የሰው ኃጢአት

የኃጢአ ትርጉም 

ኃጢአት የሚለውን ቃል ይተረጉማሉ የተባሉ ብዙ አስተሳሰቦች በየጊዜው ተሰጥተዋል፤ ትርጉሞቹም ግልጥ በሆኑ ክፍሎች ይመደባሉ። 

1. አንዳንዶች፥ ኃጢእት ቅዥት ነው፥ ኃጢአት የሚባል ነገር የለም፤ በሰው ዘንድ ድክመት ቢኖርም በቂ ጊዜ ካገኘ በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት የሚወገድ ነው ይላሉ። አንድ ሀኪም በቅርብ ጊዜ “በሥነ-አእምሮ ህክምና ኃጢአት ለሚባል አሳብ ቦታ የለንም” ብሏል። ከዓመታት በፊት ብዙ ፈላስፎች ሰው ስለ ኃጢአት የሚያስበው ከእውቀት ማነስ የተነሳ ነው በቂ እውቀት በሚያካብትበት ጊዜ ግን ኃጢአት የሚባለውን ቅዠት ከአእምሮው ይፍቃል ብለዋል። 

2. ኃጢአት ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ እና ከእግዚአብሔር ነጻ የሆነ የክፋት ዘላለማዊ መመሪያ ነው የሚሉ አሉ። ይህ ሁለት አመላካከቶችን ያቀፈ ፍልስፍና [Dualism/ዱዋሊዝም] ከጥንታዊው የሃይማኖት መሪ “ከዘርአስተር” [Zoroaster] እና ከቻይናውያኑ ከ“ያንግ” [Yang] እና “የን” [Yin] አስተሳሰብ፣ እንዲሁም ከቀድሞዎቹ ግኖስቲኮች [Gnostics ኖስቲክስ] እምነት ጋር የተያያዘ ነው። 

3. ኃጢአት ራስ ወዳድነት ነው። ይህ በብዙዎች ዘንድ የተለመደና በመጽሐፍ ቅዱስም የሚጠቀስ ይሁን እንጂ ሌሎቹን የኃጢአት ምንጮች ያጠቃለለ አይደለም። በዚህ ትርጉም መሠረት ለምሳሌ፡- ድሆችን ለመመገብ ከሀብታም የሚሰርቅ ሰው ድርጊት፥ ራሱን ከመውደድ የተነሳ ያልተፈጸመ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ድርጊቱ ኃጢአት መሆኑ አያከራክርም። የአብዛኛው የኃጢአት ምንጭ ራስ ወዳድነት መሆኑ ግን አሌ የሚባል አይደለም። 

4. በ1ኛ ዮሐንስ 3፡4 ላይ ለኃጢአት የተሰጠው ትርጉም ዓመፀኝነት (ከሕግ ውጭ መሆን) የሚል ነው። ይህ ቀላል ትርጉም ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልገዋል። ኃጢአት ምን እንደሆነ ለማሳወቅም ሕግ ምን እንደሆነ መግለጥ አለብን። የሕግን ትርጉም ለማሳወቅ ደግሞ በየትኛው የታሪክ ዘመን ላይ ሆንን እንደምንነጋገር መገንዘባችን ወሳኝ ይሆናል። ሕግ በኤደን ገነት አንድ ነገር ማለት ሲሆን፥ ሕግ በአብርሃም ዘመን፥ እንዲሁም ሕግ በሙሴ ዘመን የተለየ ትርጉም ነበረው። ዛሬ ደግሞ ሕግ፥ በአዲስ ኪዳን የተጻፉ ብዙ ትእዛዞች ናቸው። እንግዲህ ኃጢአት እነዚህን ትእዛዞች መጣስ ነው። ቁልጭ ያለ ማብራሪያ በ1ኛ ቆርንቶስ 10፡31 ላይ እናገኛለን። አማኞች የሚያደርጉትን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲያደርጉ ታዘዋል። ስለዚህ የኃጢአት አጠቃላይ ትርጉም ከእግዚአብሔር ከብር የሚያንስ ማንኛውንም ነገር መፈጸም ማለት ነው። ይህ እርግጠኛው የኃጢአት መለኪያ ስለመሆኑ በሮሜ 3፡23 ላይ ተጽፏል። 

የግል ኃጢአት 

በብሉይ ኪዳን ኃጢአትን የሚገልጡ ስምንት መሠረታዊ ቃሎች ሲኖሩ፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ፥ ቢያንስ አሥራ ሁለት አሉ። እነርሱም የሚያመለክቱት፡- 1. በግልጥ የሚታወቅና ኃጢአት የተፈጸመበት መመዘኛ ሁሌ ይኖራል፤ 2. ክፋት የተለያዩ ቅርጾች ሊኖሩት ይችላል፤ 3. የሰው ኅላፊነት ግልጥና የማያሻማ ነው፤ 4. ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ ነው። ለዚህ የሚረዱ ጥቅሶች፥ ዘፍጥ. 38፡7፤ ሕዝ. 48፡11፤ 1ኛ ነገሥ. 8፡50፤ ማቴ. 5፡21፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡9፤ ገላ. 6፡1፤ 1ኛ ጢሞ. 4፡2 ናቸው። የግል ኃጢአት ማለት ዒላማን መሳት ማለት ብቻ አይደለም፤ እግዚአብሔር ያቀደልንን ዓላማዎችና ግቦችን አለሟሟላት ማለትም ነው። 

የኃጢአታዊ ተፈጥሮ ውርስ 

ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች እንደሆንን ሐዋርያው ጳውሎስ ይገልጣል (ኤፌ. 2፡3)። ይህ ኃጢአታዊ ተፈጥሮ፣ ሰዎች ሁሉ በትውልድ የወረሱት በእግዚአብሔር ዘንድ የማያስመሰግን መልካም፥ ከፉ ወይም ገለልተኛ ነገር የማድረግ ችሎታ ነው። የሰው ባሕርይ በየአቅጣጫው እንደተበላሸ የሚነግሩን ብዙ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ አሉ። አእምሮው (2ኛ ቆሮ. 4፡4፤ ሮሜ 1፡28)፥ ሕሊናው (1ኛ ጢሞ. 4፡2)፣ ፈቃዱ (ሮሜ 1፡28)፥ ልቦናው (ኤፌ. 4፡18)፥ ሁለንተናው (ሮሜ 1፡18-3፡20) ሁሉ ተበላሽቷል። ይህ የአጠቃላይ ጎዶሎነት [Total Depravity) ቶታል ዲፕራቪቲ] ትምህርት ይባላል። አጠቃላይ ጎዶሎነት ሲባል ሁሉም ሰው በድርጊቱ ፍጹም ጎዶሎ ሆኗል፥ ወይም ሁሉም በማንኛውም ዓይነት ኃጢአት ውስጥ ይዘፈቃል፡፡ ወይም እንድ ሰው በጎ ድርጊትን አይወድም አንዲሁም አያደርግም ማለት አይደለም። ለማለት የተፈለገው፥ ኃጢአት የሰዎችን ሁለንተና እንደሚበክል፤ በዚህም የተነሳ፥ ተፈጥሯዊ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የሚያስገኝለትን ነገር እንደሚያጣ ነው። 

የኃጢአት ብክለት [Imputation/ኢምፒዩቴሽን] 

የሥነ-መለኮት ምሁራን የኃጢአትን ብክለት በተመለከተ ብዙ ተከራክረዋል። ብዙዎች የአዳም ኃጢአት ከርሱ በኋላ በተወለዱት ሁሉ ላይ ተላልፏል ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ አዳም የሰውን ልጅ ወክሉ ቢያጠፉም፥ የርሱ ኃጢአት ወደ ሌሎቹ አይተላለፍም ይላሉ። ይህ ሁሉ ከርክር፥ የሮሜ 5፡12ን ትርጉም መነሻ በማድረግ ሲሆን፤ በተለይ “ሁሉ ኃጢአትን አደረጉ” የሚሉትን ቃላት በተመለከተ ነው። የቃላቱ ትርጉም ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ናቸው ማለት ነው (ኃጢአታዊ ተፈጥሮ አላቸው ማለት ይሆናል)? ወይስ አዳም ኃጢአት በፈጸመ ጊዜ በአንዳች ሁኔታ የሰው ዘሮች ሁሉ ኃጢአት ሠሩ ማለት? ሁለተኛው አስተሳሰብ እውነት ከሆነ፥ የኃጢአትን ብክለት ያመለክታል። 

ብዙዎች ይህን አሳብ ልክ አይደለም፥ ምክንያቱም አንድ ሰው ገና ሳይወለድ ለተሠራው ኃጢአት እንዴት ጥፋተኛ ይሆናል? ይላሉ። መደምደሚያው ትክክል ቢሆንም ባይሆንም፥ ይህ አሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ ውጭ ያለ መሆኑ ግልጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ 1ኛ ሳሙ. 22፡15፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡21፤ ዕብ. 1፡9-10ን እንደ ምሳሌ ይመልከቱ።) ለምሳሌ፡- የሌባ ወይም የነፍሰ ገዳይ ልጆች ምንም እንኳን ወላጃችው ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ ሕጻናት ቢሆኑና ስለ ወንጀሉም ምንም የማያውቁ ቢሆኑም እድሜ ልካቸውን በእፍረትና በስቃይ እንደሚኖሩ ይታወቃል። 

(በሌላ በኩል አንዳንድ ሰዎች ሌሎች በሠሩት ሥራ ሲጠቀሙና የማይገባቸውን ነገር ሲያገኙ ይታያል። ለምሳሌ ያህል ገና ያልተወለዱ ልጆች እንኳን ስለ ውርስ ጉዳይ በፍርድ ቤት በሚሰጡ ውሳኔዎች ምክንያት ብዙ ጊዜ ጥቅም ያገኛሉ።) 

በኃጢአት የመበከል አሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠ ከሆነ (ይመስላልም)፥ ከዚህ ጋር ሰው በግሉ የሚሠራው ኃጢአት፥ የተፈጥሮ ደካማነቱ፣ እነዚህ ሦስቱ አንድ ላይ ተዳምረው ነው እግዚአብሔር በሰዎች ኃጢአት ላይ እንዲፈርድ ምክንያት የሚሆኑት። 

ኃጢአትና ክርስቲያን 

የኃጢአት እርግጠኛነት። ክርስቲያን መሆን አንድን ሰው ኃጢአት ከመሥራት ነጻ አያደርገውም። እርግጥ በምድራዊ ሕይወቱም ቢሆን ክርስቲያን ከኃጢአት ባሕርያት የነጻ ሊሆን ይችላል ብለው የሚያስተምሩ አሉ። የአዲስ ኪዳን ትምህርት ግን ከዚህ የተለየ ነው። ለማስረጃም ያህል ዮሐንስ በርሱ ዘመን የነበሩ ሰዎች በሐሰት የሚናገሯቸው ሦስት ነገሮች እንዳሉ በ1ኛ  ዮሐንስ 1፡8-10 አረጋግጧል። እነዚህም ቁጥር 8 የኃጢአት መመሪያ መኖርን መካድ፣ ቁጥር 9 የተወሰነ ኃጢአትን መካድ፥ ቁጥር 10 በግል ኃጢአት ማድረግን መካድ ናቸው። 

የአማኝ ግዴታዎች። የአማኝ ግዴታው “በብርሃን መመላለስ” ነው (1ኛ ዮሐ. 1፡7)። ኅብረትም የሚኘው ይህ ብርሃን መልካምንና ክፉውን እንዲገልጥ በመማለድና ለዚህ ብርሃን ሳያቋርጡ ታዛዥ በመሆን ነው። ክርስቲያን በዚህ ምድራዊ አካል እስካለ ድረስ፥ ብርሃን መሆን አይችልም፤ ነገር ግን በብርሃን ለመመላለስ መቻል ይኖርበታል። ይህን ሲያደርግ ሁለት ነገሮች ይከናወናሉ። በመጀመሪያ ከሌሎች አማኞች ጋር ኅብረት ይኖረዋል፥ ሁለተኛ ይነጻል። ይህ መንጻት በብርሃን የመመላለሱ ውበት እንጂ፥ ኃጢአትን የመናዘዝ ውጤት ሊሆን አይችልም። በሌላ አነጋገር በብርሃን መመላለሳችን ድካምና ኃጢአታችንን ስለሚያሳየን የማያቋርጥ መንጻት እንፈልጋለን። ይህ የሚገኘው ደግሞ በክርስቶስ ሞት በኩል ነው። በብርሃን መመላለስ የሚያሰናክሉንን የሕይወት ጨለማ ጎኖች በመገንዘብ ወዲያው ንስሐ እንድንገባ ያደርገናል። በዚህ ብርሃን በበለጠ መመላለሳችንም በርቀት ያለውን ጨለማ በማስወገድ፥ ከበፊቱ የበለጠ ብርሃን ያስገኝልናል። ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ይህን ጎዳና ልንክተል ይገባል። ይህ ማንኛውም አማኝ በመንፈሳዊ ጉዞው ወቅት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። 

የኃጢአት መከላከያ፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን በበሽታ ከመለከፍ፣ መከላከያ ክትባት መውሰድ ይመረጣል። እግዚአብሔርም ለአማኞች ኃጢአት መከላከያ አዘጋጅቷል። እንደኛው የእግዚአብሔር ቃል ነው (መዝ. 119፡11)። ሌላው የክርስቶስ የማያቋርጥ ምልጃ ነው (ዮሐ. 17፡15)። ሦስተኛው የመንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኑ ሕይወት የሚያከናውነው አገልግሎት ነው (ዮሐ. 1፡37-39)። 

የኃጢአት ቅጣት። 1. ማንኛውም ኃጢአት በአማኙና በሰማያዊው አባቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ይቀንሳል (1ኛ ዮሐ. 1፡6)፤ 2. አንዳንድ ኃጢአቶች፥ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት አጥፊውን ወንድም እስከማግለል እርምጃ እንዲወሰዱ የሚያደርጉ ይሆኑ ይሆናል። ያን የሚያደርጉት ግን ያ ወንድም ወደ ጌታ የሚመለስበትን ተስፋ በማሰብ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 5፡4-5)፡፡ 3. ለማያቋርጥ ኃጢአት የሚወሰኑና የተለያዩ ቅጣቶችም ይኖራሉ (ዕብ. 12፡6)፡፡ 4. በአንዳንድ አጋጣሚዎች፥ ከኃጢአት ያልተላቀቀን አማኝ በኃጢአት ልምዱ መክፋት የተነሳ ጌታ ወደ ሰማይ ይወስደው ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 11፡30)። 

የኃጢአት መፍትሔ። በማንኛውም ጊዜ ኃጢአትን ማድረጋችን ሲታወቀን በፈቃዳችን ለመናዘዝ የተዘጋጀን መሆን አለብን። በግሪክ “መናዝ” የሚለው ቃል አንድን ቃል መልሶ መናገርን ያመለክታል። መስማትን፥ በሙሉ ልብ መቀበልን ያሳያል (1ኛ ዮሐ. 1፡9)። አማኝ ኃጢአቱን ሲናዘዝ፣ እግዚአብሐር ስለዚያ ኃጢእት በተናገረው ቃል መስማማቱ ነው፤ ያለፈ ስሕተቱንና ጥፋቱን ይገነዘባል። መናዘዝ ፈጣን ይቅርታ ለማግኘት የሚደረግ ማነብነብ አይደልም። ንስሐ መግባት መናዘዝንና ኃጢአት ለመተው መሻትን ያጠቃልላል (ሐዋ. 19፡18)። ይሁን እንጂ ማነው በተናዘዘበት ኃጢአት ደግሞ ደጋግሞ ያልወደቀ? ይህ ሁኔታ ቢከሰት በኑዛዜው ላይ የጎደለ ነገር መኖሩን አያመለክትም፤ ምናልባት ከንስሐ የተወሰዱት እርምጃዎች በመንፈስ ቅዱስ በመደገፍ ለድል የሚያበቁ አይደሉ ይሆናል። 

በኃጢአት ምክንያት የተቋረጠው የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባልነት፥ በንስሐ ጊዜ ተመልሶ ይመሠረታል። ኃጢአት አንድን ሰው ከቤተሰብ አባልነቱ እያሰርዘውም፤ ነገር ግን የቤተሰቡን ሙሉ ደስታ ተካፋይ እንዳይሆን ያግደዋል። መናዘዝ ግንኙነቱን ያድሰዋል። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ያለው ዘላለማዊ ኅብረት ጨርሶ ሊበላሽ አይችልም። ነገር ግን በኃጢአት ምክንያት ሊቋረጥ ይችላል። ያንድ ሰው ኃጢአት ሌሎቹን የቤተሰብ አባላትም ሊጎዳ ሰለሚችል፥ ግንኙነቶቹን ለማስተካከል ተገቢው እርምጃ ሊወሰድ ይገባዋል። ኃጢአት እጅግ ከባድ ነገር ነው፤ እግዚአብሔርን ያሳዝናል፥ ሴሎችንና እኛንም ይጎዳል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

One thought on “የሰው ኃጢአት

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.