የክርስቶስ ሰብአዊነት

ኢየሱስ ፍጹም አምላክ ብቻ ሳይሆን፥ ፍጹም ሰውም ነው። ይህን ስንል ስለ ሰው ካለን የተለመደ አሳብ ውጭ በአንድ መንገድ የተለየ መሆኑን ባለመዘንጋት ነው። ከኃጢአት የነጻ በመሆን ከሌላ ሰብአዊ ፍጡር ይለያል። 

ተሠገዎ [Incamation/ኢንካርኔሽን] 

ተሠገዎ ክርስቶስ ሰው የሆነበት መንገድ ነው። የቃሉ ትርጉም “ሥጋ መልበስ” ማለት ሲሆን፥ ይህም የተከናወነው ከድንግል ሲወሰድ ነው። በኢሳይያስ 7፡14 ስለተጠቀሰውና “ድንግል” ስለሚለው ቃል ብዙ ክርክር ቢኖርም፥ አዲስ ኪዳን ይህን ትንቢት በመጥቀስ በማቴዎስ 1፡23 ላይ የቃሉን ትርጉም በማስረዳቱ ትክክለኛነቱ አያጠያይቅም። በተጨማሪም የሕጻኑ በድንግል ማርያም ማኅፀን መፀነስ በመንፈስ ቅዱስ እንደተከናወነ ያስረዳል (ሉቃስ 1፡35)። 

ስለ ተሠገዎ አስፈላጊነት አዲስ ኪዳን የሚከተሉትን ዓላማዎች ይዘረዝራል፡- እግዚአብሔርን ለሰው ለመግለጥ (ዮሐ. 1፡18) ለሰዎች አኗኗር ኑሮ ምሳሌ ለመሆን (1ኛ ጴጥ. 2፡21)፥ ለኃጢአት መሥዋዕት ለመሆን (ዕብ. 10፡1-10)፥ የዲያቢሎስን ሥራ ለማፍረስ (1ኛ ዮሐ. 3፡8)፥ የታመነና መሐሪ የሆነ ሊቀ ካህን ለመሆን (ዕብ. 5፡1-2)፣ በዳዊት ዙፋን ለዘላለም ይነግሣል የተባለውን ትንቢት ለመፈጸም (ሉቃስ 1፡31-33)። እነዚህ ሁሉ ዓላማዎች በስፋት መጠናታቸው አስፈላጊ ቢሆንም፥ ለጊዜው ግን ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ነው የምናየው። ክርስቶስ በስብእናው ምሳሌያችን ሆኗል። ሰው ተፈጥሮው ሟች ነው፤ ስለሆነም አዳኛችን ለመሞት ሥጋ መልበስ ነበረበት። በምድር ላይ እንደ ሰው ስለተመላለሰ፥ እንደ እውነተኛ ካህን ሊረዳንና ሊያዝንልን ይችላል። ሰብአዊነቱም ፍጹም እንደነበረ ማስታወስ አለብን (ዕብ. 4፡15፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡21)። 

የሰብአዊነቱ ማረጋገጫ 

የሰው አካል ነበረው። ምንም እንኳን ክርስቶስ የተፀነሰው ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ ቢሆንም፥ የሰው አካል ነበረው። እንደ ማንኛውም ሰው ነው ተወልዶ ያደገው (ማቴ. 1፡18፤ ገላ. 4፡4፤ ሉቃስ 2፡52)። ራሱን ሰው እያለ ነበር የሚጠራው፤ ሌሎችም በዚህ መጠሪያ ጠርተውታል (ዮሐ. 8፡40፤ 1ኛ ዮሐ. 1፡1)። 

የሰው ነፍስና መንፈስ ነበረው። የክርስቶስ ስብእና አካል፥ ነፍስና መንፈስ እንደነበረው፥ ማለትም ቁስ አካላዊ የሆነና ያልሆነ እንደነበር ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ይህ ማለት በመለኮታዊነቱ ነፍስና መንፈሱን፥ በሰብአዊነቱ ደግሞ አካሉን አዘጋጀ ማለት አይደለም። ሰብአዊነቱ ፍጹም ሲሆን፥ ይህም ቁስ አካላዊ የሆነውንና ያልሆነውን ክፍል ያዋሃደ ነበር (ማቴ. 26.383 ሉቃስ 23፡46)። 

ኢየሱስ የሰው ባሕርይ ሁሉ ነበረው። ተርቧል (ማቴ. 4፡2)። ተጠምቷል (ዮሐ. 19፡28)፥ ደክሞታል (ዮሐ. 4፡6)፣ ፍቅርና ርኅራኄ ተሰምቶታል (ማቴ. 9፡36)፥ አልቅሷል (ዮሐ. 11፡35)፥ ተፈትኗል (ዕብ. 4፡15)። 

የሰው ስም ነበረው። የአዳኝነትን ሥራ የሚያከናውነው እምላክና ከሚመጣው ንጉሥ ጋር በማዛመድ ራሱን “የሰው ልጅ” በማለት ጠርቷል (ሉቃስ 19፡10)። የዳዊት ልጅ (ማር. 10፡47)፥ ኢየሱስ (ማቴ. 1፡21) እና ሰው (1ኛ ጢሞ. 2፡5) ተብሎ ተጠርቷል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: