፥ (12) ሰማዕቱ እስጢፋኖስ ከመሰዋቱ በፊት ሰአባቱ ቀኝ ሆኖ (ሐዋ. 7፡55-56)። (13) ደማስቆ መንገድ ላይ ለጳውሎስ (ሐዋ. 9፡3-6፤ 22፡6-11፤ 26፡13-18፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡8)። (14) በዐረቢያ ምድር ለጳውሎስ (ሐዋ. 20፡24፤ 26፡17፤ ገላ. 1፡12፥ 17) 15) ቤተ መቅደስ ውስጥ ለጳውሎስ (ሐዋ. 22፡17-21፤ 9፡26-30፤ ገሳ. 1፡18)፡(16) ቂሳሪያ እስር ቤት ለጳውሎስ (ሐዋ. 23፡11)፥ (17) ለሐዋርያው ዮሐንስ (ራእይ 1፡12-20)። 

እነዚህ በብዙ የተለያዩ ሁኔታዎች የተፈጸሙ መታየቶች እና በዙሪያቸው ያሉ ማረጋገጫዎች ሁሉ ክርስቶስ ከሞት የተነሣ መሆኑን የሚመሰክሩ ብርቱ የታሪክ ማረጋገጫዎች ናቸው። 

መታየቱን አስመልክቶ ከቀረቡት ማረጋገጫዎች አያሌ ተጨማሪ ማስረጃዎች ለመጥቀስ ይቻላል። ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ መቃብሩ ባዶ ነበር (ማቴ. 28፡6፤ ማር. 16፡6፤ ሉቃስ 24፡3፥ 6፥ 12፤ ዮሐ. 20፡2፥ 5-8)። የክርስቶስ ትንሣኤ ምስክሮች ድልሎችና በቀላሉ የሚታለሉ እለመሆናቸው እርግጥ ነው። እንደውም ማረጋገጫዎችን ለመገንዘብ የዘገዩ ነበሩ (ዮሐ. 20፡9፥ 11-15፥ 25)። የትንሣኤውን እውነት ከጨበጡ በኋላ ግን፥ በክርስቶስ ላላቸው እምነት ለመሞት ዝግጁ ሆኑ። ከትንሣኤው በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ለውጥ ታይቶባቸዋል። ኀዘናቸው በደስታና በእምነት ተተክቷል። 

ከክርቶስ ትንሣኤ በኋላ በደቀ መዛሙርቱ ስለተከናወነው የመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ኃይል፥ ስላወጁት የምሥራች ቃል ኃይል እና ያን ይደግፉ የነበሩትን የማረጋገጫ ተአምራት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይመሰክራል። የጰንጠቆስጤ ዕለት ሌላው ጠቃሚ ማረጋገጫ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ እውነት ባይሆን ኖሮ በዚህ ዕለት ሦስት ሺህ ሰዎችን ለማሳመን እይቻልም ነበር። ይህ የትንሣኤ ቃል አፈ ታሪክ ብቻ ቢሆን ኑሮም እነዚያ ሰዎች ማስረጃውን የመመርመርና የማረጋገጥ ዕድል ነበራቸው። 

ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምታከብረው የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፥ ከምትፈጽመው ሥርዓቶች ደግሞ የጌታ እራትና ይቀርብ የነበረው መባ ሌሎቹ ታሪካዊ ማረጋገጫዎች ናቸው (ሐዋ. 20፡7፤ 1ኛ ቆሮ. 16፡2)። ክርስቶስ ከሞት ባይነሣ ኖሮ። ሐዋርያቱ የተሰደዱና የተገደሉባት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ጸንታ የመኖሯ እውነት ያለ በቂ መግለጫ ይቀር ነበር። የክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤ ነው አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ለሰማያዊ ሥራዋ ብቁ የሚያደርጋት። 

መ. የክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያቶች 

ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ቢያንስ ሰባት ዋና ዋና ምክንያቶችን ለመጥቀስ ይቻላል። 

1. የክርስቶስ ትንሣኤ አማንነቱ የሚመነጭበመሪን(ሐዋ. 2፡24)። 

2. ለዳዊት የተሰጠን ቃል ኪዳን ለመፈጸም (2ኛ ሳሙ. 7፡12-16፤ መዝ. 89፡20-37፤ ኢሳ. 9፡6-7፤ ሉቃስ 1፡31-33፤ ሐዋ. 2፡25-31)። 

3. የትንሣኤ ሕይወትን ለመስጠት (ዮሐ. 10፡10-11፤ 11፡25-26፤ ኤፌ. 2፡6፤ ቆላ. 3፡1-4፤ 1ኛ ዮሐ. 5፡11-12)። 

4. የትንሣኤ ኃይል ምንጭ ለመሆን (ማቴ. 28፡18፤ ኤፌ. 1፡19-21፤ ፊል. 4፡13)። 

5. የቤተ ክርስቲያን ራስ ለመሆን(ኤፌ. 1፡20-23)። 

6. ጽድቃችን ስለተከናወነልን(ሮሜ 4፡25)። 

7. የትንሣኤ በኩርዕመናን(1ኛ ቆሮ. 15፡20-23) ነው። 

ሠ. የክርስቶስ ትንሣኤ ጠቃሚነት 

የክርስቶስ ትንሣኤ ከታሪካዊነቱ የተነሣ የመለኮታዊነቱ ዋና ማረጋገጫ ነው። ትንሣኤው በሞትና በኃጢአት ላይ ታላቅ ድል እንደመሆኑ፥ ኤፌሶን 1፡19-21 ላይ እንደተጠቀሰው የዘመናችን መለኮታዊ ኃይል መለኪያም ነው። ትንሣኤ እንዲህ ያለ ጠቃሚ አስተምህሮ በመሆኑ፥ በዘመናችንም የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ መታሰቢያነት ተለይቷል። ይህ ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሩት ከታዘዙበት የሰባተኛው ቀን የሰንበት ሕግ ይልቃል። ስለዚህ ትንሣኤ ለክርስትና እምነት የማዕዘን ድንጋይ ነው። ጳውሎስ 1ኛ ቆሮ. 15፡17 ውስጥ “ክርስቶስ ካልተነሣማ እምነታችን ከንቱ ነው፤ ገና በኃጢአታችሁ ናችሁ” እንዳለው ትንሣኤውን በእርግጠኛነት እንናገራለን፥ ክርስቶስ ከሞት ስለተነሣ እምነታችን እርግጠኛ፥ ድል አድራጊነቱን እውነት፥ የክርስትና እምነታችንን ደግሞ ፍጹም ያደርገዋል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: