መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አምላክ ነውን?

ስለ መንፈስ ቅዱስ አካልነት የቀረበው ማረጋገጫ አምላክነቱን የሚመሰክር ሊሆን አይችልም። በአንጻሩ የሚያረጋግጠው ግን መንፈስ ቅዱስ አምላክ ከሆነ እንደ እግዚአብሔር አካል ያለው መሆኑን ነው። ብዙውን ጊዜ አካልነቱንና መለኮታዊነቱን መካድ የማይነጣጠሉ ሲሆኑ፥ አንዳንዶች ግን አካል መሆኑን ያምኑና መለኮታዊነቱን ይክዳሉ። 

አዎን፥ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ብቻ ባሕርያት አሉት 

1. መንፈስ ሰው ጨርሶ ሊረዳ በማይቻለው አኳኋን ስለ እግዚአብሔር ያውቃል። ይህም የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት ባሕርይ መጋራቱን ያሳያል (1ኛ ቆሮ. 2፡11-12)። 

2. ሰው ከርሱ ሊሸሽ አለመቻሉ እንደ እግዚአብሔር በሁሉ ስፍራ የመገኘት ችሎታ ያለው መሆኑን ያረጋግጣል (መዝ. 139፡7)። 

አዎን፥ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ብቻ የሚቻለውን ተግባር ሊፈጸም ይችላል 

እግዚአብሔር ብቻ ከሚቻለውና መንፈስ ቅዱስም ከሚፈጽማቸው (አምላክ መሆኑን ከሚያሳዩ) ተግባራት አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፡- 1. ዳግም መውለድ (ሰው ዳግም እንዲወለድ ማድረግ) (ዮሐ. 3፡5-6)፥ 2. ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንዲወለድ ማድረግ (ሉቃስ 1፡35)፣ 3. ዓለምን መፍጠር (መዝ. 104:30) ጥቂቶቹ ናቸው። 

አዎን፥ መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች የሥላሴ አካላት ጋር በእኩልነት ተጠቅሷል 

በብሉይ ኪዳን ከተጠቀሰው ያህዌ ጋር በአንድነት መገለጡ የመለኮታዊነቱ ጠንካራ ማረጋገጫ ነው። በብሉይ ኪዳን ያህዌ ተናግሯቸዋል የተባሉትን ቃላት አዲስ ኪዳን ሲጠቅሳቸው ተናጋሪው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይገልጣል። ይህም መንፈስ ቅዱስ እንደ ያህዌ ሙሉ መለኮት መሆኑን ያረጋግጣል (ኢሳ. 6፡1-13፤ ሐዋ. 28፡25፤ ኤር. 31፡31-34፤ ዕብ. 10፡15-17)። 

መንፈስ ቅዱስን መሳደብና ለመንፈስ ቅዱስ መዋሸት ለእግዚአብሐር መዋሸት እንደሆነ በአዲስ ኪዳን ተገልጧል (ማቴ. 12፡31-32፤ ሐዋ. 5፡3-4)። መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት ሥርዓት መጠቀሱና (ማቴ. 28፡19) በ2ኛ ቆሮንቶስ 13፡14 በሚገኘው ቡራኬ ውስጥ መገኘቱ ከሥላሴ አካላት አንዱ መሆኑን ያረጋግጣሉ። 

ስርፀት 

“ስርፀት” [Procession/ፕሮሴሽን] የሥነ-መለኮት ምሁራን የመንፈስ ቅዱስንና የሌሎቹን የሥላሴ አካላት ግንኙነቶች ለመግለጥ የሚጠቀሙበት ቃል ነው። “ስርፀት” ማለት መንፈስ ቅዱስ ከሌሎቹ የሥላሴ አካላት የበታች ወይም እኩል ያልሆነ ነበር ማለት አይደለም። ስርፀት በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አገልግሉቱን ይፈጽም ዘንድ በአብና በወልድ ወደ መሬት ተልኳል ማለት ነው። የዚህ አሳብ መነሻ ዮሐ. 15፡26 ሲሆን ይህም በቍስጥንጥንያ የእምነት መግለጫ ተጠቅሷል (381 ዓ.ም.)። በዚያን ዘመን አንዳንዶች የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት በመካድ የወልድ ተከታይ ፍጡር ነው የሚል አቋም ይዘው ነበር። ይህን አቋም የያዙት ቡድኖች “መቅዶናውያን” [Macedonians] (በመሥራቻቸው መቅዶንዮስ [Macedonius] በተባለው ሰው ስም ይጠራሉ) “በመንፈስ ላይ ክፉ የሚናገሩ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸው ነበር። ስለዚህ ሌላ ጉባኤ ተጠራና የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አወጣ፡- “እኛ የሁሉ ጌታ በሚሆን፥ ሕይወት በሚሰጥ፥ ከአብ በሰረፀ፥ ከአብና ከወልድ ጋር በከበረ፥ በነቢያቱ በተናገረ መንፈስ ቅዱስ እናምናለን።” ምንም እንኳ ይህ መግለጫ መንፈስ ቅዱስን አምላክ ብሎ ባይጠራ፥ ጉባኤው ስለ መንፈስ ቅዱስ የገለጣቸው ሁኔታዎች ለሌላ የሚሰጡ ስላልሆኑ፥ የመቄዶናውያኑን አሳብ የሚቃወም ነው። በ451 ዓ.ም. የተካሄደው የኬልቄዶን [Chalcedon] ጉባኤ የቍስጥንጥንያን [Constantinople] ውሳኔ በማጽናት የመንፈስ መለኮታዊነትን ትምህርተ ሃይማኖት [Doctrine/ዶክተሪን] መሠረተ። 

ይሁን እንጂ፥ በ589 የተደረገው የቶሌዶ [Toledo] ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች የሥላሴ አካላት ጋር ያለውን ምስጢራዊ ግንኙነት ግልጥ የማድረጉን አስፈላጊነት አመነበትና፥ በቍስጥንጥንያ መግለጫ፥ መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሰረፀ ነው የሚለው ቃል የወልድንና የአብን አንድነት ይክዳል ከሚል ድምዳሜ ደረሰ። ሰለዚህ “ፈሊዮክዌ” [Filoqe] (“እና ወልድ”) የሚል ታዋቂ ሐረግ ጨመረበትና “መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የሰረፀ ነው” በማለት ወሰነ። የምዕራቧ ቤተ ክርስቲያን ከዚያ ወዲህ በወጡት የእምነት መግለጫዎቿ ይህን ሐረግ ስትጨምር፥ የምሥራቋ ቤተ ክርስቲያን ግን፥ ይህ መንፈስ ቅዱስ ሙሉ መለኮታዊ መሆኑን ይክዳል በማለት ትምህርቱን መናፍቅነት አድርጋ ቆጠረች። 

የዚህ ታሪካዊ ክርክር ጠቀሜታ የጎላ ባይመስልም፥ ከጥናቱ ሂደት ስለ መለኮታዊነት፥ ስለ እኩልነት፥ ስለ ታናሽነት፥ ሰለ ግንኙነት አሳብ ለማግኘትና በጉዳዮቹ ላይ ስንነጋገርም ለመጠንቀቅ ይረዳናል። ትምህርተ ሃይማኖትን በጥልቀት መከታተላችን፥ እውነትን እንድንረዳ ብቻ ሳይሆን በሚገባ እንድንገልጠውም ያስችለናል። ከጥንት ከመሠረት ጀምሮ አባቶች ያደረጉትን ውይይት ማጤንም ለዚህ ይረዳል። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading