ስለ መላእክት ትምህርት

የመላእክት ዓለም ካለፉት ዘመናት ይልቅ በአሁኑ ጊዜ ይበልጥ ይታመናል። ስለ ሰይጣን ቤተ አምልኮዎች በስፋት ይነገራል። እንደዚሁም የታወቁ መጽሔቶች ሳይቀሩ ስለ አጋንንት ሥራዎች በብዛት ይጽፋሉ። በዚህም የተነሳ ሕዝቦች የመናፍስትን ዓለም መኖር ወደማመኑ፥ ያም ባይሆን ሊኖር ይችላል ወደማለቱ እድልተዋል። 

መላእክት እርግጥ አሉ? 

ማንም መላእክት የሉም ብሎ ሊያረጋግጥ አይችልም። በዓለማት ስለሚኖሩ ፍጥረታት ሙሉ እውቀት አለኝ የሚል ሰውም ፈጽሞ ማግኘት አይቻልም። አንድ ሰው ማለት የሚችለው ነገር ቢኖር፥ በእውቀቱ ከደረሰበት በመነሳት መላእክት እንዳሉ አላምንም ማለት ብቻ ይሆናል። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚገልጠው ሌላ የፍጥረታት ሥርዓት መኖሩን ይቀበላሉ። አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ማስረጃዎች ከተቀበለ፥ ስለ መላእክት መኖር ለማመን ችግር አይኖርበትም። በእርግጥ ማስረጃዎቹ ጠንካራ ናቸው። 

በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ክፍሎች ስለ መላእክት የሚገልጥ ትምህርት ይገኛል። ትምህርቱ በአንድ መጽሐፍ፥ በአንድ ጸሐፊ፥ ወይም በአንድ ዘመን የተወሰነ አይደለም። ስለ መላእክት መኖር ቢያንስ በሰላሳ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ተገልጧል። በተጨማሪም አስፈላጊ ባልሆነባቸው ጊዜ እንኳን ጌታችን ስለ መላእክት መኖር አንስቶ ተናግሯል። አንዳንዶች ጌታ ስለ መላእክት፥ አጋንንት እና ሰይጣን የተናገረው በጊዜው በነበሩ ያልተማሩ ሰዎች ዘንድ ለመከበርና ለመፈራት ሲል ነበር ይላሉ። በሌላ አነጋገር ስለ መናፍስት በሚናገርበት ጊዜ ለመታየት ያህል እንዳደረገው ይቆጥሩታል። የእርሱ ዓላማ ግን ይህ አልበረም። ያም ሆነ ይህ፣ ማንም ቢሆን ከዚህ የሚረዳው ጌታ ራሱ የመናፍስቱን መኖር መግለጡን ነው (ማቴ. 18፡10፥ 26፡53)። 

መላእክት ምን ይመስላሉ? 

መላእክት አካል ያላቸው ፍጥረታት ናቸው። እውቀትም አላቸው (1ኛ ጴጥ. 1፡12)፥ ስሜት አላቸው (ሉቃስ 2፡13)፣ ፈቃድ አላቸው (ይሁዳ 6)። መላእክት እንደ እግዚአብሔር ባይሆኑም መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው (ዕብ. 1፡14)። መላእክት አካል ሰላላቸው ውሱኖች ቢሆኑም፥ ውሱንነታቸው ግን እንደ ሰው አይደለም። ዘርን የመተካት ተፈጥሮ የላቸውም፤ ማለትም አይዋለዱም (ማር. 12፡25)፥ አይሞቱም (ሉቃስ 20፡36)፡፡ የሚጠሩት በተባዕታይ ጾታ ነው (ዘፍጥ. 18፡1-2 ምናልባት ከዘካርያስ 5፡9 በስተቀር)። ክንፍ አላቸው (ኢሳ. 6፡2)፡፡ ብዛታቸው ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም (ዕብ. 12፡22)። 

በጣም አስደናቂ ባሕርያቸው ግን የተደራጁ መሆናቸው ነው። ሊቀ መላእክት ተብሎ የሚጠራው ሚካኤል ብቻ ሲሆን (ይሁዳ 9)፥ ሌሎችም ይኖሩ ይሆናል (ዳን. 10፡13 ከዋናቹ አለቆች አንዱ ብሉ ስለሚጠራው)። በነዚህ ከፍተኛ ገዥዎች ሥር ሌላ የመላእክት ግዛት ክፍፍል ያለ ይመስላል (ኤፈ. 3፡10)። አማኛች ጠባቂ መላእክት እንዳላቸው ይገመታል (ዕብ. 1፡14)፥ ሕፃናትም እንዲሁ (ማቴ. 8፡10)። የአንዳንድ መላእክት (“ሱራፌል”) ልዩ ሥራ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው (ኢሳ. 6፡1-3)። የሌሎቹ ደግሞ (“ኪሩቤል”) ቅድስናውን መጠበቅ ነው (ዘፍጥ. 3፡22-24)። እዚህ ላይ አንድ ጠቃሚ ነጥብ አለ። ይሄውም መላእክት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማገልገል የተደራጁ ከሆኑ፥ የእግዚአብሔር ሰዎችም ለዚሁ ዓላማ መደራጀት ይገባቸዋል የሚል ነው። 

መላእክት ምን ያደርጋሉ? 

መላእክት ለተለያዩ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች የሚሰጡት አገልግሎት ግልጥና የማያሻማ ነው። 

ለክርስቶስ የሰጡት አገልግሎት። በጌታችን ሕይወት ዘመን የታየው የመላእክት እንቅስቃሴ አያሌ ነበር። ለምሳሌ መወለዱን አመልክተዋል (ሉቃስ 1፡26-33)፤ መወለዱን አብስረዋል (ሉቃስ 2፡13)፤ በሕጻንነቱ ጠብቀውታል (ማቴ. 2፡13)፤ ከፈተናው በኋላ አገልግለውታል (ማቴ. 4፡11)፤ ከጠላቶቹ ሊከላከሉት ተዘጋጅተው ነበር (ኦርሱ አልጠራቸውም እንጂ ማቴ. 26፡53)፤ በጌቴሴማኒ አበርትተውታል (ሉቃስ 22፡43)፤ ድንጋዩን ከመቃብሩ አፍ በማንከባለል ትንሣኤውን አውጀዋል (ማቴ. 28 ፡2፥ 6)። 

ለአማኞች የሚሰጡት አገልግሎት። በአጠቃላይ አማኞችን ይረዳሉ (ዕብ. 1፡14)። ይህ በተለይ ጸሉትን በመመለስ ተግባር መሳተፋቸውን ይጨምራል (ሐዋ. 12፡7)። በአደጋ ጊዜ ሲያበረታቷቸው (ሐዋ. 27፡23-24)፣ አማኞች በሚሞቱበትም ጊዜ እንክብካቤ ያደርጉላቸዋል (ሉቃስ 16፡22፤ ይሁዳ 9)። አማኞችም የድነትን (ደኅንነትን) ትርጉም በሕይወታቸው በማሳየት መላእክትን ያገለግላሉ (1ኛ ቆሮ. 4፡9፤ ሉቃስ 15፡10)። 

ለዓለም አገሮች የሚሰጡት አገልግሉት። ሚካኤል ሊቀ መላእክት መሆኑን አይተናል። በተለይም የእስራኤል ጠባቂ መሆኑም ተነግሯል (ዳን . 12፡1)። ሌሎች አገሮችም መላእከት ያላቸው ይመስላል (ዳን. 10፡21)። በፍዳ ዘመን አሕዛብ ላይ ፍርድን ለማስፈጸም በግልጥ ይሳተፋሉ (ራእይ 8፡9፥ 16)። 

ለማያምኑ ሰዎች የሚሰጡት አገልግሎት። ሄሮድስ በታበየ ጊዜ በሞት የቀጣው መልአክ ነበር (ሐዋ. 12፡23)። በመጨረሻ ዘመንም ጻድቃንን ከኃጥአን የሚለዩ መላእክት ናቸው(ማቴ. 13፡39)። 

እነዚህ መልካሞቹ መላእከት ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው። በኋላ እንደምናየው እርኩሳን መላእክትም በሰዎችና በዓለም ጉዳይ ጣልቃ ይገባሉ። እርግጥ እግዚእብሔር ዕቅዱን ለመፈጸም መላእክት ባላስፈለጉት ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ራሱ መርጧል፡፡ ይህ በመሆኑ ግን መላእክትን አናመልካቸውም። ይህም ማለት መላእክትንም ሆነ እግዚአብሔር እቅዱን ለማስፈጸም የሚጠቀምባቸውን ሁኔታዎችና ጓደኞቹን ማምለክ አለብን ማለት አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር የመረጣቸው መሆናቸውን ማጤንና ስለ እነርሱም እግዚአብሔርን ማመስገን አለብን። በስኮትላንድ በሚገኝ አንድ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ፥ ይህን ጉዳይ ሚዛናዊ የሚያደርግና “የእግዚአብሔር ኃይል ሊገዛን በቂ ሆኖ ሳለ፥ ደካሞች ከመሆናችን የተነሳ ግን መላእክቱን ጠባቂ አደረገልን” የሚል ጽሑፍ ተቀርፆ ይገኛል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.