የመንፈስ ቅዱሰ የወደፊት ሥራ

በፍዳው ዘመን 

ቤተ ክርስቲያን ከፍዳ ዘመን በፊት ትነጠቃለች የሚለውን አመለካከት ስንቀበል፥ በእግዚአብሔር መቅደስ፥ ማለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ ይገለላል ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ሥራውን ያቋርጣል ማለት አይደለም። በነዚያ የፍዳ ቀናት የሚድኑ እልፍ አእላፋት ሰዎች ይኖራሉ (ራእይ 7፡14)። ዳግም መወለድን የሚያገኙት በመንፈስ ቅዱስ በኩል ይሆናል። በፍዳው ዘመን መጨረሻ በሕይወት የሚገኙ እስራኤላውያን አዳኛቸውን የሚያውቁት በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ነው (ዘካ. 12፡10)። 

መንፈስ ቅዱስ በዚያን ዘመን በሚኖሩ አማኞች መካከል ስለሚያከናውነው ተግባር በግልጥ የተጠቀሰው ጥቂት ነው። አገልግሎቱ ልክ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረውን ከመሰለ፥ ለሰዎች ልዩ የአገልግሎት ኃይል ለመስጠት ያድርባቸው ይሆናል። ኢዩኤል 2 በሐዋርያት ሥራ 2 ይጠቀስ እንጂ በበዓለ አምሳ ዕለት ሙሉ በሙሉ እንዳልተፈጸመ ይታወቃል። ስለሆነም ፍጻሜው የፍዳን ዘመን ይጠብቃል። ምክንያቱም ጥቅሱ የመንፈስ ቅዱስን መፍሰስ ከፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ከጨረቃም ወደ ደም መለውጥ ጋር ያያይዘዋል። እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ በፍዳው ዘመን ማብቂያና ልክ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት በፊት ይከናወናሉ (ማቴ. 24፡29-30)። በተጨማሪም (ራእይ 11፡3-4) ላይ የተጠቀሱት የሁለቱ ምስክሮች አገልግሉት በፍዳ ዘመን ከሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ጋር የሚዛመድ መሆኑን ያስተውሉ (ዘካ. 4፡6)። 

በሺህ ዓመቱ አገዛዝ 

በሺህ ዓመት መንግሥት ዘመን እስራኤል እንደምትድንና መንፈስም በሕዝቦቿ ሕይወት እንደሚኖር “በእዲስ ቃል ኪዳን” ተስፋ ተሰጥቷታል (ኤር. 31፡31-34፤ ሕዝ. 36፡27)። በዚያን ጊዜ በንጉሡ በክርስቶስ ላይም መንፈስ ቅዱስ በሙላት እንደሚኖርበት ተረጋግጧል (ኢሳ. 11፡2-3)። ያኔ ከአዳም ጀምር ያልታየ የእግዚአብሔር ኃይልና ሕልውና ይሰፍናል። ምንም እንኳን የዚያን ጊዜው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የተብራራ ባይሆንም፥ አገልግሎቱ ከሌሎቹ አካላት ጋር በስፋት መገለጡ ይቀጥላል። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: