ስለ አጋንንት ትምህርት

አጋንንት ምንድ ናቸው? 

የአጋንንትን አመጣጥ አስመልክቶ ከክርስቲያኖችም ሆነ ከአሕዛብ ለዘመናት የተለያዩ መላምቶች ተሰንዝረዋል። ግሪኮች በሞት የተለዩ ክፉ ሰዎች ነፍሳት ናቸው ብለዋቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ደግሞ አጋንንት ከአዳም በፊት ከነበሩ ዝርያዎች የወጡ መናፍስት ናቸው ይላሉ። ይህ አሳብ መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረን ባይህንም፥ በመጽሐፉ ግን አይደገፍም፤ ስለ እዚህ ዝርያዎች የሚነግረን አንዳችም ነገር የለም። ነገር ግን ድጋፍ ያልተለየው ሌላ አስተያየት አለ። ይህም፥ አጋንንት አለቃቸው ተብሎ ከተጠራው ሰይጣን ጋር የወደቁ መላእክት ናቸው የሚል ነው (ማቴ. 12፡24)። በዚሁ መሠረት ሁለት ዓይነት የወደቁ መላእክት እንዳሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ እንረዳለን። እነዚህም በአንድ ወገን ያሉት እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስከተወሰነ ደረጃ ለመቃወም ነጻነት ያላቸው ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ደግሞ በእሥር ያሉ ናቸው (2ኛ ጴጥ. 2፡41 ይሁዳ 6)። ምንም እንኳ እነዚህ በሁለተኛው ወገን ያሉት ለምን ታሠሩ? የሚለው ጥያቄ ክርክር (አስፈላጊ ያልሆነ ንትርክ) ቢያስከትልም በዘፍጥረት 6፡2-4 ላይ የተጠቀሰውን ተፈጥሯዊ ያልሆነ ኃጢአት ስለሠሩ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል። ነጻ ሆነው ከሚንቀሳቀሱት አጋንንትም እንኳን አንዳንዶቹ በታሪክ ውስጥ ለተወሰነ ዘመን ብቻ ከታዩ በኋላ የደረሱበት አለመታወቁ ይነገራል (ራእይ 9፡14፥ 16፡14)። 

አጋንንት ምን ይመስላሉ? 

አጋንንት አፈጣጠራቸው እንደ መላእክት ሲሆን፥ ባሕርያቸውም ተመሳሳይ ነው። መንፈስ የሆኑ ፍጡራን መሆናቸው ቢታመንበትም፥ ሥልጣናቸው የተገደበ ስለሆነ፥ በሁሉም ቦታ ለመገኘት አይችሉም። በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ ብቻ ለመወሰን ይገደዳሉ። በማቴዎስ 17፡18 ላይ አጋንንት የተባለው በማርቆስ 9፡25 ላይ እርኩስ መንፈስ መባሉን ያስተውሉ። 

አጋንንት እንደ መላእክትና ሰይጣን ትልቅ እውቀት እንዳላቸው ይታያል። መጽሐፍ ቅዱስ አጋንንት ኢየሱስን እንዳወቁት ይገልጣል (ማር. 1፡24)። ፍጻሜያቸው ፍዳ መሆኑና (ማቴ. 8፡29)፤ የድነት (ደኅንነት) ዕቅድ መኖሩንም ቀደም ሲል ያውቁታል (ያዕ. 2፡19)። እንዲሁም የተደራጀና እየተስፋፋ የሚሄድ ትምህርት እንዳላቸው እናያለን (1ኛ ጢሞ. 4፡1-3) ። በተለይ በቤተ ክርስቲያን ዘመን ማብቂያ ላይ ማታለያ ትምህርታቸው እያደገና እየተጠናከረ ይሄዳል። 

አጋንንት ምን ያደርጋሉ? 

በአጠቃላይ አጋንንት እንደ ሰይጣን በተቻላቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ዓላማ ለማጣመም ይጥራሉ (ዳን. 10፡10-14፥ ራእይ 16፡13-16)። ይህን በማድረግ ነው የሰይጣንን ሥራ የሚያስፋፉት። በሰይጣን ሥር ያሉ አጋንንት ቁጥር እጅግ ብዙ ስለሆነና የማሳሳት ተልእኳቸውን ለማሳካት በየአቅጣጫው ስለሚሰማሩ፥ ሰይጣን በእንቅስቃሴው ውሱን ቢሆንም በሁሉም ቦታ የሚገኝ ያስመስሉለታል። 

አጋንንት ሰዎችን በተለይ በበሽታ ያጠቃሉ (ማቴ. 9፡33፤ ሉቃስ 13፡11፥ 16)፥ በእንስሳት ውስጥ ያድራሉ (ማር. 5፡13)፥ የሐሰት ትምህርት ያስፋፋሉ (1ኛ ጢሞ. 4፡1)። እግዚአብሔር እንዳንድ ጊዜ ዕቅዱን ለማከናወን በአጋንንት ሲጠቀም እንመለከታለን (1ኛ ሳሙ 16፡14፤ 2ኛ ቆሮ. 12፡7)። ይህም የሚያስገዝበን እነዚህ ፍጥረታት በእግዚአብሔር ፍጹም ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ነው)። 

አጋንንት በመንግሥታት ጉዳይም ጣልቃ የሚገቡ ይመስላሉ። በዳንኤል 10፡13 “የፋርስ መንግሥት አለቃ” የሚለው ለዳንኤል መልስ ይዞ የመጣውን መልአከ የተቃውመውን መንፈሳዊ አካል ሳይሆን አይቀርም። ይሆን መንፈስ ሊቋቋመው የቻላው ሊቀ መላእክት ሚካኤል መሆኑም ለአጋንንት እጅግ ኃይለኛነት ማስረጃ ነው። በባቢሎንና በጢሮስ መንግሥታት ጀርባም የዚህ ዓይነት የክፋት ኃይል እንዳለ ታይቷል (ኢሳ. 14፤ ሕዝ. 28)። ክፉ መናፍስት መንግሥታትን እንደሚያታልሉ በዮሐንስ ራእይም ተጠቅሷል (ራእይ 16፡13 14)። በኢሳይያስ 24፡21 ላይ እግዚአብሔር በመጨረሻ “በከፍታ ላይ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ” እንደሚቀጣቸው ያመለክታል። ከነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ በተዘዋዋሪ መንገድ የምድር ነገሥታትን የሚያሳትፍ አጠቃላይ ጦርነት እንደሚካሄድና አንዳንድ አጋንንት የመንግሥታትን ጉዳይ እስከመምራት ድረስ ኃይል የሚኖራቸው መሆኑን ነው። አጋንንት በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሚና መለየቱ ቢያዳግትም፥ ዛሬም ቢሆን ተጽእኖ እንደሚያደርጉ ግልጥ ነው። 

በአጋንንት መያዝ የሚባል ነገር አለ? 

በአጋንንት የመያዝ ጉዳይ ትኩረትን የሚሻው፥ ቀደም ሲል የተረጋገጠና አሁንም ያለ በመሆኑ ሰለሆን ብቻ ሳይን ጌታም እርገጠኛነቱን የተናገረ ስለሆነ ነው። 

እርሱም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ እጅ በመጫንና ዘይት በመቀባት፥ በፈወሰው አካላዊ በሽታና በአጋንንት ደዌ መካከል ያለውን ልዩነት ተረድተው ነበር። በአጋንንት የተያዘን በሽተኛ ለማዳን፥ ከበሽተኛው ለቆ እንዲወጣ አጋንንቱን ማዘዝ ያስፈልግ ነበር (ማቴ. 10፡8፥ ማር. 6፡13)። 

በአጋንንት መያዝን የመለየት ብቸኛ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጥ የታወቁ በአጋንንት የመያዝ ምሳሌዎች ላይ የተጠቀሱትን ባሕርያት መመልከት ነው። ይህ ካልሆን ምልክቱ ማንኛውንም ሕመም ስለሚመስል መለየቱ ያስቸግራል (ማቴ. 9፡32-33)። ያም ሆነ ይህ፥ በአጋንንት መያዝ ማለት፥ ኣጋንንት በሰው ውስጥ በማደር የሰውየውን አእምሮ ወይም አካል በቀጥታ ቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ ማለት ነው። 

በአጋንንት መያዝንና በአጋንንት ተጽዕኖ ሥር መውደቅን መለየት መቻል እጅግ ወሳኝ ነው። አጋንንት ሥራውን የሚሠራው በተያዘው ሰው ውስጥ በመዋሃድ ሲሆን፥ ተጽዕኖው ሥር መውደቅ ግን፥ አጋንንቱ ከሰውየው ውጭ በመሆን ተጽዕኖ ሲያደርስበት ነው። ይህ ነው ዋናው ልዩነት። እርግጥ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በአጋንንት የተያዘ ወይም የተለከፈ ሰው የሕመም ምልክትና ባሕርይ አንድ ዓይነት ሊሆን ይችላል። ክርስቲያንን አጋንንት ሊይዘው ይችላልን? የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱ አይችልም ነው። ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስ በአማኙ ውስጥ መኖር አጋንንትን የመሰለ ሌላ ተቀናቃኝ መንፈስ አብሮት እዚያው እንዲኖር አይፈቅድለትም። ነገር ግን ጥያቄው ክርስቲያን በአጋንንቶች ይጠቃል ወይ? የሚል ከሆነ፥ መልሱ አዎ ነው። ጥቃቱም ልክ እንደ ማንኛውም በአጋንንት እንደተያዘ ሰው ሊሆን ይችላል። ከላይ እንደተጠቀሰው አልፎ አልፎ አካላዊ ሕመም በአጋንንት የመያዝ፥ ወይም የመከበብ ውጤት ሲሆን (ማቴ. 9፡32-33)፤ አንዳንድ ጊዜም የአእምሮ መዛባት በአጋንንት ከመለከፍ የመነጨ ይሆናል (ማቴ. 17፡15)። ይህ ግን ሁልጊዜ የሚደርስ ስላለመሆኑ ዳንኤል 4ን ይመልከቱ። 

አንድ ሰው በስሜትና በአእምሮ ተረብሾ ሲታይ፥ ምክንያቱ አንድ ወይም ብዙ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን፥ ብዙ ሆነው ነው የሚገኙት። ከዚህም የተነሳ ለችግሩ መፍትሔ ለመሻት በጣም ያስቸግራል። የህክምና እርዳታ ብቻ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሲኖር፥ ከዚህ ለተለየ በሽታ ግን አጋንንት ወደሚወጣበት መንፈሳዊ ስፍራ መውሰድ ያስፈልግ ይሆናል። አጋንንትን ማስወጣት የሚቻል ይሁን እንጂ፥ ተግባሩ ግን ቀላል አይደለም። ጌታ አጋንንት ከተባረሩ በኋላ፥ ከነሱ የከፉትን አጋንንት በመጨመር ወደለቀቁት ሰው እንደሚመለሱና የበለጠ አደጋ እንደሚያደርሱበት አስጠንቅቋል (ሉቃስ 11፡24 26)። አጋንንት ከአንድ ሰው እንደወጣ የሚያድርበት ሌላ ሰው መፈለጉ አይቀርም። 

የአጋንንት ፍጻሜ 

አንዳንድ አጋንንት ለጊዜው ታሥረዋል። ለምሳሌ በክርስቶስ የሕይወት ዘመን ነጻ የነበሩት ወደ ጥልቁ ተወርውረዋል (ሉቃስ 8፡31)። አሁን የታሠሩት ደግሞ በፍዳ ዘመን ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ይለቀቃሉ (ራእይ 9፡1-11፥ 16፡13-14)። ይሁን እንጂ፥ አጋንንት በመጨረሻ ከሰይጣን ጋር ወደ እሳት ባሕር ለዘላለም ይጣላሉ (ማቴ. 25፡41)።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: