የክርስቶስ ትንሣኤና ዕርገቱ

የትንሣኤውእውነተኛነት። 

ክርስቶስ በአካል የመነሣቱ እውነተኛነት በመጽሐፍ ቅዱሳችን በስፋት ተገልጧል። ሰዎች ባዶ መቃብር ነው ያዩት። ለምን ባዶ እንደሆነ ለማስረዳት ብዙ ምክንያቶች ይደርደሩ እንጂ፥ ከሞት መነሣቱን ከሚያረጋግጡት አባባሎች በቀር ሌሎቹ የሚታመኑ አይደሉም። ደቀ መዛሙርቱ በስሕተት ሌላ መቃብር ስፍራ ሄደው፥ ባዶ መቃብር ስላጋጠማቸው ነው የሚሉ አሉ። ይህን ለማመን ያዳግታል፤ ምክንያቱም፥ ሮማውያን ወታደሮችና መላእክት የክርስቶስን መቃብር ይጠብቁ ስለነበር ደቀ መዛሙርቱ መቃብሩን በቀላሉ ማግኘት አልተሳናቸውም ነበር። በዚያኑ ሰሞን በድኑ ተሰርቋል የሚል የፈጠራ ወሬ ተናፈሰ (ማቴ. 28፡11-15)። ታዲያ ይህ እርግጥ ከሆነ፥ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል ብለው መስበክ ሲጀምሩ ለምን በድኑ ለማስተባበያነት አልቀረበም? እንዲያ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ስብከታቸውን ወዲያውኑ ማስቆም በተቻለ ነበር። ስለዚህ በድኑ ተሰርቋል ማለት፥ ደቀ መዛሙርቱ ሐሰት መሆኑን ለሚያውቁት ነገር ሰማእትነትን ለመቀበል ፈቅደው ነበር ብሉ እንደመደምደም ይቆጠራል። መቃብሩ ስፍራ የታየው የከፈን ጨርቅ በሥርዓት መገኘቱም በድኑ ተሰርቋል የሚለውን ወሬ ሐሰተኛነት ያረጋግጣል። ሌቦች ከፈኑን ከበድኑ ላይ የሚገፉበት ምክንያት ካለመኖሩም በላይ፥ አድርገውትም ቢሆን ኖሮ ጨርቁ በወጉ ሳይሆን፥ በተመሰቃቀለ ሁኔታ በተገኘ ነበር (ዮሐ. 20፡6-7)። ስለዚህ የዚያን ባዶ መቃብር ምስጢር ከትንሣኤ ሌላ ሊገልጠው የሚችል ቃል አይኖርም። 

ሁለተኛ፣ ከትንሣኤው በኋላ የጌታ መታየት ከሙታን መነሣቱን ሲያረጋግጥ፥ የታየውም በተለያዩ ቦታዎች ለተለያዩ ሰዎችና በተለያየ ሁኔታ ነበር። ይህ ሁሉ ለማታለል የተቀነባበረ ትርኢት ሊሆን እንደማይችል እንረዳለን (ዮሐ. 20፡11-17፤ ማቴ. 28፡9-10፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡5፤ ሉቃስ 24፡13-35፥ 36-43፤ ዮሐ. 20፡26-29፥ 21፡1-23፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡6)። ክርስቶስን ከትንሣኤው በኋላ ያዩት የዓይን ምስክሮች ቁጥር ብዛት እራሱ፣ ትንሣኤው በጥቂቶች የተፈጠረ ታሪክ ነው የሚለውን አሳብ ውድቅ ያደርገዋል። 

ሦስተኛ፥ በተከታታይ በታሪክ የተከናወኑት ድርጊቶችም የክርስቶስን ትንሣኤ ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ በበዓለ አምሳ ዕለት ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ከሁለት ወራት በፊት ከሙታን ተለይቶ መነሣት በኢየሩሳሌም ሲሰብክ የተቃረነው ወይም የተቃወመው ሰው አልነበረም። እንዲያውም 3000 ያህል ሰዎች ስብከቱን ሰምተው አመኑ። በጴጥሮስም ሆነ አብረውት በነበሩ ሰዎች ላይ የታየው መንፈሳዊ ለውጥ፥ የቤተ ክርስቲያን እድገት፥ የአምልኮ ቀን እሁድ መሆን፥ በአጠቃላይ የትንሣኤው ውጤቶች ናቸው። 

የትንሣኤው ባሕርይ። 

ክርስቶስ በአካል ነው ከሞት የተነሣው፡፡ ይህ የመንፈሱን ወይም “የተጽዕኖሎ” ትንሣኤ አይደለም። ትንሣኤው፥ በደፈናው ትዝታው ብቻ አብሮን ይኖራል ማለት ሳይሆን ተጨባጭና አካላዊ ነበር። በትንሣኤ የከበረ አካሉም፣ ለደቀ መዛሙርቱ ታይቷል፥ ተዳሷልም (ሉቃስ 24፡39፤ ዮሐ. 20፡27)። ከእነርሱ ጋር በመመገብም አካላዊ ድርጊቶቹን አሳይቷቸዋል (ሉቃስ 24፡42-43)። ከመቃብር የተነሣው አካል ከተሰቀለውና ከተቀበረው አካል ጋር አንድ መሆን በግልጥ ተረጋግጧል። 

ነገር ግን ልዩ የሆነበት ሌላ ነገር ተፈጥሯዊ ገደቦች የማይወስኑት መሆኑ ነው። ለምሳሌ ከትንሣኤው በኋላ በተዘጉ በሮች ውስጥ ማለፍ ችሏል (ዮሐ. 20፡19)። ከሁሉም የላቀው ቁም ነገር ግን፥ ዳግመኛ የማይሞት መሆኑ ነው (ሮሜ 6፡9)። 

የትንሣኤው ጥቅም 

ትንሣኤው ክርስቶስ ስለ ራሱ የተናገረውና ያስተማረው ሁሉ እውነት መሆኑ የተረጋገጠበት ነው። ባዶው መቃብር አጠገብ የነበረው መልአክ ይህን አጠናክሮታል (ማቴ. 28፡6)፤ ጴጥሮስም በበዓለ አምሳ ዕለት ደግሞታል (ሐዋ. 2፡30-31)። 

ትንሣኤው ለኃጢአት ይቅርታ ዘላለማዊ ዋስትና ነው (1ኛ ቆሮ. 15፡17)። እምነታችን በተረት ወይም ሰው ሠራሽ በሆን ታሪክ ሳይሆን፥ እውነተኛ በሆነና በተረጋገጠ ወንጌል ነው። 

የክርስቶስ ትንሣኤ የሰዎችን ሁሉ ከሞት መነሳት የሚያረጋግጥ ዋስትና ሲሆን፥ ይህም ያመኑት ለዘላለም ሕይወት፥ ያላመኑት ለዘላለም ስቃይ የሚነሱበት ይሆናል (ዮሐ. 5፡28-29)። ፈራጁ ከሞት ስለተነሣ፥ ወደፊት ፍርድ መኖሩ እርግጥ ነው (ሐዋ. 17፡31)። 

ትንሣኤው ለአማኙ ሕይወትና የአገልግሎት ኃይል በመስጠት፥ የትንሣኤ ራስ ከሆነው ክርስቶስ ጋር ያለውን ኅብረት ያጠነክርለታል (ኤፌ 1፡19-22)፤ የሚራራለት ሊቀ ካህን እንዳለውም እርግጠኛ እንዲሆን ያደርገዋል (ዕብ. 4:14-16)። 

የዕርገቱ ጥቅም 

ጌታችን እንደሚያርግና እንደሚከብር ራሱ ተንብዮ ነበር (ዮሐ. 6፡62፥ 17፡1)። ይህ ከትንሣኤው አርባኛ ቀን በኋላ ተፈጽሟል (ሐዋ. 1፡9-11)። የዕርገቱ ጥቅም የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡- 

1. በምድር የነበረው የውርደትና የውሱንነት ጊዜ ማብቃቱን፥ 2. በአብ ቀኝ በክብር ከፍ ከፍ የሚልበት ጊዜ መጀመሩን (ኤፌ. 1፡20-23)፥ 3. በቀዳሚነቱ፥ እንደ መልህቅ ሆኖ ለነፍሳችን እረፍት እንደሚሰጣት (ዕብ. 6፡20)፣ 4. ለእኛ እንደ ሊቀ ካህን በመሆን የአሁን አገልግሎቱን መጀመሩን (ዕብ. 4፡14-16) በአባቱ ዘንድ መኖሪያ እያዘጋጀልን መሆኑን (ዮሐ. 14፡2)፥ እና 5. የቤተ ክርስቲያን ራስ ሆኗልና አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ስጦታ በመላክ ላይ መሆኑን ነው (ቈላ. 1፡18፤ ኤፌ. 4፡8)። 

የክርስቶስ የአሁን ዘመን አገልግሎት 

የጌታችን የአሁን ዘመን አገልግሎት፥ ከአማንያን ጋር በይበልጥ የተዛመደ ሲሆን፥ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ደግሞ ለማያምኑ ሰዎች አብርሆተ እግዚአብሔርን መስጠትና ዳግም መወሰድ የመሳሰሉትን ጉዳዮች ይጨምራል። ከክርስቶስ እገልግሎቶች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው። 

(1.) ለሕዝቡ በመጸለይ ላይ ነው። ይህ ለአማኞች አያሌ ጥቅም አለው፡- ዘላለማዊ ደኅንነታቸውን ያረጋግጣል (ዕብ. 7፡25)፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የቤተሰብነት ኅብረት ያጠነክርላቸዋል (1ኛ ዮሐ. 2፡1)። ኃጢአትን የመከላከል ኃይል ይሰጣቸዋል (ዮሐ. 17፡15)። 

(2) ክርስቶስ ለእኛ የዘላለም መኖሪያ ቦታ በማዘጋጀት ወደ እርሱ የምንወሰድበትንና ከእርሱ ጋር የምንሆንበት ቀን በመጠበቅ ላይ ነው (ዮሐ. 14፡3)። 

(3.) አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን እየገነባ ነው (ማቴ. 16፡18)። 

(4.) እንደ ቤተ ክርስቲያን ራስነቱ አካላቱ የሚሆኑትን አማኞች ወክሎ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል። እንዳረገ ለሰዎች ሁሉ ስጦታ መሰጠቱን ተመልክተናል (ኤፈ. 4፡11)። ይህ ስጦታ ማንኛውም ሰው ተግባሩን በትክክል እንዲያከናውን የሚረዳ ነው። ክርስቶስ ራሱም አካሉ በሆነ ማንኛውም አማኝ ያድርበታል (ገላ. 2፡20)። እርሱ በእኛ ይኖራል፥ በተጨማሪም በእኛ ውስጥ የሚኖር መንፈስ ቅዱስን ልኮልናል። በእኛ የመኖር ኃይሉ የሚለካው በትንሣኤውና በዕርገቱ ነው (ኤፈ. 1፡18-20)። ትንሣኤው ኃይሉ ከመሸነፍ በኋላ ድልን ማስገኘቱን፥ በአብ ቀኝ መቀመጡ ደግሞ ኃይሉ በውርደት ፋንታ ክብር ማምጣቱን ያረጋግጣል። ከዚህም ሌላ አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በመንከባከብና በማሳደግ ላይ ነው (ኤፌ. 5፡29)። የነዚህ ቃላት ዋና አሳብ ጌታችን የሕዝቡን እድገት በጥንቃቄ የሚንከባከብና የሚጠብቅ መሆኑን ነው የሚያስረዳን። ራስ እንደመሆኑ አንድነትንና አመራርን ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣል (ኤፈ. 2፡20-21)። 

(5 .) ጌታ ጸሎታችንን በመመመለስ ተግባር ላይ ነው (ዮሐ. 14፡14)፡፡ በስሙ ስንጸልይ መልስ ይሰጣል፡፡ ውጤቱም በምድር ሳለ ካደረገው የላቀ ነው (ዮሐ. 14፡12)። ይህም እጅግ የሰፋ (ሁለንተናዊ የሚሆን) በዓይነትም የገዘፈ (መንፈሳዊ በረክቶችን ሁሉ የሚያቅፍ) ነው። 

(6.) ለተለያዩ ችግሮች እርዳታ ይሰጣል (ዕብ. 4፡16)። ችግር በገጠመን ጊዜ እርዳታው እንደማይለየን በዚህ ጥቅስ መሠረት ቃል ገብቶልናል። ይህም ፈተና በገጠመን ጊዜ የሚደረግልንን እርዳታ ይጨምራል (ዕብ. 2፡18)። 

(7.) ተከታዮቹ ፍሬያማ እንዲሆኑ ይፈልጋል (ዮሐ. 15፡1-16)። 

ክርስቶስ ሕያው ባይሆን ኖሮ እነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች ዛሬ ተግባራዊ ባልሆኑ ነበር። 

የወደፊቱ የክርሰቶስ አገልግሎት 

የወደፊቱ የጌታችን አገልግሎቶች፥ በቤተ ክርስቲያን ንጥቀት ወቅት የራሱ የሆኑትን ለመውሰድ መምጣት (1ኛ ተሰ. 4፡13-18)፥ በምድር ላይ በሚደርሰው የፍዳ ዘመን “የበጉን” ቁጣ ማፍሰስ (ራእይ 6፡16-17፥ ዮነገሥታት ንጉሥ፥ የጌቶች ጌታ ሆኖ ዓለምን በብረት ዘንግ ለመግዛት መመለስ (ራእይ 19፡11-16) ሲሆኑ፥ ንጉሥነቱም በመጀመሪያ የሺህ ዓመቱን መንግሥት ከዚያም ዘላለማዊ አገዛዙን ይጨምራል። እነዚህን ጉዳዮች በምዕራፍ 9 ላይ በስፋት እናጠናቸዋለን። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.