እግዚአብሔር ወልድ፡- ለቅዱሳኑ መምጣቱ

ሀ. ያልተፈጸመ ትንቢት 

በዚህ ምዕራፍ የተመረጠው አስተምህሮ እጅግ ጠቃሚ ከሆኑት ያልተፈጸመ ትንቢት ጉዳዮች አንዱ ነው። የዚህ ጽሑፍ አንባቢ ሊረዳው የሚገባ ነገር፥ ትንቢት እግዚአብሔር አስቀድሞ የተናገረውና በጽሑፍ የሰፈረ ታሪክ መሆኑን ነው። ስለዚህ እንደ ማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይታመናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍ አንድ አራተኛ የሚሆነው ከፍሉ በትንቢት መልክ ነበር። ብዙው ትንቢት ተፈጽሟል፥ እያንዳንዱ ፍጻሜ ልክ በትንቢት እንደተነገረው ነው። ከልደቱ ብዙ ዓመታት በፊት እንደተተነበየው ክርስቶስ የመጣው ከይሁዳ ነገድ፡ከአብርሃም ልጅ፥ ከዳዊት ልጅ፥ ቤተልሔም ውስጥ ከአንዲት ድንግል በመወሰድ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የአሟሟቱ ዝርዝር መዝሙረ ዳዊት ውስጥ ከሺህ ዓመታት በፊት በተተነበየው መሠረት በትክክል ተፈጽሟል። 

የእግዚአብሔር ቃል በአሁኑ ጊዜ ያልተፈጸሙ ብዙ ትንቢቶች አሉት። ስለሆነም ትንቢቶቹ በአሁኑ ጊዜ እንዳሉት እንደ ሌሎቹ የእግዚአብሔር ሥራዎች ሁሉ ያለጥርጥር እንደሚፈጸሙ ማመኑ ተገቢና እግዚአብሔርንም በእምነት ማክበር ነው። 

ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ ወደ ሰማይ በሄደበት አኳኋን፥ “ይህ…ኢየሱስ” በዕረገበት አካሉና በደመናት ታጅቦ (ሐዋ. 1፡11) የሚመለስ መሆኑ በትንቢት ቃሎች በሚገባና በስፋት ተገልጧል። በታላላቅ የክርስትና እምነት መግለጫዎች ውስጥም ታክሏል። ይህ እውን ቢሆንም፥ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት አስተምህሮ ልዩ ጥንቃቄ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። 

ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትንቢትን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጋር በተዛመደ አኳኋን ሲመለከቱ፥ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያኑ መምጣቱን (የአማኞች ወደ ሰማይ መነጠቅ) እና ግልጥ ከሆነው ዳግም ምጽአት (መንግሥቱን ለመመሥረት እና ለሺህ ዓመታት ለመግዛት ከቅዱሳኑ ጋር ከመምጣቱ) ይለያዩታል። በነዚህ ሁለት ክንውኖች መካከል ብዙ ዋና ዋና ክስተቶች ይታያሉ፤ የዓለም አቀፊቱ ቤተ ክርስቲያን ብቅ ማለት፥ በአምባገነን መሪ የሚተዳደር ዓለም አቀፍ መንግሥት መመሥረት፥ እና እጅግ አሠቃቂ ጦርነቶች መቀስቀሳቸው የሚጠቀሱ ናቸው። እርሱ መንግሥቱን ሊያቆም እስኪመጣ ጦርነቶቹ ይካሄዳሉ። ትንቢቶች ቃል በቃል ከተተረጎሙ የሚኖረው ቅደም ተከተል በመጀመሪያ ከርስቶስ ለቤተ ክርስቲያኑ የመምጣቱ ክንውን ነው። 

ምንም እንኳን ከቤተ ክርስቲያን መነጠቅ በኋላ የፍጻሜው ዘመን ክንውኖች በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ትንቢቶች ቢጠቀሱ፥ ክርስቶስ መጀመሪያ ለቤተ ክርስቲያኑ የመምጣቱ እውነት መጀመሪያ ብሉይ ኪዳን ውስጥ አልተገለጠም፤ የአዲስ ኪዳን ትንቢት ነው፡፡

ለ. ስለ መነጠቅ የተነገሩ ትንቢቶች 

ክርስቶስ ከፍጻሜው ዘመን ክንውኖች በፊት ለቅዱሳኑ የመምጣቱን መገለጥ፥ በመሰቀሉ ዕለት ዋዜማ በላይኛው ክፍል ውስጥ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። ዮሐንስ 14:2-3 ውስጥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፡- “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ”። 

ደቀ መዛሙርቱ ያን ትንቢት ለመስማት ፈጽሞ የተዘጋጁ አልነበሩም። ማቴዎስ 24፡26-31 ውስጥ ክርስቶስ መንግሥቱን ለመመሥረት ዳግም በክብር ስለመምጣቱ ተነግሯቸዋል። እስከዚያች ሰዓት ድረስ ከርስቶስ መጀመሪያ ወደ ሰማይ እንደሚወስዳቸውና በመጨረሻው ዘመን ከሚፈጸሙ ክፉ ነገሮች እንደሚጠብቃቸው ደቀ መዛሙርቱ አልተገነዘቡም ነበር። ዮሐንስ 14 ውስጥ እንደተጠቀሰው ክርስቶስ ስፍራ ሊያዘጋጅላቸው የሚሄድበት የአብ መኖሪያ በሰማይ መሆኑ ግልጥ ነው። ስፍራ ካዘጋጀ በኋላ ሊወስዳቸው እንደሚመለስ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ዓላማው ደቀ መዛሙርቱን ከምድር ወደ አባቱ ቤት መውሰድ ነው። ይህን ተስፋ ሐዋርያው ጳውሎስ በዝርዝር ገልጿል። 

ጳውሎስ በቅዱሳን ትንሣኤና ክርስቶስ በምድር ላሉት ቅዱሳን በመምጣቱ መካከል ስላለው ጉዳይ የተሰሎንቄ ሰዎች ለነበራቸው ጥያቄ መልስ ሲጽፍ የዚህን ታላቅ ክንውን ዝርዝር ገልጧል (1ኛ ተሰ. 4፡13-18)። ከ16-17 ባሉት ቁጥሮች እንዲህ ብሏል፡- “በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፥ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን”። 

የክርስቶስ ለቅዱሳኑ መምጣት ሁኔታዎች ቅደም ተከተል የሚጀምረው ክርስቶስ ከዙፋኑ ተነሥቶ ከምድር በላይ ወዳለው አየር ሲወርድ ነው። ሲመጣ ድምፅ ይሰጣል። ያም ድምፅ የትእዛዝ ድምፅ” ነው። ይህ ሁኔታ በመላእክት አለቃ ሰሚካኤል የድል ድምፅና የእግዚአብሔር መለኮት ይታጀባል። ሙታን ክርስቲያኖች የክርስቶስን ድምፅ በመታዘዝ ( ዮሐ. 5፡28-29) ከመቃብር ይነሣሉ። ሰiኛ ተሰሎንቄ 4፡14 ላይ እንደተጠቀሰው የሙታኑ ነፍሳት ክርስቶስን ያጅቡታል። ምክንያቱም ቃሉ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋል” ይላልና። እነዚህ ነፍሳት ጌታን አጅበው ከመጡ በኋላ መቃብር ውስጥ ከነበረውና ከሚያርገው አካላቸው ጋር ይገናኛሉ። በክርስቶስ ያንቀላፉት (የሞቱት) ከተነሣ በኋላ፥ በሕይወት ያሉት ክርስቲያኖች “ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና ይነጠቃሉ”። በዚህ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን ከምድር ትወሰድና፥ በአብ ዘንድ በመኖር ዮሐንስ 14 ውስጥ የተጠቀሰውን ተስፋ ትፈጽማለች። 

ተጨማሪ ዝርዝር 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-58 ውስጥ ተሰጥቷል። ጌታ ለቤተ ክርስቲያኑ የሚመጣበት ሁኔታም “ምስጢር” ተብሏል። ይህ ማለት፥ እውነታው በብሉይ የተሸሽገና በአዲስ ኪዳን የተገለጠ ነው ለማለት ነው (ሮሜ 16፡25-26፤ ቈላ. 1፡26)። ክርስቶስ መንግሥቱን በምድር ለመመሥረት የመምጣቱ እውነት በብሉይ ኪዳን የተገለጠ ሲሆን፥ ንጥቀት ግን በአዲስ ኪዳን ብቻ ነው የተገለጠው። ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ውስጥ ክንውኑ ወዲያውኑ “ሰቅፅበተ ዓይን” እንደሚሆን ገልጧል። የሙታኑ አካል የማይበሰብስ፥ የማያረጅና የማይሞት ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 15፡53)። 

አዲሱ አካላችን ኃጢአት አልባ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያስረዳል (ኤፌ. 5፡27፤ ፈልጵ. 3፡20-21)። በመቃብርም ሆነ በሕይወት ያሉት አካላት ለመንግሥተ ሰማያት የሚስማሙ አይደሉም። ለዚህ ነው ጳውሎስ “እኛ ሁላችንም እንለወጣለን” (1ኛ ቆሮ. 15፡51) ያለው። ከቤተ ክርስቲያን (አማኞች) ትንሣኤና መነጠቅ ጋር ሲነጻጸር፥ ከጰንጠቆስጤ ዕለት በፊት የሞቱ፥ ወይም ከመነጠቅ ክንውን በኋላ የሚሞቱ ቅዱሳን ትንሣኤና ንጥቀት ክርስቶስ መንግሥቱን ሊመሠርት እስኪመባ ይዘገያል (ዳን. 12፡1-2፤ ራእይ 20፡4)። ኃጢአተኞች ግን እስከ ክርስቶስ የሺህ ዓመታት አገዛዝ ፍጻሜ ድረስ አይነሡም (ራእይ 20፡5-6፥ 12-13)። 

ሐ. ክርስቶስ ለቅዱሳኑ መምጣቱ እና ከቅዱሳኑ ጋር መምጣቱ ሲነጻጸሩ። 

መነጠቁ የሚከናወነው ከፍጻሜው ጊዜ ቀድሞ ነው የሚለው አስተምህሮ፥ ቅድመ ፍዳ አመለካከት ይባላል። ከዚህ ጋር የሚነጻጸረው ሌላ አመለካከት ደግሞ ድኅረ ፍዳ ዘመን የተሰኘው ሲሆን፥ የክርስቶስን ለቅዱሳኑና ከቅዱሳኑ ጋር መምጣት እንደ አንድ ክንውን የሚያይ ነው። ከነዚህ ሁለት አመለካከቶች የቱ ነው ትክክል ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሆነው፥ ትንቢትን በትክክል የመተርጎሙ ውጤት ይሆናል። 

በሁለቱ ክንውኖች መካከል አንዳንድ ልዩነቶች ይታያሉ። 

1, ክርስቶስ ቅዱሳኑን በሰማይ ወዳለ አባቱ ቤት ለመውሰድ የመምጣቱ ሂደት፥ ከምድር ወደ ሰማይ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሲሆን፥ ከቅዱሳኑ ጋር የመምጣቱ ክንውን ግን ከሰማይ ወደ ምድር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። ይህም ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተገልጦ መንግሥቱን የሚመሠርትበት ጊዜ ይሆናል። 

2. በሕይወት ያሉ ቅዱሳን በሙሉ በመነጠቅ ጊዜ ቀሚለወጡ ሲሆን፥ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ግን ቅዱሳን አይለወጡም። 

3. በመነጠቅ ጊዜ ቅዱሳን ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሲሆን፥ በዳግም ምጽአቱ ግን ሳይለወጡ በምድር ላይ ይኖራሉ። 

4. በመነጠቅ ጊዜ ዓለም የማይለወጥና የማይፈረድበት ሆኖ በኃጢአቱ ይቀጥላል፥ በዳግም ምጽአት ግን ይፈረድበታል፥ ጽድቅም በምድር ላይ ይመሠረታል። 

5. ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀሙ ከሚመጣው የቁጣ ቀን ለመሳኝ ሲሆን፥ ዳግም ምጽአቱ ግን በክርስቶስ በማመን በመከራው ጊዜ ሁሉ ታግሠው የቆዩትን ለማዳን ነው። 

6. መነጠቅ ሳይታሰብና በቅፅበት ሊሆን እንደሚችል የተገለጠ ሲግ፥ ዳግም ምጽአቱ ግን ብዙ ምልክቶችና ድርጊቶችን ተከትሎ የሚፈጸም ይሆናል። 

7. መነጠቅ በአዲስ ኪዳን ብቻ የተገለጠ እውነት ሲሆን፥ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ግን በቅድሚያ ሊከናወኑ ካሉ ምልክቶችና ሁኔታዎች ጋር በብሉይም በአዲስም የተጠቀሰ እውነት ነው። 

8. መነጠቅ የዳኑትን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፥ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ግን ሁለቱንም ማለት የዳኑትንና ያልዳኑትን ይመለከታል። 

9. በመነጠቀ ጊዜ ሰይጣን ስለማይታሰር በቀጣዮቹ ጊዜያት ከበፊቱ ይልቅ ይበረታል። በዳግም ምጽእት ግን ይታሰራል። ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ይጠበቃል፥ ይከለከላል። 

10. መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ስተመሠረተችበት ወቅትና ስመነጠቋ መካከል ይህ እንዲከናወን የግድ መፈጸም ያለበት ትንቢት የለም። ንጥቀት ቅፅበታዊ ነገር ነው። ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ቀደም ብሎ ግን መፈጸም የሚገባቸው ብዙ ምልክቶች አሉ። 

11. ክርስቶስ መንግሥቱን ለመመሥረት ወደ ምድር በሚመጣበትና ከቅዱሳን መነጠቅ ጋር በተያያዘ ሁኔታ፥ የሕያዋን ቅዱሳን በዚያው ጊዜ መለውጥ በብሉይም ሆን በአዲስ ኪዳን አልተጠቀሰም። እንደውም ሕያው ቅዱሳን በሺሁ ዓመት መንግሥት ውስጥ ለማገልገል በተፈጥሮ አካላቸው መኖር ስላለባቸው ይህ ዓይነቱ አስተምህሮ የማይሆን ነገር ነው። 

12. የክርስቶስን ወደ ምድር መምሰስ በሚገልጠው ቅደም ተከተል ውስጥ ንጥቀትን የሚመስል ሌላ ክንውን የለም። በማቴዎስ 25፡31-46 መሠረት ከክርስቶስ መመለስ ቀጥሎ በመጣው የፍርድ ወቅት እማኞችና የማያምኑ ሰዎች ተደባልቀዋል። በመሆኑም ክርስቶስ ወደ ምድር በሚመለስበት ወቅት የዳኑትን ካልዳኑት የሚለይ መነጠቅ፥ ወይም ሌላ መለያ አልተከናወነም። 

13. ክርስቶስ መንግሥቱን ለመመሥረት መምጣኝ፥ እንዲሁም ከዚያ ቀድመውና ተከትለው የሚከናወኑ ነገሮችን የሚገልጠውን አስተምህሮ ማጥናት፥ ክንውኖቹ ቤተ ክርስቲያንን ሳይሆን እስራኤልንና፥ ያመኑ አሕዛብን እንዲሁም ያላመኑ አሕዛብን የሚመለከቱ መሆናቸውን በግልጥ ለመገንዘብ ይረዳል። ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ምዕራፍ ይገለጣል። 

የኢየሱስ ክርስቶስ ባልተጠበቀ ጊዜ ወይም ድንገት ለቤተ ክርስቲያኑ መምጣት ነቅተን እንድንኖር የሚያደርገን እውነት ነው። የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች 1ኛ ተሰሎንቄ 1 ፡10 ውስጥ “ከሙታን ያስነሣውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቁጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ” ተብሎ ተነግሯቸዋል። ተስፋቸው በፍዳው ውስጥ ማለፋቸው ሳይሆን፥ በምድር ላይ ሊዘንብ ካለው የእግዚአብሔር ቁጣ መዳን ነው (1ኛ ተሰ. 5፡9፤ ራእይ 6፡17)። እዲስ ኪዳን ውስጥ እንደተገለጠው፥ መነጠቅ አጽናኝ ተስፋ ዮሐ. 14፡1-3፤ 1ኛ ተሰ. 4፡18)፥ የሚያነጻ ተስፋ (1ኛ ዮሐ. 3፡1 -3) እና የተሳረከ ወይም የደስታ ተስፋ (ቲቶ 2፡13) ነው። ክርስቶስ መንግሥቱን ምድር ላይ ለመመሥረት እስከሚመጣ ድረስ ዓለም አያየውም፤ ክርስቲያኖች ግን በመነጠቅ ጊዜ በክብሩ ያዩታል። ያም ጊዜ “የታላቁን አምላካችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ” የሚመለከቱበት ይሆናል (ቲቶ 2: 13)።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: