ከርስቶስ ኃጢአት ሊያደርግ አይችልም ነበር የሚለው ጉዳይ ብዙ አከራክሯል። አንዳንዶች ክርስቶስ ከኃጢአት የነጻ አልነበረም ሲሉ፥ ሌሎቹ ደግሞ ኃጢአተኛ አይደለም ይላሉ። ኃጢአተኛ አይደለም በሚሉት ዘንድ ሁለት ዓይነት አመለካከት አለ። በአንድ ወገን ያሉት ኃጢአት ላለማድረግ ብቃት ነበረው ሲሉ፥ ሌሎቹ ደግሞ ኃጢአት ለማድረግ አይችልም ነበር ይላሉ። በሁለቱም በኩል ኃጢአተኛ አለመሆኑ ይገለጥ እንጂ፥ በአንድ በኩል ያሉት ግን ኃጢአት ሊሰራ የመቻሉን ሁኔታ ይጠቁማሉ፡፡ ይህን የሚሉት ወገኖች ለማሳመኛነት የሚያቀርቡት ክርክር፥ ክርስቶስ ኃጢአት ለመፈጸም እስካልቻለ ድረስ የመፈተኑን እውነተኛነት ለመረዳት አዳጋች ይሆናል የሚል ነው፡፡ መፈተኑ እና ኃጢአት ያለመፈፀሙ ግን የታመነ ነገር ነው። እዚህ ላይ ደግሞ ኃጢአት ሊያደርግ እስካልቻለ ፈተናውስ እንዴት እውነተኛ ይሆናል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
መልሱን በከፊል ለማግኘት ዕብ. 4፡15 ላይ የተጻፈውን በማንበብና ካልተጻፈው ለይተን በማመዛዘን መረዳት ያሻል። ጥቅሱ ቃል በቃል “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደኛ የተፈተነ ነው” ይላል እንጂ፣ ክርስቶስ የተፈተነው በኃጢአት ለመሸነፍ ከማሰብ የተነሳ ነው አይልም። ከኃጢአት የነጻ መሆኑን ለማረጋገጥ ነበር የተፈተነው። እንደዚሁም ጥቅሱ በሰው ላይ በሚደርሰው በንኛውም የፈተና ዓይነት ተፈትኗል አይልም። ሰው በሚፈተንባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ማለት፥ በሥጋዊ ምኞት፣ በዓይን አምሮትና በገንዘብ መመካት ነበር የተፈተነው (1ኛ ዮሐ. 2፡16)። በነዚህ አቅጣጫዎች የደረሱበት ፈተናዎች በእኛ ላይ ከሚደርሱት ፍጹም ይለያሉ። በጥቅሱ ውስጥ “እንደ እኛ” የሚለው ቃል የኃጢአተኛን ሥጋ ስለለበሰ ለመፈተን መቻሉን ያስረዳል። ከኃጢአት በቀር የሚለው ቃል የኃጢአት ባሕርይ ስለሌለው ማለት ሲሆን እኛ በምንፈተንበት ሁኔታ የማይፈተን መሆኑን ያሳያል።
በፈተናዎቹ ውስጥ እንዲያልፍ የተደረገው፥ ኃጢአት ለፈጽም ይችል እንደሆነ ለማየት ሳይሆን ኃጢአት ለመፈጸም አለመቻሉን ለማረጋገጥ ነው። ፈተናዎቹም እርግጠኞች ነበሩ። የአንድ ፈተና እርግጠኛነት የሚለካው በተፈታኙ ሥነ-ምግባራዊ ተፈጥሮ ወይም በፈተና ላለመውደቅ መቻል ላይ በመመርኮዝ አይደለም። የክርስቶስ ለእኛ ርኅራኄ የማሳየት ችሎታ ልክ እኛ በተፈተንበት መንገድ መፈተንን አይጠይቅም።
ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡