እግዚአብሔር አለን?

እውቀት ዓለምን እንደ ማእበል ባጥለቀለቀበት ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በብዙዎች ዘንድ እግዚአብሔርን የማወቅ ጥበብን የሚያህል፥ የእውቀት ሁሉ ቁንጮ መዘንጋቱ እጅግ የሚያስገርም ነው። በሌሎች ፈለኮች (ፕላኔቶች) ሳይ ፍጡራን መኖራቸው ተደረሰበት ብንል እንኳን፥ ይህ ግኝት በሰማያት የሚኖረውን አምላክ ከማወቅ እኩል የሚቆጠር አይሆንም። ሰዎችን ከጨረቃ የማድረስ ብቃታችንም ነፍሳትን ለመንግሥተ ሰማያት ለማዘጋጀት ከሚደረገው ጥረት እኩል ሊደነቅ አይገባም። እግዚአብሔርን ማወቅ ከሁሉ የላቀ ነውና! 

የእግዚአብሔርን ሕልውና በማሳየት ረገድ ከልማድ የተወረሱ ሁለት የክርክር መስመሮች አሉ። 

ሥነ-ተፈጥሯዊ መከራከሪያዎች 

ልማዳዊ ማስረጃ ፍልስፍናዊ ስለሆነ፥ አማኒ-እግዚአብሔር ያልሆነን ሰው ያረካ ወይም አያረካ ይሆናል። ማስረጃዎቹ ግን እንዲህ ነው የሚሉት። ይህ የማስረጃ ነጥብ በመጀመሪያ መንስዔና ውጤትን በማመልከት፥ ሰዎች በዙሪያቸው ያለውን ዓለምና አካባቢያቸውን ቢመለከቱ ውጤት እንደሚያገኙ ያስታውሳቸዋል። በሌላ አባባል፥ ፍጥረታዊው ዓለም፥ ግኝት ወይም ውጤት ነው። ይህ ሁኔታ የውጤቱን ምክንያት እንዲረዱ ያስገድዳቸዋል። በመሠረቱ ለዚህ ሁለት መልሶች ይኖራሉ። (1) ለዓለም መፈጠር መነሻ የለም፤ (ነገር ግን ያለ መነሻ የተገኘ ውበት ምንጊዜም አልታየም) የሚል ወይም (2) አንድ ነገር ለዚህ ዓለም መገኘት ምክንያት ሆኗል የሚል፤ ይህ አንድ ነገር “ዘላለማዊ የፍጥረታት እንቅስቃሴ” ወይም አጋጣሚ ይሆን ይሆናል፥ ወይም እግዚአብሔር ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ምንም እንኳ ይህ በምክንያትና ውጤት ላይ የተመረኮዘ ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን እግዚአብሔር መኖር ሊያረጋግጥ ባይችል፥ ከሌላው ሁሉ ግን የሚቀል መልስ ነው። ምክንያቱም ይህን የምንኖርበትን ሰፊና ጥልቅ ዓለም በአዝጋሚ ለውጥ ወይም በአጋጣሚ መጣ ብሎ ማመን በእግዚአብሔር ተፈጠረ ብሎ ከማመን ይከብዳልና። 

ሁለተኛው ፍልስፍናዊ የክርክር ታጥብ፥ በፍጥረት የምናየውን ዓላማ በማስገንዘብ ረገድ ያለው ነው። በሌላ ቃል ፍጥረትን ብቻ አይደለም የምናየው (እንደ መጀመሪያው ክርክር)፥ ነገር ግን ፍጥረት ዓላማ ያለው መሆኑንም ይሆናል። ታዲያ ለዚህ መልሱ ምንድነው? ከሀዲ የሆነ ሰው፥ ሁሉ ነገር የሆነው በአጋጣሚና በተፈጥሯዊ ምርጫ ነው ይላል። ጥያቄው ግን፥ በአጋጣሚና “በዘፈቀደ” የተከናወነ ድርጊት በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀን ዓለም ሊያስገኝ ይችላልን? የሚለው ነው። ይቻላል የሚለውን መልስ ለመቀበል ታላቅ እምነት ይጠይቃል። ክርስትና ለጥያቁው የሚሰጠው መልስም እምነትን ይጠይቅ ይሆናል፤ ቢሆንም የተሻለ ተዓማኒነት አለው። 

ሦስተኛው ማስረጃ የሰውን ተፈጥሮ ይመለከታል። ይህ የአስተሳሰብ ክፍል፥ የሰው ሕሊና፥ ግብረገብ፥ የማሰብ ችሎታ፥ የአእምሮ እውቀት ከየት ተገኘ? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል። እግዚአብሔር የለም የሚል ሰው ለዚህ የሚኖረው መልስ፥ ሰፊና ዝርዝር ማስረጃ በማቅረብ በአዝጋሚ ለውጥ ተገኘ የሚል ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ ያለው አዝማሚያ ሰው አካላዊና ባህላዊ፥ ወይም ልዕለ-አካላዊ ተፈጥሮ እንዳለውና ይህም በአጋጣሚ የተገኘ እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ነው። ይህ አቀራረብ ስለ ሕሊና ወይም ከሁሉ በላይ የሆነውን ፈጣሪ የማምላክን ሁለንተናዊ እምነት (ምንም እንኳን ስለዚህ ፈጣሪ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ቢሆን) ሊገልጥ ይችላልን? የሰውስ መኖር የእግዚአብሔርን መኖር ያመለክታል? ጳውሎስ ለአቴና ፈላስፎች እንዲህ ብሏል፡- “እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ እይገባንም” (ሐዋ. 17፡29)። 

አልፎ አልፎ የሞራልን ማስረጃ ከሰው አፈጣጠርና ማኅበራዊ ኑሮ ጋር በመያያዝ በግልጥ ለማቅረብ ሲሞክር ይታያል። ይህም የመልካምና ክፉ፥ የትክክልና የስሕተት አሳብ በሰው ልጅ ባህል እንዴት ታየ? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። ሰው አስፈላጊ የሆነውን ካልሆነው የሚለይበት ችሉታ አለው። ይህ ችሎታ ከየት ተገኘ? አስፈላጊ የሆነውን ካልሆነው የሚለይበት መሠረትስ ምንድነው? ጥቂቶች ለዚህ ያላቸው መልስ፣ ሰው መልካምን የማወቅና በሞራል ፍጹም የሆነውን ነገር የመገንዘብ ጥማቱን አይቶ እግዚአብሔር የሰጠው ነው። ይህም የእግዚአብሔርን መኖር ያመለክታል ይላሉ። በሌሎች ፈላስፎች የሚተላለፉት የሥነ-ምግባር ትምህርቶች ደግሞ፥ ሰዎች የክርስትናን እምነት፥ እንዲሁም ስለ መልካምና ክፉ ያለውን አመለካከት ችላ ካሉ፥ ሥራቸው ሁልጊዜ ቅራኔና ግጭት ይኖረዋል ይላሉ። ለምሳሌ “ሂዩማኒስት” [Humanist] የተባለው የእምነት ክፍል ተከታይ ፍጹም የሆነ መመዘኛ የለም ብሎ ሲያምን፥ በሌላ በኩል ግን፥ ራስህን አሻሽል በማለት ሌሎችን ሲያደፋፍር ይታያል። 

አራተኛው ነጥብ ደግሞ ለመረዳት የሚያስቸግርና በጣም ውስብስብ ይመስላል። ይህም የ“እንታላጂካል” [Ontological] ማስረጃ ጉዳይ ነው (የቃሉ ትርጉም በግሪክኛ “መሆን” ማለት ነው)። ይህ የክርክር ነጥብ ሰው ፍጹም ሕያው ስለሆነው አካል መገንዘብ እስካልቻለና በአሳቡም ያንን ፍጹም አካል እስከጨመረ ድረስ እግዚአብሔር ሕልውና ሊኖረው እንደሚገባ ያመለክታል። ይህ ፅንሰ አሳብ በሰዎች አእምሮ ካለ፥ ፍጹም የሆነ አካል አለ ማለት ነው። ወይም በሌላ አባባል፥ እግዚአብሔር ሊታሰብ የሚገባው ፍጹምና ሕያው አካል በመሆኑ የሱ ነባሪነት አጠራጣሪ ሊሆን አይችልም። አይኖርም ቢባል፥ ከሱ የላቀ አካል መኖሩን ማሰብ ይቻል ነበርና። ይህ ባለመቻሉ እግዚአብሔር ሕያው ነው። ብዙዎች (አማኑኤል ካንትንም ጨምሮ) ይህ ክርክር ዋጋ የለውም ይላሉ። አሳቡ የፈለቀው፥ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከኖረው አንሰለም [Ansela] የተባለ ሰው ነው። 

እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ የፍልስፍና አስተሳሰቦች ራሳቸውም ቢሆኑ፥ የእውነተኛውን አምላክ መኖር ሊያረጋግጡ አይችሉም። ያም ቢሆን አናንቀን አንመለከታቸውም። ይህ ገለጣቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተመለከተው እግዚአብሔር ሕልውና ለማስረዳት ይጠቅማል። በተለይ ዳግም ያልተወለደ ሰው ስለ እግዚአብሔር ተጨማሪ እውቀት እንዲገበይ ይረዱታል። በተቃራኒውም ይህን እውቀት ረግጦ ከእግዚአብሔር በረከት እንዲርቅ ያደርጉት ይሆናል። እንዲህ ያሉ ምክንያታዊ ነጥቦች በጥልቀት ለማሰብ መነሻ ሲሆኑ፥ የወንጌልን እውነት በትክክል ለማቅረብ መንገድ ይከፍታሉ። 

የተአምራትን መኖር የሚጠራጠር ሳይንስ በመነሳቱ እና ሕዝቡ አዝጋሚ ለውጥን በሰፊው በመቀበሉ፥ በእግዚአብሔር መኖርና በተአምራት የሚያምኑ ሁሉ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ስለ አዝጋሚ ለውጥ በምዕራፍ 7 ላይ የሚገለጥ ቢሆንም በዚህ ስፍራ ጥቂት መጠቃቀሱ መልካም ነው። 

የተአምር ትርጉም (ሂዩም [Hume] የተባለው ፈላስፋ እንደገለጠው) የተፈጥሮን ሕግ የሚጥስ ማለት ከሆነ፥ ተአምራት አይከሰቱም ባይባልም የመፈጸማቸው ሁኔታ እጅግ ውሱን ይሆናል። ነገር ግን ተአምራት እኛ የተፈጥሮ ሕግ ብለን ከምናውቀው የተለየ ከሆነ በምናውቀው ሕግ ላይ ሌላ አዲስ ክስተት ማስተዋወቅ ሊሆን ነው። ይህ አዲስ ተአምራታዊ ክስተት ተፈጥሮን አይቃወምም። ምክንያቱም ተፈጥሮ በራሱ ምሉእ ሳይሆን፥ የምሉኡ እውነት አካል ነው። ስለዚህ ተአምር ከተፈጥሮ በላይ በሆነ፥ ታላቅ ሥርዓት ውስጥ ነው ያለው። እውነት ነው፥ ተፈጥሮ በራሱ ተአምራትን ማድረግ አይችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር እንዳለ የሚያምን፥ ተአምራትም እንደሚኖሩ ያምናል። አንድ ሰው ኃጢአት፥ ደኅንነትና ምልክቶች እንዳሉ እስካመነ፥ ተአምራት አስፈላጊ መሆናቸውን ይቀበላል። 

ክርስቲያን ተአምርን ከችግር የመውጫ አቋራጭ መንገድ አድርጎ አይመለከተውም። ነገር ግን በዓለም ታሪክ ውስጥ ተለዋጭ ሚና ያለው እውነተኛ ክንውን እንደሆነ ይገነዘባል። ብዙ የታሪክ ተመራማሪዎች የሚያሳምኑበትን ማስረጃ ሁሉ ሳይሞክሩ የተአምርን መኖር አይቀበሉም። ይሁን እንጂ የተአምራትን መኖር መጠራጠር በአንድ ቦታና በአንድ ወቅት የተፈጸመን የታሪክ ክንዋኔ ውሸት ነው፥ ወይም አይታመንም ለማለት አያስደፍርም። ለምሳሌ፥ አንድ መደብር ውስጥ ገብቶ ዕቃ በመግዛት ሚሊዮነኛ ለሆነ ሰው ሽልማት ቢሰጥና እንደ አጋጥሚ ያ ሰው እርስዎ ቢሆኑ፥ ጓደኞችዎ ይህን አሌ ማለት የለባቸውም። ዕድላኛው እርስዎ ይሆናሉ ብሎ ማመን ቢሳናቸውም፥ እርስዎ ዕድለኛ መሆንዎ ግን ሊታመን ይገባል። 

ከተፈጥሮ በላይ የሆነው አምላክ የታላቅነት መጠን ለክርስትና እጅግ ጠቃሚ ሲሆን፥ በታሪክም ተደጋግሞ ታይቷል። ስለዚህ አንድን ተአምር ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ ለመግለጥ እንዳይሞክሩ ይጠንቀቁ። ደግሞም ተአምራትን መካድ፥ የእምነታችን መሠረትና ተስፋ የሆነውን የክርስቶስን ትንሣኤ መካድ እንደሆነ ያስተውሉ። 

መጽሐፍ ቅዱሳዊ መከራከሪያዎች 

ሌላው ማረጋገጫ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርበው ሲሆን፥ ይህንም አሳጥረን እንመለከተዋለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን መኖር ሙሉ በሙሉ ስለሚቀበል ብዙ ጊዜ በዚህ ጉዳይ መከራከር አያሻም። መጽሐፍ ቅዱስ ከመነሻው ጀምሮ የእግዚአብሔርን ሕልውና መቀበል እንጂ፥ ስለ ሕልውናው ክርክር አያነሳም። እንዲያ ቢሆን ኖሮ ታሪኩ የተሟላ አይንም ነበር። መዝሙር 19ን በመመልከት ዳዊት፥ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ዙሪያ መኖሩን እንደገለጠ ማስታወስ ይጠቅማል። ኢሳይያስም ወደ ጣኦት አምልኮ ለተመለሱ ሰዎች በዙሪያቸው ያለውን ተፈጥሮ እንዲመለከቱና በእጃቸው ጠርበው የሠሯቸው ጣኦታት እንዲያ ያለ ዓለም ለመፍጠር ብቁ መሆን አለመሆናቸውን እንዲያሰላስሉ ያሳስባቸዋል፡፡መልሱ ለመፍጠር ብቁ አይደሉም የሚል ነው። ከዚያም እንዲህ ይላል፡- “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንስታችሁ ተመልከቱ፥ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን ቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው። ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም” (ኢሳ. 40፡26)። ጳውሎስም ክርስቲያን ላልነበሩ አድማጮቹ ሲገልጥ፥ የዝናብና የወራት መለዋወጥ የእግዚአብሔርን መኖር ይመሰክራሉ ብሏል (ሐዋ. 14፡12። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር መኖር ያስረዳል፥ ያረጋግጣል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: