ምርጫ ምንን ያካትታል?

የድነት (የደኅንነት) ትምህርት ቀላልም ውስብስብም ነው። ብዙ ሰዎች በአንድ በኩል ቢያንስ ዮሐ. 3፡16ን ወይም ጳውሎስ የፊልጵስዩስ እሥረኞች ጠባቂ ስለመዳን ላቀረበለት ጥያቄ የሰጠውን መልስ ሊጠቅሱ ይችላሉ (ሐዋ. 16፡31)። በሌላ በኩል ግን ሰው የሆነው ቅዱስ አምላከ እንደ ኃጢአተኛ እንደተቆጠረና እንደሞተ ማን ሊያብራራ ይችላል? እጅግ ጥልቅ የሆነውን የምርጫ ጉዳይ ማን ይመረምራል? (ይህ የድነት ትምህርት አንዱ ክፍል ነው) ድነት በትክክል ልንረዳው የሚገባ፥ እጅግ ወሳኝ የእምነት ትምህርት ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ፍጡር (መላእክትም ሆኑ ወይም ሰባኪ) ከእውነተኛው ወንጌል የተለየ ትምህርት ቢሰብክ መርገም በራሱ ይሸከማል። ስለዚህ የድነትን (ደኅንነትን) ወንጌል በትክክል መረዳትና ያለማዛነፍ ለመግለጥ መቻል በጣም አስፈላጊ ነው። የዚህን ጠቀሜታ ይበልጥ የምንረዳው፣ አንዳንድ በራሪ ጽሑፎችን በምናነብበት ጊዜ፥ ወይም በራድዮ የሚተላለፉትን መንፈሳዊ መልእክተች በምንሰማበት ወቅት ግልጥ ያልሆነና ግራ የሚያጋባ የወንጌል ትምህርት ደጋግሞ ሲያጋጥመን ነው። 

የድነት ትምህርት ከዚህ በፊት ካጠናነው የክርስቶስ ትምህርት ተለይቶ የማይታይና በእጅጉ የተያያዘ ነው። የግንኙነቱ ምክንያትም ግልጥ ነው! የድነት ታላቅነት በአዳኙ ታላቅነት ላይ ይመሠረታልና። እርሱ እንደ ሰዎች ኃጢአተኛ ቢሆን ኖሮ፥ ሞቱ ከራሱ ኃጢአት በስተቀር የማንንም ዕዳ ሊከፍል ባልቻለም ነበር። በብሉይ ኪዳን የፋሲካ በግ ከመታረዱ በፊት ያለ ነውር መሆን እንዳለበት ሁሉ፥ የጌታችን ሕይወትም ፍጹምና ለኃጢአታችን ምሥዋዕትነት ብቁ መሆኑ ተረጋገጠ (ዘዳግ. 12:5-6)። ይህን ጉዳይ ምዕራፍ 4 ላይ በሚገባ የተመለከትነው ስለሆነ እዚህ አንደግመውም። ቀጥለን የምንመለከተው የመዋጀትን ሥራና ገጽታዎቹን ይሆናል። 

የምርጫን ትምህርት መረዳቱ ለማንም ቢሆን አስቸጋሪ መሆኑ አያከራክርም። ቢሆንም ትምህርቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ከድነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ወደ ጐን ብለን የምናልፈው ጉዳይ አይሆንም። 

ፅንሰ አሳቡ 

ምርጫ ለድነት በዋናነት የሚታይ ባይሆንም በዙሪያችን ያለ ጉዳይ ነው። የተወለድነው ከተለያየ ቤተሰብ እንደመሆኑ የአእምሮ ችሎታችንም እኩል አይደለም፤ በዘር እንለያያለን፥ የተለያዩ የሕይወት ገጠመኞች ይኖሩናል ወዘተ። እነዚህ ሁሉ የአጋጣሚ ጉዳዮች ናቸው ብለን እንደ ዋዛ እንለፋቸው እንጂ፥ የመታደል ወይም የፍርጃ፥ አለበለዚያም የአካባቢ ተጽዕኖ ጣልቃ ገብነት እንዳለባቸው አድርገን የምንወስዳቸው ናቸው። 

የመጽሐፍ ቅዱስ የምርጫ ትምህርት ይህንኑ ያለመመሳሰል መመሪያ ይይዛል። ይህን ጉዳይ እግዚአብሔር የተለያዩ ሰዎችን ለተለያየ ዓላማ መምረጡን ያመለክታል ብሎ መተርጎም ይቻላል። ትርጉሙ ሰፋ ያለበት ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ሰዎች፥ ወይም ቡድኖች፥ መመረጣቸውን ለማካተት ነው። ለምሳሌ፡- 1. እስራኤል በመንግሥትነት ተመርጣ ነበር (ዘዳግ. 4፡37፤ 1ኛ ዜና 16፡13)። ይህ ዳግም የተወለዱትንና ያልተመለዱትን የሚያጠቃልል ነበር፤ 2. ንጉሥ ቂሮስ ምንም እንኳን እኛ እስከምናውቀው ያልዳነ ቢሆንም፥ በእግዚአብሐር የተመረጠ ተብሎ ተጠርቷል (ኢሳ. 45፡1-4)፤ 3. ክርስቶስ በእግዚአብሔር የተመረጠ ተብሏል (ኢሳ. 42፡1)፤ 4. በፍዳ ዘመን ከቤተ ክርስቲያን የተለዩና የተመረጡ ሕዝቦች ይኖራሉ (ማቴ. 24፡ 22፥ 24፥31)፤ 3. በኢየሱስ ያመኑትን እግዚአብሔር ዛሬ በመምረጥ ላይ ነው (ቈላ. 3፡ 12፤ ቲቶ 1፡1)። በዚህ በመጨረሻው ነጥብ መሠረት ምርጫ የክርስቶስ አካል ለመሆን የሚድኑትን ለመምረጥ እግዚአብሔር የሚፈጽመው ተግባር ነው። 

የምርጫ ፅንሰ አሳብ በእግዚአብሔር ባሕርይ (አሠራር) ላይ የተመሠረተ ነው። በሌላ አባባል ምርጫ ከሌሎች አሠራሮቹ ጋር የተስማ የእግዚአብሔር ተግባር ነው። ይህም ማለት፡- 

1. ምርጫ ፍቅር ነው፥ ስለሆነም ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር ከፍቅር ውጭ አንዳች ነገር አያደርግም (ኤፌ. 1፡4)። 

2. የእግዚአብሔር ምርጫ በጥበብ ነው፥ ምክንያቱም እርሱ ጥበብ ነውና (ይሁዳ 25)። 

3. የእግዚአብሔር የምርጫ ዓላማ ዓለም ሳይፈጠር በፊት የተወሰነ ነው (ኤፌ. 1፡ 4)፤ ወደፊትም ለዘላለም ይቀጥላል (ሮሜ 8፡30)። 

4. የምርጫ ክንዋኔ፥ እግዚእብሔር የፈጠረውንና እርሱም የሚያከብረውን የተፈጥሮ ሕግ የሚጥል አይሆንም። ስለሆነም ምርጦቹ የሚድኑት፥ ድንገት መልአክ ከሰማይ ወርዶና ወንጌል ሰብኮላቸው ሳይሆን፥ እንደ ማንኛውም ሁኔታ ከሰዎች ምስክርነት በመስማትና በማመን ነው (ሮሜ 10፡ 14)። የመዝራትና የማጨድ ተፈጥሯዊ ሕጎችም ተግባራዊ ይሆናሉ። ስለዚህም ባለማመኑ የሚጸና ሰው ያለማመኑ ውጤት ለሆነው የእሳት ባሕር ይዳረጋል። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ ኅላፊነቱን በተግባር የመተርጎም ብቃቱ በአጠቃላዩ የምርጫ ዕቅድ ውስጥ ድርሻ አለው። 

5. ምርጫ በመጨረሻ ውጤቱ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ያከብራል (ኤፌ. 1፡12-14)። በአንዳንድ ሁኔታዎች የተነሳ ይህን ሀቅ ለመመስከር ያስቸግረን ይሆናል። ከእግዚአብሔር አጠቃላይ ዕቅዶች የምናየው በጣም ትንሹን ክፍል ብቻ በመሆኑ እርሱ በሚያደርገው ነገር ላይ ፍርድ ለመስጠት በምንም አኳኋን የማንችል መሆናችንን ማስታወስ አለብን። 

መጽሐፍ ቅዱሳዊው መሠረት 

በአዲስ ኪዳን ስለ ምርጫ የሚናገሩት ክፍሎች ኤፈ. 1፡3-14 ፤ ሮሜ 9፡6-24፥ 8፡28-30፤ ዮሐ. 6፡44፤ ሐዋ. 13፡48፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡8 እና ራእይ 17፡8 ናቸው። እነዚህ ክፍሎች የኛን መብት ከእግዚአብሔር የመምረጥ መብት ጋር በማመላከት ለሚነሳው ጥያቄ መልስ የሚሰጡ ሲሆን፥ እግዚአብሔር የሚያድናቸውን ሰዎች መርጦ ሌሎችን እንደሚተው ያመለክታሉ። በእነዚህ ምንባቦች የተጠቀሱትን ብዙ ቁም ነገሮች መረዳቱ ቀላል አይደለም። ነገር ግን ማመን ብንጀምር (ሙሉ በሙሉ ባይገቡንም ምርጫን ከእግዚአብሔር አንጻር መመልከት እንጀምራለን። 

አሠራሩ 

በግልጥ እንደሚታየው የተመረጠ ሕዝብ አለ። በኤፈሶን 1፡4-5 እንደተገለጠው ይህ ሕዝብ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በፍቅር የተመረጠ ነው። እንደ 2ኛ ዮሐንስ 1፡13፤ ሮሜ 6፡131 እና ገላ. 1፡ 15-16 ያሉ ጥቅሶች ይህ ሕዝብ የተመረጡ ግለሰቦች ስብስብ መሆኑን ሲያሳይ፥ ዮሐ. 13፡18፤ ሮሜ 9፡22፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡8 ደግሞ፣ የተወሰኑ ወገኖች ወይም ሰዎች ከዚህ ሕዝብ ጋር እንዳልተደመሩ ያሳያሉ። እግዚአብሔር ምርጫውን ለምን በዚህ አኳኋን አደረገው ለሚለው ጥያቄ መልስ የለንም። ከባሕሪው የሚቃረን ነገር እንደማያደርግ ግን እርግጠኞች ነን። ምርጫ ማን እንደሚያምን አስቀድሞ ከማወቅ የላቀ ነው፤ ምርጫ  ማን እንደሚያምን የመምረጥ ተግባር ነው። 

የመምረጥን ሂደት ፍሬያማ የሚያደርግ የአሠራር መንገድ አለ። ከነዚህም የአሠራር መንገዶች ውስጥ፥ አዳኝ የሆነውን ክርስቶስን እንዲሞት መላክ፥ ሥጋ ለብሶ ከመጣ በኋላም ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት፥ ዛሬ ደግሞ ወንጌልን በመላው ዓለም እንዲሰበክ ማድረግና ሰዎችም ይድኑ ዘንድ እምነት አስፈላጊ መሆኑ ይገኙበታል። ምርጫ የሰውን የኅላፊነት ግዴታዎች አይደመሰስም። ሰዎች እንዲያምኑ ታዘዋል (ሐዋ. 16፡31፤ 17፡30)፥ ማንም ሳያምን አይድንም (ኤፈ. 2፡8-9)። በሌላ አገላለጥ እንዲህ ማለትም እንችላለን፡- ዛሬ በሕይወት ከሚኖሩት ውስጥ ያልዳኑ፥ ግን የተመረጡ ሰዎች አሉ። እነዚህ ቢመረጡም እንኳን እስካላመኑ ድረስ አይድኑም፥ የጠፉ ናቸው። ይህ አሳብ ራሱን በራሱ የሚቃረን ቢመስልም እውነት ነው። ይህን አለማስተዋል የዚህን ትምህርተ ሃይማኖት ሁሉ አሳብ አለመረዳት ይሆናል። 

የምርጫው ውጤት አለ፤ እሱም መልካም የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው (ኤፌ. 2፡10)። እንደ “እግዚአብሔር ምርጦች” ለመታወቅ እኛም “ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን” መልበስ አለብን (ቆላ. 3፡12)። የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነትና ሉዓላዊነት መረዳት ወደ ኃጢአት የሚመራ ሳይሆን በአስደናቂ አኳኋን ትሁት የሚያደርግና ወደሚቀድስ ምስጋና የሚወስድ ነው (ሮሜ 11፡33-36)።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.