የመጀመሪያው አስፈላጊ ነጥብ

ይህ ጽሑፍ የሚያወሳው መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምራቸው ነገሮች ነው። ሌላ ስያሜ መስጠት ቢያስፈልግ “የሚያስፈልገን እውቀት”፥ ወይም “ለዘመኑ የሚያስፈልግ እውነት” በማለት ልንሰይመው እንችል ነበር። ግን ለምን? ጽሑፉን በይዘቱ መሠረት ተገቢ ስም እንስጠውና፥ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለመገንዘብ የሚረዳ መጽሐፍ ነው እንበለው። 

እንዳንዶች ለዚህ ከሺህ ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አሳብን ለያዘ “ዘመን ያለፈበት” መጽሐፍ ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊ ነው ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ “የካንት [Kant ትምህርትን” ወይም “የቻርልስ ዳርዊን [Charles Darwin] አሳሶችን” የሚገልጡና የሚያብራሩ መጻሕፍት አሉን። ታዲያ ከካንትም ሆነ ከዳርዊን ዘመን በፊት ስለነበረው መጽሐፍ በማስተማራችን ለምን ይቅርታ እንጠይቃለን? ከየትኛውም መጽሐፍ በላይ በብዛት ታትሞ ሰልተሠራጨውና ጊዜ ስለማይሽረው መጽሐፍ መዘገባችንስ ለምን ቅር ያሰኛል? ዛሬ ኮሌጆቻችንና ዩኒቨርሲቲዎቻችን ስለ ሥነ-አእምሮ፥ ስለ ማኅበራዊ ኑር፥ ሰለማስተማር ዘዴዎችና ስለመሳሰሉት ኮርስ መስጠት ተገቢና ጠቃሚ እንደሆነ ያስገነዝባሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ የትምህርት መስኮች ሁሉ ከሰው ልጅ ታሪክ አንጻር ሲታዩ ዘይተው የመጡ ናቸው። ስለዚህ ከማንኛውም የትምህርት መስክ ይልቅ፥ የጊዜን ፈተና ያለፈውን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ለምን የሚያሳፍር ይሆናል? 

ይህን መጽሐፍ ለማንበብ ሲዘጋጁ ዘመን ስላለፈበት መይም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውድቅ ስለሚሆነው ትምህርት ለማጥናት የተነሳሱ ይመስልዎ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጊዜ ማባከን ነው ብለው የሚያስቡና ዘመኑ ያለፈበት በመሆኑም ክለሳ እንደሚያሻው የሚያምኑ አሉ። እንዲህ የሚያስብ ሰው የሚያስፈልገው ወደ እስራኤል በመሄድ የአገሪቱ መሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በመጥቀስ የሚሰጧቸው መመሪያዎች ምን ያህል ተፈጻሚነት እንዳገኙ በዓይኑ አይቶ መመስከር ይሆናል። ሪደርስ ዳይጀስት” [Reader’s Digest] የተባለው መጽሔት እንኳን በነሐሴ 1966 (እ.ኤ.አ.) ባወጣው እትም ላይ “ዘመን የማይሽረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጠልቆ የመግባት ችሎታ” በሚል ርእስ ያሰፈረውን ጽሑፍ መመልከቱ ሌላ በቂ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ ይችላል። በጣም የሚያስደንቀው ሌላ ነገር ደግም፥ አያሌ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከማይጠበቅ የሕይወት አቅጣጫ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት በመመለስ ላይ መሆናቸው ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለዚህ ዘመን እጅግ ወቅታዊና ተገቢ ይሆናል። 

በዚህ ምዕራፍ ርእሰ እንደተጠቀሰው እንባቢያን ልናውቀው የሚገባን “ የመጀመሪያ አስፈላጊ ነጥብ” ወይም ፍሬ አሳብ፥ እነሆ እንደሚከተለው ቀርቧል። ማንኛውም ሰው ለሚያስበውም ሆነ ለሚያደርገው ነገር ሁሉ፥ የሥልጣን መሠረት አለው። አንዳንድ ጊዜ ይህ ሥልጣን ውስብስብ ነው! ምከንያቱም የሥልጣን ምንጮች የተለያዩ ከመሆናቸውም በላይ ሰዎች የሥልጣን መሠረት እንዳላቸው ከቶውኑ ባለመረዳታቸው ነው። ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው የሥልጣን መሠረት አለው። 

ለማስረጃ ያህል ጥቂቶቹን እንጥቀስ፡- ከክርስትና እምነት ውጭ ከሆኑት ሃይማኖቶች እንደ ሂንዱይዝም ወይም እስልምና ተከታይ የሆነ ሰው የነዚህን ሃይማኖቶች ትምህርትና መጻሕፍቶቻቸውን ይቀበላል። እውነተኛ ተከታይ እስከሆነም ድረስ ራሱን ለትምህርቱ ተገዢ ያደርጋል። በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ክርስትናን ይቃወማል። ምክንያቱም ክርስትና፥ አማኙ የሥልጣን ምንጩ አድርጎ ከተቀበለው ትምህርት ጋር አይጣጣምለትም። 

ከሀዲ [Atheist/ኤቲይስት] የሆነ ሰው እግዚአብሔር የለም ይላል። ከዚህም የተነሳ መለኮታዊ ከሆነ ኃይል የሚመነጭ ምንም ዓይነት ተአምር ወይም መገለጥ ይኖራል ብሎ አይጠብቅም። ለሕይወቱም መመሪያ ሌሳ ውጫዊ ባለሥልጣን አይሻም። መሠረታዊ እምነቱ የተሳሳተ ከሆነ ጠቅላላ የትምህርተ መለኮቱ አሠራር መለወጥ አለበት። 

(“አግናስቲሲዝም”” [Agnosticism] የተሰኘው የፍልስፍና ዘርፍም ቢሆን የሚከተለው መስመር ከዚህ ከታመቀው የክህደት ትምህርት [Atheism ኤቲይዝም] ጋር የሚቀራረብ ነው። እንደ ኤቲይዝም በደፈናውና በድፍረት እግዚአብሔር የለም ሳይል፥ ለዘብና ለስለስ ብሎ እግዚአብሔር መኖሩን ማንም ሊያውቅ አይችልም ይላል። ይህ ነው አግኖስቲክሳውያን [Agnostics/ እግናስቲክስ] የሚመሩበት የእምነት አቅጣጫ። ይህ የእምነት መሠረት በሰው ልጅ የማወቅ ክህሎት የሚፈርስ ቢሆንም፥ እግኖሳዊው ግን እንደ መሰሎቹ ማወቅ አይቻልም ይላል። 

በምንኖርበት ዘመን ነገሮችን ሁሉ ጥቁርና ነጭ ብሉ በቀላሉ መለየት ያስቸግራል። ስለሆነም የሥነ-መለኮት እመለካከቶችን በማያሻማ አኳኋን መመደቡ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ፡- ኒዮ-ኦርቶዶከሲ” [Neo Orthodoxy] የተባለው እምነት የሥልጣን ምንጭ ክርስቶስ እንደሆን ይገልጣል። ይህም ትምህርቱን በልቀን እስከምንመረምረውና መሠረታዊ አሳቡ ምን እንደሀን እስከምናውቅ ድረስ መልካም ይመስላል። ይሁን እንጂ “ባርቲያን” [Barthian] የተባለውን (ከዚሁ የእምነት ዘርፍ) እምነት ስንመለከት የሥልጣን ምንጩ ክርስቶስ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የተሳሳተ ነው ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ የተሳሳተ ከሆነ (ስለ ክርስቶስ የሚያስረዳን ብቸኛ መጽሐፍ ነውና) እምነታችንን መሠረት በማድረግ በዘፈቀደ ሥልጣን እንዲኖረው ካላደረግን፥ ክርስቶሰ እንዴት ባለሥልጣን ይሆናል? በዚህ በተዳቀለ አስተሳሰብ ሳቢያ የባርቲያን እምነትና ስብከት እውነት ይምሰል እንጂ ልብ ብሎ ላጤነው ግን ለዘብተኛች [Liberals! ሊበራልስ] ለዘመናት ሲያስተምሩት ከነበረው እምነት እምብዛም አይለይ። 

የለዘብተኛነት እምነት [Liberalism/ሊበራሊዝም] የሥልጣን ምንጭ ሰው ራሱ፥ በተለይም የአስተሳሰብ ችሎታው ነው። ለዘብተኛ ለሆን ሰው፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው የአስተሳሰብ ውጤት ሲሆን፥ ይዘቱም ሰው ስለ እግዚአብሔር፥ ስለዚች ዓለምና ስለ ራሱ ያለው አስተሳሰብ ውጤት ብቻ መሆኑን ይገልጣል። በአጭሩ ለዘብተኛነት፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ሃይማኖታዊ እምነት ታሪካዊ እድገት የሚያሳይ ይሁን እንጂ የመለኮት ተሳትፎ ሳይኖርበት የተጻፈ ነው ሲል ያስተምራል። ከዚህም በመነሳት፥ ሞራል የሰው አእምሮ ውጤት ነው ከሚለው መደምደሚያ ይደርሳል። ምንም እንኳን ለዘብተኞች በታሪክ ከነበሩ ታላላቅ ሰዎችና ከኢየሱስ ትምህርቶች የወሰዷቸው የሥነ-ምግባር መመሪያዎች ቢኖሯቸው፥ መሠረታዊ አሳባቸው ግን ማንኛውም ሰው የራሱን ሕይወት መመሪያ ደንቦች ሊደነግግ ይችላል የሚል ነው። 

በሌላ መልኩም “እግዚአብሔር ሞቷል” የሚለው ፍልስፍና ዘርፍ ተከታዮች የሚያሰራጩት ትምህርት ከለዘብተኞች እምብዛም የተለየ አይደለም። እነዚህ ሥነ-መለኮታውያን በትምህርታቸው የኢየሱስን ስም ለይስሙላ ያህል ቢጠቅሱም፥ የሥነ-ምግባሩ ወሳኝ ያው ግለሰቡና ኅብረተሰቡ ነው ከማለት አይርቁም። እግዚአብሔር በሰዎች አስተሳሰብና ሕይወት ውስጥ እንደገና እንዲገለጥ ከተፈለገ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንደሞተ ቆጥረን ልንረሳውና ስለ እርሱም መነጋገር ልናቆም ይገባል በማለት ያስተምራሉ። ይህም ተደርጎ ቢገለጥ እንኳን መጠሪያው ወደፊት በሚደረስበት ሌላ ስም ይሆናል ይላሉ። ስለዚህ በነሱ አባባል ከሃይማኖት ለሚገኝ ሥልጣን ምንጩ የሰው አእምሮ ነው። ይህ ዘመን አመጣሽ ትምህርት ከአዝጋሚ ለውጥ Evolution/ኢቮሉሽን እምነት ጋር ተዳምሮ ሰብአዊውን መሠረት ያጠናክረዋል። 

በክርስትና የሥነ-መለኮት ትምህርት ዙሪያ ደግሞ በቅድሚያ ካቶሊኮችን ብንመለከት፥ የሮምን ቤተ ክርስቲያን የሥልጣን ምንጭ አድርገው እንደሚቀበሉ እንረዳለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ቢያምኑም፥ ቃሉን የመተርጎሙ ሥልጣን የቤተ ክርስቲያኒቱ ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ ለነሱ የሮም ቤተ ከርስቲያን የመጨረሻዋ ባለሥልጣን ስትሆን፥ የምታስተላልፈው ትእዛዝ ሁሉ ተፈጻሚነት አለው። 

የወንጌላውያን ክርስቲያኖች የሥልጣን መሠረት ግን፥ በእግዚአብሔር መለኮታዊ መገለጥ ላይ ያተኩራል። ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቷል አላለም ብላችሁ ትገረሙ ይሆናል። እግዚአብሔር እራሱን በተለያየ መልክና ሁኔታ ገልጧል። ሰለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መለኮታዊ መገለጥ አንዱ ክፍል ሆኖ ይጠቃለላል። እነዚህ ሁሉ ለክርስቲያን የሥልጣን ምንጮቹ ናቸው። እግዚአብሔር በሥነ-ፍጥረት፣ በታሪክ ውስጥና በተለያዩ ሁኔታዎች ለምሳሌ በምሕረት ሥራው፥ በተአምራት፥ ለነቢያት በሰጠው ትንቢትና ባሳየው ራእይ ወዘተ. ራሱን ገልጧል። ከሁሉም ሌላ እግዚአብሔር ራሱን በክርስቶስና በቃሉ ነው የገለጠው። ሥነ-ፍጥረት ስለ እግዚአብሔር የተወሰነ ነገር ይነግረናል፥ ግን ሁሉንም አይሆንም። እንደዚሁም የዚህ መጽሐፍ ዓላማ አይደለም እንጂ፥ ታሪክን በክርስትና መስፈርት አንጻር ማጥናት እጅግ ጠቃሚ ነው። ያም ሆኖ ሰለ ክርስቶስ የምናውቀው ከመጽሐፍ ቅዱስ በምናገኘው እውነት ነው። የእግዚአብሔር መለኮታዊ መገለጥ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ክርስቲያን ያለውን የሥልጣን መሠረት እውቀት ለመረዳት ወሳኝ ነው። 

እስካሁን የሥልጣን መሠረታቸውን የቃኘነው የተለያዩ ሃይማኖቶች ጥልቅ እምነት አላቸው። ስለዚህ ክርስቲያንም “ይህ ነው የማምነው” የሚለው ነገር ሊኖረው ይገባል። ታዲያ አንድ ሰው ስለ እምነቱ ሲያጠና እግዚአብሔር በሰጠው አእምሮ መጠቀም ይገባዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ዋና ዋና አሳቦች መረዳቱ ቀላል ይምሰል እንጂ እውነቱ ግን የተለየ ነው፤ ትምህርቱን ለመረዳት ጥልቅና ሰፊ ምርምርን ይጠይቃል። በመሆኑም ትኩረታችን በመጽሐፍ ቅዱስ በሚገኘው የሥልጣን መሠረት ክልል ላይ መሆን ይገባዋል። አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያለ ጥናትና ምርምር ሊቀበል የሚችል ከመሰለው ተሳስቷል። እርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በሙሉ ለመረዳት የግሪክን፥ የዕብራይስጥንና ሌሎቹን የሴማዊያን ቋንቋዎች ማወቅና ማጥናት ይጠይቅ ይሆናል። እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበረውንና አሁን ያለውን የሥነ-መለኮት ትምህርት ይዘት፥ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ሌሎችንም ትምህርቶች ጠንቅቆ ማወቅን ይጠይቃል። ከዚህም ሌላ አመለካከታችንን በማስፋት፥ ቀደም ሲል ያልተገነዘብናቸውን እውነቶች እንድንረዳ የእግዚአብሔር እርዳታ ያሻናል። ቃሉ አዲስ የእውቀት ውጋጋን ስለሚፈነጥቅልን ስለ ዓለምም ሆነ ስለ ራሳችን ያለን ግምት ይለውጣል። ሕይወታችንም ትርጉም ያለው ይሆናል፡፡

ምናልባት እሰከ አሁን የተነጋገርንበት መሠረተ አሳብ ከጥርጣሬ ላይ የጣለው ሰው ቢኖር ይሆን መጽሐፍ ማንበብና ማጥናቱን እንዲገፉበት እናሳስበዋለን። ፍርድ ከመስጠት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ የሚለውን ማወቅ አይሻልም? በመጀመሪያ ከምስክሮች ሳይሰሙ ቀና ፍርድ መስጠት አይቻልም። ስለዚህ ስለ ሥልጣን መሠረት ያለዎት እምነት ባይጠከር እንኳን፥ ለምን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ የሚለውን አያጤኑም? 

በእንደዚህ ዓይነቱ አነስተኛ መጽሐፍ አንድን ትምህርተ-መለኮት ለመደገፍ ማስረጃ የሚሆኑ ጥቅሶችን ሁሉ ማስፈር አይቻልም። ስለሆነም ብዙዎቹን ጥቅሶች አንባቢው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚያገኛቸው ሌሎች ማስረጃዎች ጋር ሊያገናዝባቸው ይገባል። ስለ ሥነ-መለኮት ትምህርት የተጻፉ አንዳንድ መጻሕፍት በጣም ብዙ ጥቅሶችን ይደረድራሉ። ይህ ስሕተት አይደለም። ቢያንስ ነጥቡን የሚደግፉ ብዙ ጥቅሶች እንዳሉ ያሳያል። ነገር ግን አንባቢው በዚህ ረጅም ዝርዝር ተሰላችቶ አንዱንም ሳይመለከት ያልፋል። ለዚህ ሲባል በዚህ መጽሐፍ የተመለከቱት ጥቅሶች የተወሰኑ ናቸው። የተዘረዘሩትም በጠቃሚነታቸው ቅደም ተከተል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በርግጥ ስለ እነዚህም ሆነ ስለ ሌሉች የተለያዩ ጥቅሶች ያስተምራልን? ብለው ለማረጋገጥ ሲሉ እንደሚመለከቷቸው ተስፋ አደርጋለሁ። 

ወደዚህ ጥናት ከመግባትዎ በፊት ማበረታቻ የሚሆን ቃል ይሄውልዎ! መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ሁሉ እንዲረዱ የእግዚአብሔር ዕቅድ እንደሆነ ይወቁ። ይህ ማለት ግን መጽሐፉን አንድ ጊዜ፥ ከዚያም አልፎ በሕይወትዎ ዘመን ሁሉ በማንበብ እውነቱን ሁሉ ይጨብጣሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን ብዙ ሊማሩና ሊያውቁ እንደሚችሉ እርግጠኛ ይሁኑ። እግዚአብሔር ሊገባን በሚችል ቋንቋ ነው የሚናገረን። ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት እርሱ የሚናገረው ሁሉ እርግጥ እንደሆነ ይመኑ። ያልተረዱት ነገር ሲገጥምዎ ደጋግመው ይመልከቱት። እንዲሁም፥ መንፈስ ቅዱስ እውነቱን ሁሉ በመግለጥ እንደሚረዳዎ የተሰጠዎትን የተስፋ ቃል ያስታውሱ (ዮሐ. 16፡13፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡12)። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: