እግዚአብሔር ወልድ፡የምትክነት ሞቱ

ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለዓለም ሁሉ ኃጢአት መሥዋዕትነት መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል። በዚሁ መሠረት መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ሲያስተዋውቅ፡- የዓለምን ሁሉ ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1፡29) ብሏል። ኢየሱስ የሞተው ለሌሎች መሥዋዕትነትና ምትክነት ነው። “ምትክ” የሚለው ቃል በግልጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባይሆንም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአተኞች ምትክ የመሆኑ እውነት ግን በመጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ ተረጋግጧል። ክርስቶስ በምትክነት ሞቱ የማይለካውን እግዚአብሔር በኃጢአተኞች ላይ ያለውን የጽድቅ ፍርድ ተሸከመ። የዚህ የምትክነት ጸጋ ውጤት ግልጥና፥ የተከናወነም ነው። አዳኝ የሆነው ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቁጣ ሊያበርድ በሚችል ሁኔታ በኃጢአተኞች ሳይ የነበረውን መለኮታዊ ፍርድ ተሸክሟል። ሰዎች ይህን የእግዚአብሔር ማዳን ተቀብለው የምሥራቹን እንዲያምኑ፥ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታቸው መሞቱን እንዲገነዘቡ እና እርሱ የግል አዳኛቸው መሆኑን እንዲቀበሉ ተጠይቀዋል። 

“ምትክነት” የሚለው ቃል፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት አማካይነት የተፈጸመውን ሥራ በከፊል ብቻ ይገልጣል። በመሠረቱ ይህን ሥራ የሚገልጥ አጠቃላይ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ አልዋለም። “ሥርየት” የሚለው ቃል ትምህርተ-መለኮት ውስጥ ብዙ ጊዜ አጠቃላይ ገላጭ ሆኖ አገልግሏል። ይሁን እንጂ በብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰ ተመሳሳይ ቃል የሰውም። ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሥርየት ጽንሰ አሳብ ያገለገሰው ኃጢአተኛ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካይነት ኃጢአት ለጊዜው የመሸፈኑን ተግባር ለመግለጥ ነበር። ይህ ድርጊት ለጊዜያዊ ይቅርታ መሠረት ሆኗል። “ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለመተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው” (ሮሜ 3፡25)። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ኃጢአትን ይቅር በማለት ፍጹም በሆነ ጽድቅ ይሠራ ነበር። ኃጢአትን ለጊዜው መሸፈን ብቻ ሳይሆን፥ ለዘላለም የሚያስወግደውንና እንደ መሥዋዕት በግ የሚሆነውን የልጁን መምጣትም አስቀድሞ አቅዷል (ዮሐ. 1፣ 29)። 

ሀ. የልጁ ሞት የሚያከናውናቸው ነገሮች 

የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ሙሉ ዋጋ ለማገናዘብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርከት ያሉ ጠቃሚ እውነቶች ተጎልጠዋል። 

1. የክርስቶስ ምታ እግዚአብሔር ለኃጢአተኞች ያለውን ፍቅር ያረጋግጣል (ዮሐ. 3፡16፤ ሮሜ 5፡8፤ 1ኛ ዮሐ. 3፡16፤ 4፡9)። አማኝ በእግዚአብሔር የመወደዱ እውነት፥ አማኝን የማያምን ሰው በማይችለው ላቅ ያለ ሥነ-ምግባራዊ ኑሮ መኖር የሚጠበቅበት ያደርገዋል (2ኛ ቆሮ. 5፡15፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡11-25)። 

2. የክርስቶስ ምታ፥ ኃጢአተኛውን ከኩነኔ ለመቤዠት የእግዚአብሔር ጻድቅ ፍርድለሚጠይቀው የቤዛነት ዋጋ የተከፈለ ነው ተብሏል። ኃጢአተኛውን ከእግዚአብሔር ጻድቅ ፍርድ ለማዳን የተከፈለ የቤዛነት ዋጋ ነው (ማቴ. 20፡28፤ ማር. 30፡45፤ 1ኛ ጢሞ. 2፡6)። የክርስቶስ ሞት ስለ ኃጢአተኛ የተከፈለ ተገቢ ቅጣት ነበር (ሮሜ 4፡25፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡21፤ ገላ. 1፡4፤ ዕብ. 9፡28)። 

ክርስቶስ ዕዳችንን በመክፈል ነጻ አወጣን። ይህን አሳብ ለመግለጥ ሦስት ጠቃሚ የግሪክ ቃላት አዲስ ኪዳን ውስጥ ተጠቅሰዋል። 

(ሀ) “አጎራዞ፥ “ከበያ መግዛት” ማለት ይሆናል። (“አጎራ ማለት “ገበያ” ነው)። ሰው በኃጢአቱ ሳቢያ ከሞት ፍርድ በታች እንደሆነ ተቆጥሯል (ዮሐ. 3፡18-19፤ ሮሜ 6፡23)፥ ማለት “ለኃጢአት የተሸጠ” ባሪያ (ሮሜ 3፡14) ሆኗል። ነገር ግን የመቤዥት ተግባር በሆነውና የኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካይነት ተገዝቷል (1ኛ ቆሮ. 6፡20፤ 7፡23፤ 2ኛ ጴጥ. 2፡1፤ ራዕይ 5:9፤ 14፡3-4)። 

(ለ) “ኤክሳጎራዞ”፥ “ጎዝቶ ከገበያ ማውጣት” ማለት ሲሆን፥ አሳቡ መግዛት ብቻ ሳይሆን፥ ከግብይት ማውጣትንም ያካትታል (ገላ. 3፡13፤ 4፡5፤ ኤፌ. 5፡16፤ ቆላ. 4፡5)፤ አባባሉ ነጻ የማውጣቱ ተግባር ለዘላለም መሆኑንን ያመለክታል። 

(ሐ) “ሉትሮ፥ “መፍታት” ወይም “በነጻ መልቀቅ” (ሉቃስ 24፡21 ፤ ቲቶ 2፡14፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡18) ማለት ነው። ይህ ቃል ባሪያን ነጻ ማድረግን ያመለክታል (ሉቃስ 21:28፤ ሮሜ 3፡24፤ 8፡23፤ 1ኛ ቆሮ. 1፡30፤ ኤፌ. 1፡7፥ 14፤ 4፡30፤ ቆላ. 1፡14፤ ዕብ. 9፡15፤ 11፡35)። በዚሁ መሠረት መቤዥት የሚለው አሳብ፥ መግዛትን፥ ከግብይት ማውጣትን እና የተቤዠውን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት፥ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ፍጹም ነጻ ማውጣትን ይጨምራል። 

የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለኃጢአት የቀረበ መሥዋዕት ነው። መሥዋዕቱ በብሉይ ኪዳን ዘመን ይቀርብ እንደነበረውና ኃጢአትን ለጊዜው እንደሚሸፍነው፥ እንዲሁም የጽድቅን ፍርድ ያዘገይ እንደነበረው የእንስሳት መሥዋዕት ዓይነት አልነበረም። ክርስቶስ በመሥዋዕትነቱ ኃጢአታችንን ለዘላለም ተሸክሟል (ኢሳ. 53፡7-12፤ ዮሐ. 1፡29፤ 1ኛ ቆሮ. 5፡7፤ ኤፌ. 5 ፡2፤ ዕብ. 9፡22፥ 26፤ 10፡14)። 

3. የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት፥ ኃጢአተኞች ለተላለፉት ሕግ ጋን ለመክፈል የታዛዥነት ተግባር ነው። ይህ መታዘዝ ኃጢአተኛ በበደሉ ምክንያት ይቀበሰው የነበረውን የእግዚአብሔር ፍጹም ፍርድ ያሟላል። ሄላስቴሪዮን” የሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን፥ ማስተሥረያውን (ዕብ. 9፡5) ማለትም ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የነበረና በታቦቱ ውስጥ የነበረውን ሕግ የሸፈነ ኪዳንን የሚያመለክት ነው። ሰሥርየት ዕለት (ዘሌዋ. 16፡14) ማስተሥረያው ላይ ከመሠዊያው የተወሰደ ደም ይረጭበታል፤ ይህ ክንውን የፍርድን ዙፋን ወደ ምህረት ዙፋንነት ይቀይረዋል (ዕብ. 9፡11-15)። በተመሳሳይ ሁኔታ የእግዚአብሔር ዙፋን በኢየሱስ ክርስቶስ የማስተሥረይ ሥራ የጸጋ ዙፋን ይሆናል (ዕብ. 4፡14-16)። 

የዚህ ቃል ተመሳሳይ የሆነውና ሂላስሞስ የሚለው የግሪክ ቃል የማስተሥረይን ተግባር ይገልጣል (1ኛ ዮሐ. 2፡2፤ 4፡10)። ትርጉሙ ክርስቶስ በመስቀል ሞቱ አማካይነት እግዚአብሔር ከሰው ኃጢእት የሚጠይቀውን ዋጋ (ሞት) ፍጹም በሆነ መንገድ አርክቷል ማለት ነው። ሮሜ 3፡25-26 ውስጥ እንደተገለጠው፥ እግዚአብሔር ኃጢአትን ይቅር በማለቱ ጳድቅ ተብሏል። ይህ በመስቀሉ ፊት የሚደረግ ይቅርታ፥ በመጨረሻ ጊዜ ክርስቶስ በሞቱ የጽድቅን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ የሚያረካ የመሆኑ መሠረት ነበር። በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ኃጢአተኛን በመቅጣት የሚረካ ሆኖ አልታየም። ይልቁንም የፍቅር አምላክ ስለሆነ ኃጢአተኛውን ይቅር በማለት ደስ የሚሰኝ መሆኑ ተገልጧል። የሥርየትና የመቤዥት ተግባር፥ በክርስቶስ ለሚያምን ሰው ሁሉ ዕዳው ሙሉ ለሙሉ እንደተከፈለለት፥ ከኃጢአት ባርነት ነጻ መውጣቱ እና ኃጢአተኛ ይደርስበት የነበረ የእግዚአብሔር ቁጣ ሙሉ ለሙሉ የቀረለት መሆኑን ያረጋግጣል። 

4. የክርስቶስ ምት ኃጢአተኛውን የዋጀና ሥርየት ያመጣለት ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን ያረካና ዓለም ከእርሱ ጋር የታረቀበት መሠረትም ነው። ካታላሶ፡የሚለውና “ማስታረቅ” የሚል ትርጉም ያለው የግሪክ ቃል ሰውን ሙሉ በሙሉ መለወጥ ከእግዚአብሔር ጋር ማገናኘት የሚል አሳብ አለው። ይህ ማስታረቅ የሚል ቃል አዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ቦታ ተጠቅሷል (ሮሜ 5፡10-11፤ 11፡15፤ 1ኛ ቆሮ. 7፡11፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡18-20፤ ኤፌ. 2፡16፤ ቆላ. 1፡20-21)። መታረቅ በሚለው ቃል ውስጥ ያለው ፅንሰ-አሳብ፥ እግዚአብሔር ይለወጣል ማለት ሳይሆን፥ በክርስቶስ ነጻ የማድረግ ሥራ አማካይነት ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት ይቀየራል ማለት ነው። ሰው ነው ይቅር የተባለ፥ የጸደቀ እና ከእግዚአብሔር ጋር ሊታረቅ በሚችልበት ደረጃ በመንፈስ ካፍ ያስ። አሳቡ የሚገልጠው እግዚአብሔር ከኃጢአተኛ ጋር መታረቁን ማለትም ከኃጢአተኝነት ጋር መስማማቱ ሳይሆን፥ ኃጢአተኛው ከእግዚአብሔር ቅዱስ ባሕርይ ጋር እንዲስተካከል መደረጉን ነው። እግዚአብሔር ዓለምን በሞላ ነጻ እንዳደረገና ለኃጢአት ሁሉ ሥርየትን እንደሰጠ፥ እርቅም እንዲሁ የተሰጠ ነው፤ ሆኖም ዓለም ሁሉ ይህን እልተጠቀመበትም (2ኛ ቆሮ. 5፡19፤ 2ኛ ጴጥ. 2፡1፤ 1ኛ ዮሐ. 2 ፡1-2)። ይህ የእግዚአብሔር መቤዥት አስደናቂ ስጦታ ከሁሉ የላቀ ዋጋ ያለው ነው። ሥርየትና የማስታረቅ ሥራም እንዲሁ ናቸው፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን፥ እግዚአብሔር በዚህ ስጦታው አማካይነት ከዓለም ጋር ይታረቃል(2ኛ ቆሮ. 5፡18-19፤ ኤፌ. 2፡16)። 

5. በክርስቶስ ምት የሰውን ልጅ ከውድቀቱ የሚያመጣ የኃጢአት ዕዳ ተከፍሏል። በዚሁ መሠረት እግዚአብሔር የሥርየት ዋጋን በመከፈል ሰውን ከራሱ ጋር አስታርቋል። ከእንግዲህ ወዲህ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ የሚያምን ሰው ሁሉ እግዚአብሔር እንዳይቀበለው የሚያደርግ አንዳች እንቅፋት የለበትም (ሮሜ 3፡26)። ዓለማት ተሰብስበው ከሚያከናውኑት ነገር ሁሉ ይልቅ እግዚአብሔርን ያረካ የክርስቶስ ሞት ነው። በመሆኑም ይህ እርካታ የእግዚአብሔር ቅድስና ከኃጢአተኞች የሚፈልገውን ዋጋ በመክፈል ፍቅርና ኃይሉን እንዲለግስ አድርጎታል። 

6. ክርስቶስ በሞቱ የኃጢአተኞችን ቅጣት ሰመሸከም የእነሱ ምትክ ሆኗል (ዘሌዋ. 16፡21፤ ኢሳ. 53፡6፤ ማቴ. 20፡28፤ ሉቃስ 22 ፡37፤ ዮሐ. 10፡11፤ ሮሜ 5፡6-8፤ 1ኛ ጴጥ. 3፡18)። ይህ እውነት ለድነት ወደ እግዚአብሔር ለሚቀርቡ ሁሉ የዋስትና መሠረት ነውዬ ማንኛውም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረው ግንኙነት ኃጢአትን አስመልክቶ ያለውን ጥያቄ ሁሉ የሚፈታ እውነትም ነው። ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ ሞቷል የሚለው አጠቃላይ እምነት በቂ አይደለም። ክርስቶስ ኃጢአቴን ተሸክሟል የሚል የግል እምነት ያስፈልጋል፤ ይህም ዕረፍት ደስታና እርካታን ያስገኛል (ሮሜ 15፡13፤ ዕብ. 9፡14፤ 10፡2)። ድነት በክርስቶስ ለሚያምን ሁሉ በቅጽበት የሚሰጥ የእግዚአብሔር ኃያል ሥራ ነው። 

ለ. የወልድን ሞት አስመልክቶ ያለ የተሳሳተ ግንዛቤ 

የክርስቶስ ሞት ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ ትርጉም ይሰጠዋል። ክርስቲያን ሁሉ እነዚህን ዛሬ እየሰፉ የመጡ ስሕተተኛ ገለጣዎችን በሚገባ መረዳት አለበት። 

1. እግዚእብሔር የበደለውን ኃጢአት በንጹሑ ሰው ላይ እያኖርም ከሚለው እሳብ በመነሣት የምትክነት ወይም የቤዛነት ሥራ ተገቢ አይደለም ተብሏል። ክርስቶስ ፈቃደኛ ያልሆነ በደል ተሸካሚ ሲሆን ኑሮ ይህ አገላለጥ ምናልባት ልክ ይሆን ይሆናል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጠው፥ ክርስቶስ በሙሉ አሳብ ለአባቱ ፈቃድ የታዘዘና በዘላለም ፍቅር ያደረገው መሆኑን ነው (ዮሐ. 13፡1፤ ዕብ. 10፡7)። በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር አብ ራሱ ነበር በማይመረመር ጥበቡ በክርስቶስ በኩል ዓለምን ከራሱ ጋር ያስታርቅ የነበረው (2ኛ ቆሮ. 5፡19)። ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በፍጹም ፍቅርና መሥዋዕት አማካይነት ቅድስናው የሚጠይቀው ፍርድ ይሞላ ዘንድ ቅጣቱን በራሱ መሸከሙን ይህ ያሳያል። 

2. ክርስቶስ በሰማዕትነት ሞተ የሚሉ ክፍሎች አሉ። የሞቱንም ፋይዳ ለእምነቱ የተከፈለ የደፋርነትና የታማኝነት አርአያነት እንደሆነ ይቆጥሩታል። ለዚህ የተሳሳተ አመለካከት በቂ መልስ አለ። ይኸውም፥ ክርስቶስ ለመሥዋዕትነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ በግ ስለሆነ፥ ማንም ሕይወቱን አልወሰደበትም (ዮሐ. 10፡18፤ ሐዋ. 2፡23)። 

3. ክርስቶስ የሞተው የመልካም ሥነ-ምግባር አርአያ ለመሆን ነው የሚሉም አሉ። እንደነሱ አባባል የክርስቶስ መስቀል የሚያመለክተው፥ መለኮታዊውን የኃጢአት ዋጋ በመሆኑ፥ ይህን የሚረዱ ሰዎች ከኃጢአተኛነት ይቆጠባሉ። ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ይህ ፅንሰ-አሳብ፥ እግዚአብሔር በአሁኑ ጊዜ ሰውን ከነበረበት ሁኔታ ላማሻሻል እንደሚፈልግ ያምናል። እውነቱ ግን የክርስቶስ መስቀል የዳግም ልደት መሠረት መሆኑ ነው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: