ከኃጢአት ኃይል ነጻ መውጣት

ሀ. ከኃጢአት ነጻ መሆን ለክርስቲያኖች ብቻ 

ከኃጢአት ኃይል ነጻነት፥ እግዚአብሔር ከኃጢአት በደልና ቅጣት ላዳናቸው ሰዎች የተሰጠ ምሕረት እንደመሆኑ፥ ይህ ትምህርት ክርስቲያኖችን ብቻ የሚመለከት ይሆናል። ክርስቲያኖች በክርስቶስ የዳኑና ዋስትና ያገኙ ቢሆኑም፥ ኃጢአታዊ ባሕርይ ስላላቸው፥ ኃጢአት ይሠራሉ። ይህን እውነት በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃልም ሆነ ሰብአዊ ልምድ አያሌ ማረጋገጫ ይሰጣሉ። ክርስቲያኖች ኃጢአት ይሠራሉ በሚለው እውነት ላይ በመመሥረት፥ ከዚህ የኃጢአት ድርጊት ነጻ ለመሆን ይቻል ዘንድ ከመለኮት የተሰጠውን መንገድ አዲስ ኪዳን ይገልጣል። 

ክርስቲያን ኃጢአት አይሠራም ወይም ለኃጢአት አይጋለጥም ከሚለው ስሕተት የተነሣ ብዙ አዲስ አማኞች ግራ ይጋባሉ፥ ይጨነቃሉም። ኃጢአት በሕይወታቸው የሚኖረውን ኃይል ሲገነዘቡም ድነታቸውን እስከመጠራጠር ይደርሳሉ። ኃጢአት የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያስቆጣ ስለሆነ፥ ስለ ኃጢአት መጨነቃቸው መልካም ነው። ታዲያ ድነትን ከመጠራጠር ወይም ለኃጢአት እጅን ከመስጠት ይልቅ፥ ነጻ የመሆኛ መንገድ የሆነውን የእግዚአብሔር የምሕረት ስጦታ መማር አለባቸው። 

ከድነት መንገድ ቀጥሎ ሰብአዊ አእምሮ ሊገነዘበው የሚገባ ጭብጥ፥ መለኮታዊ ዕቅድ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ክብር እንዲኖር ነው። ይህን ከመገንዘብ የሚበልጥ ጠቃሚ ነገር የለም። አለማወቅና ስሕተት እሳዛኝ መንፈሳዊ ውድቀትን ያስከትል ይሆናል። ወንጌል በሚሰበክበት ጊዜ ከኃጢአት ኃይል ነጻ መውጣትን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትክክለኛ ገለጣ መስጠቱ እጅግ ያስፈልጋል። 

ለ. የኃጢአት ችግር በክርስቲያን ሕይወት 

ማንኛውም በእምነት የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው መለኮታዊ ተፈጥሮን የተቀበለ ቢሆንም (2ኛ ጴጥ. 1፡4)፥ አሮጌው ተፈጥሮም አብሮት ስላለ ሁለት ተፈጥሮዎች አሉት ለማለት ይቻላል። አንደኛው ኃጢአት ለመሥራት የማይችል፥ ሌላው ቅዱስ ሊሆን የማይችል ናቸው። አሮጌው ተፈጥሮ አንዳንድ ጊዜ “ኃጢአት” ይሚባለው (የኃጢአት ምንጭ ለማለት ነው) እና “አሮጌው ሰው”ን የሥጋ አንዱ አካል ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አገላለጥ “ሥጋ” የሚለው ቃል ሥነ-ምግባራዊ ሁኔታን ለመግለጥ ሲውል፥ መንፈስንና ነፍስን እንዲሁም እካልን ያመለክታል። ይህ በተለይ የሚያገለግለው፥ ዳግም ያልተወለደን ሰው በሚመለከት ነው። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ የሚለው፡- 

በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና” (ሮሜ 7፡18)። በሌላ በኩል ሐዋርያው ዮሐንስ ስላገኘነው መለኮታዊ ተፈጥሮ ሲናገር፥ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፥ ከእግዚአብሔር ተወልደልና” (1ኛ ዮሐ. 3፡9) ይላል። ይህ ምንባብ የሚያስተምረው፥ ማንኛውም ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የተወለደ እንደመሆኑ፥ ኃጢእት የማያደርግ ወይም በኃጢአት ድርጊቱ የማይቀጥል መሆኑን ነው። “አያደርግም” በሚል ቃል የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ግሥ የአሁን ጊዜንና የሚቀጥልን አሳብ ያዘለ ነው። ይሁን እንጂ፥ ይሄው የዮሐንስ መልእክት ማንኛውም የእግዚአብሔር ልጅ የሆን ክርስቲያን ኃጢአታዊ ተፈጥሮ የለኝም እንዳይል (1፡8)፥ ወይም ኃጢአት አልሠራሁም እንዳይል (1፡10) ያስጠነቅቃል። 

በአማኙ ውስጥ ያሉ እነዚህ ሁለት የድርጊት ምንጮች ገላትያ 5፡17 ውስጥም ተጠቅሰዋል። እዚያ እንደተጠቀሰው መንፈስ ቅዱስና ሥጋ ሁልጊዜ ይቃረናሉ። “ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህ እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ።” ሐዋርያው የሚጽፈው በጣም መንፈሳዊ ስለሆነው እንጂ ስለ ሥጋዊ ክርስቲያን አይደለም፤ ይልቁንም የሥጋን ምኞት ለማይፈጽመው (5 ፡16) ነው። እንዲህ ባለው ክርስቲያን ውስጥ እነዚህ የሥጋና የመንፈስ ተቃርኖዎች አሉ። እንዲህ ያለው ሰው ከሥጋ ምኞት ነጻ ቢሆን እንኳ፥ እንዲያ ሊሆን የቻለው በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ስለሚመላለስ ነው። 

ሐ. ሕግ እንደ ሕይወት መመሪያነት 

ከኃጢአት ነጻ ማድረጊያ የሆነውን የእግዚአብሔር ፕሮግራም ከመረዳት ጋር፥ እንደ ሕይወት መመሪያነታቸው በሕግና በጸጋ መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘቡ ተገቢ ነው። “ሕግ” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያየ ግንዛቤ ጥቅም ላይ ውሏል። አንዳንዴ እንደ ሕይወት መመሪያ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ ሁኔታ በሚያገለግልበት ጊዜ የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። 

1. በድንጋይ ጽላት ላይ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉት አሠርቱ ትእዛዛት (ዘጸ . 31፡18)። 

2. በምድሪቱ ውስጥ የነበረ የእስራኤል መንግሥት ጠቅላላ እሠራር፤ ትእዛዛቱን ጨምሮ (ዘዳ. 20፡1-26)፥ ፍርዶቹ (ዘዳ. 21፡1-24፡11)፥ እና ሥርዓት (ዘዳ. 24 ፡12-31 ፡18)። 

3. የሕግና የነቢያት ፍጻሜ የተባሉትና ወደፊት በምድር የሚመሠረተው የመሢሑ መንግሥት መተዳደሪያ መርሆች(ማቴ. 5፡1-7፡29፤ በተለይ 5፡17-18፤ 7፡12)። 

4. ማናቸውም ለሰው የተገለጡ የእግዚአብሔር ፈቃዶች (ሮሜ 7፡22፥ 25፤ 8፡4)። 

5. ሰዎች ለመንግሥታቸው አስተዳደር ያወጧቸው ሕግጋት (ማቴ. 20፡15፤ ሉቃስ 20፡22፤ 2ኛ ጢሞ. 2፡5)። “ሕግ” የሚለው ቃል ለጥቂት ጊዜ በሥራ ሳይ የሚውል ኃይል ሆኖም አገልግሏል (ሮሜ 7፡21፤ 8፡2)። 

6. “ሕግ” ሱብሉይ ኪዳን ውስጥ በተለይ በድርጊት እንደሚገለጥ ኪዳን ተደርጎ ቀርቧል። በዚህ ግንዛቤ መሠረት የሕግ ከልሉ በሥነ ጽሑፍ ከሰፈረው የሙሴ ሥርዓትና ከመንግሥቱ ሕግ የሰፋ ሆኗል። ይህ ብቻም ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር መልካም አጸፋን ለማግኘት ሲባል የሚደረገውን ማንኛውንም ሰብእዊ ሙከራ (በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ሆነም አልሆነ ይጨምራል። የሕግ መመሪያ “መልካም ብታደርግ እባርክሃለሁ” ይላል። ስለዚህ አንድ ሰው ሕግን የሚፈጽመው መልካም ነገርን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያገኘ መሆኑን በመገንዘብ መሆኑ ቀርቶ፥ በራሱ መልካም ሥራ የእግዚአብሔር ሰው ለመሆን ከሆነ፥ ድርጊቱ ሙሉ በሙሉ በሕግ ለመዳን የሚደረግ ጥረት ይሆናል። 

1. ሕግ በሥጋ የመደገፍ መመሪያ ሆኖም ቀርቧል። ሕግ አክባሪዎቹ የሰጣቸው ምንም ጉልበት የለም። ተፈጥሯዊው ሰው በአካባቢው ካለው ይበልጥ እንዲሰጥ አልተጠየቀም፥ አልሰጠምም። በመሆኑም በሥጋ ኃይል የሚከናወን ነገር ሁሉ በባሕርይው ሕግ የመፈጻም ተግባር ነው። ምንም ሆነ ምን፥ የተገለጠ የእግዚአብሔር ፈቃድ፥ በሕግ የተጻፉ ትእዛዛት ሁሉ፥ የጸጋ ማነሣሣት ወይም ማንኛውም መንፈሳዊ ድርጊት ቢሆንም በሥጋ ኃይል እስከተሠራ ድረስ የሕግ ሥራ ነው የሚሆነው። 

መ. ጸጋ እንደ ሕይወት መመሪያ 

በጸጋ ሥር ለሆነ ክርስቲያን ማንኛውም የሕግ ጫና ተውግዶለታል (ዮሐ. 1፡16፥ 17፤ ሮሜ 6፡14፤ 7፡1-6፤ 2ኛ ቆሮ.3፡1-18፤ ገላ.3፡19-25፤ ኤፌ.2፡15፤ ቆላ. 2፡14)። 

1. የሙሴ ሥርዓት ክፍል የነበሩት የሕግ ትእዛዛትና የመንግሥቱ መተዳደሪያ የን ሕግጋት፥ አሁን የክርስቲያን መማሪያዎች እይደሉም። በአዲስ ጸጋ በተሟሉና ባሕርይን በሚቀርፁ መመሪያዎች ተተክተዋል። ይህ የጸጋ ሕግ በቀደመው ሕግ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና ነገሮችን የራሱ በሆነ ልዩ ሥርዓትና ሁኔታ ሥር ያስቀምጣቸዋል። 

2. በጸጋ ሥር የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ክርስቲያን የሥራ ኪዳን ሕግ ስም ተወግዶለታል። አሁን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት እይጥርም። በክርስቶስ በኩል ተቀባይነትን እንዳገኘ ሰው ለመኖር ነጻ ነው (ኤፌ. 1፡6)። 

3. ክርስቲያን በሥጋው ብርታት እንዲኖር አይደለም የተጠራው። በውስጡ ሰሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይኖር ዘንድ እንዲህ ካለው የሕግ አሠራር ነጻ ወጥቷል። የሙሴ ሕግ የመጣው ለእስራኤል በመሆኑ፥ በክርስቶስ ሞት ከሕግ ትእዛዛት ነጻ የምትሆነውም እርሷ (እስራኤል) ብቻ ነበረች። ይሁን እንጂ፥ አይሁዳውያንም ሆኑ ሌሎች ሕዝቦች ተስፋ ቢስ ከሆነው ሰብአዊ የሥራ ሕግና ጥቅም የለሽ የሥጋ ጥረት በኢየሱስ ሞት አማካይነት ነጻ ወጥተዋል። 

4. ከሕግ ተቃራኒ፥ ጸጋ” የሚለው ቃል አንድ ሰው የማይገባውን ሞገስ ማግኘቱን ያመለክታል። ይህም ከአዳም ጀምሮ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ያካሂድ የነበረውን መለኮታዊ አሠራር ይወክላል። በጸጋ አሠራር እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያስተናግዳቸው እንደየበደላቸው አይደለም። ዳሩ ግን መልካምነታቸውን ሳይመለከት ገደብ በሌለው ጸጋና ምሕረት ይቀርባቸዋል። እግዚአብሔር በኃጢአተኞች ላይ ቅድስናው የሚጠይቀውን ትክክለኛ ቅጣት ለመፈጸም ነጻ ነው። ነገር ግን ልጁ (ኢየሱስ ክርስቶስ) የኃጢአተኞችን ቅጣት ተሸክሞላቸዋል። 

የእስራኤል ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ጸጋ በብዙ መንገዶች ቢለማመዱም፥ እንደ ሕይወት ሕግ ግን ከጻጋ ግንኙነት ወደ ሕግ ግንኙነት ተሸጋግረዋል። በዘጸአት 19፡3-25 እንደተገለጠው የእግዚአብሔርን ሕግ ሲቀበሉ፥ ጸጋ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የማግኛ ብቸኛ መሠረት መሆኑን ባለማወቃቸው የእግዚአብሔርን ሕግ ለመጠበቅ እንደሚችሉ በሞኝነት ገምተው ነበር። እስራኤል በሕግ አሠራር ሥር ያሳለፈችው ገጠመኝ፥ በሕግ መመሪያነት ከኃጢአት ኃይል ለመላቀቅ የማይቻል መሆኑን ለሰዎች ሁሉ ያስገነዝባል። 

5. ከሕግ ሲነጻጸር፥ ጻጋ በሦስት የተለያዩ ገጽታዎች ይገለጣል። እነርሱም፡- (ሀ) በጸጋ መዳን፥ (ለ) በጸጋ መጠበቅና (ሐ) ከድነት በኋላ ጸጋን ለሕይወት መመሪያነት መጠቀም ናቸው። 

(ሀ) እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በጸጋ ያድናል፤ ከዚህ ውጭ ለሰው ልጆች የተሰጠ የድነት መንገድ የለም (ሐዋ. 4፡12)። የድነት ጸጋ ወሰን የለውም። በክርስቶስ አማካይነት የሚያድነው ጸጋ በርሱ የመሥዋዕትነት ሞት የተገኘውን ጽድቅ ትክክለኛና የማይለወጡ ትእዛዛት በአግባቡ ለሚቀበሉ ኃጢአተኞች የሚሠራ የማይታቀብ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ጸጋ ከፍቅር በላይ ነው፤ ይህም ፍቅር እግዚአብሔር በኃጢአተኛው ላይ የሚበይነውን የጽድቅ ፍርድ ወይም ቅጣት ድል ይነሣል። 

እግዚአብሔር አንድን ኃጢአተኛ ሰጻጋው በሚያድንበት ወቅት፥ ኃጢአትን ቸል በማለት ሳይሆን በመቅጣት ነው። ይህ ካልሆነ፥ ኃጢአቶቹ ፍርድን ስለሚያስከትሉ ለጸጋው እንቅፋት መሆናቸው አይቀሬ ነው። በመሆኑም በልጁ ሞት ለኃጢአት ሁሉ መፍትሔ ሰጥቷል። ከዚህም በላይ፥ ለድነት የሚጠየቅ ማንኛውም ግዴታ መወገዱ ግድ አስፈላጊ ነበር። በዚህም መሠረት ድነት ፍጹም የእግዚአብሔር ስጦታ ሆኖ ለሰው ልጆች ቀርቧል (ዮሐ. 10፡28፤ ሮሜ 6፡23፤ ኤፌ. 2፡8)። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ማንኛውም ለድነት የሚደረግ ሰብአዊ ጥረት መተው አለበት። ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚያከናውነው ተግባር በምንም ዓይነት በሰዎች ሰናይ ምግባር ላይ ሊመሠረት የማይገባ እና መሠረቱ ሉዓላዊ ጸጋው ብቻ መሆኑ እንዲረጋገጥ ነው (ሮሜ 3፡9፤ 11፡32፤ ገላ. 3፡22)። ማንኛውም ሰብአዊ ነገር ከግንዛቤ የማይገባ ሲሆን፥ የጸጋ ወንጌል ግን ለሚያምኑ ሁሉ ዘላለማዊ ሕይወትና ዘላለማዊ ክብር የሚሰጥ፥ ታላቅ፥ ነጻ አውጪና የሚለውጥ የእግዚአብሔር ጸጋ አዋጅ ነው። 

(ለ) በጸጋ አማካኝነት የመጠበቁ መለኮታዊ ዕቅድ የሚያመለክተው፥ እግዚአብሔር የዳኑትን ሰዎች በጻጋ ብቻ የሚጠብቃቸው መሆኑን ነው። እግዚአብሔር ጽድቁ ከኃጢአት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ነጻ ሆኖ የሚሠራበትን መንገድ ካቀረበ፥ ከሰው ልጆች የሚጠበቀውን ዋጋ ካስወገደና እያንዳንዱን ሰብአዊ ምግባር ለዘላለሙ ካራቀ በኋላ የሚያከናውነው ነገር፥ የዳነው ሰው ጸጋን እየተለማመደ ለዘላለሙ ተጠብቆና ዋስትናን ተጎናጽፎ እንዲኖር ማድረግ ነው። እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ፥ አማኝ በጸጋ ይቆማል (ሮሜ 5፡2፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡12)። 

(ሐ) ይህ ብቻም አይደል፥ እግዚአብሔር በጸጋ መርህ ላይ በመመሥረት ላዳኑ ሰዎች የሕይወትን መመሪያ ይሰጣል። የዳኑና የተጠበቁ ሰዎች እንዴት በጸጋ ሊኖሩ እንደሚገባና በዘላለማዊ ክብሩ እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ ያስተምራቸዋል። ሕግ ለእስራኤላውያን ሙሉ የሥነ-ምግባር መመሪያ ሆኖ እንደሰጣቸው ሁሉ፥ እግዚአብሔርም ለክርስቲያኑ ሙሉ የሥነ-ምግባር መመሪያ ሰጥቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቀረሱት የጸጋና የሕግ መመሪያዎች በራሳቸው ምሉአን ስለሆኑ አንዱን ከሌላው ማጣመሩ አስፈላጊ አይደለም። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ከሕይወት መመሪያነት አንጻር ከሕግ በታች ሳይሆን፥ ከጻጋ መመሪያ ሥር ነው። ከጸጋ ሥር ሆኖ የሚሠራው ነገር፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ በጎ ነገርን እንዲያገኝ ሳይሆን፥ አፍቃሪው እግዚአብሔር ቀደም ብሎ ስለተቀበለው ብቻ የሚያደርገው ነው። ይህም በሥጋ ጉልበት የሚካሄድ ሳይሆን አማኙ ውስጥ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል መገለጫና ተግባራዊ አኗኗር ነው። የዚህ ዓይነቱ ሕይወት “ጻድቅ በእምነቱ በሕይወት ይኖራል” በሚለው የእምነት መርሕ ላይ የተመረኮዘ ነው። እነዚህ መመሪያዎች በወንጌላትና በመልእክቶች ውስጥ ተገልጠው ይገኛሉ። 

ሠ. ብቸኛው የድል መንገድ 

ክርስቲያን ከኃጢአት ኃይል ነጻ የሚወጣበትን መንገድ ለማሳየት የሚጥሩ ብዙ ትምህርቶች ቀርበዋል። 

1. ክርስቲያን በቂ ደንቦችን ከጠበቀ ለእግዚአብሔር ክብር ለመኖር ይገደዳል ተብሏል። ይህ የሕግ መመሪያ ሊላቀቁት በሚገባ ኃጢአተኛ ሥጋ ላይ የሚታመን በመሆኑ፥ ለውድቀት የተዳረገ ነው (ሮሜ 6፡14)። 

2. ክርስቲያን የአሮጌውን ባሕርይ ጨርሶ ለማጥፋት በመምከር ለዘለቄታው ከኃጢአት ኃይል ሊሳቀቅ ይችላል የሚል ትምህርት አለ። ይህን ንድፈ-አሳብ የሚቃወሙ ወገኖች ሲኖሩ ምክንያታቸውን እንደሚከተለው ያቀርባሉ። 

(ሀ) አሮጌውን ባሕርይ ጭራሽ የማጥፋት ንድፈ-አሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም። 

(ለ) አሮጌው ባሕርይ የሥጋ አንድ አካል በመሆኑ፥ ሥጋ ከክርስቲያን ኃያላን ጠላቶች አንዱ ነው። ክርስቲያንን ዓለም፥ ሥጋና ሰይጣን ይፈታተኑታል። እግዚአብሔር ደግሞ ክርስቲያን በነርሱ ላይ ድል እንዲያገኝ መንፈሱን ይሰጠዋል እንጂ፥ ዓለምን፥ ሥጋን ወይም ሰይጣንን አያጠፋቸውም (ገላ. 5፡16፤ 1ኛ ዮሐ. 4፡4፤ 5፡4)። በአሮጌው ተፈጥሮ ላይ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ድልን ይሰጣል (ሮሜ 6፡14፤ 8፡2)። 

(ሐ) የአሮጌው ባሕርይ መጥፋት ንድፈ-አሳብ በእውነተኛ የሰው ልጅ ገጠመኝ አይደገፍም። ይህ ንድፈ-አሳብ እውነት ሲሆን ኑሮ፥ ይህን ዓይነቱን ሕይወት የኖሩ ወላጆች በኃጢአት ያልወደቁ ልጆች በወለዱ ነበር። 

(መ) በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ይህን ንድፈ-አሳብ ከተቀበልን፥ ውስጣችን የሚኖረው መንፈስ ቅዱስም ሆነ የሚሰጠን አገልግሎት ትርጉም ያጣል። ይሁንና፥ እጅግ መንፈሳዊ የሆኑ ክርስቲያኖች እንኳ በመንፈስ በመመላለሱ፥ በእምነት፥ በመሰጠት፥ ኃጢአት እንዳያነግሥ በመከላከሉ፥ በማስወገዱ፥ በጭምትነትና በጽናት በመኖሩ አስፈላጊነት ላይ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። 

3. አንዳንድ ክርስቲያኖች በመዳናቸው ብቻ ከመንፈስ ቅዱስ ርዳታ ውጭ ከእግዚአብሔር ክብር ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስባሉ። ሮሜ 7፡15-8፡4 ውስጥ ሐዋርያው ከዚህ ንድፈ-አሳብ ጋር የነበረውን ገጠመኝ ይገልጣል። መልካም የሆነውን እንደሚያውቅና ዳሩ ግን የሚያውቀውን እንዴት እንደሚፈጽም አለማወቁን ይናገራል (7 ፡18)። ስለሆነም ከሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሷል፤ (ሀ) ሰብልቶች ውስጥ ለአፍታም የማይለየው የኃጢአት ሕግ በመኖሩ ምክንያት፥ ከሁሉም የላቀ ጥረት ቢያደርግም እንኳን ሁልጊዜ ይሸነፋል (7፡23)፤ (ለ) እንዲህ ባለ ሁኔታ ላይ መገኘት ጎስቋላነት ነው (7፡24)፤ (ሐ) ድነትን ቢያገኝም፥ ነጻ ያወጣው የራሱ ሥራ ሳይሆን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ነበር (8፡2)፣ (መ) የእግዚአብሔር ሙሉ ፈቃድ በአማኙ እማካኝነት ሳይሆን፥ በአማኙ ውስጥ ተፈጽሟል (8፡4)። 

ከኃጢአት ኃይል ነጻ መውጣት የሚቻለው በኢየሱስ በኩል ነው። ከኃጢአት ነጻ መሆን ከእግዚአብሔር ጽድቅ ጋር የተያያዘ ስለሆነ፥ ነጻነት ሊመጣ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። መንፈስ ቅዱስ እማኝ ባልሆነ ሰው ሕይወት ያላን በኃጢአት የወደቀ ባሕርይ ሊቆጣጠር አይችልም። ዳሩ ግን የክርስቲያኑ በኃጢአት የወደቀ ባሕርይ ከክርስቶስ ጋር በመሰቀሉ፥ በመሞቱና በመቀበሩ የተፈረደበት መሆኑ ሮሜ 6፡1-10 ውስጥ ተገልጧል። ይህም በአማኙ ውስጥ የሚያድረው መንፈስ ቅዱስ የመኖሪያ ስፍራ ሰማግኘት ሥን ምግባራዊ ድልን እንዲሰጠው ያደርጋል። የእነዚህ ሁኔታዎች መሟላት፥ አማኙ በአዲሱ የሕይወት መመሪያ እንዲመላለስ ይረዳዋል። ይኸውም ራሱን ለኃጢአት እንደሞተ ቆጥሮ (6፡4፥ 11)፥ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ብቻ በሚደገፍ መመሪያ መመላለስ መቻሉ ነው። ስለሆነም፥ ከኃጢአት ኃይል ነጻ መውጣት የሚቻለው፥ በክርስቶስ በኩል ነው። 

ረ. ድል በመንፈስ ቅዱስ 

ቀደም ሲል በመንፈስ ቅዱስ አስተምህሮ ጥናቶች ውስጥ እንደተመለከተው፥ አንድ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ከኃጢአት ኃይል ነጻ ሊወጣ ይችላል። በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” (ገላ. 5፡16)። ከኃጢአት ኃይል መዳን፥ ከእግዚአብሔር ሲሆን፤ ከሰው የሚጠበቀው የእምነት ቁርጠኛ አቋም ነው። እንዲሁም ከኃጢአት ቅጣት ድነትን ማግኘት ከእግዚአብሔር ሲሆን፥ የሰውን የእምነት እርምጃ ያመለክታል። ጻድቅ በእምነት ይኖራል። ይህ እምነት በእግዚአብሔር ኃይል ላይ የሚደገፍ ነው። ጻድቅ በምድራዊ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ሙሉ ለሙሉ ከመደገፍ የሚቆጠብበት ጊዜ ከቶውንም አይኖርም። 

አማኝ መንፈስ ቅዱስ ላይ መደገፍ የሚኖርበት ሦስት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው። 

1. አማኝ በጸጋ ትምህርቶች ሥር ሆኖ፥ ከማይሞከሩ ሰማያዊ የሕይወት መመዘኛዎች ጋር ይጋፈጣል። ሰማያዊ ዜጋ (ፊልጵ. 3፡20)። የክርስቶስ አካል ብልት (ኤፌ. 5፡30)፥ እና የእግዚአብሔር ቤተሰብ በመሆኑ (ኤፌ. 2፡19፣ 3፡15)፥ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ከተሰጠው ሰማያዊ ስፍራው አንጻር እንዲመላለስ ተጠርቷል። ይህ ከሰብአዊነት የላቀ አኗኗር በመሆኑ (ዮሐ. 13፡34፤ 2ኛ ቆሮ. 10፡5፤ ኤፌ.4፡1-3፥ 30፤ 5፡20፤ 1ኛ ተሰ. 5፡16-17፤ 1ኛ ጴጥ.2፡9) ክርስቲያን በውስጡ ሳደረው መንፈስ ቅዱስ ላይ መደገፍ የግድ ይሆንበታል (ሮሜ 8፡4)። 

2. ክርስቲያን ዓለምን ከሚገዛው ጠላት፥ ከሰይጣን ጋር ይጋፈጣል። ስለሆነም፥ በጌታ የበረታ ሊሆን ይገባዋል (ኤፌ. 6፡10-12፤ 1ኛ ዮሐ. 4፡4፤ ይሁዳ 9)። 

3. ክርስቲያን ሊቆጣጠረው የማይቻለው አሮጌ ባሕርይ እውስጡ ይዟል። 

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጠው፥ እግዚአብሔር ከኃጢአት በደል ብቻ ሳይሆን፥ ከኃጢአት ኃያልም ያድናል። በመጨረሻም ክርስቲያን ምሉእ ሆኖ በመንግሥተ ሰማይ ሲቆም ኃጢአት ክርሱ ይለያል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: