የክርስቶስ ሞት

ውጤቶቹ 

ለኃጢአት ምትክ ነበር። የክርስቶስ ሞት ትርጉም ብዙ ገጽታዎች ቢኖሩትም፥ ዋናውና ያለ እርሱ ሌሎቹ ትርጉም የለሽ የሚሆንበት ፅንሰ አሳብ ግን ለኃጢአት ምትክ መሆኑ ነው። ይህም በቀላሉ ክርስቶስ በኃጢአተኛች ፋንታ መሞቱን ያመለክታል። “አንታይ” የሚለውን ግሪክኛ መስተዋድድ “ምትክ” (“ፋንታ”) የሚለው ቃል ይወከለዋል። ይህ ቃል፥ ለምሳሌ ከክርስቶስ ሞት ጋር ባልተያያዘ ክፍል ጥቅም ላይ ውሏል (ሉቃስ 11፡11)። ጌታችን ስለ ራሱ ሞት ትርጉም በገለጠባቸው ክፍሎች ግን ይበልጥ ጉልህ ሆኖ ይታያል (ማቴ. 20፡28፤ ማር. 18፡45)። ሞቱ ለብዙዎች ቤዛነት እንደሆነ ተናግሯል። 

“ሁፐር [huper] የሚል ሌላ መስተዋድድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ ውሏል። ቃሉ ሁለት ትርጉሞች አሉት። አንዳንዴ “ለሌሎች ጥቅም ሲል” የሚል ትርጉም ሲኖረው፥ አንዳንዴ ግን “ምትክ” የሚል ትርጉም አለው። ክርስቶስ የሞተው በእኛ ፋንታና ለእኛ ጥቅም ሲል ስለሆነ፥ “ሁፖር” የሚለው ቃል እነዚህን የከርስቶስን ሞት የሚገልጡ ሁለት አሳቦች የማይዝበት ምክንያት አይኖርም። ለምሳሌ 2ኛ ቆሮ. 5፡21 እና 1ኛ ጴጥ. 3፡18ን ይመልከቱ። “ምትክ” ለሚለው ቃል ትርጉም ጥሩ ምሳሌ የሚሆን በፊሊሞና 13 ውስጥ ይገኛል። 

አሳቡ ግልጥ ነው። ጳውሎስ ሮም ሁኖ በፊት ከጌታው የሸሸውንና ኋላም አዲስ አማኝ የሆነውን ባሪያ፥ አናሲሞስን በቈላስይል ወደሚኖረው ጌታው ወደ ፊሊሞና ሲመልሰው ያሳያል። “አሁን” ይላል ጳውሎስ ለፊሊሞና “አናሲሞስን በሮም ከእኔ ጋር በወንጌል እሥራት ያገለግለኝ ዘንድ ባንተ ምትክ (ሁፐር) ባስቀረው እወድ ነበር።” የዚህ ቃል ትርጉም ስለ ፊሊሞና ጥቅም ሲባል ማለት አይሆንም፥ ምከንያቱም ፊሊሞና ሳይሆን ጳውሎስ ነበር በአናሲሞስ ሮም መቆየትና በፊልሞና ፋንታ ቢያገለግለው የሚጠቀመው። ቃሉ ከአዲስ ኪዳን ውጭም የምትክነትን አሳብ መያዙ ሌላው ምሳሌ ነው። 

የክርስቶስ ሞት ከኃጢአት መዋጀትን አስገኝቷል። የመዋጀት ትምህርት በሦስት የአዲስ ኪዳን ቃላት ላይ የተመሠረተ ነው። የመጀመሪያው ቀላል ትርጉም “መግዛት ወይም የአንድን ነገር ዋጋ መክፈል ነው”። ይህ በየቀኑ ጥቅም ላይ የሚውል ቃል ነው። መሬት ውስጥ ስለተሸሽገው መዝገብ (ሀብት) በተነገረው ምሳሌ ሰውየው መሬቱን እንዲገዛ (እንዲዋጅ የገፋፋውን ምክንያት በማጤን ስለ ቃሉ ይበልጥ ለመረዳት ይቻላል (ማቴ. 13፡44)። ከድነታችን (ከደኅንነታችን) ጋር በተያያዘ ሁኔታ ደግሞ ቃሉ የሚያመለክተው ስለ ኃጢአታችን የሚጠየቀው ዋጋ ተከፍሎ መቤዠታችንን ነው። የመዋጀት ክልል ያልዳኑትን የሐሰት አስተማሪዎች እንኳን እንደሚጨምር በ2ኛ ጴጥሮስ 2፡1 ላይ ተገልጿል። ለዚህም የሚያበቃቸው የክርስቶስ ቤዛነት ነው። በራእይ 5:9 ላይ መዋጃው የክርስቶስ ደም መሆኑን፥ የመዋጀት ውጤቱ ደግሞ በሥጋችን እግዚአብሔርን ማክበር መሆኑን በ1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19-20 የተጠቀሰውን ያንብቡ። 

ሁለተኛውም ቃል የሚገልጠው ከላይ የተጠቀሰውን መሠረታዊ ቃል ሆኖ፥ ትርጉሙን በጣም ለማጠናከር መስተዋድድ ተጨምሮበታል። ይህ በቀላሉ ወደ አማርኛ ሲመለስ የመስተዋድዱ ትርጉም “ከ…ውስጥ” የሚል ይሆናል። ሁለተኛው ትርጉም “ከገበያ ውስጥ መግዛት” ማለት ነው። ይህ አሳብ የከርስቶስ ሞት የኃጢአትን ዋጋ መክፈሉን ብቻ ሳይሆን፥ ወደ ኃጢአት እሥራትና ቅጣት ላለመመለስ ሙሉ እርግጠኞች እንሆን ዘንድ ከኃጢአት ገበያ ያወጣን መሆኑንም ያመለክታል። የክርስቶስ ሞት ዓላማ፡- “እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግም በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ” (ገላ. 4፡5) ነበር። በዚህ ጥቅስ የተገለጠው ድርብ ትርጉም የሚያስረዳው የልጅነት ጸጋችንን እንደማናጣ፥ ወደ ባርነትም እንደማንመለስ ዋስትና የተሰጠን መሆኑን ነው። 

ስለ መዋጀት የተጠቀሰው ሦስተኛው ቃል በጣም የተለየ ነው። መሠረታዊ ትርጉሙ መፍታት ማለት ሲሆን፥ ይህም የተገዛ ሰው ወይም ባሪያ ነጻ መሆኑን ወይም ሙሉ ነጻነት ማግኘቱን ያመለክታል። ይህ ነጻነት በክርስቶስ ምትክነት የተገኘ ነው (1ኛ ጢሞ. 2፡6)፤ መሠረቱ የክርስቶስ ደም ሲሆን (ዕብ. 9፡12)፥ የመጨረሻ ውጤቱም መልካም ሥራ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያለውን ሕዝብ ማንጻት ነው (ቲቶ 2፡14)። ስለዚህ የመዋጀት ትምህርት ማለት፥ አንድ አማኝ በክርስቶስ ደም ተገዝቷል፥ ከእሥራት ተላቋል፥ ነጻ ሆኗል የሚለውን የምስራች የሚያበስር ፅንሰ አሳብ ማለት ነው። 

የከርስቶስ ደም ያስታርቃል። ማስታረቅ ማለት መለወጥ ማለት ነው። በክርስቶስ ሞት እርቅ ማግኘት ማለት ከእግዚአብሔር ተለይቶ የነበረው ሰው ድነትን (ደኅንነት) ያገኝ ዘንድ ተለወጠ ማለት ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡19)። አንድ ሰው ሲያምን ከእግዚአብሔር ተለይቶ ከመኖር ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ አባልነት ይለወጣል (2ኛ ቆሮ. 5፡19)። እግዚአብሔር በደልን ሽሮ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ፍቅሩን ለመስጠት የሚችል በመሆኑ የማስታረቁ ሥራ ዓላምን ሁሉ ይመለከታል እንላለን። እኛ አማኞችም ይህን ስጦታ በግል ስንቀበል እንድናለን (ሮሜ 5፡1)። የእርቅ መሠረቱ የክርስቶስ ሞት ነው (ሮሜ 5፡10)። በዚህ እርቅ የሚለወጠው ሰው እንጂ እግዚአብሔር እንዳልሆነ ማስተዋል ጠቃሚ ይሆናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚለውጥ ከሆነ ባሕሪው ወይም ቅድስናው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። መለወጥ የሚያስፈልገው ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም። በእርቅ ጊዜ የሚከናወነውም ይህ ነው። 

ማስተስሪያን ይሰጣል [Popitiation/ፕሮፒቪኤሽን]፡፡ ማስተስረይ ማለት አምላከን ማርካት ወይም ቁጣውን ማብረድ ማለት ነው። ይህ አባባል ለምንድነው የአምላክን ቁጣ ማብረድ የሚያስፈልገው? የሚል ጥያቄ በእእምሮአችን ይፈጥራል። ለዚህ ጥያቄ የመጽሐፍ ቅዱስ መልስ እውነተኛው አምላክ በሰው ልጅ ኃጢአት ምክንያት ተቆጥቶ ስለነበር ነው ይላል። የክርስቶስን ትምህርት ጨምሮ የእግዚአብሔርን ቁጣ በተመለከተ የተጻፉ ብዙ ከፍሎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ (ማር. 3፡29፤ 14፡21)። ቁጣው የምከንያትና ውጤት ቀላል አሠራር ሳይሆን፥ በሰው ጉዳይ የእግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት ያሳያል (ሮማ 1፡18፤ ኤፌ. 5፡6)። 

የክርስቶስ ሞት እግዚአብሔርን አርክቶታል፤ ቁጣውን በመመለስም በአረካው ልጁ የሚያምኑትን ሁሉ እንደ ቤተሰቡ ሊቀበላቸው ፈቅዷል። የክርስቶስ እግዚአብሔርን የማርካት ተግባር ስለ ዓለም ሁሉ የሚሆን ነው (1ኛ ዮሐ. 2፡2)፣ የፈሰሰ ደሙ ነው የዚህ ሁሉ መሠረት (ሮሜ 3፡25)። 

በከርስቶስ ሞት እግዚአብሔር ረክቷል። ይህን በተመለከተ ከሰው የምንጠይቀው ነገር ሊኖር አይገባም። የረካን ለማርካት መሞከር የማያስፈልግ ድካም ይሆናል። ይህ ቢሆንማ ሰው ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት እግዚአብሔር መርካት አለመርካቱን ለማወቅ እርግጠኛ መሆን ባልቻለም ነበር። ለዚህ ነው ቀራጩ ሰውዩ ቃል በቃል ሲጸልይ “እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ” (ሉቃስ 18፡13)፣ ወይም በግሪክ ቋንቋ እንደሚለው “በእኔ እርካ” ያለው። ዛሬ ይህ ዓይነቱ ጸሎት አስፈላጊ አይደለም። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት ረክቷል። ስለዚህ ለሰዎች የምናስተላልፈው መልእክት፥ እግዚአብሔርን ምንም በማድረግ ሊያስደስቱት እንደማይችሉ፥ ነገር ግን የእርሱን ቁጣ የመለሰው የክርስቶስ መሥዋዕትነት በቂ መሆኑን እንዲያምኑ ነው። 

የክርስቶስ ሞት በኃጢአት ባሕርይ ላይ ፈርዷል (ሮሜ 6፡1-10)። የክርስቶስ ሞት የኃጢአት ባሕርይ ኃይል በሥጋችን እንዳይነግሥ በማድረግ ረገድ ታላቅ ጥቅም አለው። ይህ ለመረዳት የሚከብድ አሳብ ቢሆንም፥ ጳውሎስ እንዳለው፥ ከክርስቶስ ጋር በጥምቀት አንድ የሆነው ሞቱን በመካፈል ለኃጢአት መምታችንን ለማሳየት ነው። ጥምቀቱ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መሆን አለበት። ምክንያቱም ምንም ዓይነት የውኃ ብዛት በዚህ ክፍል የተጠቀሰውን ሥራ ሊያከናውነው አይችልም፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለጠው፥ የሥጋ ሞት ለሚያምነውም ሆነ ለማያምነው መጥፋትን ወይም አለመኖርን ሳይሆን የመንፈስን ከሥጋ መለየት ነው የሚያመለክተው። መንፈሳዊ ሞትም ከእግዚአብሔር መለየትን እንጂ፥ እንቅስቃሴ ማቆምን ወይም ሥጋዊ ሞትን አይገልጥም። ያልዳኑ ሰዎች በሥጋ ሕያው ቢሆኑም በመንፈስ ከእግዚአብሔር የተለዩ ናቸው። ዘላለማዊ ሞት እንኳን መጥፋት ማለት እይደለም፤ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ለዘላለም በእሳት ባሕር መኖር ማለት ነው። 

ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሏል ማለት በሕይወቱ ነግሦ ከነበረው ኃጢአት ተለይቷል ማለት ነው። በቁጥር 1 ላይ “በኃጢአት እንኑርን?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ ከክርስቶስ ጋር ሞተናልና አይሆንም ነው። ይህ ከክርስቶስ ጋር መሞት የኃጢአት አገልጋይ የሆነውን ሥጋ “እጥፍቶታል”። “ማጥፋት” የሚለው ቃል ግን ፍጹም ማጥፋት ማለት አይደለም። ይህ ቢሆን ኖሮ የኃጢአት ባሕሪያችን ሙሉ በሙሉ በተወገደ ነበር። ይህ እንደማይቻል ከሰዎች ጋር የምናደርገው የዕለት ከዕለት ግንኙነት ያረጋግጥልናል፡፡ ማጥፋት ማለት የኃጢአት ባሕርይ ውጤታማ እንዳይሆን ማድረግ ነው። እኛ ግን ከክርስቶስ ጋር ተሰቅለናል ስንል ከክርስቶስ ጋር በአዲስ ሕይወት ተነስተናል ማለታችን ነው (ሮሜ 6፡4)። ይህ የሚያሳየው ከአሮጌው ሥጋ መለየታችንን ብቻ ሳይሆን፥ ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋር አዲስ ኅብረት እንዳለን ነው። ከቁጥር 4 እስከ 10 ባሉት ክፍሎች የተብራራውም ይህ ነው። ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን የሚለው ቃል የሚያብራራልን የአርጌውን ኃይል ከእኛ መወገድ ብቻ ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆናችንንና በዚህም አዲስ ኃይል የምንኖር መሆናችንን ነው። 

ይህ የሆነው ወይም የሚሆነው መቼ ነው? በታሪክ እንዳየነው ክንዋኔው የተፈጸመው ክርስቶስ በሞተና በተነሣ ጊዜ ነው። እኛን በተመለከተ ግን፥ ይህ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን ክርስቶስን አዳኝ አድርገን በመቀበል በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አንድ እስካልሆን ድረስ እውን አይሆንም። በሌላ አባባል የክርስቶዕ ሞትና ትንሣኤ ታሪካዊ ክንዋኔ ሥራ የእኛም የግል ታሪክ የሚሆነው ባመንን ጊዜ ነው። 

እርግጥ እነዚህ እውነቶች በየቀኑ የሕይወት ልምዳችን ውስጥ በተግባር ይኖሩ፥ ወይም አይኖሩ ይሆናል። ከክርስቶስ ጋር መሰቀላችንና የኃጢአት ባሕርይ ኃይል ከኛ መወገዱ እርግጥ ቢሆንም፥ ድርጊቱ በኛ ክንውን ብቻ ላይ የሚመሠረት አይደለም። ለውጤቱ በክርስቶስ መታመንና ራሳችንን ለእርሱ ቁጥጥር መስጠት ይኖርብናል። የኃጢአት ባሕርይ ለክርስቲያን በክርስቶስ ሞት ከሥልጣኑ እንደተሻረ ጨቋኝ ገዥ ነው። አማኝ ምንም እንኳን የኃጢአት ድምጽ የሚሰማና አንዳንዴም የሚከተል ቢሆንም፥ አሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት ለመምራት ነጻ ይሆናል፡፡ በምንም እኳኋን ከመለወጡ በፊት እንደነበረው፥ ኃጢአት በሕይወቱ ሊነግሥ አይችልም። 

የክርስቶስ ምት የሙሴን ሕግ ፈጽሟል። ሞቱ የሙሴን ሕግ ፍጻሜ ያደረሰ መሆኑ በአዲስ ኪዳን የተገለጠ እውነት ነው (ሮሜ 10፡4፤ ቁላ. 2፡14)። የዚህም እውነት ጥቅም 1. ከጽድቅ 2. ከቅድስና ጋር የተዛመደ ሲሆን፥ ከሁለተኛው ፅንሰ አሳብ ይልቅ የመጀመሪያውን ማየት ይቀላል። ምክንያቱም ሕግ ኃጢአተኛን አለማጽደቁ በቀላሉ ይታያል (ሐዋ. 13፡39፤ ሮሜ 3፡20)። ስለዚህ ሰዎች ለመጽደቅ የሚፈልጉ ከሆነ ሌላ የመጽደቂያ መንገድ መዘጋጀት አለበት። ሕግ ለሰው ችግሩን ያሳየዋል እንጂ መፍትሔ አይሰጠውም (ገላ. 3፡23-25)። ስለዚህ የክርስቶስ ሞት፥ ጽድቅ የሚገኝበትን የእምነት ብቸኛ መንገድ ከፈተ። 

ይሁን እንጂ የሕግ ፍጻሜ ከቅድስና ጋር ያለውን ግንኙነት መረዳቱ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ከሙሴ ሕጎች ብዙዎቹ ለአማኙ ቅድስና ይረዱ ዘንድ በአዲስ ኪዳንም በድጋሚ ተጠቅሰዋል። ከዚህም ሌላ ሕጎቹ ከተወሰነ ክፍል ብቻ የተውጣጡ አይደሉም፤ (ለምሳሌ ከአሥርቱ ትእዛዛት)። ከአሥርቱ ትእዛዛት ዘጠኙ ሲደገሙ ሌሎች የሕግ ክፍሎችም እንዲሁ ተጠቅሰዋል (ሮሜ 13፡9)። ሰለዚህ ከአሥርቱ ትእዛዛት ውጪ ሌላው ሕግ ተሽሯል ማለት ጨርሶ አይቻልም። 

እንዲሁም 2ኛ ቆሮ. 3:7-11 ላይ አሥርቱ ትእዛዛት (በድንጋይ ላይ የተቀረፁት) እንደተሻሩ ያለማወላወል ይገልጣል። ታዲያ እነዚህን እውነቶች እንደምን አስማምቶ ለማጠቃለል ይቻላል? ክርስቲያን ለቅድስናው ከሙሴ ሕግ በታች ነው ወይስ አይደለም? 

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ እውነተኛ መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ብሉ የሚያስበው ሕግና በሕጉ ውስጥ የተካተቱትን ትእዛዛት ለይቶ መመልከትን ነው። የሙሴ ሕግ እግዚአብሔር በታሪክ ከሰጣቸው አያሌ ሕግጋት አንዱ ሲሆን፥ እንደ መመሪያነቱ በጊዜው አገልግሎቱን ሰጥቶ ተፈጽሟል። አሁን አማኞች የሚኖሩበት መመሪያ “የክርስቶስ ሕግ” (ገላ. 6፡2) ወይም “የሕይወት መንፈስ ሕግ” ነው (ሮሜ 8፡2)። 

አንድ መመሪያ ሲያበቃ በሌላ መተካቱ እውን ሲሆን፥ በአዲሱ ውስጥ የሚካተቱት መመሪያዎች ግን ሁሉም አዲስና የተለዩ አይሆን ይሆናል። ሥጋ ለመብላት በክርስቶስ ሕግ ተፈቅዷል (1ኛ ጢሞ. 4፡3)፤ ይህ ከጥፋት ውኃ በኋላ ለኖኅ በተሰጠው መመሪያ ውስጥም ነበር (ዘፍጥ. 9፡3)። እንዲሁም አንዳንድ የሙሴ ሕጎች በክርስቶስ ሕግ ሲካተቱ ሌሎቹ አልተጨመሩም። ነገር ግን የሙሴ መምሪያ እንደ መመሪያነቱ አብቅቶለታል። 

ይህ ታዳጊ ልጆች ባሉት ቤተሰብ ውስጥ ከሚኖር መመሪያ ጋር ይመሳሰላል። በተለያዩ የእድገት ደረጃዎች ለሚገኙ ታዳጊዎች የተለያዩ መመሪያዎች ይወጣሉ። ከነዚህ አንዳንዶቹ አንዳንድ ጊዜ በድጋሚ ይታያሉ። ስለዚህ የበፊቱ መመሪያ ከነትእዛዛቱ ተሽሯል ቢባልና፥ በአዲሱ መመሪያ ውስጥ የበፊቱ ትእዛዛት መገኘታቸው ቢታወቅ፥ የሚቃረን አሳብ አይመስልም። ልክ እንደ አካላዊ እድገት ይቆጠራል። ለማደግ ግን፥ የክርስቶስ ሞት የሙሴን ሕግ ለቅድስና የማያስፈልግ እንዳደረገው መረዳት ያስፈልጋል። 

የክርስቶስ ሞት ለአማኞች ከኃጢአት መንጻት መሠረት ነው (1ኛዮሐ. 1:7)። የክርስቶስ ደም (ሞት) የማያቋርጥ መጽደቂያችን ነው። ይህ ለት ግን ዳግም ስቅለት፥ ወይም በኃጢአት የሳተው ክርስቲያን የሚነከርበት ደም ያስፈልጋል ማለት ሳይሆን፥ ለአንዴና ለሁሌም የሞተው ጌታ፥ አማኙ ሳያቋርጥ ከኃጢአት የሚነጻበትን ሁኔታ የፈጠረለት መሆኑን ነው የሚያመለክተው። ቤተሰባዊው ግንኙነታችን በርሱ ሞት ተስተካክሏል፥ በንስሐም ታድሷል። 

የክርስቶስ ምት ከመስቀሉ በፊት የነበረውን ኃጢአት ለማስወገድም መሠረት ነው (ዮሐ. 17፡30፤ ሮሜ. 3፡25)። ሰለ ድነት (ደኅንነት) በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰ ግልጥ ነገር የለም። ሙሉ በሙሉ የኃጢአት ስርየት ማስገኛ ሁኔታዎች አልነበሩም። ሰለዚህ በመሥዋዕት ተሸፍኖ የነበረ የኃጢአት ዕዳ ሁሉ በክርስቶስ ሞት ተወግዷል። የክርስቶስ ሞት ለየትኛውም ዘመን የኃጢአት መወገድ መሠረት ሲሆን፥ ለዚህ አስፈላጊውም እምነት ነው። በእርግጠኛነት የማናውቀው ነገር ቢኖር እያንዳንዱ ዘመን ይጠይቅ የነበረውን ልዩ የእምነት ይዘት ነው። 

የከርስቶስ ሞት በሰይጣንና በአጋንንቱ ለመፍረድ መሠረት ነው (. 2፡13፤ ዮሐ. 12:3)። በሰይጣን ላይ የተላለፉት ፍርዶች በተለያዩ ደረጃዎች የተከናወኑና ወደፊትም የሚፈጸሙ ቢሆንም፥ የፍርዶቹ ሁሉ መሠረት ከርስቶስ በመስቀል አማካይነት በሰይጣንና በጭፍሮቹ ላይ የተቀዳጀው ድል ነው። 

ምሳሌዎቹ 

በብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ሞት የሚያስረዱ ብዙ ምሳሌዎች ቢኖሩም፥ የሚከተሉት ግን በጥልቅ መጠናት የሚገባቸው ናቸው። 1. የይስሐቅ በአብርሃም ለመሥዋዕትነት መቅረብ (ዘፍጥ. 22)፣ 2. የፋሲካ በዓል (ዘጸ. 12)፥ 3. በዘሌዋውያን ከ1 እስከ 5 ያሉት አምስቱ መሥዋዕቶች፥ 4. የክርስቶስን ሞት የማያቋርጥ የማንጻት ኃይል የሚያሳየው ቀይ ጊደር (ዘኁል. 19)፥ 5. የቤዛነት ቀን (ዘሌዋ. 16)፥ 6. የመገናኛው ድንኳን ዝግጅቶች ናቸው። 

የተሳሳቱ አሳቦች 

በታሪክ ሂደት የተለያዩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሞት የተሳሳቱ አሳቦች አቅርበዋል። አንዳንዴ አሳባቸው ጨርሶ ሐሰት ሲሆን፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከፊል እውነትነት አለው። ይሁን እንጂ የሞቱን ምትክነት ዋና አሳብ ስለሚዘሉት ትምህርታቸው የተሟላ አይደለም። 

1. “የክርስቶስ ሞት ለሰይጣን የተከፈለ ቤዛንት ነው።” ይህ ሐሰት ነው። መሥዋዕትነት ቤዛነት መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ቢገለጥም፥ መሥዋዕትነቱ ለሰይጣን የተከፈለ ነው አይልም። 

2. “የክርስቶስ ምት ለኃጢአት ዋጋ አስፈላጊ አይደለም።” ይህም ሌላው የተሳሳተ አመለካከታቸው ነው። የክርስቶስ ሞት የእግዚአብሔርን ፍቅር በማሳየት፥ ግብረገባዊ ተጽዕኖ በማሳደርና ልባችንን በማለዘብ ወደ ንስሐ ይመራናል። 

3. “የክርስቶስ ሞት ኃጢአት አያስተስርይም ወይም እግዚአብሔር ኃጢአትን ይቅር እንዲል እያደርገውም።” ይህም ሌላው ስሕተታቸው ነው። የክርስተስ ሞት ለሰዎች የእምነትና የታዛዥነትን እቅጣጫ ያመለከታል። ይህ አቅጣጫ ወደ ሕይወት የሚመራ ሆኖ ለኑሯችንና ለሕይወታችን የክርስቶስን ምሳሌ እንድንከተል ያነሳሳናል። 

4. “ክርስቶስ የእግዚአብሔርን አገዛዝ ለማርካት የሞተ ንጹሕ ሰው ነው፤ ይህ የሆነው የእግዚአብሔር አገዛዝ ፍትሃዊ እንጂ፣ እድሏዊ አለመሆኑን ለማሳየት ነው።” የክርስቶስ ሞት ግን ከዚህ እጅግ የላቀና፥ ሕግ ኃጢአትን እንዴት እንደሚመለከተው የሚገልጥ ነው። 

5. አክራሪ ያልሆኑ የዘመኑ ንድፈ አሳቦች ስለ ቤዛነት ያላቸው ሌላ አመለካከት። ለምሳሌ የክርስቶስ ሞት በምሳሌነቱ፥ ግብረገባዊ የሆነና እግዚአብሔር ለኃጢአት ያለውን ጥላቻና ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር የሚገልጥ ነው የሚል አሳብ አላቸው። ሆኖም የክርስቶስ ሞት ለኃጢአት የተከፈለ ቤዛነት መሆኑን ገለል ያደርጋሉ። 

የክርስቶስ ሞት ቤዛነት ስፋት 

የክርስቶስ ቤዛነት እስከምንድነው? የሞተስ ለሰው ዘር ሁሉ፥ ወይስ ለምርጦቹ ብቻ? የሚለው ጥያቄ ለዘመናት ሲያከራክር ቆይቷል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የክርስቶስ ቤዛነት ለአንድ የተወሰነ ክልል ብቻ ነው ይላሉ። ለምሳሌ፡- “ለበጎች” በዮሐንስ 10፡15፤ “ለቤተ ክርስቲያን” በኤፌሶን 5፡25፥ “ለብዙዎች” በማቴዎስ 20፡28። አንዳንዶቹ ጥቅሶች ደግሞ፥ የክርስቶስ ቤዛነት ሰዎችን ሁሉ የሚያጠቃልል መሆኑን ያመለክታሉ። በተለይ ዮሐ. 1፡29፥ 3፡17፤ 2ኛ ቆሮ 5፡19፤ 1ኛ ጢሞ. 4፡10፤ 2ኛ ጴጥ. 2፡1 እና 1ኛ ዮሐ. 2፡2ን መመልከት ይበቃል። እርግጥ የክርስቶስ ቤዛነት ውሱን አለመሆኑን የሚያመለክቱ ጥቅሶች ውስንነቱ ውስጥ ያለውን እውነት ያካትታሉ። ያም ሆነ ይህ፥ የክርስቶስ ሞት ወይም ቤዛነት ለሁሉም ነው ማለቱ ይመረጣል። የክርስቶስ ቤዛነት ለሰዎች ሁሉ ቢሆንም የሚያገለግለው ግን አምነው በግል የተቀበሉትን ብቻ ነው።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.