የለዘብተኛነት ትምህርት ሰው በራሱ ጥረት እግዚአብሔርን ሊያውቅ ይችላል ይላል። በተቃራኒው ካርል ባርት [Karl Bart] የተባለ ሰው፥ በአዲሱ የሥነ መለኮት ትምህርቱ ዓለምን ባናወጠበት ወቅት ያደረገው “ጥሩ” ነገር ቢኖር፥ እግዚአብሔር በራሱ አነሳሽነት ራሱን ካልገለጠና ካላሳወቀ በስተቀር ምንም ዓይነት መረዳት እንደማይኖር ለሰዎች ማስገንዘቡ ነው። በሌላ አነጋገር ይህ ጉዳይ ሶፋር የተባለ ሰው ከጥቂት ሺህ ዓመታት በፊት “…ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክን ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን?” (ኢዮብ 11፡7) በማለት ለኢዮብ ካቀረበለት ጥያቄ ጋር ተመሳሳይ ነው። ለዘብተኛው አዎ የሚል መልስ ሲሰጥ፥ እምነት አጥባቂው [Conservative/ከንሰርቫቲቭ] ግን አይቻልም ይላል። (ባርትም አይቻልም ብሏልና እምነት አጥባቂ ነው ማለት አይደለም። ምክንያቱም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት እንዲያ አለመሆኑን ያመለክታል።)
እግዚአብሔር ራሱን ለመግለጥ የመጀመሪያውን እርምጃ ወሰደ ከተባለ፥ በምን አኳኋን ነው ይህን ያደረገው? ለዚህ ጥያቄ መልስ፥ አሳባችን በፍጥነት ወደ ክርስቶስና ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ይሄድ ይሆናል። አዎ፥ ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም መልሱ፤ እንደ ፍጥረትና ታሪክ ያሉ ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ። የኋለኞቹን ሁለት መልሶች ከመጀመሪያው ለየት የሚያደርጋቸው ጉዳይ አለ። ስለ እግዚአብሔር አብራርተው አያስረዱንም። በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር ራሱን የገለጠባቸው አጠቃላይና ልዩ የሆኑ መንገዶች ያሉ ይመስላል። በፍጥረትና በታሪክ ራሱን የገለጠበት መንገድ አጠቃላይ መገለጥ ሲባል፥ ሌሎቹ የመገለጥ መንገዶች ልዩ ተብለው ይጠራሉ።
ያጠቃላይ መገለጥ ባሕርያት ምንድናቸው? መዝሙር 19፡1-6ን ይመልከቱ። በመዝሙር ቁጥር አንድ ላይ የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ማረጋገጫዎች የእጁ ሥራዎች እንደሆኑ ታትቷል። ቁጥር ሁለት ስለ ቀንና ምሽት በመጥቀስ (ሰማያት ሁልጊዜ መኖራቸው ሰው እንዲያያቸው ነውና ከፊተኛው የሚቀጥል ማብራሪያ መሆኑን ያረጋግጣል። በቁጥር ሦስት ላይ ይህ በፍጥረታቱ የታየው መለኮታዊ መገለጥ ድምጽ የሌለው መገለጥ እንደሆነ ተጠቅሷል። ከቁጥር አራት እስከ ስድስት፥ መገለጡ ለመላው ዓለምና ለሰው ልጆች ሁሉ እንደሆነ ይናገራል። (ቁጥር ስድስትን ያስተውሉ፥ ዓይነ ስውር እንኳን የፀሐይ ሙቀት ሊሰማው ይችላል።) በሮሜ 1፡18-20 የዚህ ትምህርት ሌላ ጠቃሚ ከፍል “የእግዚአብሔርን የዘላለም ኃይልና አምላክነቱን” በተጨማሪ ያስረዳል። እግዚአብሔር ራሱን በታሪክ ውስጥ የገለጠው በተለያዩ መንገዶች ነው። ለሰዎች ዝናብና ፍሬያማ ወራትን ሰጥቷል (ሐዋ. 14፡17)። ስለ ማንነቱና ስለ ኃይሉ በተለያየ ሁኔታ ለእስራኤላውያን ገልጧል (ስለ ተአምራታዊ ኃይሉ በመዝሙር 78፡13፥ ስለ ቁጣው ቁጥር 21፥ ፍጥረትን እንደሚቆጣጠር ቁጥር 26፥ ስለ ፍቅሩ ቁጥር 38 ላይ ተገልጧል)። እግዚአብሔር ስለ ራሱ በታሪክ የገለጠው፥ በፍጥረት ከገለጠው ይበልጥ ጉልህ ነው።
እግዚአብሔር እራሱን በክርስቶስ በኩል መግለጡ በዮሐንስ 1፡18 ላይ “ተረከው” በሚል ቃል በስፋትና በጥልቀት ተገልጧል። የክርስቶስም ተአምራቶች የእግዚአብሔርን ክብር የሚያሳዩ ነበሩ (ዮሐ. 2፡11)። በትምህርቱ የአብን እንክብካቤ አሳይቷል (ዮሐ.14፡2)፤ በእርሱነቱ አብን ገልጧል (ዮሐ. 14፡9)። ከሌላው መገለጥ ይልቅ እግዚአብሔርን የማወቂያ መንገድ በልጁ በኩል ነው፡፡
የልዩ መገለጥ ሌላው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዚህ ዘመን፥ አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከወልድ ያነሰ መገለጥ ነው፥ እንዲያውም ስለ መጽሐፉ ብዙ መናገር መጽሐፍ ቅዱሱን ማምለክ ነው (እንደ ጣኦት) ይላሉ። ነገር ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ካልተናገርን፥ ሰለ ወልድ የምናውቀው እጅግ ጥቂት ይሆናል። ስለ ወልድም ያለን ብቸኛ መረጃ (ስለ አብ ጭምር) መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ደግሞም ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚታመኑት አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው የሚል አጋጣሚ ካለ፥ ሰዎች የሚታመኑ የሚመስላቸውን ብቻ ይወስዱና ስለ ክርስቶስ የሚኖራቸው ግንዛቤ ውሱን ይሆናል። በሌላ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ እውነት ካልሆነ የራሳችንን ግምት ወይም የተሳሳተ መረጃ የምንሰጥ እንሆናለን። ኢየሱስ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ የእርሱን ማንነት በሚገባ እንደገለጠ ተናግሯል (ሉቃስ 24፡27፥ 44 45፤ ዮሐ. 5፡39)። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር የሚናገረው ሌላ ብዙ ነገር አለ፡፡ለምሳሌ ከዚሁ መጽሐፍ ብቻ የምንረዳቸውን የተለያዩ ዕቅዶቹን ባሰብን ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ለማስተማር የማይነጥፍ የመረጃ ምንጭ ነው እንላለን።
ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡