የክርስቶስ ራሱን ባዶ ማድረግ [Kenosis/ኪኖሲስ]

የክርስቶስን አካልና ተሠገዎ በተመለከተ የፊልጵስዩስ 2፡1-11 ትርጉም ብዙ ክርክር አስነስቷል። የክርክሩ መነሻ በቁጥር 7 ላይ ባለው ጥቅስ ውስጥ የሚገኘውና “ራሱን ባዶ አደረገ” የሚለው ግስ ነው። ጥያቄው በቀላሉ ሲገለጥ ክርስቶስ ወደ ምድር ሲመጣ ባዶ ያደረገው መለኮታዊነቱን በሙሉ፥ ወይስ ጥቂቱን ክፍል? የሚል ይሆናል። 

ሥጋ ከመልበሱ በፊት መለኮታዊ ባሕርይ እንደነበረው የዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 6 ያሳያል። ጥቅሱም ክርስቶስ በሥጋ በነበረበት ጊዜ በአምላክ መልክ መኖሩንም የሚያረጋግጥ ይመስላል። “መልክ” የሚለው ቃል ትርጉም ውጫዊ መመሳሰልን ሳይሆን፥ የመለኰት መተካከልን ነው የሚያመለክተው። በእግዚአብሔር የተመሰለ ሳይሆን እግዚአብሔር ነበር። በቁጥር 6 ላይ “በእግዚአብሔር መልክ” በሚል እና በቁጥር 7 ላይ “የባሪያ መልክ” በማለት የተጠቀሱት ሁለቱም አባባሎች እኩል እውነትነት አላቸው። ክርስቶስ ባሪያ (የሰው ዘር ከነበረ፥ መለኮታዊነት የለውም የሚሉ ወገኖች እንደሚሉት ሳይሆን፥ በርግጥ ክርስቶስ እግዚአብሔርም ነበር። በምንባቡ መሠረት የአንዱን እውነት ከሌላው መለየት አይቻልምና! 

ይሁንና ጳውሎስ ክርስቶስ ሥጋ በለበሰ ጊዜ ራሱን ባዶ አደረገ ሲል ምን ማለቱ ነው? “ባዶ አደረገ” የሚለው ትርጉም ክርስቶስ በምድር በነበረ ጊዜ፥ መለኮታዊ ባሕሪውን እንደተወ ወይም እንዳጣ አድርጎ ስለሚያሳይ፥ ትርጉሙ አሳሳች ይመስል ይሆናል። “ራሱን ባዶ አደረገ” የሚለው ቃል የሚያሳየው መለኮታዊ ባሕሪውን መቀነሱን ሳይሆን፥ ሰብአዊነትን ከውሱንነቱ ጋር መጨመሩ እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። እርግጥም ከጥቅሶቹ አኳያ ከተመለከትነው “ባዶ አደረገ” የሚለው ግስ እንደሚከተለው በሦስት መንገዶች ሊገለጥ ይችላል፡- 1. የባሪያን መልክ መያዙ፥ 2. እንደ ሰው መሆኑ፥ 3. በሰው መልክ መገኘቱ ናቸው። ራሱን ባዶ ማድረጉ በጥቅሱ በተጨማሪ ሲብራራ “ራሱን አዋረደ” ይላል። ሥጋ መልበሱም ሰብአዊነትን ከነውሱንነቱ በመውሰድ ራሱን ማዋረዱን ሲያሳይ፥ መለኮታዊ ባሕሪውን ግን በምንም ሁኔታ እንዳልተወ ያመለከታል። 

ጌታችን ወደ ምድር በመጣ ጊዚ መለኮታዊ ባሕርያቱን ቢተው ኖሮ፥ መሠረታዊ ባሕሪው ስለሚለውጥ በምድር በነበረበት ወቅት ፍጹም አምላክ መሆን ባልቻለም ነበር። ሰው ማንነቱን እስካልለወጠ ድረሰ ጠባዬ ሲለውጥ አይችልም። ብዙ ጊዜ ባሕርይን የሚቀንሱ ጐዳዮች ከሀሊነትንም ይቀንሳሉ (ሁሉን አዋቂነቱን፥ ሁሉን ቻይነቱን፥ አድራጊነቱን፥ በሁሉ ስፍራ መገኘቱን)። ገር ግን ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት በተናገርንበት ክፍል፥ በሥጋ በተገለጠበት ጊዜ እነዚህን ባሕርያት በሙሉ ይዞ እንደነበር አሳይተናል (ማቴ. 28፡18፤ 18፡20፤ ማር. 2፡8)። ስለዚህ ክርስቶስ በተሠገዎ ጊዜ መለኮታዊ ባሕሪውን ትቶ ነበር የሚል ማንኛውም ትምህርት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ አካልና ተሠገዎ ከቀረበ ማንኛውም ማስረጃ ጋር ይቃረናል። 

ይህ “ራሱን ባዶ አደረገ” የሚለው ትምህርት በትክክል ያዘለው መልእከት ምንድነው? ክርስቶስ ሥጋ ከመልበሱ በፊት የነበረው ክብር መጋረዱን (ዮሐ. 17፡5)፥ ኃጢአተኛ ሥጋ በመልበስ ራሱን ዝቅ ማድረጉንና (ሮሜ 8፡3)፥ በምድር በነበረበት ጊዜ ከመለኮታዊ ባሕርያቱ እንዳንዶቹን በፈቃዱ ሳይጠቀምባቸው መቅረቱን ይጨምራል (ማቴ. 24፡36)። ሰብአዊነቱ የከበረ ስላልነበር ለፈተና፥ ለድካም፥ ለሕመም፥ ለኅዘን የተጋለጠ ነበር። መለኮታዊ ባሕሪውን በፈቃዱ ሙሉ በሙሉ አልተጠቀመበትም፤ ይህ መለኮታዊ ባሕሪውን ቀንሷል ከማለት ይልያል። በእጅ ባለ ነገር አለመጠቀም ማለት የዚያን ነገር ባለቤትነት መቀነስ ማለት አይደለም።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: